
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አዲሱ ታሪፍ ዓለምን እያመሰ ይገኛል። የትራምፕ ታሪፍ ቀድሞ ያጠቃው ወዳጃቸውንና አጋራቸውን ኤለን መስክ ነው። ልብ በሉ ከታሪፉ ወዲህ መስክ 31 ቢሊየን ዶላር ከስሯል። ዓለማችን ደግሞ ከሽርክና ገበያው ከ10 ትሪሊየን ዶላር በላይ ከሥራለች። ታዲያ ኤለን መስክ የትራምፕን የታሪፍ ውሳኔ ድድብና ነው ቢል ይፈረድበታል። የትራምፕን የኢኮኖሚ አማካሪ ለዚያውም የሀርቫርድ ምሩቁን ባለ ፒኤችዲውን ናቫሮን ሞሮን ገገማ ሲለው የሰሙ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” አስብሏል። የኤለን መስክ ወንድም የቴስላ ዳይሬክተር እንዲሁ በትራምፕ ታሪፍ ላይ ተሳልቋል። አሁን ትራምፕና መስክ “እልል በቅምጤ” እንዳላሉ ጥላቸው አንድ ሐሙስ የቀረው ይመስላል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ትቅደም፤ አሜሪካ ወደ ቀደመ ክብሯ ትመለስ ማለታቸው ለእሳቸው ሙዝ እንደመላጥ ቀላል ነበር። ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆርጣል። እኔ ብመረጥ ይሄን ሁሉ ታሪክ አደርገዋለሁ አሉ። ታይቶ የማይታወቅ ብልፅግና አመጣለሁ ብለው ፎከሩ። ፎክረው አልቀሩም። ጠላትና ወዳጅ ያልለየ የቀረጥ ናዳ አዥጎደጎዱ። በሜክሲኮ በካናዳ በአውሮፓ ሕብረት በእንግሊዝ በኢትዮጵያ በሌሴቶ … ማን ቀራቸው።
ካናዳ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነት እሳት ጎርሳ እሳት ለብሳ፤ አራስ ነብር ሆና አሜሪካ ወዳጄ ናት ስል ትራምፕ ከጀርባ ወጉኝ አለች። ለክፉ ቀን ወዳጅ ወሮታው ይሄ አልነበረም አለች። አጸፋዊ ታሪፍ እጥላለሁ አለች። ካናዳውያንም ተቆጡ። ከመንግሥታቸው ጎን ቆሙ። ከአሜሪካ ምርቶች ታቀቡ። የአሜሪካ የሆነውን ሁሉ ቦይኮት አደረጉ። ሜክሲኮም አጸፋዊ ምላሽ እሰጣለሁ አለች። ትራምፕ ግን በአቋማቸው ጸኑ። ቻይና ደግሞ ጭራሽ የማኦን የኮሪያ ጦርነት ወቅት ቅስቀሳ ቪዲዮ አቧራውን አራግፋ እጅ አንሰጥም እያለች ነው። ይህ ቪዲዮ በተጫነ በአጭር ጊዜ ወደ 20 ሚሊዮን ቻይናውያን የምን እጅ መስጠት በሚል መንፈስ ይመስላል ተቀባብለውታል።
ብሔርተኛ ቻይናውያን አሜሪካ 145 በመቶ ታሪፍ ከጣለችብን ምን ሊቀርብን፤ በቃ ታይዋንን እንጠቅልል እያሉ ነው። ለዚህ ይመስላል የMSNBCው ጋዜጠኛ ሎረንስ ከታሪፍ ወደ ጦርነት ብሎ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያለው። አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው እንዲሉ ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ ትራምፕ ከቻይና የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ ሴሚኮንዳክተሮችን፣ ቺፕስ እና የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ከማዕቀብ ነፃ አድርገዋል።
ቻይናም እንደ መንደር ጎረምሳ ማስፈራራት እኔ ላይ አይሠራም። ከንግድ ጦርነት ማንም አትራፊ አይሆንም ካለች በኋላ ከአሜሪካ ወደ ሀገሯ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ 125 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ይህ የቻይና ታሪፍ በተለይ የአሜሪካን ገበሬዎች ክፉኛ ይጎዳል ተብሎ ተሰግቷል። ከዚህ ቀደም ብሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉትን የታሪፍ ጭማሪ ተከትሎ ቻይና ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የ84 በመቶ ታሪፍ መጣሏ አይዘነጋም።
ትራምፕ ይህን አልበቃ ብሏቸው በቻይና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ወደ 145 በመቶ ከፍ ሲያደርጉ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒግ ደግሞ ወደ 125 በመቶ ከፍ አደረጉት። ሁለቱም ኃያላን ለመነጋገር ዝግጁ ነን ቢሉም ማን መታበዩን ኢጎውን አሸንፎ መጀመሪያ ይደውል። ዥንፒንግ እንኳን በዓለም ሁለተኛውን ግዙፉን ኢኮኖሚ ይዘው እና የአሜሪካ ወዳጆች ከትራምፕ ጋር ትከሻ እየተለካኩ ባለበት ድሮም ሰውየው በቀላሉ አይበገሩም።
የትራምፕ ታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካ የሽርክና ወይም የአክሲዮን አልያም የስቶክ ገበያ እንዲዋዥቅ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ከሰባት ትሪሊየን ዶላር በላይ ከስሯል። ለዚህ ነው የትራምፕ ታሪፍ በገዛ ሽጉጥ ራስን ማቁሰል እስከ መባል የደረሰው። ትራምፕ ከገዛ ሕዝባቸውና ከመላው ዓለም የበረታ ተቃውሞ ሲገጥማቸው፤ እቀንሰዋለሁ ያሉት ኑሮ በጣሉት ታሪፍ የተነሳ ሲባባስ ከቻይና በስተቀር የጣልኩትን ታሪፍ ለ90 ቀን አንስቼዋለሁ ቢሉም የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም እንዲሉ ያደረሱትን ጉዳት መመለስ አይችሉም።
ጄፒ ሞርጋንን ጨምሮ በርካቶች የአሜሪካ ኢኮኖሚ እድገቱን አቁሞ መንሸራተቱ አይቀርም እያሉ። ከ1929-39 እኤአ በአሜሪካ የተከሰተው ዓይነት Great Depression አይቀሬ ነው እያሉ እያሟረቱ ነው። ቁጥር አንድ የዓለማችን የውጭ ምንዛሪ መገበያያ እና በየቀኑ በ10 ትሪሊየኖች ክፍያ ይፈጸምበት የነበረው ዶላር እድሜ ለትራምፕ እምነት እንዲታጣበት ሆኗል።
አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላው ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ከፍ በማድረግ እርስ በርስ የታሪፍ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው ለማንም የማይበጅ የንግድ ጦርነት ቀስቅሷል። በአሜሪካና በአውሮፓ መካከል ንፋስ መግባቱን ያስተዋሉት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከትራምፕ ታሪፍ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ኅብረትም ከቻይና ጎን በመቆም የአሜሪካን ምጣኔ ሀብታዊ ማንአለብኝነት “ጭቆና”ን እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።
ጂንፒንግ በፍጹም ልበ ሙሉነትና በራስ መተማመን በድጋሚ ለአሜሪካ እብሪት ሸብረክ አንልም። ሆኖም በንግድ ጦርነት ማንም አሸናፊ አይሆንም ብለዋል። ትራምፕ ግን ከቤይጂንግ ጋር ድርድር በማድረግ “ለሁለቱም ሀገራት የሚጠቅም” ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተስፋ ቢያደርጉም ቤጂንግ ግን የአባ ቢላዋ ልጅ ወይ ፍንክች እያለች ነው።
ይህ የንግድ ጦርነት እየተጋጋለ ሄዶ ከ1930ዎቹ እና ከ2008 የከፋ የምጣኔ ሀብት ድቀት እንዳያስከትል ቢሰጋም፤ አበው የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ መጣሁ መጣሁ እያለ ነው። 60 የሚደርሱ ሀገራት ላይ የተጣለው ቀረጥ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ በሰዓታት ውስጥ ነው ትራምፕ ያልተጠበቀ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ታሪፍ በተጣለባቸው ሀገራት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት ለ90 ቀናት እንዲዘገይ የወሰኑት ይለናል ቢቢሲ።
የትራምፕ ውሳኔ በአስተዳደራቸው እና በመራጮቻቸው መካከል መከፋፈል ፈጥሯል። ከካቢኒ አባላት የተወሰኑት ታሪፉ የመደራደርን አቅም ለማሳደግ የተጣለ ነው ሲሉ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑት ደግሞ የምን ድርድር ታሪፉ የጸና ነው ብለው ነበር። በዚህ ታሪፍ የተነሳ ኤለን መስክ ደስተኛ አለመሆኑን እየገለጸ ነው። አሜሪካና አውሮፓ አይደለም የታሪፍ እሰጥ እገባ ውስጥ መግባት በመሀላቸው ታሪፍ ሊኖር አይገባም። ዜሮ ዜሮ ነው ሊሆን የሚገባው እያለ ነው።
ነገ ተነስተው ትሩዝ ላይ ምን እንደሚሉ ባይታወቅም ትራምፕ ከሀገራቱ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል እና ሁሉም ሀገራት የሚከፍሉት ዝቅተኛ የሆነው 10 በመቶ ቀረጥ ወይም ታሪፍ እንዲቀጥል ወስነዋል። በየሰዓቱ በሚቀያይሩት ውሳኔና አቋም የተነሳ ተገማች እንዳይሆን ከማድረጋቸው ባሻገር አስተዳደራቸው መረጋጋት እንደተሳነው ቀጥሏል። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የትራምፕ ታሪፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ግዙፍ ቀውስ ያመጣ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ወርቅ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ችሏል።
የኢኮኖሚ ተንታኞች እንደሚሉት ቻይና እና አሜሪካ የገፉበት የታሪፍ ጦርነት በሁለቱም ሀገራት ንግድ ላይ መዋዠቅ ከማስከተሉ ባሻገር ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማሻከሩ አይቀርም። ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አጋጣሚውን በመጠቀም ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከሚነቅፉ ሀገራት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው። ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል። በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ካምቦዲያን፣ ቬትናምንና ማሌዢያን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካ የንግድ ዘርፍ ተወካይ ጄሚሰን ግሬር በበኩላቸው “አሜሪካ የንግድ ዘርፉ ውስጥ የተለያዩ አማራጮችን ማማተር አለባት” ብለው ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ መተማመን “አደገኛ ነው” ማለታቸው ቢቢሲ ያወሳል። በሌላ በኩል የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንኮይስ ባርዩ በበኩላቸው ቻይና አሜሪካን በንግድ አጋርነት ልትተካ እንደምትችልና ይህም “አስፈሪ” እንደሆነ ተናግረው፤ የአውሮፓ ኅብረት በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።
በተመሳሳይ ዜና የአየርላንድ የገንዘብ ሚንስትር ፓስካል ዶንሆ “በዓለም ገበያ ለውጥ እያየን ነው” ያሉ ሲሆን፤ ከአውሮፓ ኅብረት የፋይናንስ ሚንስትር ጋር በፖላንድ መዲና ዋርሶ ከተገናኙ በኋላ የአውሮፓ ኅብረትን እና የዩሮን ዋጋ ለማስጠበቅ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል። ባለፉት ቀናት የአሜሪካ ዶላር ዋጋ በገበያው ላይ በሦስት ዓመታት ውስጥ ባልታየ መጠን ቀንሷል። ከሌሎች ሀገራት መገበያያ ገንዘቦች አንጻር ዶላር ዋጋው ቀንሷል።
ትራምፕ የለኮሱት የታሪፍ ጦርነት እነ ቻይና እና ራሽያ ዶላርን በሌላ ዓለም አቀፍ መገበያያ ለመቀየር የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲገፉበት መግፍኤ ሆኗል። ሁለቱ ባለ ግዙፍ ምጣኔ ሀብቶች አሜሪካ እና ቻይና ተፋጠዋል። አሜሪካ የቀሰቀሰችው የንግድ ጦርነት የመቀዛቀዝ ምልክት የሚያሳይ አይመስልም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ በእጥፍ ይጨምራል ብለው ዝተዋል። ትራምፕ ከዛቱ ከሰዓታት በኋላ ቻይና ፍንክች እንደማትል፤ እስከ መጨረሻው ለመታገል ቃል ገብታለች።
ቻይና ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ኮምፒውተሮች፣ ቪዲዮ ጌምን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ለአሜሪካ ትልካለች። ትራምፕ በዚያ ሰሞን እነዚህን ተጨማሪ ታሪፎች ተግባራዊ ለማድረግ እስከ አለፈው ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም ቻይና ከአቋማ ፍንክች አላለችም። ቻይና ጥላው የነበረውን 34 በመቶ ታሪፍ እንድታነሳ ትራምፕ በማስፈራራት ጭምር ቢጠይቁም ቻይና በጀ ባለማለቷ ልዩነቱ እየተካረረ መጥቶ ዛሬ ላይ ደርሷል።
“ቻይና ታሪፉን በብቸኝነት ታነሳለች ብሎ ማሰብ ስህተት ነው” በማለት ‘ዘ ኮንፈረንስ ቦርድ’ በተሰኘው የምርምር ተቋም የቻይና ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አልፍሬዶ ሞንቱፋር ሄሉ ይናገራሉ። ትራምፕ ከመቶ በላይ በሚሆኑ ሀገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ተከትሎ የዓለም አክሲዮን ገበያ አሽቆልቁሏል። በተለይም የእስያ አክሲዮን ገበያ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ በከፋ ሁኔታ የወረደ ሲሆን፤ ማክሰኞ መጋቢት 30/2017 ዓ.ም. በተወሰነ መጠን አገግሟል።
ትራምፕ ከ100 ሀገራት ላይ ታሪፍ ሲጥሉ ሩሲያ ላይ ማዕቀብ አለመጣላቸው እያነጋገረ ነው። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ ቢጥሉም ሩሲያ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም ይለናል ቢቢሲ። ለዚህም ምክንያቱ የባይደን አስተዳደር በሩሲያ ላይ የጣለው የቀደመ ማዕቀብ በመኖሩ ነው የዋይት ሃውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮላይን ሌቪት መናገራቸውን የአሜሪካው ሚዲያ አክሲዮስ ዘግቧል።
ሆኖም ከአሜሪካ ጋር ያነሰ የንግድ ልውውጥ ያላቸው እንደ ሶሪያ ያሉ ሀገራት የትራምፕ ታሪፍ ተጥሎባቸዋል። ሶሪያ በባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ 11 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን መላኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ የተሰኘው ተቋም አስፍሯል። ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ አሜሪካ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ ግን በሩሲያ ላይ እየተከተሉት ያለው ፖሊሲ መሻሻል አሳይቷል። የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ንግግር ጀምረዋል። የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር በቀጠለበት ሰሞኑን አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ፕሬዚዳንት ፑቲንን ለማነጋገር ወደ ሩሲያ ያቀኑ ቢሆንም ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ባለፈው ወር ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተኩስ አቁም ስምምነት ካልተስማሙ የሩስያን ዘይት በሚገዙ ሀገራት ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል በሚል አስጠንቅቀው ነበር።
ሩሲያ በትራምፕ ታሪፍ ዝርዝር ውስጥ ያልገባችው በተጣለባት ማዕቀቦች ምክንያት መሆኑን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ዕለት አጽንኦት ሰጥተው ዘግበዋል።“በሩሲያ ላይ ታሪፍ አልተጣለም፤ ይህ ለየት ያለ ስፍራ ስለተሰጠን አይደለም። ምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ በሀገራችን ላይ ቀድሞውኑ ስለጣሉ ብቻ ነው” ሲል መንግሥታዊው ሮሳያ 24 ቴሌቪዥን ዘግቧል። ሩሲያ በታሪፍ ዝርዝር ውስጥ አለመካተቷ “አብዛኛው ምዕራባውያኑን ያናደደ ነው” ሲልም ነው ሌላኛው መንግሥታዊ ሚዲያ የዘገበው። ሆኖም አሜሪካ በአውሮፓውያኑ በ2024 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከሩሲያ ማስገባቷን ከአሜሪካ የንግድ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አሜሪካ ከሩሲያ በዋነኝነትም ያስገባችው ማዳበሪያ፣ የኒውክሌር ነዳጅ እና ብረቶችን መሆኑንም ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ እና የሩሲያ ሚዲያዎች ሪፖርት አድርገዋል። አንዳንድ የሩሲያ ሚዲያዎች በተለይም በአውሮፓ ላይ የተጣለውን ታሪፍ በምጸትና በመዘባበት ነው የዘገቡት። በሌላ በኩል ዩክሬን ወደ አሜሪካ በምትልካቸው ምርቶቿ ላይ 10 በመቶ ታሪፍ ተጥሎባታል። የዩክሬን ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪደንኮ አዲሱ የአሜሪካ ታሪፍ በአብዛኛው አነስተኛ አምራቾችን ይጎዳል ብለዋል። ዩክሬን የተሻሉ የንግድ ውሎችን ለማሰር ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 ዩክሬን ለአሜሪካ 874 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርቶችን ስትልክ ከአሜሪካ ያስገባችው ደግሞ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ምርቶችን እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ገልጸዋል። “ዩክሬን ለአሜሪካ እንደ ታማኝ አጋር እና ደጋፊ የምትሰጠው ብዙ ነገር አላት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለውም “ ፍትሃዊ ታሪፍ ሁለቱንም ሀገራት ይጠቅማል” ብለዋል። በአሜሪካ እና ዩክሬን መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ አነስተኛ ቢሆንም አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ጦርነት ከፍተኛ የቁሳቁስ ድጋፍ ለዩክሬን አድርጋለች።
ትራምፕ ሀገራቸው ለዩክሬን ያደረገችው ድጋፍ ከ300-350 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሀገሪቱ በአጠቃላይ በአውሮፓ ለምታደርገው ስልጠና እና የመከላከያ ክምችቷን ለመሙላት የፈጀችው 182.8 ቢሊዮን ዶላር ነው ብሏል። አሜሪካ እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ እንዲሁም ጦርነቱ ሰላማዊ እልባት እንዲሰጠው ዩክሬን የከበሩ ማዕድናቷን እንድትሰጣት እየጠየቀች ትገኛለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፍ ብሎ ለመጠቆም እንደተ ሞከረው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን እና አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ቻይና ላይ ከተጣለው 145 በመቶ ታሪፍ ነፃ አድርገዋል። የአሜሪካ ጉምሩክ እና የድንበር ጠባቂ በመግለጫው ላይ እንዳለው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ትራምፕ በአብዛኛዎቹ ሀገራት ላይ ከጣሉት የ10 በመቶ ታሪፍ አይካተቱም።
ይህ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሏቸው ታሪፎች ላይ የታየ ትልቅ ለውጥ ሲሆን፣ ውሳኔውን አንድ የምጣኔ ሀብት ተንታኝ “ማርሽ ቀያሪ የሆነ” ሲሉ ገልጸውታል። ሆኖም በትራምፕ አቋም ርግጠኛ መሆን አልተቻለም። ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ወደ ማያሚ ሲጓዙ፣ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ስለተነሱት ታሪፎች ተጨማሪ ዝርዝሮችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ወደሚሳፈሩት ኤርፎርስ ዋን ልዩ አውሮፕላን እያመሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “በጣም ቁጥብ እንሆናለን። ነገር ግን ብዙ ገንዘብ እያገኘን ነው። እንደ ሀገር ብዙ ገንዘብ እያገኘን ነው” ብለዋል ይህ የፕሬዚዳንቱ ርምጃ የመጣው በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ዋጋ፣ የሚመረቱት ቻይና በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት ማሳደራቸውን ተከትሎ ነው። የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እና መለዋወጫዎቻቸው ከመጋቢት 27 ጀምሮ ከታሪፍ ነፃ እንዲሆኑ ነው የተወሰነው። በዌድቡሽ ሴኩሪቲስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ምርምር ኃላፊ የሆኑት ዳን ኢቭስ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ይህ ለቴክኖሎጂ ባለሀብቶች ያልታሰበ ሲሳይ ነው” ሲሉ ለጥፈዋል።
“ቻይና ላይ የተጣለውን ታሪፍ ስናይ ስማርት ስልኮች እና ቺፕሶች ነፃ እንዲሆኑ መደረጉ ጨዋታ ቀያሪ ለውጥ ነው” ይህንን ውሳኔ ተከትሎ እንደ አፕል፣ ኒቪዲ፣ ማይክሮ ሶፍት እና ሌሎች ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ እፎይታ ይሰማቸዋል ሲሉ አክለዋል። ኋይት ሀውስ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ታሪፍ እንዲነሳ የተደረገው ኩባንያዎች ፋብሪካቸውን ወደ አሜሪካ ለማዘዋወር በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚል ነው ብሏል። የኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት “ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ እንደ ሰሚኮንዳክተሮች፣ ቺፕስ፣ ስማርት ስልኮች እና ላፕቶፖች ያሉ ወሳኝ ቴክኖሎጂዎችን ለማምረት በቻይና ላይ መተማመን እንደማትችል ግልፅ አድርገዋል” ሲሉ በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም