የኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ማነቆ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ዋነኛው የሃይል ማነስ ተጠቃሽ ነው።አዲስ አበባ ዙሪያን ጨምሮ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ደብረ ብርሃን እና ሐዋሳ የሚገኙት የተለያዩ የኢንደስትሪ ልማቶች ወደ ሌሎችም የከተማ መዳረሻዎች እንዲስፋፉ የሐይል አቅርቦትን መጨመር የግድ ነው።በመሰረታዊነት የአገሪቱን የሃይል አቅርቦት አቅም ከሚጨምረው መካከል ደግሞ መጠናቀቁ በጉጉት የሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዋነኛው ነው።
የግድቡ መገንባት አሁን ኢትዮጵያ የምታመርተውን የኤሌክትሪክ ሃይል በ6ሺህ ሜጋዋት በመጨመር መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሥራው በስፋት ከመከናወኑ ጋር ተያይዞ ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመር ከሚችልበት ደረጃ ደርሷል።ይህን ተከትሎ ህዝቡ የግድቡን መገንባት በመደገፍ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ሲሆን፤ አሁንም ባለው አቅም በከፍተኛ መጠን እየደገፈ ይገኛል።
ህዝቡ በገንዘብ የሚያደርገውን ተሳትፎ አንድም ጊዜ ሳያቋርጥ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት መቀጠሉን የሚናገሩት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብረሃም እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት እስከ አለፈው ሰኔ ሰላሳ ድረስ በአጠቃላይ 13 ቢሊየን 679 ሚሊየን ብር ድጋፍ መሰብሰብ ተችሏል።
አቶ ኃይሉ እንዳሉት፤ድጋፉ የተሰበሰበው በቦንድ ግዢ፣ በስጦታ፣ በ8100(A)፣ በቦንድ ሳምንት፣ በሩጫ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እግር ኳስ እና በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ነው።እነዚህ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስገኙት ገቢ ጨምሯል።8100 (A) በመጀመሪያው ዙር 80 ሚሊየን ያስገኘ ሲሆን፤ 130 ሚሊየን የሚጠጋ ገንዘብ ማስገኘት ተችሏል።ዘንድሮ ካለው መነሳሳት ጋር ተያይዞ የሰኔ ወርን ጨምሮ መጋቢት፣ ሚያዚያ፣ ግንቦት እና ሰኔ መጨረሻ ድረስ 29 ሚሊየን 156ሺህ ብር በ8100 (A) መሰብሰብ ተችሏል።በሰኔ ወር ብቻ ደግሞ በቦንድ ግዢ በ8100 (A) እና በስጦታ 87 ሚሊየን 259ሺህ 751 ብር ተሰብስቧል።ይህ በዚህ ዓመት ከተሰበሰበው መካከል ከፍተኛ ነው።በአጠቃላይ በዘንድሮ ዓመት ብቻ 714 ሚሊየን 827ሺህ ብር ተሰብስቧል።ይህም ከሐምሌ 1 ቀን 2011 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ድረስ የተሰበሰበ ነው።
በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ይሰበሰባል የሚል ዕቅድ ቢኖርም፤ በተከሰተው ዓለም አቀፍ የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች አለመካሄዳቸውን ዳይሬክተሩ ይጠቅሳሉ።ከእነዚህ መካከል የቦንድ ሳምንት መጋቢት 15 አካባቢ መዘጋጀት ቢጀምርም፤ ሊገፋበት አልተቻለም።ሌላው የእግር ኳስ እና ሌሎችም የመድረክ ሥራዎች በሙሉ በመቋረጣቸው በእነዚህ በኩል ይገኝ የነበረውን ገንዘብ ማግኘት አልተቻለም ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ሃይሉ ገለፃ፤አሁንም 8100 (A)፣ በቦንድ ግዢ እና በቦንድ ስጦታ ህብረተሰቡ ለመደገፍ ተነሳሽነት እያሳየ ነው።አንዳንድ ሰዎች የልጆቻቸውን ልደት ከማክበር ይልቅ ቦንድ በመግዛት ስጦታ እያበረከቱ መሆኑንም ባሳለፍነው ሳምንት ማየት ተችሏል።
ሌላው የኮቪድ ወረርሽኝ የአለምን የኑሮ ሁኔታ ቀይሮታል።አጠቃላይ ግንኙነቱ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ከባድ ነው።በብዙዎች ህይወት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።ይህ ሁሉ እያለ ግን የግድቡ ድጋፍ ቀጥሏል።በተረፈ ግን ባለሃብቱ የገባውን ቃል ከመጠበቅ አንፃር ክፍተቶች ተስተውሏል።3 ነጥብ 9 ቢሊየን ቃል ገብተው የሰጡት ግን ከአንድ ነጥብ አምስት ብዙም አልራቀም።ያ ማለት ከ50 በመቶ በታች ነው።በእርግጥ ቃል የገቡትን በሙሉ የሰጡ ባለሃብቶች መኖራቸውም መረሳት የለበትም።ነገር ግን የባለሃብቱ ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ለማለት ያስደፍራል ይላሉ።
መከላከያ ሰራዊቱ፣ ፖሊስ እና አጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛው ተሳትፎ ጥሩ ነው።በተለይ መከላከያ እና ፖሊስ ከሚጠበቅባቸው በላይ እየሰጡ ናቸው።እስከ ሰባት እና ስምንት ዙር ደመዛቸውን እየሰጡ ነው።በተጨማሪ በላባቸው እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሲሆን፤ ቀን በሃሩር ሌሊት በቁር ነቅተው እየጠበቁ ነው።
ህብረተሰቡም የሚቻለውን ድጋፍ እያደረገ ነው።በእርግጥ ምንም ድጋፍ ያላደረገ ይኖራል።ነገር ግን ብዙሃኑ ህዝብ በተለያየ መልኩ በስልክ መልዕክትም ሆነ በሎተሪ ብቻ በየትኛውም መልኩ ድጋፍ ያደረገው ሰው ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ይገልፃሉ።
ጉጉቱ ድጋፉን እያከታተለው መሆኑን አቶ ኃይሉ ይጠቅሳሉ።በማይመች ሁኔታ ውስጥም በመሆን በ8100 (A)፣ በቦንድ ስጦታ እና በግዢ በአጠቃላይ መጋቢት፣ ሚያዚያ፣ ግንቦት ላይ 180 ሚሊየን 900ሺህ ብር ተገኝቷል።በሰኔ ብቻ ደግሞ 87 ሚሊየን ብር ተገኝቷል።ኮቪድ እያለ አሁንም ይህን ያህል ድጋፍ ማግኘት መቻሉ እጅግ የሚያበረታታ ነው።በ8100 (A) አንድ ሰው በቀን አንድ ብር ብቻ እንዲደግፍ የሚያግዝ ነው።በ6ወር 20 ሚሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 29 ሚሊየን ብር ማግኘት ተችሏል።
ቀድሞ ለግድቡ ግንባታ የተፈለገው ከ80 ቢሊየን ውስጥ ከ15 እስከ 20 በመቶ ከህዝቡ ይሰበሰባል የሚል ግምት ነበር።አስከአሁን 13 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል።ይህ ማለት ከ15 በመቶ በላይ ነው።ነገር ግን የግድቡ ግንባታ አንደኛ ግዙፍ በመሆኑ ተጨማሪ በጀት ይጠይቃል።ከነበረውም የግንባታ ፍጥነት ጋር ተያይዞ ወደ ኋላ መጓተት ወጪው እንዲጨምር አድርጎታል።አሁን ግድቡ ከ130 እስከ 150 ቢሊየን የሚገመት ሲሆን፤ የህዝቡ ድጋፍም ተያይዞ መጨመር ይኖርበታል ብለዋል።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በክልል ፅህፈት ቤቶችም ድጋፍ የሚሰባሰብ ሲሆን፤ በተያዘው አመት ግን የክልሎች እንቅስቃሴ ብዙም የተነቃቃ አለመሆኑን ይናገራሉ።አንደኛው በኮሮና ምክንያት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ያልተቻለ ሲሆን፤ ሌሎችም ምክንያቶች ያሏቸው አሉ።አንዳንድ ክልሎች በፅህፈት ቤታቸው አንድ ሰው ብቻ ያላቸው ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ የተሟላ የሰው ሃይል አላቸው።
የተሟላ የሰው ሃይል ያላቸው በመጠኑም ቢሆን የተሻለ ሥራ ይሠራሉ።ለምሳሌ በትግራይ እና በደቡብ ክልል ላይ የተሟላ የሰው ሃይል ያለ ሲሆን፤ክልሎቹ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ እና ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው።ኦሮሚያ ላይ ደግሞ በፅህፍት ቤቱ ሁለት ሰው ብቻ የተቀጠረ ሲሆን፤ የሚሰበሰበው ድጋፍም እንደ ደቡብ እና ትግራይ ክልል አመርቂ አይደለም ይላሉ።በብሔራዊ ደረጃ የሚካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራት በክልል ያልተካሄዱበት ሁኔታ አለ።ለምሳሌ በአዲስ አበባ አባይን በህጻናት አንደበት በሚል በ12 ትምህርት ቤቶች አፀደ ህፃናት አንድ ሺህ ተማሪዎች የሚያስደንቅ ትዕይንት አሳይተዋል።ይህ በክልሎች እንዳልተካሄደ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ሃይሉ ገለጻ፤ ምንም እንኳ በክልሎችም በኮቪድ ምክንያት ፕሮግራሞች ሳይካሄዱ ቢቀሩም ግድቡ የደረሰበት ደረጃ በህብረተሰቡ ዘንድ መነሳሳት በመፍጠሩ ድጋፉ ቀጥሏል።ከሶስትዮሽ የድርድር ሂደቱ እና ከውሃ መሙላት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ሙግት እና የተደረሰበት ደረጃ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት ፈጥሯል።ህዝቡ ላይ ከዲፕሎማሲው ጋር ተያይዞ የሶስተኛ ወገን መግባት እና የግብፅ የተባበሩት መንግስታት ጋር መሄድ እጅግ በማስቆጨቱ ማህበረሰቡ ችግር ውስጥ ሆኖ ሳይቀር ድጋፉን እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡
‹‹በራሳችን ወንዝ ለመደራደር ፍቃደኛ ሆነን በእነርሱ በኩል ያለው አካሄድ ፈፅሞ ሉዑላዊነትን እና ሰብአዊነትን ያልጠበቀ አካሄድን መከተላቸው ህዝቡን አስቆጥቶታል።ውሃ አሞላሉ በኛ ፈቃድ ይሁን የሚለው ሙግት እና በገዛ ወንዛችን የመጠቀም መብታችን ላይ የተቃጣው አካሄድ የፈጠረው መነሳሳት የሚናቅ አይደለም፡፡›› ይላሉ።
ይሄ ሁሉ ውሃ ላለበት በክረምት ለሚሞላ ግድብ ግብፅ ንትርክ ውስጥ መግባቷ ህዝቡን ቢያበሳጭም፤መንግስት ለድርድር ቅድሚያ መስጠቱ የሚያስመሰግነው ነው በማለት የሚናገሩት አቶ ሃይሉ፤ ዋናው ጉዳይ ይሄ ቁጭት የፈጠረው መልካም አጋጣሚ ለድጋፍ ማሰባሰብ መጠቀም ቢቻል መልካም መሆኑን ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ኮቪድ ባይኖር እና የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች የሚደረጉበት ሁኔታ ቢኖር፤በፊት እንደሚደረገው በየቦታው ድንኳን እየተተከለ ቦንድ ቢሸጥ፤ እግር ኳሱም ሆነ ሌላ ፕሮግራም ቢካሄድ ከዚህ በላይ ገቢ ማሰባሰብ እና ቦንድ መሸጥ ይቻል ነበር።ያም ሆነ ይህ አሁንም ትልልቅ ተቋማት ቦንድ እየገዙ ነው።ለምሳሌ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአንድ ሚሊየን ብር ቦንድ ገዝቷል።ከግለሰቦች ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የ200ሺህ ብር ስጦታ ሰጥታለች።በላይነህ ዴንሳሞ ከአሜሪካ ሆኖ ለኮሮና 100ሺ ብር ሲሰጥ ለህዳሴው ግድብም 100ሺህ ብር ሰጥቷል። ቤተሰቦችም በህፃናት ስም ለልጆቻቸው ቦንድ እየገዙ ነው።ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች እየተሳተፉ ሲሆን ድጋፉ ቀጥሏል።ነገር ግን እንደበፊቱ ቢቀጥል ከዚህ በላይ ማግኘት ይቻል ነበር።
ሌላው አቶ ሃይሉ እንደተናገሩት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ያለው አዲስ አበባ ነው።ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 35 ሚሊየን ብር ሰብስበዋል።አቃቂ ክፍለ ከተማ እያሰባሰበ ነው፤ እስከ አሁን ወደ 11 ሚሊየን ብር ማሰባሰቡን ይፋ አድርጓል።ስለዚህ በአዲስ አበባ በቀሪዎቹ ክፍለ ከተሞች ዋንጫው ሲዞር ከዚህ የበለጠ ለማሰባሰብ እንደሚቻል ይገመታል።ይህ ሲታይ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገመታል።
ሌላው ፅህፈት ቤቱ በበሽታው ወረርሽኝ ምክንያት ፕሮግራሞችን ማካሄድ ባይችልም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን እየተጠቀመ ነው።ምሁራንን በስፋት በማሳተፍ እየተሰራ ነው።አረብኛ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ለአገራቸው የቆረጡ ሰዎች መሳተፍ ጀምረዋል ካሉ በኋላ ይህም ትልቅ ድጋፍ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
‹‹ግድባችን ከአገር ጉዳይ አልፎ ወደ ዓለም ዓቀፍ መድረክ ሄዷል።አሁን ድርድሩ ተመልሶ በአፍሪካ ደረጃ ነው፡፡›› የሚሉት አቶ ሃይሉ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ የሱዳን እና የግብፅ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአረቡ ዓለም የኢትዮጵያን ትክክለኛነት እና የመጠቀም መብቷን በሚመለከት እንዲያውቁ፤ አረቦችም ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ራሷን ከድህነት ለማላቀቅ ሲሆን ይህም መብቷ መሆኑን ድርጊቷም በግብፅም ሆነ በሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ እንዲረዱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በአረብኛ ውይይት በማካሄድ በአረብ ሚዲያ እየተሞገተ ነው።ይህ በራሱ ትልቅ ድጋፍ ነው።ይህ የአረብኛው ውይይት ሁለት ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ትልቅ ግንዛቤን የፈጠረ ነው።በአፍሪካ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚግባቡ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን ለማስረዳትም ብቁ የሆኑ ተናጋሪዎችም የሚፈለጉ መሆኑን በመጠቆም፤ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ጥሪ ያቀርባሉ።
እንደአቶ ሃይሉ ገለፃ፤ አሁንም ግን ግብፆች የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እየተቀበሉ አይደለም።ትንሽ ሰበብ እየፈለጉ ውይይቶችን እና ድርድሮችን እያፈረሱ ነው።ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ህብረታቸውን እና አንድነታቸውን አጠናክረው መቆም አለባቸው።ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን መቀጠል ይጠበቅባቸዋል።ከወረርሽኝ አንፃር 8100 (A) ከምንም ንክኪ ነፃ በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህ በኩል መልዕክት ቢልክ በየቀኑ 1 ብር ብቻ እየተቆረጠበት ድጋፍ ያደርጋል።
‹‹በግለሰብ ደረጃ አንድ ብር ምንም ማለት አይደለም።ሲጠራቀም ግን ብዙ ነው፡፡›› ካሉ በኋላ፤ 1ሚሊየን 87 ሺህ ዜጎች 29 ሚሊየን ብር መላካቸውን አስታውሰዋል።ይህ ማለት አንድ አንድ ብር ተጠራቅሞ ሲመጣ ትልቅ ብር ይሆናል፤ ስለዚህ በዚህ የሚገኘው ድጋፍ ከፍተኛ ነው።ሞባይል ተጠቃሚ የሆነ በሙሉ አንድ ብር ቢልክ ታሪክ ይሰራል።
የአሁኑ ጦርነት በከባድ መሳሪያ ፊት ለፊት የሚካሄድ ሳይሆን የሃሳብ ጦርነት ነው።በመንፈስ አንድ በመሆኑ ለግድቡ በሞባይል መልዕክት አንድ ብር በመላክ የዜግነት ግዴታን መወጣት ይገባል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ከምንም በላይ ግን ብሔራዊ መግባባቱ፣ ሰላም እና አንድነቱ በራሱ የበለጠ መጠናከር ከቻለ ምንም ነገር እንደማያዳግት እና የግድቡም ግንባታ እውን እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
ምህረት ሞገስ