
እያገባደድነው ባለው ሳምንት መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በአውሮፓ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነችው የኢጣልያኗ ከተማ ሮም ሲገኙ በዚያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ጥያቄ በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ ኢትዮጵያን ጎብኝተው አፀፋ የጉብኝት ግብዣ ካስተላለፉላቸው የኢጣልያኑ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋርም ተገናኝተዋል፡፡
የኢጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በፓላዞ ቺጊ ብሄራዊ ቤተ መንግስት አቀባበል አድርገውላቸው ባካሄዱት የሁለትዮሽ ውይይት ከአዲስ አበባ ምፅዋ በሚዘረጋው የባቡር ሃዲድ ዙሪያ ትብብር ስለማድረግ ፣ በኢጣልያን የረጅም ጊዜ የልማት ትብብር መሰረት ለትምህርት እድሜያቸው የደረሱ ህፃናትን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ መርሃግብሮች ላይ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የኢጣሊያኑን ፕሬዚዳንት ሰርየጎ ማታሬላን በክዩሪናል ቤተ መንግስት አግኝተውም በአገራቱ መካከል ስላለው ታሪካዊ ግንኙነትና በቀጣይ በሚከናወኑ ቁልፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ትብብሮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፤ ፕሬዚዳንት ማታሬላ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየውን ለውጥና አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ እየተጫወተች ያለችውን ሚና አድንቀዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሮም ከተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆዜ ግራዚያኖ ዳሲልቫ ጋር ሲወያዩ፤ ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እየተጫወተች ያለውን ሚናና በቀጣናው ሰላምን ለማምጣት የሚደረገውን የፖለቲካ አመራር ሲያደንቁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በበኩላቸው የቀጣናው ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የምግብ ዋስትናንና ግብርናን በተመለከተ የአነስተኛ ገበሬዎች ዋና ፍላጎት የገበያ ትስስር በመሆኑም የተቀናጀ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያስፈልግና በሌሎች መስኮችም ትብብራቸውን ለማጠናከር መስራት ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በሮም ጉብኝታቸው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንና የቫቲካን ራስ አገዝ ከተማ መሪ ቅዱስነታቸው አቡነ ፍራንሲስን፣ በቅዱስ ከተማዋ ዋና አስተዳዳሪ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በኢትዮጵያና በቫቲካን የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ አነጋግረው፤ በቫቲካን የሚገኘውን የቅዱስ እስጢፋኖስ የአቢሲኒያ ቤተክርስቲያንን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ከኢጣልያ ጉብኝታቸው ቀጥሎ የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ወደሚካሄድባት የሲዊዘርላንዷ ከተማ ዳቮስ ያቀኑ ሲሆን፤ በእዚያም ከጉባኤው አስቀድሞ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ከግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሆውንግቦን፣ ከተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊንን በግብርናና በምግብ ሰብል ልማት ላይ በቀጣይ በሚደረገው እገዛ ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ የዓለም ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚደንት የሆኑትን ክርስታሊና ጂኦርጂቫንን በቴክኒክና በገንዘብ ድጋፍ መስክ ስላሉ ቀጣናዊና ብሄራዊ ፋይዳ ስላላቸው ፕሮጀክቶች፣ የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ መስራችና ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕሮፌሰር ክላውስ ሻዋብ ጋር ቁልፍ የሆኑ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለመፍታት በንግድ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ፣ በሲቪል ማህበረሰብ ውስጥ የተቀናጀ አሠራርን አስፈላጊነትን በተመለከተ ውይይት አድርገው፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ 2020 የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ አካል የሆነውን የዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ በአፍሪካ የሚሰኘውን ስብሰባ እንድታስተናግድም ተስማምተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ከዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ጎን ለጎን ከቤልጅየሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርልስ ማይክል፣ ከአሊባባ ሊቀመንበር ጃክማ ፣ የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ተባባሪ ሊቀመንበር ከሆኑት ቢል ጌትስ ጋር ተገናኝተው በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በጤና፣ ግብርናና በአቅም ግንባታ ዘርፎች የሚደረግ ድጋፍና ትብብር ላይ ስምምነት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ከበርካታ አገሮች ከተመረጡ ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ጋር የግል ኢንቨስትመንት መሳብ የሚቻልባቸው ዕድሎችን ለመለየት የሚያስችል ስትራቴጂክ ውይይት አካሂደዋል። ይህ ጠንካራ ውይይት በኢትዮጵያ ያለውን ያልተነካና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅምና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነጥቦችን ማመላከቱ ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በዳቮስ ከኦፕን ሶሳይቲ ኢኒሼቲቭ ኃላፊ ጆርጅ ሶሮስ ጋር በምርጫ፤ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ በፍትህ እና በኢኮኖሚያዊ ተሣትፎ እንዲሁም በተቋማዊና እና የቁጥጥር ማሻሻያዎችና ተግዳሮቶቻቸው ላይ ሲወያዩ፤ የሲቪል ማህበራትን በማስፋፋትና በተሻሻለ የስደተኞች ህግ ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ ላሳየችው እመርታም ኃላፊው አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ቆይታቸው የዱባይ ኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑትን መሀመድ አል ሼይባንን ሲያነጋግሩ፤ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ በመስተንግዶና በእርሻ ቢዝነስ መዋእለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በዓለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ለዓለም መሪዎች ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ወራት ስላስመዘገበቻቸው የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላም ወዘተ… ስኬቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዳቮስ ሲውዘርላንድ የነበራቸውን የአውሮፓ ቆይታም በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀው ወደ ብራስልስ ቤልጅየም መጓዛቸው ይታወሳል፡፡
የዚህ ሳምንት የጠቅላይ ሚኒስትሩ እረፍት የለሽ ሩጫ የአገርን መልካም ገፅታ መገንባት፣ ከአገራት ጋር ያለንን ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትስስር ማጠናከር የቻለ የዲፕሎማሲ መድረክ መሆኑ ጣምራ ድልን ያጎናፀፈ ስለሚያደርገው አድናቆት ሊሰጠው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2011