የተማሪዎችና መምህራን እምቅ የፈጠራ ችሎታ የታየበት አውደርዕይ

ትምህርት ቤቶች በንድፈ ሀሳብ ከሚሰጡ ትምህርቶች ባሻገር በፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል:: በመሆኑም ሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷል:: ይህን ተከትሎም ትምህርት ቤቶቹ የፈጠራ ሀሳቦችና ሥራዎች መፍለቂያ መሆን ችለዋል::

የተማሪዎችና የመምህራን የፈጠራ ሥራዎች ከየትምህርት ቤቱ ተመርጠው በየደረጃቸው እንዲወዳደሩ ይደረጋል:: ከእነዚህ መካከል የተመረጡት ደግሞ በከተማ ደረጃ በሚካሄድ አውደ ርዕይ ላይ ቀርበው እንዲወዳደሩ ይደረጋል::

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮም የየትምህርት ቤቶቹን የፈጠራ ሥራዎች እያወዳደረ በከተማ ደረጃ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው አውደርዕይ ለእይታ እንዲቀርቡና እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል:: ዘንድሮም 10ኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስ የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ ከሚያዚያ 16 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ “በፈጠራ ሥራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና!” በሚል መሪ ሀሳብ በወዳጅነት ፓርክ ተካሂዷል::

አውደ ርዕዩ ተማሪዎች በክፍል በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር በመግለጽ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ እንደሚያበረታታ ታምኖበታል:: ቢሮው ተማሪዎችና መምህራን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያላቸውን ክሕሎትና ተሰጥኦ እንዲያዳብሩ ምቹ መደላድል በመፍጠር ለፈጠራ ሥራዎች መጎልበት በትኩረት እየሠራ ይገኛል::

ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ በዘንድሮው አውደ ርዕይ ከትምህርት ቤት ጀምሮ በተካሄደው ውድድር ከአምስት ሺ በላይ ተማሪዎችና መምህራን ተወዳዳሪዎች በቡድንና በግል ተሳትፈዋል:: ከሶስት ሺ አንድ መቶ በላይ የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎች ለእይታ ቀርበዋል:: በትምህርት ቤት፣ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ ተመርጠው ጎልተው የወጡ የፈጠራ ሥራዎች በ39 ዘርፎች ቀርበዋል::

በከተማ ደረጃ የቀረቡት 424 ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ከተመረጡ የፈጠራ ሥራዎች መካከል የምርጦች ምርጥ፤ የአሸናፊዎች አሸናፊ የሆኑ 128 ተማሪዎችና መምህራን ለሽልማት ይቀርባሉ:: በአውደ ርዕዩ የቀረቡት እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ሀገሪቱ ያላትን የወደፊት ተስፋ የሚያሳዩ ናቸው:: ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን እናስቃኛችኋለን::

በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዱ መምህር ዮሴፍ መሐመድ ናቸው:: መምህሩ የመጡት ከልደታ ክፍለ ከተማ መዝገበ ብርሃን ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የሰሩትን የብሎኬት ማምረቻ ማሽን ይዘው ቀርበዋል::

መምህር ዮሴፍ ማሽኑን ለመሥራት መነሻ ሀሳብ ከሆኗቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ቤት ለመሥራት የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ነው:: ይህን ወጪ ለመቀነስ ቀላል ነገሮችን መጠቀም ፈለጉ:: ሁለተኛው ደግሞ በአካባቢ ላይ ብክለት የሚያስከትሉ የፕላስቲክ ውጤቶች መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው:: ተማሪዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች በራሳቸው መፍትሔ በመስጠት ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን ለመሥራት እንዲችሉ እንደ መምህር አርአያ ለመሆን ማሰብም ሌላው ምክንያቸው መሆኑን አብራርተዋል::

መምህሩ እንዳሉት፤ ማሽኑ አካባቢ ላይ ከፍያቸው የሚገኙትን ብክለት የሚያስከትሉ እንደ ፌስታል ያሉ ፕላስቲኮች፣ የማዳበሪያ ከረጢቶች፣ የቴሌቪዥንና የቴፕ ከቨር እና የመሳሳሉትን አንድ ላይ በማቅለጥና ቅርጽ በማውጣት ተገጣጣሚ የፕላስቲክ ብሎኬት ያመርታል::

ብሎኬቱም በጣም ጠንካራ፣ ቢወድቅ በቀላሉ የማይሰበር ለብዙ ዓመታት ያህል አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ነው ሲሉም አብራርተዋል:: አሁን ለግንባታ የሚውለው ብሎኬት ከ30 እስከ 40 ዓመት ቢያገለግል ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ አደጋ ተቋቋሚነቱም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእሳት በቀላሉ የማይበገር መሆኑንም አብራርተዋል::

ብሎኬቱን ለተለያዩ አገልግሎቶች ማዋል እንደሚቻልም ጠቁመዋል:: በኮሪደር ልማቱ የመጸዳጃ ቤቶችን ለመሥራት፣ ለዶሮ እርባታ ቦታዎች፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታና ፓርቲሽን መከፋፈያነት ሊውል እንደሚችልም አመላክተዋል:: እንደ ሴራሚክ ተገጣጥሞ ለወለል ምንጣፍ ቢደረግም ለረጅም ጊዜያት አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚችል ጠቁመዋል::

ማሽኑ ከወዳደቁ ብረታ ብረቶችና ከእንጨት በእጅ በመገጣጠም የተሠራ ነው የሚሉት መምህር ዮሴፍ፤ ማሽኑን ለመሥራትም አምስት ቀናት ብቻ እንደ ወሰደባቸው ይገልጻሉ:: ማሽኑ አካባቢንና ከተማን ጽዱ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ ብሎኬቱንም ማንኛውም ሰው በቀላሉ ገጣጥሞ ሊሠራው እንደሚችል አመላክተዋል:: ቴክኖሎጂውን እንደ ሀገር ብዙ በመሥራት ማሳወቅ እንደሚገባም አመልክተዋል::

እሳቸው እንዳብራሩት፡- ብሎኬቱ ሻካራ ስለሆነ ጅብሰምና ቀለም በቀላሉ ይቀበላል:: ለስላሳ ብሎኬቶችን ማምረት ያስችላል:: ሞልዱን በመቀያየር የተለያዩ ብሎኬቶችና ሌሎች ጠንካራ ነገሮችን መሥራት ይቻላል::

ማሽኑ ፕላስቲኮችን አንዴ ካቀለጠ በኋላ ሙሉ ቀን ከሠራ ከ200 እስከ 300 ያህል ብሎኬቶች ሊያመርት እንደሚችል ይጠቁማሉ:: ብሎኬቱን ለማምረት የሚያገለግሉት ግብዓትነቶች በአካባቢው እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ግብአቶቹን በብዛት ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢን ከብክለት ለመታደግ እንዲሁም የአካባቢ ጽዳትን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል::

‹‹በተለይ በአካባቢያችን ላይ ለቴሌቪዥን ሽፋን የሚውሉ ፕላስቲኮችን የመሳሳሉ ቁሳቁስ በብዛት በየቦታው ሲጣሉ ይታያል››ያሉት መምህሩ፣ እነዚህን ሰብስበን በማቅለጥ ለብሎኬት መሥሪያነት መገልገል እንችላለን:: አንድ ብሎኬት ለመሥራት ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎ የፕላስቲክ ምርቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ›› ሲሉም አብራርተዋል::

በቀጣይ ይህንን ማሽን ወደ ገበያ በማውጣት ሕብረተሰቡ እንዲጠቀምበትና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ መምህሩ አስታውቀው፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው የግል ባለሀብቶች የፈጠራ ሀሳቡን በመደገፍ ማሽኑ ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል:: ይህ ተግባር አካባቢያችንንና ከተማችንን ጽዱ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ አመልክተው፣ የሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት እንዲሰጡት አስታውቀዋል::

ሌላኛው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ተማሪ ፉአድ ገቢ ይባላል:: የቂሊንጦ ቁጥር ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: የሰራው ሞተር ሳይክል ይዞ ነው በዓውደ ርዕዩ ላይ የተገኘው::

ተማሪ ፉአድ ለፈጠራ ሀሳቡ መነሻ የሆነው ከልጅነቱ ጀምሮ ቁሳቁስን በእጁ በመነካካት፣ በመፈታታትና መልሶ በመገጣጠም እየሞከረ ማደጉ መሆኑን ይናገራል:: በቴሌቪዥን መስኮትና በአካባቢው ላይ የሚመለከታቸው ነገሮች የፈጠራ ሀሳብ እንዲያመነጭ ምክንያት እንደሆኑት ጠቅሶ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ እንዲኖረው የሚፈልገው ዓይነት ሞተር ሳይክል ለመሥራት አልሞ እንደ ሠራ ይገልጻል፡

እሱ እንዳለው፤ ሞተር ሳይክሉ በተለምዶ ከሚታወቁት ሞተር ሳይክል አይነቶች ይለያል:: በተለይ ለልጆች ምቾች እንዲሰጥና በቀላሉ መቆጣጠር የሚቻል እንዲሆን አድርጎ ሰርቶታል::

ሞተር ሳይክሉ የወዳደቁና የተጣመሙ ብረታ ብረቶችን በመጠቀም ነው የሠራው:: ሞተር ሳይክሉ የሚሠራው በዲናሞ ነው:: መቆጣጣሪያ ሪሞት አለው:: በሰዓት 12 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል:: ጨለማ በሚሆንበት ወቅት ብርሃን በመስጠት ለመንዳት ያስችላል:: ሞተር ሳይክሉን ለመሥራት ሰባት ሺ 500 ብር በላይ ወጪ አድርጓል::

በተለይ ሪሞቱ ከሌሎች ሞተር ሳይክሎች እንዲለይም ያደርገዋል:: ሳይክሉን ያለመቆጣጠሪያ ሪሞቱ ሞተር ሳይክሉን ማሽከርከር እንደማይችል ጠቅሶ፣ ሰዎች ሞተሩን አቁመው ቢሄዱ እንዳይሰረቁ እንደሚረዳ ይገልጻል:: ሞተር ሳይክሉን ለማሽከርከር የሚያስችል መመሪያ ማንዋል ማዘጋጀቱንም ይገልጻል::

ይህን የፈጠራ ሥራ እያሻሻለና እያሳደገ ትልቅ ደረጃ የማድረስ ሕልም እንዳለው የሚገልጸው ተማሪው፣ የፈጠራ ሥራውን በማሳደግ መኪና ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል:: ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ካገኘ ይህንን የፈጠራ ውጤት በማሻሻል ትልቅ ደረጃ ለማድረስና ሌሎች ፈጠራዎችን ለመሥራት ፍላጎቱ እንዳለው አስታውቋል:: ትምህርቱን ሲጨርስ መሀንዲስ የመሆን ምኞት እንዳለውም ጠቁሟል::

ሌላኛው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ተማሪ ጆሲ ታዴ የወንድራድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው:: የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ ማሽን ሰርቶ ይዞ ቀርቧል::

ለዚህ ፈጠራ መነሻ የሆነው ያደገበት ገጠር አካባቢ በአብዛኛው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ ነው:: የተፈጥሮ ማዳበሪያውን አጠቃቀሙም ሆነ ሲመረት የሚወስደው ጊዜ ረጅም መሆንም ሌላው ምክንያቱ መሆኑን ይገልጻል:: ማዳበሪያው የሚመረተው መሬት ውስጥ ነው፤ ይህ መሆኑም ከአፈር ጋር እንዲቀላቀል የሚያደርገው በመሆኑ ትክክለኛ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማግኘት እንደማይቻል መመልከቱን ይናገራል:: ከልጅነቱ ጀምሮ ላየው ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ሲያስብ ቆይቶ ማሽኑን ለመሥራት መቻሉን አስታውቋል::

እሱ እንዳለው፤ አሁን በሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሥራት ከአራት ወራት እስከ ስድስት ወራት ይወስዳል:: ይህ ሁኔታ ማዳበሪያ በሚፈለገው ልክና በበቂ ጊዜ ማግኘት አያስችልም:: ይህንን ማሽን የሠራው እነዚህ ችግሮች ለመፍታት አስቦ መሆኑን ተናግሯል::

ተማሪ ጆሲ እንዳብራራው፤ አዲስ ማሽኑ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ያስችላል:: የሚበሰብሱ ነገሮችን ይፈጫል፤ ግብአቱ እየደቀቀ በሄደ ቁጥር የመበስበስ አቅሙም ከፍ ይላል:: የእርጥበት ማውጫ፣ የኦክሲጂን ማስገቢያና ማቀላቀያ እንዲሁም ኢንኩቤተር እንደተገጠመለት አመልክቷል:: ከተፈጨ በኋላም በእርጥበት ማውጫ እርጥበቱ እንዲወጣ፣ የኦክሲጂን ማስገቢያና ማቀላቀያው ደግሞ እንዲብላላ ያደርገዋል:: ኢንኩቤተሩም ጥሬው እቃውን ለማበስበስ ያስችላል::

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሥራት በግብዓትነት የሚውለው ጥሬ እቃ በውስጡ የራሱ ንጥረ ነገሮች አለው የሚለው ተማሪ ጆሲ፣ ለግብዓትነት የሚውሉት መበስበስ የሚችሉት እንደ ቅጠላቅጠል፣ የሽንኩርት ልጣጭና፣ አጥንት ከሰልና የመሳሳሉ ተረፈ ምርቶች የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለመሥራት እንደሚያገለግሉም አብራርቷል::

በእነዚህ ግብአቶች ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች በማመጣጠን መጠቀም እንደሚቻል ጠቅሶ፤ ለአብነትም ሌሎች ተረፈ ምርቶችን 50 በመቶ ያህል ጨምረን የስንዴ ገለባ 50በመቶ ስንጨምር የምናገኘው ናይትሮጂን ከፍ ይላል ሲል ጠቁሟል::

‹‹ሁሉንም ንጥረ ነገሮች በመመጠን ማዳበሪያው የምንፈልገውን አይነት ንጥረ ነገር እንዲኖረው እያደረግን የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ማምረት እንችላለን›› ሲል ተማሪ ጆሲ አስታውቋል:: ይህንን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከተለመደው ለየት የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ምንም አይነት መጥፎ ጠረን የሌለው መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህ በመሆኑም በሰዎች ጤና ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ ይገልጻል::

እሱ እንደሚለው፤ ማሽኑ የተሠራው ከአንዳንድ እቃዎች በስተቀር ትምህርት ቤት ከጥቅም ውጪ ከተደረጉ ፋይል ካቢኔቶች፣ ጠረጴዛዎችና ከመሳሳሉት የወዳደቁ ቁሳቁስ ነው:: ማሽኑን ለመሥራት ሁለት ወራት ፈጅቷል:: በሃያ አራት ሰዓት 25 ኪሎ ግራም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረት ይቻላል:: ማሽኑ አንድ ቶን እንዲያመርት ማድረግም ይቻላል::

በቀጣይ ማሽኑ ወደ ሥራ ማስገባት አርሶ አደሩ በቅናሽ ዋጋ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማግኘት እንዲችል ለማድረግ እንደሚጠቅም የሚገልጸው ተማሪ ጆሲ፤ አሁንም ቢሆን ማዳበሪያውን እያመረተ በአንድ ኪሎ መጠን ለፈላጊዎች እየሸጠ መሆኑን ይገልጻል::

የፈጠራ ሥራውን ሲሠራ ወላጅ አባቱ ሁል ጊዜ እንደሚደግፉትና እንደሚያበረታቱት ገልጾ፤ ከትምህርት ቤቱ ርዕስ መምህር ጀምሮ መምህሮቹ ድጋፍ ሲያደርጉለት እንደነበር ይገልጻል::

‹‹ያደኩበት አካባቢ ሕብረተሰብ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት በማሰብ ማሽኑን ሰርቼለሁ›› ሲል ተናግሮ፣ በዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ለችግሩ መፍትሔ ማምጣት ችያለሁ›› ሲል ተማሪ ጆሲ አስታውቋል:: ለሌሎች ተማሪዎች በአካባቢያቸው ለሚያጋጥማቸው ችግሮች በራሳቸው መፍትሔ ለማምጣት ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝቧል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You