የሕግ ክፍተቶችን ማሻሻል የሚሻው ጾታዊ ጥቃት

ዳጊ ማራኪ ሰውነት የደስ ደስ የተላበሰው የፊት ገጽታዋ ጀርባዋ ላይ ዘንፈልፈል ብሎ ከተኛው ሀር መሳይ ፀጉሯ ጋር ሲታይ የማንንም ዓይን ይስባል:: እድሜዋ ከ15 ዓመት ባይበልጥም ሸንቀጥቀጥ ያለው መለሎ ቁመቷ ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ያስመስላታል:: አለባበሷም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ ፀአዳ እና ‹‹ሽክ ›› የሚሉት ዓይነት ነው:: ታዳጊዋ አዲስ የሚባል የአለባበስ እና የፀጉር ስታይል የማያመልጣት ፋሽን ተከታይ ነች::

ይህ ልምዷን ዘመናውያኑ ምሁራን ወላጆቿ እና ሌሎች ቤተሰቦቿ ቢወዱላትም በርካቶች ግን ለጥቃት አጋላጭ እንደሆነ ይነግሯታል::”ብዙዎች አለባበሴን ለጥቃት አጋላጭ ነው ይሉታል:: ወጣት ወንዶች፤ በሚገርም ሁኔታ አያቴ የሚሆኑ ትልልቅ ሰዎች ሳይቀሩ ‹‹ክላክስ›› እያደረጉ በመጥራት፤ በእግሬም ስሄድ እየተከተሉ በማናገር ጭምር ይለክፉኛል›› የምትለው ታዳጊዋ በዚህ ምክንያት ከሚለክፏት ወንዶች ጋር ስትጋጭ ትልልቅ እናቶች ሳይቀሩ ”ማን እንዲህ ለብሰሽ ውጭ አለሽ›› ይሏታል:: ለለከፋ ያጋለጣት አለባበሷ እንደሆነ በመግለጽም ለጥቃት አድራሽ ወንዶቹ ወግነው እንደሚናገሯት ትጠቅሳለች::

”የፈለኩትን መልበስ መብቴ ስለመሆኑ የሚረዳልኝ ማሕበረሰብ የለም›› የምትለው ታዳጊዋ የምትከተላቸው ፋሽኖች ምንም እንኳን የውጭ ቢሆኑም ከኢትዮጵያ ወግና ባሕል በማፈንገጥ እርቃን አካሏን ለእይታ የሚያጋልጡ እንዳልሆኑም በእርግጠኝነት ትናገራለች::

”ኢትዮጵያ ውስጥ ርቃናቸውን የሚሄዱ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ:: በነዚህ ብሔረሰቦች ተወላጅ ሴቶች ላይ ጥቃት ያደረሰ ወንድ ጥቃት ያደረስኩባት ራቁቷን ስለሆነች ነው ሊል ነው ወይ ፤ ማሕበረሰቡስ በዚህች ዓይነቷ ሴት ጥቃት ሲደርስ ምን ሊል ነው ? »ስትልም ትጠይቃለች::

በኢትዮጵያ ሕጉ ለነዚህ ዓይነቶቹ የሴቶች ጥቃት ከለላ እንደማያደርግና የሴቷን መብት እንደ መጋፋት ሳይሆን እንደ ቀላል እንደሚያያቸው ታነሳለች:: ከራሷ ገጠመኝ ተነስታ እንደምትለው አንዳንድ የሕግ አንቀጾች ላይ ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ጾታዊ ትንኮሳ ተብሎ ቢቀመጥም አተገባበሩ ለይስሙላ ነው ባይ ነች:: ሁኔታው በተደጋጋሚ ገጥሟት ግጭት ውስጥ ገብታ እንዳየችው ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የፍትህ አካላትም ለወንዱ ለከፋ ምክንያት የሚያደርጉት የሴቷን አለባበስ ነው:: ጥፋተኛ የሚያደርጓትም እሷኑ ነው::

‘አስገድዶ መድፈር በአደባባይ እንደማይፈፀም ይታወቃል” የምትለው ደግሞ ወጣት ሐና ዘመድኩን ናት:: እንደ ሐና እሳቤ ሕጉ እንዲህ ዓይነት ጥቃት የደረሰባት ሴት አጥቂውን መጠየቅ የሚያስችላት ክስ ለመመስረት ትችል ዘንድ ማስረጃ እንድታቀርብ ይጠይቃል:: ማስረጃው ደግሞ በቀላሉ አይገኝም:: ሴቷ ተገድዳ በተደፈረችበት ወቅት የለበሰችውን ሳታወልቅ፤ ሳትታጠብ፤ ጥቃት የደረሰባት አልቤርጎ ውስጥ ከሆነ ለማሳያ የሚሆኑ ማስረጃዎች ይዞ እንደ ፖሊስ ትዕዛዝ ሆስፒታል መሄድ ከባድ ነው::

ይህ አይነቱ አካሄድ ተጠቂዋ ያለችበትም ሆነ የማሕበረሰቡ የአኗኗር ሁኔታ የሚፈቅደው አይደለም:: ሁኔታውን መፈፀም በብዙዎች ዘንድ እንደ ነውር ነው የሚታየው:: አጋጣሚው እሷን መጠቋቋሚያ የሚያደርጋትም ይሆናል:: እንዲህም ሆኖ መረጃዎቹን በሕጉ መሰረት ስንቶቹ ሴቶች ያገኙዋቸዋል ተብሎስ ይታሰባል ስትል ትጠይቃለች::

” እኔ በለስ ቀንቶኝ እነዚህን ሕጉ የሚጠይቃቸውን ማስረጃዎች አቅርቤም ቢሆን ፈጣን ፍትህ አላገኘሁም” ትላለች:: ድርጊቱን አልፈፀምኩም፤ በቦታውም አልነበርኩም ብሎ የካደው ጥቃት ያደረሰባት ሰው ባቀረበችበት ማስረጃ ጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ቢያምንም ፈጣን ውሳኔ ግን አላገኘችም:: እሱም ቢሆን ለጥፋቱ ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት አልተጣለበትም::

ሐና ለደረሰባት በደል ያገኘችው ካሳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: በአጠቃላይ ወጣቷ እንደነገረችን ቅርቧ በሆነ ሰው አማካኝነት በምሳ ግብዣ ሰበብ ቀርቧት በፋንታ ቶኒክ ውስጥ ራሷን የሚያስት ንጥረ ነገር በመጨመር የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ባደረሰባት ሰው ብዙ ተንገላታለች:: ምክንያቱም እሷ ክስ በመሰረተችበት የዛሬ 10 ዓመት አካባቢ ሕጉ የአመራር ቁርጠኝነት ክፍተት የነበረው ጭምር በመሆኑ ነው::

ይሄም ወንጀሉ እለት ተእለት እየተባባሰ በመሄድ ዛሬ የደረሰበት አስከፊ ደረጃ ላይ እንዲገኝ የራሱ አሉታዊ አስተዋጾ እንዲኖረው ምክንያት ስለመሆኑም ትናገራለች:: በወንድ ጓደኞቻቸው፤ በባሎቻቸው፤ ለአፈቀርናችሁ ጥያቄያችን ምላሽ አልሰጣችሁንም በሚሉ ወንዶች የተገደሉ፤ የአሲድ በሰውነታቸው ላይ መደፋትና የአሰቃቂ ድብደባ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እንዲሁም የወራት እድሜ ካላቸው ጀምሮ አሥር ዓመት እንኳን ባልሞላቸው ሕፃናት ላይ የተፈፀመውን አሁንም ተባብሶ የቀጠለውን የአስገድዶ መድፈርን ጥቃት በማሳያነትም ታነሳለች ::

ይህ እውነት በጾታዊ ጥቃት ዙሪያ የሚመለከታቸው የሕግ አካላት ወይም አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ ስለመሆኑም ትጠቅሳለች:: ይሄ ደግሞ አመራሩ ወይም የፍትህ አካሉ በራሱ እስኪደርስበት የሚጠብቅ ዓይነትም ያስመስለዋል::

እኛም እዚህ ጋር በተለይ ከለውጡ በፊት በጾታዊ ጥቃት ዙሪያ የሕግ ብቻም ሳይሆን የአመራር ቁርጠኝነት ክፍተት ጭምር የነበረ መሆኑን ሳናነሳ ማለፍ አንወድም:: በአንድ የጾታዊ ጥቃት ወንጀል እየተባባሰ መምጣቱን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ይህን እውነተኛ ታሪክ ሰማን:: አመራሩ በወቅቱ ከፍ ያለ ሥልጣን ላይ ነበሩ:: ቤታቸው የሚኖር አንድ ዘመዳቸው የጎረቤታቸውን ልጅ ይደፍርና ይከሰሳል:: አመራሩ በሥልጣናቸው ክሱን ማስቀረት ባይችሉም በዛም በዚህም ብለው ቅጣቱ እንዲቀልለት ያደርጋሉ::

አስተያየት ሰጪያችና ሐና ሕጉ በአስገድዶ መድፈር ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት የመስጠት ሰፊ ክፍተት አለበት እንዳለችው ሁሉ በጥፋቱ ለረጅም ዓመታት በእስር ማሳለፍ ይገባው የነበረው የአመራሩ ዘመድም ለትንሽ ጊዜ ታስሮ ይፈታል:: የሚያሳዝነው ከተፈታ ከዓመት በኋላ የራሳቸውን የአመራሩን ልጅ ደፈረ::

ሐና ወዳካፈለችን የራሷ ታሪክ ስንመለስ ጥቃት ያደረሰባት ሰው ታዋቂም ፤ ሀብታምም ነበር:: በወቅቱ እድሜዋ 16 ዓመትን አልደፈነም:: ይሁን እንጂ ከ18 ዓመት በላይ ናት፣ .ወዳ እና ፈቅዳ ነው ያደረገችው ሲል ተናገረ፤ ክሱን የመሰረተችውም በሀሰት ነው እያለ ቅጣቱን ለማስቀረት ሞከረ:: በስተመጨረሻም ቢሆን ለእሱ አሳልፎ የሰጣት የቅርቤ የምትለው ሰውም ሆነ እሱ የተጣለባቸው ቅጣት ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ አልነበረም:: ለእሷ ካሳ ተብሎ የተሰጣትም ጥቂት ብር ከደረሰባት ጉዳት አንፃር እዚህ ግባ አይባልም:: በኋላም ቢሆን ጥቃት ያደረሰበትና ተባባሪው በማታውቀው ሁኔታ የተለቀቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል::

ሐና እንደምትለው በእንዲህ ዓይነቱ ያልተመጣጠነ ቅጣት እና የፍትህ መዛባት ተቀልበው ከሥር ቤት በሚወጡ ደፋሪዎቻቸው ዳግም እስከ ግድያ የዘለቀ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ሴቶች አያሌ ናቸው::

በቅርቡ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ባዘጋጀው ተያያዥ መድረክም የጾታዊ ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱ ተጠቁሟል:: የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ፦ የዚህ አንዱ ምክንያት ወጣቷም እንዳለችው በአጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ እና አስተማሪ ቅጣት አለመጣሉ፤ እንዲሁም ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተቀመጡ ሕጎች ክፍተት ያለባቸው ስለ መሆናቸው አንስተዋል:: በመደበኛ የወንጀለኛ ሕጉ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያወጣው የጥቃት አወሳሰን መመሪያ መኖሩን፤ መመሪያው የወጣው የቅጣት መዘበራረቅን ለማስቀረት እንደሆነ ፤ ሆኖም በዚህ መሰረት የሚሰራበት ሁኔታ እንደሌለም ሚኒስትሯ ተናግረዋል::

በዚሁ በመፍትሄዎቹ ላይ ጭምር ባተኮረና የተለያዩ የፍትህና የፀጥታ አካላት በተሳተፉበት መድረክ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በሕፃናት እና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በአጥፊዎች ላይ የሚጣለውን ያልተመጣጠነ እና አስተማሪ ያልሆነ ቅጣት ለማስቀረት እንደሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ክፍተት ያለባቸው ሕጎች እንዲሻሻሉ የሚመክሩ መድረኮችን ከማዘጋጀት ባሻገር ብዙ ርቀት መኬዱን ያነሳሉ::

የተጠቃለለ የሕፃናት ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ የተሄደበትንም ለአብነት ይጠቅሳሉ:: በአጠቃላይ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በተለያየ መንገድ ሲሠራ መቆየቱን ያወሳሉ:: የቤጂንግ መግለጫና የድርጊት መርሃ-ግብር፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልዎችን ለማስወገድ የወጣው ስምምነት፣ የሕፃናት መብቶች ስምምነት የማፑቶ ፕሮቶኮል፣ የዘላቂ ልማት ግቦች እና ሌሎች ዓለም አቀፍና አሕጉራዊ ስምምነቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው መሰረት በማድረግ ትኩረት አድርጎ ሲሠራባቸው ቆይቷል:: ሆኖም ከችግሩ ስፋት እና እየተባባሰ ከመምጣቱ አንፃር በቂ ነው ተብሎ እንደማይታመን ያሰምሩበታል::

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነህ ብርሃን (ዶ/ር) እንዳሉት የጾታዊ ጥቃት ረቀቅ ባለ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል:: ለጥቃቱ መባባስ ምክንያቶቹ የሕግ ክፍተቶች ናቸው:: ለምሳሌ ያህል የሕጎች ግልፅነት ማጣት ፣ አሻሚ ትርጉም መኖር፤ የቅጣቶች ማነስ፤ በተለያየ መንገድ ሊከሰቱ የሚችሉ ቅጣት አፈፃፀም ላይ ያሉ ክፍተቶች እንዲሁም ከዋስትና መብት እና ከሌሎች ጋር የተያያዙ የሕግ ክፍተት የሚጠቀሱ ናቸው::

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው በአጠቃላይ ሕጉ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚመለከቱ አንቀጾች፤ በተለያዩ መልኩ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን በበቂ መልኩ የሸፈነበት የለም:: ፍትህ ሚኒስቴር እነዚህ እንዲሸፍን ሕጎች እንዲሻሻሉ፤ አዳዲስ ሕጎች እንዲወጡ ከማድረግ ጀምሮ ከሌሎች ጋር ሲሠራም ቆይቷል::

መድረኩን የመሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማሕበራዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ ፆታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደጊዜ መልኩንና አይነቱን በመቀየር ውስብስብ እየሆነ ስለመምጣቱ ያነሳሉ ::

ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም በተጎጂዎቹ ላይ ሥነ ልቦናዊና አእምሯዊ ጫናዎች እያስከተለ መገኘቱን የተለያዩ ጥናቶች ማመልከታቸውንም ይጠቅሳሉ:: በመሆኑም መፍትሄው በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ሁሉን አቀፍ ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳን የያዘ፣ የተጠቃለለ ሕግ አስፈላጊ ሆኖ ስለመገኘቱም በአጽንኦት ያሳስባሉ::

በዚሁ መድረክ የተገኙት ሌላዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግሥቴ እንዳሳሰቡት የተጠቃለለው ሕግ ወደ ሥራ በፍጥነት መግባት እና መተግበር እንደተጠበቀ ሆኖ ጎን ለጎን መሠራት የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ::

ጥቃት ፈፃሚውን አስሮ እና ቀጥቶ መሄድ የሚታሰብ አይደለም:: ለጥቃቱ ምላሽ ከመስጠቱና ከመከላከሉ ጋር ተያይዞ ዋነኛው ቁም ነገር ሊሆን የሚገባው የሕፃናትና የሴቶችን ጥቃትን መፀየፍ የሚችል ዜጋ መፍጠር የሚያስችል ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ማከናወን ነው:: ግንዛቤ ፈጠራው ሥራውም ሰፊውን ሕዝብ ያሳተፈ ሊሆን ግድ ይለዋል::

ግንዛቤ ፈጠራው አንዴ ተሟሙቆ ሌላ ጊዜ የሚቀዘቅዝ ሳይሆን ችግሩ እስከሚቀረፍ በሚዘልቅ በንቅናቄ መልኩ የሚሠራ መሆንም ይገባዋል:: ሰብሳቢዋ ከዚሁ ከመከላከልና ምላሽ መስጠት ጋር አያይዘው እንዳከሉት ባሕልና ልምዳችንንም በብርቱ መፈተሽ ግድና አስፈላጊ ይሆናል:: ሥራው ለወንድ፣ ለሴት ተብሎ ሳይሆን ለሀገር ተብሎ በቁርጠኝነት መሠራት አለበት::

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You