በትግራይ ክልል ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እየተከፋፈለ ነው

– በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ የተጎዱ የተፈጥሮ አካባቢዎች ለመታደግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል ለ2017 የምርት ዘመን ከ100 ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለገበሬው እየተከፋፈለ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ። በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ የተጎዱ የተፈጥሮ አካባቢዎች ለመታደግ እየተሠራ መሆኑ ተመለከተ።

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አበራ ከድነው ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ለገበሬው አስፈላጊ የሆኑት ግብዓቶች እና ምርጥ ዘሮች ተሟልተው ቀርቧል።

የባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በገበሬዎች እና በምርምር ማእከላት የተባዙ የተለያዩ የአዝርእት ዓይነቶች ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እተሠራ መቆየቱንም አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ እርሻ ኮርፖሬሽን ሥራዎች ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመሆን ከ 100ሺ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በማከፋፈል ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

250 ሺ ሄክታር መሬት በስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ሰሊጥ እና ሌሎች ምርቶች በኩታ ገጠም የእርሻ ምርት ለማሳደግ በክልሉ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና ፤ በክልሉ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ የተጎዳው ተፈጥሮ አካባቢን ለመታደግ እየተሠራ መሆኑን የዕፅዋት ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ተስፋይ ግደይ አስታወቁ።

አቶ ተስፋይ ግደይ እንዳመለከቱት ፤ በተለይ ዴስአ አካባቢ የሚገኘው ብሄራዊ ደን ለመንከባከብ የሚያስችል ስምምነት ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተፈርሟል።

የማህበራዊ ኃላፊነት አካል የሆነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና እንክብካቤ ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ጠቁመው ፤ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊዘርላንድ እና ሌሎች አጋዥ ድርጅቶች በሚገኘው ድጋፍ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የዴስአ ብሄራዊ ደን ለአካባቢ ጥበቃ እና ሥነሕይወት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች የሚሰጥ አካባቢ ነው፤ ይሁን እንጂ በእርሻ መስፋፋት፣ የደን ጭፍጨፋ እና የአየር ንብረት ለውጥ የመቦርቦር አደጋ ገጥሞታል ብለዋል።

አዲሱ ፕሮጀክት የዴስአ ደን ለማዳን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮውን ለማሻሻል እና የደኑ ብዝሃ ሕይወት ወደ ነበረበት ለመመለስ እንዲሁም ለሌሎች ደኖች አርአያ በሚሆን መልኩ እንደሚሠራ አመልክተዋል።

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You