የአይቀሬው የኢትዮጵያ ብልፅግና ማሳያዎች!

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያዝያ 17 እስከ 18/2017 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በዝርዝር ሲመክር የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ በለውጥ ዓመታቱ የተከናወኑ ተግባራት እንደ ሀገር በ2018 ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር፤ በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን፤ በ2040 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርአያ ለመሆን የተቀመጡ ግቦች እንደሚሳኩ ፍንጭ የታየባቸው ስለመሆኑ በጉባኤው ማጠቃለያ ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል::

ይሄም እንደ ፓርቲም፣ እንደ መንግሥትም በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ለሚጠበቀው ሁሉን አቀፍ ብልጽግና መሳካት የተጀመረው መንገድ እየተቃና ስለመሆኑ፤ የተያዘውም ፍኖት (ፍኖተ ብልጽግና) ትክክል መሆኑን አመላካች ስለመሆኑም ነው ኮሚቴው አያይዞ የገለጸው:: ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ በቃል የሚተረክ ሳይሆን፤ በመሬት ላይ የሚታይና የሚኖር እውነት ስለመሆኑም በበርካታ አብነቶች አስደግፎ አብራርቷል::

የዚህ የብልፅግናው አይቀሬነትም ሆነ የፍኖተ ብልጽግና ትክክለኛነትን አመላካች ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ፤ ትብብርን ወደላቀ ደረጃ የማሳደግ፣ ሀገራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን የማጽናት፣ እንዲሁም የተረጋጋ ሰላምን የመፍጠር ጉዞው ስኬታማነት ነው:: ለምሳሌ፣ አያሌ የዲፕሎማሲ ስኬት የተገኘባቸው ባለ ብዙም ሆነ የሁለትዮሽ ትብብሮች ተፈጥረዋል:: ለአብነትም፣ ከሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ተፈትቷል:: የባሕር በር ጥያቄውም ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል:: በጥቅሉም የኢትዮጵያን ተፈላጊነት ማሳደግ ተችሏል::

በፖለቲካውም ቢሆን፣ ከተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በየደረጃው ምክክርና ትብብር በመፍጠር፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ያደረጉ ሥራዎች ተሠርተዋል:: አብሮነትን በማጎልበት ረገድም፣ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች ማጠናቀቅ ተችሏል::

ሰላምን ከማጽናት አኳያም፣ በሁሉም አካባቢዎች በተሠሩ ሥራዎች የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሰላም እየሰፈነ ነው:: ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል ስለ ሰላም ሲባል በተከናወኑ ያልተቆራረጡ ተግባራት፤ በሌላ በኩል እየተወሰዱ ባሉ የሕግ ማስከበር ርምጃዎች ታግዞ የተፈጠረ ነው:: በዚህም ወደ ሰላም የሚመለሱ ኃይሎች ቁጥር ከእለት ወደ ዕለት እያደገ መጥቷል::

በኢኮኖሚው መስክ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችም፣ የብልጽግናውን ፍኖት ትክክለኛነት የሚናገሩ ናቸው:: ለምሳሌ፣ በተያዘው ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በስምንት ነጥብ አራት በመቶ ያድጋል:: የመንግሥት ገቢም ቢሆን በእጅጉ ያደገ ሲሆን፤ የውጭ ብድርንም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ወደ 13 ነጥብ ሰባት በመቶ ማውረድ ተችሏል:: የወጪ ምርቶችም እስከ 386 በመቶ (እንደየምርቱ ቢለያይም) የሚደርስ ዕድገት ታይቷል::

በዚህ ሂደት ግን በተለይም ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ ወገኖች ላይ ጫና እንዳያሳድር ለማድረግ፣ በማዳበሪያ፣ በነዳጅ፣ በዘይት፣ በደመወዝ እና በሴፍቲኔት ከፍተኛ የድጎማ አሠራርን ዘርግቶ ተግባራዊ አድርጓል:: ከሥራ ዕድል ፈጠራ፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ከማሳደግ እና የመንግሥት የልማት ተቋማትን አቅም ከመፍጠር፤ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደግ፣ ብሎም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ አኳያ የተከናወኑ ሥራዎችም እጅጉን የሚበረታቱ ናቸው::

ቀድሞ ለሀገር አቅም ከመሆን ይልቅ ወደ ሀገር ሸክምነት የተሸጋገሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አልቆ ከመፈጸም፤ አዳዲስ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ጀምሮ በጊዜያቸው ከማጠናቀቅ እና የሀገር አቅም ከማድረግ አኳያም የተከናወኑ ተግባራት ሌላ አብነቶች ናቸው:: ለዚህ ደግሞ 98 ነጥብ 66 በመቶ ላይ የደረሰው የዓባይ ግድብ፤ ወደ ፍጻሜ የተቃረቡ በርካታ የመስኖ ግድቦች፤ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በ65 ከተሞች እየተከናወነ ያለው በደረጃው ከፍ ያለ የኮሪደር ልማት ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው::

በትምህርት፣ በጤና እና በመዝናኛ (በስፖርት እና ቱሪዝም) ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፤ ሀገር በእውቀት የተገነባ፤ ጤናው የተጠበቀ፣ በአካልም የተገነባ እና ምቹ የተዝናኖት ከባቢ ላይ የሚኖር ዜጋ ባለቤት እንድትሆን የማስቻል ሂደቱ ሕያው አብነቶች ናቸው::

እነዚህ ስኬቶች ደግሞ እንደ ሀገር የአይቀሬው ሁለንተናዊ ብልፅግና ጉዞው መጀመሪያዎች ናቸው:: የሚያኩራሩ እና የሚያዘናጉም ሳይሆኑ፤ የሚያነሳሱና ለቀጣይ አቅም የሚሆኑ ናቸው:: በመሆኑም በሁሉም መስክ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠል እና ወደ ብልጽግናው የሚደረገውን ግስጋሴ ማፋጠን ይገባል:: ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል ስኬቶቹን ይበልጥ ማስፋትና ማጽናት፤ በሌላ በኩል ለስኬቶቹ ማሳለጫ የሚሆኑ ጎዳናዎችን አልቆ ማደላደል እና እጥረቶችን በጽናት መፍታት ይጠይቃል!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You