ከተሜነት ሲባል በመጀመሪያው ፊት ለፊት የሚመጣው የቤቶች ግንባታ ጉዳይ መሆኑን በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበበ ይናገራሉ። ለዚህ በምክንያትነት የሚያስቀምጡት ባዶ ከተማ፣ ከተማ ሊባል አይችልም የሚለውን ነው። ስለዚህም በከተማ ውስጥ የሚኖረው ሰው የግድ መጠለያ የሚያስፈልገው እንደሆነ ያመለክታሉ።
እንደ ኢትዮጵያ የከተሜነት ደረጃ ወደ 22 በመቶ አካባቢ ነው። ይህ ከአፍሪካ በጣም ዝቅተኛ የከተማ ደረጃ መሆኑን አመላካች ነው። ነገር ግን የከተሜነት ምጣኔው በየዓመቱ 5 ነጥብ 4 በመቶ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ የሕዝብ ፍልሰት በዋናነት ሦስት መሠረታዊ ምንጮች አሉት። የመጀመሪያ ከገጠር ወደከተማ የሚፈልሰው ነዋሪ፣ ሁለተኛ የከተማ ነዋሪው በራሱ በውልደት ምጣኔ መጨመር፣ ሦስተኛ ደግሞ ትንንሽ መንደር የሚባሉት አካባቢዎች በፍጥነት ወደከተማነት እየተቀየሩ መሆናቸው ነው። ስለዚህ የከተሜነት መስፋፋትን በጣም ፈጣን የሚያደርጉት በዋናነት እነዚህ ሦስቱ ናቸው።
የከተሜነት መስፋት ችግር ብቻ ሳይሆን ዕድልም ነው፤ ነገር ግን በአግባቡ ካልተመራ ችግር ነው። በደንብ ካለመመራቱ የተነሳ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ የመኖሪያ ቤት ችግር ነው። የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የነበሯት መንግሥታት የተለያዩ የየራሳቸው የቤት ልማት መርሃግብር እንዳላቸውም ነው የሚነገረው።
የቅርቡን ለማስታወስ ያህል የተጀመረ የቤቶች ልማት መርሃግብር አለ፤ ይህም የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም የሚባለው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ያለ ነው። ከዛ በፊት በርካታ መርሃግብሮች እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ማህበራትን በማደራጀት በርካታ ሰዎች የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል። ከዛ ቀደም ሲልም በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንዲሁ የተገነቡ ቤቶች እንዳሉ ይታወቃል።
አቶ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ በቅርቡ በቤቶች ልማት መንግሥት በስፋት ሄዶበታል። መርሃግብሩ በአዲስ አበባ በተለይ የተቀናጀ የቤቶች ልማት መርሃግብር የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ የሚባለው በ1996 ዓ.ም ተጀምሮ ወደየክልሎች እንዲሰፋ የተደረገው ነው። ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት ብቻ እስካሁን ባለው መረጃ ከ400 ሺህ ቤቶች በላይ ተገንብቷል፤ ከእነዚህ ውስጥ ግማሹ የተላለፈ ገሚሱም በግንባታ ላይ ያለ ነው።
ይህ መርሃግብር በክልል ደረጃ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ቆሟል። ሲቆምም በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው። ለዚህ ምክንያቱ በክልል ከተሞች ያለው የቤት ፍላጎትና በተለይ ለጋራ መኖሪያ ቤት ያለው ፍላጎትና በአገሪቱ ደግሞ በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ያለው የመኖር ባህል በወቅቱ ሰዎች ፍላጎት ባለማሳየታቸው ነው። ሁለተኛ በአፈፃፀም በግንባታ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች፣ የፋይናንስ አጠቃቀምና አጠቃላይ ሂደቱ በክልሎች አዋጭነቱ ላይ ጥያቄ ስላስነሳ ነው። ስለሆነም ግንባታው በክልሎች እንዲቆም ተደርጓል። ይህ በመንግሥት ቀርቶ በተለያዩ ማህበራትና በግለሰቦች እንዲቀጥል ነው የተደረገው።
በአዲስ አበባ የቤት ችግሩ በጣም ከፍ ያለ ስለሆነ መርሃግብሩ እንዲቀጥል ተደርጓል። በሥራ ላይ ያሉ ስምንት አማራጮችን የያዘ አለ። ከእነዚህም መካከል በመንግሥት 10/90፣ 20/80 እና 40/60 የሚባሉ መርሃግብች ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ በግለሰቦች፣ በማህበራት፣ በመንግሥትና የግል አጋርነት እና ሌሎችም መርሃግብሮች ናቸው፤ ለዚህ ደግሞ በመተግበር ላይ ያለ ስትራቴጂ አለ፤ ይህ ስትራቴጂ አተገባበሩ በጥናት ተፈትሾ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ተገኝተዋል። ስለዚህ መንግሥት ወደሚቀጥለው የዜጎችን ችግር ከመሠረቱ ለመቅረፍ ጥናት አድርጎ ስትራቴጂውን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የቤቶች ልማት መርሃግብር ሪፎርም ያስፈልገዋል ተብሎ ዕቅድ ተይዞ በጥናት ከተለየ በኋላ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን (4 ሚሊየን 4 መቶ ሺህ አንድ መቶ ነው) ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል። ማለትም ይህ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት ሲገነባ አንደኛ በአገሪቱ ባሉት ሁሉም ከተሞች ነው።
የተጠቀሰውን ያህል ቤት ለመገንባት ሲታሰብ የራሱ የሆነ ዳራ መነሻ በማድረግ ሲሆን፣ ይህም ሦስት ምንጭ አለው። አንደኛ አሁን ያለው የቤት ብዛትና የህዝብ ብዛት ሲታይ ልዩነት አለው። ልዩነት ሲሰላ አንድ ሚሊየን አካባቢ ቤቶች እጥረት ያሳያል። በከተሞች ያለው ቤትና በከተማው ያለው አባወራ ብዛት ሲነፃፀር የአንድ ሚሊየን ልዩነት አለው።
ሁለተኛው ደግሞ አብዛኞቹ ከተሞች ያረጁ ናቸው። ጥናቶች የሚያሳዩት 74 በመቶ የሚሆን ቤት ከደረጃ በታች ነው። ከዚሁ ከ74 በመቶ ውስጥ ደግሞ 34 በመቶ ሙሉ ለሙሉ መታደስና መሻሻል ያለባቸው ናቸው። እነዚህን ቤቶች ወደ አንድ ሚሊየን አካባቢ መሻሻል ያለበት ቤት ነው ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ሚሊየን ቤት እንደ አዲስ የሚሆን ይኖራል እንደማለት ነው።
ሦስተኛው ምንጭ ከተሜነት ያለበት ደረጃ 22 በመቶ ላይ ነው። ጥናቱ እንደሚያመለክተው በቀጣይ አሥር ዓመት ውስጥ ወደ 35 በመቶ ያድጋሉ። ይህ ከሆነ የከተሜነት ምጣኔው የቤት ፍላጎት በሦስት ሚሊየን አካባቢ ይጨምራል። በጥቅሉ የተፈለገው ወደ አምስት ሚሊየን ቤት ነው። ይህ ተጨማሪ ቤት ለከተማ ነዋሪው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
አቶ ታደሰ እንደሚሉት፤ አምስት ሚሊየኑን ቤት በአሥር ዓመት ማጠቃለል አይቻልም። ቢያንስ ግን የዕቅዱን 80 በመቶ መሥራት ቢቻል ሲሰላ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ይሆናል ማለት ነው። ይህንን አሁን ካለው ነገር ጋር ለማነፃፀር ተሞክሯል።
አሁን ያለው የቤት አቅርቦት በመቶኛ ሲሰላ ወደ 64 አካባቢ ነው። እንዲህ ሲባል በቂ የመሠረተ ልማት ያለው ቤት ለማለት ነው። ይህን ግን ወደ 80 በመቶ ማሳደግ ያስፈልጋል። ወደ 80 ለማሳግ ደግሞ እንደተባለው 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት ያስፈልጋል ይላሉ።
ይህ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት በማን? መቼ? ይገነባል ወደሚለው ሲመጣ፤ በብዙ ክፍል ለማስቀመጥ ተሞክሯል። የመጀመሪያው በመንግሥት የሚገነቡ ቤቶች በሚል የተለየ ሲሆን፣ በመንግሥት ተጨማሪ ቤቶች ይገነባሉ ማለት ነው። በጥቅሉ የመንግሥት ሚና እና የግል ሚና የሚባል ነገር አለ። የመንግሥት ሚና ከዚህ በኋላ እየቀነሰ እንደሚሄድ በመንግሥትም አቅጣጫ ተቀምጧል፤ ስትራቴጂውም የሚያሳየው ያንኑ ነው። የመንግሥት ድርሻ እየቀነሰ የግለሰቦች ድርሻ እየጨመረ መሄድ አለበት።
የመንግሥት ሚና 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ከሚገነቡ ቤቶች ውስጥ 20 በመቶውን ብቻ ነው። በዚህ ውስጥ 10/90፣ 20/80 እንዲሁም 40/60 ግንባታቸው ይቀጥላል። 10/90 አዲስ አበባ ላይ ቆሞ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን በጥናት በመለየቱ ይቀጥላል። ቀሪዎቹ በፊትም ያሉና አሁንም የሚቀጥሉ ይሆናሉ።
እንደ አዲስ የተጨመረው የኪራይ ቤቶች በስፋት የሚገነቡ መሆናቸው ነው። ስለሆነም በተቻለ መጠን ሰዎች በገቢ ልካቸው ሊከራዩ የሚችሉ ቤቶችን መንግሥት መገንባት አለበት። መንግሥት ለኪራይ የሚያቀርባቸው ቤቶች በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን ብቻ ነው። ስለሆነም የኪራይ ቤቶች በስፋት መገንባት አለባቸው በሚል በመንግሥት የሚገነቡ ቤቶችን ወደ አራት ደረጃ ከፋፍለናል ሲሉ ይናገራሉ።
ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የማህበራት ቤቶች የሚባለው ነው። ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የሚገነቡት ቤት ይገነባል ተብሎ ከተያዘው ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቤት 35 በመቶ ያህሉን ነው። በግሰቦች አሊያም በማህበራት ለሚገነባው ቤት መንግሥት የማደራጀትና መሬት የማቅረብ ድጋፍ ያደርጋል።
በሦስተኛ ደረጃ የግለሰቦች ቤት ሲሆን፣ ግለሰቦች በራሳቸው ነባር ይዞታ ላይ ወይም መንግሥት በሚያወጣው የሊዝ ጨረታ ላይ ተሳትፈው ቤቶችን መገንባት እንዲችሉ አቅጣጫ ተቀምጧል። በእነሱ እንዲገነባ በዕቅድ የተያዘው የቤት መጠን ደግሞ ወደ 15 በመቶ ያህል ነው።
በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው አማራጭ በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚገነባው ቤት ሲሆን፣ እንዲህም ሲባል መንግሥት የተወሰነ ያመጣል፤ ግለሰቦችም እንዲሁ። በዚህም 15 በመቶ ያህል የሚገነባ ይሆናል።
አምስተኛው አማራጭ ሪልስቴት ሲሆን፣ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ በስፋት እንዲገነቡ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል። በዚህም የሚገነባው 10 በመቶ ያህሉ ይሆናል።
ሪል ስቴትን ለመደገፍ አዋጅ እያዘጋጀን ነው ያሉት አቶ ታደሰ፣ ሪልስቴት እንዴት ይገነባል? ምን ይሠራል? እንዴት ይመዘገባል? እንዴትስ ፈቃድ ይወስዳል? የገንዘብ ምንጩንስ እንዴት ያገኛል? የሚሉ ነገሮች በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል ብለዋል።
ሌላው በመንግሥትና በግል ባለሀብቱ (ፒፒፒ)ም ቅድመ አዋጭ ጥናት ተጠንቶ ፀድቋል። ሚኒስቴሩ ዝርዝር ጥናት እንዲያጠና አቅጣጫ ተሰጥቶ እየተጠና ነው።
ሌላው አማራጭ በግሉ ዘርፍ የሚመደብ በሽርክና የሚሠራ ሲሆን፣ ግለሰብን ከግለሰብ ጋር በመሻረክ የሚሠራው የቤት ግንባታ ነው። ስለዚህ በመንግሥት ብቻ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት ሊመጣ አይችልም። በመሆኑም ነው በዝርዝር በስትራቴጂው የተቀመጠው። ስትራቴጂው በሚኒስቴሩ ደረጃ ውይይት ተካሂዶበት የፀድቀ ሲሆን፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲያፀድቁት ተልኳል።
በቀጣዩ ክፍል ቤቶቹ የሚገነቡባቸውን ቦታዎችና የቤት ግንባታው ስለሚከተለው ቅይጥ የቤት ልማት መርሃግብርና የሚከተለውን ስልት የተመለከተ ጽሁፍ ይዘን እንቀርባለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
አስቴር ኤልያስ