ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች በብዛት እየተስፋፉ ከመጡባትና ኢንቨስትመንትን በስፋት እየሳበች ካለችው ደብረብርሃን ከተማ ተነስቶ አንኮበር ይዘልቃል።ከአንኮበር በአዋሽ በኩል ወደጂቡቲ ወደብ ከሚወስደው መስመር ጋር በቀጥታ በመገናኘትም የከተማዋን ገቢና ወጪ ምርት ያሳልጣል ተብሎ ተገምቷል።በአንኮበር አካባቢ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ እንደሚያነቃቃውም ታምኖበታል።በልዩ ልዩ ምክንያቶች መዘግየቱ ግን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦውን ወደጥቅም መቀየር እንዳልተቻለ ይነገርለታል – የደብረብርሃን- አንኮበር መንገድ ፕሮጀክት።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደብረብርሃን – አንኮበር መንገድ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክስተት ደጀኔ እንደሚገልፁት፤ 41 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ፕሮጀክቱ 730 ቀናቶች ተይዘውለትና 856 ሚሊዮን ብር በባለስልጣኑ ተመድቦለት እ.ኤ.አ በጥቅምት 23 ቀን 2018 በይፋ ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ባለቤትነት ፣ በሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ ተቋራጭነትና በኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ አማካሪነት እየተከናወነ ይገኛል።የመንገድ ፕሮጀክቱ ስፋት በገጠራማ አካባቢዎች ላይ 10 ሜትር ሲሆን፤ በቀበሌ መቀመጫ ከተሞች ላይ 12 ሜትር ይሰፋል።እንደ ደብረብርሃን ባሉ ትላልቅ ከተሞች ላይ ደግሞ 30 ሜትር ስፋት ይይዛል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት የመንገድ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም 45 ነጥብ 6 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ አራት ወራት ብቻ ይቀሩታል።ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ ከቀሩት ጥቂት ወራቶች አኳያ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል።የመንገድ ፕሮጀክቱ አፈፃፀም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለውም ከዲዛይን ጋር የተያያዙ ለውጦች በመደረጋቸው ሲሆን፤ በተለይ ከመንገዱ 37 ኪሎ ሜትር በኋላ እስከ መንገዱ መጨረሻ ድረስ በአንኮበር ከተማ አካባቢ ህብረተሰቡ የመንገዱ ዲዛይን እንዲቀየር ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩ እየታየ ይገኛል።
ከመንገዱ መነሻ እስከ 37 ኪሎ ሜትር ካለው የአፈር ስራ ውስጥ 50 ከመቶው የሚገኘው ከ37 ኪሎ ሜትር በኋላ ባለው 4 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የመንገዱ ክፍል ውስጥ በመሆኑና ከፍተኛ የስራ ጫና በመኖሩ ነው።በተጨማሪም የአፈር ቆረጣና ሙሌት ስራም በዚሁ የመንገዱ ክፍል ውስጥ በመሆኑ ለመንገድ ፕሮጀክቱ መዘግየት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በሌላ በኩል የመንገዱ ዲዛይን በወቅቱ ሲሰራ የደብረብርሃን ከተማ እምብዛም የሰፋች ባለመሆኗ በገጠር ከተማ ስታንዳርድ በ10 ሜትር ስፋት ነበር።ይህንንም ተከትሎ የከተማዋ ነዋሪ ስፋቱ ወደ 30 ሜትር እንዲሰፋ ጥያቄ በማቅረቡና ይህንኑ ለመቀየርና ዲዛይኑ ተሻሽሎ ርክክብ እስኪደረግ ድረስ ከሰባት ወር በላይ በመፍጀቱ ለመንገድ ፕሮጀክቱ መጓተት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘም ከአቅም በላይ የሆነ አዲስ የካሳ ግምት አዋጅ መምጣቱን ተከትሎ መመሪያው ገና ባለመውጣቱ ገማቹ ቡድን ገምቶ ክፍያውን ለአርሶ አደሮች ከፍሎ ንብረቶቹ የሚነሱበት መንገድ አስቸጋሪ ሆኗል። በዚህም ምክንያት መንገዱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ላይ ያልተነሱ ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ መስመር ማስተላለፊያ ምሰሶዎችና የውሃ መስመሮች ለስራው እንቅፋት በመሆናቸውና በጊዜ ባለመነሳታቸው የመንገድ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቅ አስተጓጉለዋል።
ስራ አስኪያጁ እንደሚገልፁት፤ በአሁኑ ወቅት በኮንትራክተር በኩል የ37 ኪሎ ሜትሩ የመንገድ ክፍል የአፈር ስራ 98 ከመቶ ደርሷል። የወሰን ማስከበር ስራ ካልተሰራባቸው ቦታዎች ውጪ የሰብ ቤዝ /ገረጋንቲ/ ስራዎችም 50 ከመቶ ደርሰዋል።የድሪኔጅ ስትራክቸር ስራዎችም ከከተማ ክልል ውጪ ካሉት በስተቀር አብዛኛዎቹ ተጠናቀዋል።የትቦ ቀበራና የውሃ ማፋሰሻ ስራዎችም አልቀዋል። የአፈር ቆረጣና የሙሌት ስራዎችም እንዲሁ ተከናውነዋል።
እንደኮንትራክተር የዝግጅት ስራዎችም እየተ ከናወኑ ሲሆን፣ የአስፓልት መስሪያ ማሽኖች ተዘጋጅተዋል።ከ40 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የሚሆን ጠጠርም ተፈጭቷል።ለአስፓልት ስራ ካሊብሬሽን ምዘናና ጥራት ማረጋገጫ ለደረጃ መዳቢዎች ባለስልጣን ተሰጥቷል።እነዚሁ ስራዎችን በክረምቱ ወቅት ማጠናቀቅ የሚቻል ከሆነና ከወሰን ማስከበርና ከዲዛይን ጋር በተያያዙ ያሉ ችግሮችን መፍታት ከተቻለ በቀጣዩ ዓመት 37 ኪሎ ሜትር የመንገዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ አስፓልት ይለብሳል።የአንድ ድልድይ ስራም ይጠናቀቃል።ከ37 ኪሎ ሜትር በኋላ ያለው የመንገዱ ክፍል ችግርም በተመሳሳይ ከተፈታ ከነዚሁ ስራዎች ጎን ለጎ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል።በዚሁ መሰረት የመንገድ ፕሮጀክቱ በቀጣዩ ዓመት ሰኔ መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ይደረጋል።
ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት፤ በተያዘለት የኮንትራት ስምምነት መሰረት ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በጥቅምት 21 ቀን 2020 ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል ተብሎ እየተሰራ የሚገኝ ቢሆንም ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ተጓቷል።የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮና አብዛኛዎቹ ስራዎችም የዝግጅት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ተጨማሪ መዘግየቶች ይፈጠራሉ።
ፕሮጀክቱ በኮንትራት ስምምነቱ መሰረት በቀሩት አራት ወራት ውስጥ መጠናቀቅ የሚጠበቅበት ቢሆንም፤ የቤዝ ኮርስ፣ የአስፓልትና የመጨረሻ የአስፓልት ስራዎች ገና የሚቀሩ ከመሆኑ አኳያ በነዚህ ወራቶች ውስጥ መንገዱን አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ ያዳግታል።ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም ተጨማሪ የመስሪያ ቀናት ከአሰሪው በኩል መሰጠቱ አይቀርም።
የደብረብርሃን- አንኮበር የመንገድ ፕሮጀክቱ ትልቅ ኮሪደር መሆኑ የሚነገርለት ሲሆን፤ሀገሪቱ ከጂቡቲ ወደብ በአዋሽ በኩል ነዳጅና ሌሎችም ምርቶች ከምታስገባበት መስመር ጋር የሚገናኝ በመሆኑ የደብረብርሃን ከተማ ኢኮኖሚን ይበልጥ ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከተማዋ የሰሜን ሸዋ ዞን መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ከከተማዋ በመነሳት አንኮበር – ዱለቻ- አዋሽ ድረስ በማገናኘት ወደሌሎች አካባቢዎች ለሚደረገው ጉዞ መንገዱ አጭር አቋራጭ ሆኖ እንደሚያገለግልም ይገመታል።በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴም ያነቃቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
አስናቀ ፀጋዬ