ባለፉት ዘጠኝ ወራት የ10 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፡- በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የ10 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ። በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ 518 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አመለከተ ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ እንደተናገሩት፤ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሁሉም አካባቢ ለማምረት ዕድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው ልዩ ድጋፍ በማድረግ እየተሠራ ይገኛል፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች የ 10 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ151ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ደረጃ በደረጃ የመቀነስ ሥራው ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ፕሮግራም 205 ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ጠቅሰው፤ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ምርትን በስፋት በማምረት የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ 518 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል። የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ በተሠራው ጠንካራ ሥራ 57 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል።

ለኢንዱስትሪዎች ማነቆ የሆነውን የፋይናስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎች በየደረጃው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገሩ፣ የምርት ጥራታቸው እንዲሻሻል እና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በአንድ ወረዳ ቢያንስ ሶስት አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ አብዱልፈታ ገልጸዋል።

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You