ዳዊት ወልዴ በጃፓን ጊፉ ግማሽ ማራቶን አሸነፈ

በጃፓን ጊፉ ከተማ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ዳዊት ወልዴ አሸንፏል፡፡ የቀድሞው ኦሊምፒያን ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት ውድድር ርቀቱን

1፡00፡06 በሆነ ሰዓት በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ በሴቶች መካከል በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጎይተይቶም ገብረሥላሤ 1:08:29 በሆነ የራሱ ምርጥ ሰአት በሁለተኝነት አጠናቃለች፡፡

በ2012 የለንደንና በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ በ1500 ሜትር ወክሎ በመወዳደር የሚታወቀው የቀድሞ የመካከለኛ ርቀት ኮከብ አትሌት ዳዊት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረቱን በጎዳና ላይ ውድድሮች አዙሯል። በጃፓን ጊፉ ግማሽ ማራቶን ያስመዘገበው ውጤትም ፊቱን ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ካዞረ በኋላ በጉልህ የሚጠቀስለት ነው።

ምቹ በሆነ የአየር ፀባይ በተካሄደው ውድድር ዳዊት ገና ከመጀመሪያ አንስቶ ከበርካታ ኬንያውያን አትሌቶች ጋር ብርቱ ፍልሚያ ገጥሞታል። ከአስር ኪሎ ሜትር በኋላ ግን የ33 ዓመቱ አትሌት ዳዊት ሲቶኒክ ኪፕሮኖ ከተባለው ኬንያዊ አትሌት ጋር ወደ ፊት በመውጣት ፉክክሩ በሁለቱ አትሌቶች መካከል ብቻ ሆኗል። ከ20 ኪሎ ሜትር በኋላ ግን ዳዊት ፍጥነቱን ጨምሮ ተፎካካሪውን በመቁረጥ ፉክክሩን ከሰዓት ጋር አድርጓል። ልዩነቱን በማስፋትም የውድድሩ ፍፃሜ እስከሆነው ናጋራጋዋ ስቴድየም ድረስ ብቻውን ሮጦ የአሸናፊነት ክሩን በጥሷል። “ኪፕሩኖ አስደናቂ ፅናት ነበረው፣ ያም ሆኖ በመጨረሻ ኪሎ ሜትሮች ፍጥነቴን ጨምሬ በመሮጥ በማሸነፌ ተደስቻለሁ” በማለት ባለድሉ አትሌት ከውድድሩ በኋላ አስተያየት ሰጥቷል።

ብርቱ ፉክክር አድርጎ በመጨረሻ ኪሎ ሜትሮች እጅ የሰጠው ኪፕሩኖ በ1:00:13 ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ዬጎን ቪንሰንት 1:01:17 በማጠናቀቅ ሦስተኛ ሆኖ ፈፅሟል።

በሴቶች መካከል የተካሄደው ውድድር በረጅም ርቀት ልምድ ያላቸውና አዳዲስ አትሌቶችን ያፋለመ ነበር። የ21 ዓመቷ ኬንያዊት አትሌት ጃኔት ነይቫና የቀድሞዋ የዓለም ማራቶን ቻምፒዮን ኢትዮጵያዊቷ ጎይተይቶም ገብረሥላሤ ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ ድንቅ ፉክክር አሳይተዋል። ከአስራ ስምንት ኪሎ ሜትር በኋላ ግን ኬንያዊቷ አትሌት ፍጥነቷን ጨምራ 1:07:37 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ያደረጋትን ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሩን ቋጭታለች።

ውድድሩ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እስኪቀሩት በአስደናቂ ፉክክር እንዲታጀብ ያደረገችው የ2022 የዓለም የማራቶን ቻምፒዮን እንዲሁም የ2023 የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጎይተይቶም 1:08:29 በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ባህሬዊቷ አትሌት ዩኒስ ቹምባ በ1:09:07 ሰዓት ሦስተኛ መሆን ችላለች።

በሲድኒ 2000 የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ እና የጊፉ ከተማ ተወላጅ በሆነው ናኦኮ ታካሃሺ የተመሠረተው ይህ በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር በጃፓናውያን ዘንድ አትሌቲክስን የበለጠ ማስተዋወቅን ዓላማው አድርጎ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያ ለአስራአራተኛ ጊዜ ሲከናወንም ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን አፎካክሯል።

የውድድሩ መስራችና ሊቀመንበር የሆነው የቀድሞው ወርቃማ ጃፓናዊ ኦሊምፒያን ናኦኮ ታካሃሺ፣ ተወዳዳሪ በነበርኩባቸው ዘመናት የረጅም ርቀት ሩጫ ፅናትን የሚጠይቅ፣ ለማየት ካልሆነ እየተዝናኑ ለመሮጥ የማይሆን ተደርጎ ይቆጠር ነበር፣ ከ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ በኋላ በሰጠሁት ቃለምልልስ “አዝናኝ 42 ኪሎ ሜትሮች ነበሩ” ማለቴ ግርምት ፈጥሮ ነበር፣ ያኔ ያልኩትን ነገር ዛሬ ሰዎች ተሰባስበው እየሮጡ ሲዝናኑ ስመለከት ደስ ብሎኛል፣ የውድድሩ ዓላማም ፕሮፌሽናልና አማተር ሯጮች በአንድ ላይ ልምድ እየተለዋወጡ የሚዝናኑበትን መድረክ መፍጠር ነው” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

ቦጋለ አበበ

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You