አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና እንደራሴ በነበሩበት ወቅት / ልዑል ተፈሪ መኮንን ሳሉ/ በ1915 ዓ.ም አንድ ዘመናዊ ትምህርት ቤት አስገነብተዋል። ትምህርት ቤቱ ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ተብሎ በስማቸው የተሰየመ ሲሆን፣ ለግንባታው 430 ሺህ ማርትሬዛ ወጪ እንደተደረገበት ይገለፃል።
ለአዳሪዎቹ ተማሪዎች ለመኝታ የሚሆን ባለሦስት ወለል አንድ ትልቅ ህንፃ በ1916 ዓ.ም ተሠራ። በዚያው ዓመት 25 ሄክታር መሬት ተኩል የሆነው የትምህርት ቤቱ ግቢ በድንጋይ ካብ ታጠረ።
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን አውሮፓን ለማየት ሄደው ሲመለሱ የትምህርት ቤቱ ግንባታ በመጠናቀቁ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከአውሮፓ አዘው ማስመጣታቸውም ይነገራል። ግብዓቶቹም በጥር ወር 1917 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ።
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የተማሪ ቤቱን ደንብ 53 አንቀጽ አዘጋጅተው በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ታትሞ በሚያዝያ ወር 1917 ሕዝብ እንዲያውቀው አደረጉ። ተማሪ ቤቱንም ሚኒስትሮች፣ መኳንንትና ወይዛዝርት እንዲሁም ኮር ዲፕሎማቲክና ታላላቅ የውጭ አገር ሰዎች በተገኙበት ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መርቀው ከፈቱ።
ትምህርት ቤቱ ከምኒልክ ትምህርት ቤት በስፋትም የሚበልጥና ዘመናዊም እንደነበር ይነገራል። ይሰጥ የነበረው ትምህርት በአብዛኛው ወደ ፈረንሳይኛ ያዘነበለ ነበር። ለተከታታይ ዓመታትም የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተሮች ፈረንሳውያን የነበሩ ሲሆን፣ ተማሪዎች የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ብቃታቸውን ለማወቅ በየዓመቱ የፈረንሳይ መንግሥትን ፈተና ይወስዱ እንደነበር ይገለፃል።
ትምህርት ይሰጥ የነበረውም በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዝኛ ነበር። ፈረንሳይኛ የሚከታተሉ 124 ተማሪዎች ሲሆኑ፣ እንግሊዝኛ የሚከታተሉ ደግሞ 76 ነበሩ። ይህ የዘለቀው እስከ እ.ኤ.አ 1929 ድረስ እንደሆነም ነው የሚነገረው። አብዛኛዎቹ መምህራን ፈረንሳዮችና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሊባኖሳውያን ነበሩ። የሚሰጡትም የትምህርት አይነቶች ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ዓረብኛ፣ ሂሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ታሪክ፣ ጅምናስቲክና ስፖርት ነበሩ።
በዝቅተኛ ክፍል ደረጃም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በኢትዮጵያውያን መምህራን ይሰጥ እንደነበር ይገለፃል። ሀብት ወይም ብቃት ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች በአዳሪነት ትምህርት ለመማር 9 ማርትሬዛ ይከፍሉ የነበረ ሲሆን፣ የመክፈል አቅሙ የሌላቸው ግን ለምግባቸውና ለማደሪያቸው ሳይከፍሉ በነፃ ይማሩ ነበር።
ንጉሡ የምኒልክ ትምህርት ቤት ተመራቂ ሲሆኑ፣ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት ከፍተኛ ፍልጎት ነበራቸው። ብዙ ተቃውሞ እያጋጠማቸውም ነበር እ.ኤ.አ በ1925 የተፈሪ መኮንን ትምርት ቤትን የከፈቱት ይባላል።
ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ያሠሩት፣ አገራቸው በልጽጋ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ ገና አልጋ ወራሽ እያሉ በራሳቸው የግል ገንዘብ እንደነበር ይነገራል። ‹‹ዘመናዊ ትምህርት በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በአቶ ከበደ ፍሬሰንበት ከተዘጋጀ ሰነድ ነው ጽሁፉን ያቀናበርነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
አስቴር ኤልያስ