የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ግብዓት አምራቾችን አቅም ለማጎልበት በትብብር መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

– በሀገር ውስጥ የሚመረተው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት 25 በመቶ ብቻ ይሸፍናል

አዲስ አበባ፡- የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ግብዓት አምራቾችን አቅም ለማጎልበት በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። በሀገር ውስጥ የሚመረተው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት 25 በመቶ ብቻ እንደሚሸፍን ጠቆመ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ግብዓት አምራቾች ጋር ሰሞኑን ባደረገው ውይይት ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከዓመታት በፊት ለኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ከውጭ ሀገር ያስገባ ነበር።

አሁን ላይ ለሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ፍላጎቱን በተወሰነ ደረጃ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አመልክተው ፤ በዚህም የውጪ ምንዛሬን ማዳን፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይነት በዘርፉ ያለውን የግብዓት ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፤ ተቋሙ ከሀገር ውስጥ አምራቾች ጋር በቅርበት በመሥራት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ብለዋል።

አምራቾችም የመሠረቷቸውን ማህበራት አጠናክረው እርስ በርስና ከአገልግሎቱም ጋር በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ትስስር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መገርሳ በበኩላቸው፤ አምራቾች የሚያቀርቡት ግብዓት ለኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማትን ለማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ተቋሙ ከሚፈልጋቸው ግብዓቶች ውስጥ በሀገር ውስጥ አምራቾች የሚሸፈነው 25 በመቶ ብቻ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፍ ጨረታ እየወጣ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ግብዓቶች ወደሀገር ይገባሉ። ለዚህም ተቋሙ በየዓመቱ ከ14 እስከ 20 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ እንደሚያወጣ ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመው፤ አምራቾችም ይህን መልካም እድል ተጠቅመው የበለጠ በመሥራት የተቋሙን ሰፊ የግብዓት ፍላጎት ለማሟላት መሥራት እንደሚገባቸው፤ የሚያቀርቧቸው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እና በወቅቱ ሊደርሱ እንደንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ ተሳታፊ የነበሩ የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት አምራቾች፤ መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን አንስተው፤ ያሉባቸውን ችግሮች እና የሚፈልጉትን ድጋፍ አቅርበው በተቋሙ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You