መንደርደሪያ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የዓባይ ጉዳይ ዛሬም በሞቅታ ላይ ነው። በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ የግድቡ ጉዳይ ዓይነተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከምድሯ በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ዕለት አንስቶ ግብጽና በዙሪያዋ ያሉ ደጋፊዎቿ ሁሉ የተለያዩ የተቃውሞና የውግዘት ናዳዎችን በኢትዮጵያ ላይ ሲወረውሩ ኖረዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ከዜጎቿ መቀነት በሚዋጣ ገንዘብ በራሷ አቅም ብቻ ግድቡን በመገንባት ዛሬ ላይ ወደአዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጋለች። ግድቡም ግንባታው ከ73 በመቶ በላይ በመድረሱ ውሃ በመያዝ የተወሰነ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ታሪካዊ ጊዜ ላይ ደርሷል።
ግብጽ ታዲያ ግድቡ ወደወሳኙ ምዕራፍ እንዳይሸጋገር እንደወትሮዋ የማጥላላትና የማደናቀፍ ዘመቻዋን ቀጥላለች። በግብጻውያን በኩል በዓባይ ወንዝ ላይ በመሪዎች፣ በምሁራንና በሕዝቡ ዘንድ አስገራሚ የሃሳብ አንድነትና መግባባት አለ።
ይህ ብሄራዊ ጥቅማችን ነው ላሉት ጉዳይ እንደአንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የያዙት የሃሳብ አንድነት እንዲሁ በአንድ ጀንበር የተገነባ አይደለም። ይልቁንም የዓባይ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ተጠቃሚዎች እነርሱ ብቻ ስለመሆናቸው ለሺዎች ዓመታት ሲወርድ ሲዋረድ በጽኑ የተገነባ ጠንካራ ግን ደግሞ የተሳሳተ ዕምነት ስላላቸው ነው።
በኢትዮጵያ በኩል ያለው ደግሞ ከግብጻውያን ፍጹም በተቃራኒው ነው። ዓባይ ከምድራችን ቢፈልቅም ተጠቅመንበት አናውቅም። በዘፈን እያሞጋገስን ወደ ሱዳንና ግብጽ አሻግረን ከመላክ በስተቀር ወንዙን እንደወሳኝ የሕዳሴያችን ዋልታ ሳንመለከተው ኖረናል።
ያም ሆኖ ግድቡ መገንባት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ያለው አመለካከትና የተግባር ድጋፍ አዲስ ገጽታን የተላበሰ ነው። ዓባይን የብልጽግናችን ሁነኛ መፍትሄ አድርገን ወደማመን ተሸጋግረናል። አሁን አሁን ደግሞ ዓባይ የሕልውናችን መሰረት ስለመሆኑም ወደማመን እየተሸጋገርን ነው።
እናም ይህ አመለካከት በእውነተኛ መረጃዎች ተመስርቶ ጠንካራ እንዲሆንና ለትውልድ እንዲሸጋገር በዓባይ ዙሪያ ጠቃሚ መረጃዎችን ለሕዝብ በማቀበል ማንቃት ያስፈልጋል። የዚህ ጽሁፍ መሰናዳት ዓላማውም ይኸው ነው።
ናይል የ11ዱም አገራት ሃብት ነው!
“ዓባይ” የሚለው ቃል የጥንት የኢትዮጵያውያን የሥልጡንነት ቋንቋ ከሆነው ከግዕዝ ቋንቋ የተገኘ ቃል ነው። ትርጓሜውም ታላቅ እንደማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ለወንዙ ይህንን ስም መስጠታቸውም የወንዙን ታላቅነት ስለሚገልጽ ትክክለኛ ስያሜ ነው – የወንዞች ሁሉ ቁንጮ፣ የምድራችንም ረዥሙ ወንዝ ነዋ።
የኢትዮጵያን ለም አፈር ተሸክሞ በጣና ሐይቅ ላይ የሚጋልበው ወንዝ ጥቁር ዓባይ ነው። ጥቁር ዓባይ ከኢትዮጵያ ፈልቆ ሱዳን ከደረሰ በኋላ መዲናዋ ካርቱም ላይ ከዩጋንዳ ሌክ ቪክቶሪያ ከሚመነጨው ወንድሙ ነጭ ዓባይ ጋር ይቀላቀላል።
ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ መላው ዓለም የኢትዮጵያን ወንዝ ስሙን ለውጠው ናይል ይሉታል። እሱም ለሱዳን ገጸ-በረከቱን ሰጥቶ በረሃማዋን ግብጽን አቀዝቅዞ ወደ ሜዲትራንያን ባህር ይገባል።
ናይል በ11 የተፋሰሱ አገሮች ለሚኖሩ ከ280 ለሚልቁ ሕዝቦች የኑሮ ዋልታና ማገር ነው። ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ከ85 በመቶ የሚልቅ የውሃ መዋጮ አላት። ከ110 ሚሊዮን ከሚበልጠው ሕዝቧም ግማሽ ያክሉ በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ ይኖራል፤ ቢሆንም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሕልውና መሰረት ነው ዓባይ።
ግብጽና ሱዳን ለወንዙ እፍኝ የውሃ አስተዋጽኦ የላቸውም። ያም ሆኖ የግብጽ ሕዝብ በሙሉ፤ የሱዳንም እንዲሁ ከ90 በመቶ የሚልቀው ሕዝብ የኑሮውን መሰረት በዓባይ ላይ ያደረገ ነው።
ዑጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ሩዋንዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል የሚችለው ሕዝባቸው የናይልን ተፋሰስ ተከትሎ ይኖራል። ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ብሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ኤርትራም ሳይቀር ወሳኝ ቁጥር ያለው ሕዝባቸው የናይልን ወንዝ ተከትሎ ነው የሚኖረው።
ይሁንና ወንዙን በብቸኝነት ሊባል በሚችል መልኩ ከምትጠቀመው ግብጽ እና በግብጽ መልካም ፈቃድ የሹካ ያክል ከወንዙ ፉት ከምትለው ሱዳን በስተቀር ሌሎቹ አገራት በወንዙ አልተጠቀሙበትም።
የዚህ ኢፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መሰረታዊ መነሻው ድህነት የወለደው የአገራቱ የአቅም ማጣት ቢሆነም ቅሉ የግብጽ ስግብግብነትና መሰሪነት ደግሞ የተፈጥሮ ሃብቱን ከግብጽ በስተቀር ቀሪው ከ200 ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ የበይ ተመልካች እንዲሆን አድርጎታል።
ዓባይ ለግብጽ
የግብጽ የሥልጣኔ መነሻ የዓባይ ወንዝ ነው። ዛሬም 99 በመቶ ለሚሆነው የግብጽ ሕዝብ የኑሮ መሰረትና የውሃ ምንጫቸው ዓባይ ነው።
ግብጽ በበረሃማው ምድሯ ላይ የአስዋን ግድብን ገንብታለች። ግድቡ 162 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ አዝሎ 2100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ነው የሚያመነጨው። ያም ሆኖ አገሪቱ ከአስዋንና ከሌሎች የዓባይ ላይ ግድቦቿም ሆነ ከሌሎች አማራጭ የኃይል ምንጮቿ በአጠቃላይ 98 በመቶ ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ነው።
በአስዋን ግድብ ምክንያት በበረሃው ምድር ላይ የተዘረጋው የናስር ሐይቅ ደግሞ ለግብጽ ሕዝብ የትራንስፖርትና የቱሪዝም እንዲሁም የአሳ ሃብት ምንጭ ነው። በመስኖ የሚለማው የግብርና ሥራ ደግሞ የአገሪቱ የምግብ ዋስትናን አረጋግጧል።
ዓባይ ከኢትዮጵያ ለም ምድር ጠራርጎ በማጓዝ በግብጽ አሸዋማ መሬት ላይ በሚያስተኛው ደለል ግብጻውያን ከፍተኛ የሩዝና የስንዴ ምርት ያፍሳሉ። በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም ስመ-ጥር ናት ግብጽ።
ከራሷ ተርፋም ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደውጭ አገራት በመላክ ረብጣ ዶላሮችን ታፍሳለች። (እኔም ከወራት በፊት ለሥራ ጉዳይ ጅግጅጋ ከተማ በሰነበትኩበት ወቅት የግብጽ ብርቱካን በኮንትሮባንድ ገብቶ ሕዝብ እየተረባረበ ሲሸምተው ተመልክቼ በሃፍረት ልቤ መሰበሩን አልዘነጋውም።)
በግብጽ ዝናብ የለም ማለት ይቻላል። አገር ምድሩም በረሃማ ነው። በዚሁ መነሻ ከአስዋን ግድብ ላይ በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በላይ በትነት ይባክናል።
በዚህ ላይ ደግሞ የግብጽ ገበሬዎች የውሃ አጠቃቀም ከፍተኛ ብክነት እንዳለበት ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይም ውሃ-መጣጭ የሆኑትን እንደ ሩዝና ጥጥ ያሉ ሰብሎችን በስፋት ስለሚያመርቱ ግብጻውያን ዓባይን እንደፈለጋቸው ማባከኑን ለሺህ ዘመናት ተለማምደውታል።
እንዲህም ሆኖ ግብጽ የኢትዮጵያውያንን እና የሌሎቹን በድህነት የሚማቅቁትን የተፋሰሱን አገሮች ከድህነት የመላቀቅና የመልማት መብት ወደ ጎን በመተው አገራቱ ወንዙን እንዳይጠቀሙና የውሃ ድርሻዋ እንዳይቀንስ ነው የምትታገለው። የአስዋን ግድቧ የውሃ መጠንም እንዲቀንስባት አትሻም።
ይሁንና የግብጽን ስግብግብ አካሄድ የሚቃወሙና የእነ ኢትዮጵያን የመልማት መብት የሚደግፉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግብጽ በተለይም በሕዳሴው ግድብ መገንባት የከፋ እንደማይደርስባት ነው። ኢትዮጵያም ግብጽና ሱዳንን የሚጎዳ አድራጎት እንደማትፈጽም እሙን ነው።
ግብጽ እንደዓይን ብሌን የምትሳሳለት የአስዋን ግድብ 162 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ተሸክሞ ውሃውን ለበረሃ ትነት እያጋለጥ ያችን ታክል ኃይል ያመነጫል። ግብጽ ታዲያ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት መጠኑ ይቀንስብኛል ብትልም ቅሉ ከፍተኛ የሆነ የውሃ መቀነስ እንደማይኖረውና እንደውም የህዳሴ ግድብ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት ስለሚልክለት ደህንነቱ እንዲጠበቅ እንደሚያደርግለት ነው የቴክኒክ ጥናቶች የሚያሳዩት።
ያውም ቢሆን የአስዋን ግድብ መጠኑ ዝቅ ብሎ እስከ 131 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ እንኳ አሁን የሚሰጠውን ጥቅም አሳምሮ መስጠቱን እንደሚቀጥል ነው ጥናቶች የሚያረጋግጡት።
እናም ግብጽ ለዘመናት በብቸኝነት የያዘችው ያልተገባ የውሃ መጠን በሌሎች የወንዙ ተፈጥሯዊ የጋራ ባለቤቶች ጥቅም ላይ ሲውል መቃወሟ ከስግብግብነት ውጪ ሌላ ስያሜ ሊሰጠው አይችልም።
ዓባይ ለኢትዮጵያ
85 በመቶ የሚሆነው የናይል ወንዝ ምንጭ የሆነው የጥቁር ዓባይ መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ ወንዙን አለመጠቀሟ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው።
አገራችን የበርካታ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አካላት ባለቤት በመሆኗ የአፍሪካ የውሃ ማማ መሰኘቷ እንደተጠበቀ ሆኖ 70 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የውሃ አቅም የተመሰረተው በዓባይና በገባሮቹ ላይ ነው።
ይሁንና 110 ሚሊዮን ከሚጠጋው ሕዝቧ ከ40 በመቶ በታች የሚሆነው ነው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆነው። እናቶቻችን ዛሬም እንደትናንቱ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት የተነሳ የማገዶ እንጨት በመሸከም ጀርባቸው ተልጧል። የእንጨት ጭስ የዓይናቸው የቀን ከሌት ምግብ ነው። በአንጻሩ ግብጽ አሁን ኢትዮጵያ ካላት የኤሌክትሪክ አቅም በ15 እጥፍ ስለምትጠቀም መላ ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ነው።
ኢትዮጵያ ከዚህ አስከፊ ድህነት ለመላቀቅ ታዲያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ታዳሽ የኃይል ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ ውስጥ ግንባር ቀደሙ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ነው።
75 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመያዝ 6500 ሜጋ ዋት ገደማ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም የሚኖረው የሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በውጤታማነትና በግዙፍነቱ ከአፍሪካ አንደኛው ይሆናል።
ከፍተኛ ትነት ባለበት የግብጽ በረሃ ከተገነባውና 162 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የሆነ ግዙፍ ውሃ አዝሎ 2100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ከሚያመነጨው የአስዋን ግድብ ጋር ሲነጻጸር በአነስተኛ ውሃ ያውም በጉባ ተራራማ ስፍራዎች የሚገነባው የሕዳሴ ግድብ የቱን ያክል ውጤታማ ግድብ መረዳት ይቻላል።
በሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ፍላጎቷን በከፍተኛ መጠን እንደምታሳድግ ይጠበቃል። ከራሷ ፍላጎት ተርፎ ለጎረቤቶች ከምትሸጠው ኤሌክትሪክ በየዓመቱ ከ580 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታገኝ ተስፋ ተጥሎበታል። በዚህ የተነሳ ሌሎቹም የተፋሰሱ አገራት ከልማቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው።
በግድቡ የተፈጠረውና የሚፈጠረው የሥራ ዕድል፣ የቱሪዝም አቅም እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከፍተኛ ነው። የዓለም የኃይድሮ ፓወር የልሕቀት ማዕከል ወደመሆንም ይሸጋገራል።
የቅኝ ግዛት ስምምነት ተብዬዎቹ
ግብጽ ያለአንዳች ሀፍረትና መሸማቀቅ ዛሬም ድረስ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን እያጣቀሰች የውሃው ብቸኛ ተጠቃሚ እኔ ነኝ ትላለች። ነገር ግን ስምምነቶቹን መሰረት አድርጎ መሟገት ከዓለም አቀፍ መርሆዎች አንጻር ተቀባይነት የለውም። አመክንዮውን እንመልከተው…
ጊዜው 1929 ዓ.ም. እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ነው። የዛሬዋ “እዚህ ግቢ” የማትባል አገር እንግሊዝ ያኔ በከፍታ ማማ ላይ ሆና ዓለምን በሞላ በቅኝ ቁጥጥሯ ሥር አድርጋ “በእንግሊዝ ምድር ጸሀይ አትጠልቅም” የተባለላት ዘመን ነበር።
ያኔ ታዲያ እንግሊዝ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ነጻዋን ኢትዮጵያን ሳይጨምር ሌሎችን የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የቅኝ ግዛቶቿ አድርጋ ነበር። በዚህ ወቅት ነበር እንግሊዝ አሳፋሪም አስቂኝም ሥራ በዓባይ ላይ የሰራችው።
በአንድ በኩል ግብጽ (ነጻ አገር ሳትሆን እንደነጻ ተቆጥራ) በሌላ ጎን ደግሞ እንግሊዝ የናይል ውሃ ስምምነትን ተፈራረሙ። በወቅቱ እንግሊዝ ሱዳንን፣ ዑጋንዳን፣ ኬንያንና ታንዛንያን (የያኔዋን ታንጋኒካን) ወክላ ነበር ከግብጽ ጋር ስምምነት ፈረምኩ ያለችው።
በዚህ ስምምነት ተብዬ ውል መሰረት ግብጽ ብቸኛዋ የናይል ውሃ ተጠቃሚ የመሆን መብቷ ተረጋግጦ በደማቁ ሰፈረላት። ይባስ ብሎም በሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች በናይል ላይ በሚሰሩ የእርሻ ልማቶች ላይ “ቬቶ ፓዎር” ተጎናጸፈች። ያለእሷ ፈቃድና ይሁንታ ሌሎቹ አገሮች ናይልን በእፍኛቸው እንኳ እንዳይነኩት ተከለከሉ።
ነገር ግን ይህ ስምምነት በሁለት የዓለም አቀፍ መርሆዎች መሰረት እንደስምምነት ሊቆጠር የማይችል ሰነድ ነው። የመጀመሪያው ግብጽም ሆነች ሌሎቹ አገሮች ነጻ አገራት ሆነው በፈቃዳቸው የተፈራረሙት አልነበረም።
ይልቁንም እንግሊዝ የቅኝ ግዛቶቿን ወክያለሁ በማለት ያደረገችው በመሆኑ በተለይም ዛሬ ባሉት ነጻ ሕዝቦችና አገራት ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የለውም። ግብጽ የእንግሊዝ ቅኝ አገር ስለነበረች እንግሊዝ ለይስሙላ በሌሎቹ አገሮች ጎን ቆማ ከግብጽ ጋር አደረገችው የተባለ ስምምነት ቢሆንም እውነታው ግን ኢንግሊዝ ከእንግሊዝ ጋር ያደረገችው የቅኝ ግዛት ዘመን የመሰሪነት ማሳያ የሆነ ሕገ-ወጥ ስምምነት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ስምምነቱ ከምንም በላይ የውሃው 85 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያን ያገለለና ምንም ያልተሳተፈችበት በመሆኑ የቅኝ ገዥዎችን የአግላይነት ፖሊሲ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ውዴታም ሆነ ፈቃዷ የሌለበት በመሆኑ በምንም ተዓምር የማትገደድበት ስምምነት ነው።
ከዚህም ባሻገር ተንኮታኩቶ ከተቀበረው ቅኝ ግዛት ጋር ለዘለዓለም መቀመቅ መውረድ የሚገባው ሰነድ ሆኖ ሳለ ጥቁር-ጠል የሆነችው ግብጽ ግን ዛሬም ድረስ ይህንን አሳፋሪ ስምምት እየጠቀሰች የውሃው ታሪካዊና ሕጋዊ ተጠቃሚ ስለመሆኗ ታላዝናለች።
ሁለተኛው ስምምነት እ.ኤ.አ. የ1959ኙ ውል ነው። ይሄኛውም ከ1929ኙ የባሰ አሳፋሪና የግብጽ አልጠግብ ባይነትና የቅኝ ገዥዋ የእንግሊዝ ሴራ የታየበት ስምምነት ነው።
ይህ ስምምነት ግብጽና ሱዳን ብቻ ያደረጉት ነው። ግብጽና ሱዳን ይባል እንጂ አሁንም የቀድሞ ቅኝ ገዣቸው እንግሊዝ ስለነበረች ሂደቱን ከጀርባ የዘወረች ራሷ በመሆኗ እንግሊዝ ከእንግሊዝ ያደረገችው ስምምነት ስለመሆኑ ልብ ይሏል።
ስምምነቱ ከግብጽና ሱዳን ውጪ ሌሎቹን አገሮች ሙሉ በሙሉ ያገለለ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም የናይልን ውሃ ለግብጽና ሱዳን ለሁለት ማከፋፈል ነበር።
በስምምነቱ መሰረትም በወቅቱ ናይል ይኖረዋል ተብሎ ከተጠናው 84 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ዓመታዊ ውሃ ውስጥ ግብጽ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ፤ ሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ እንዲደርሳቸው ሆኖ ተከፋፈሉት። ቀሪው 10 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ደግሞ በየዓመቱ የሚተነው ውሃ ሆኖ ታሳቢ ተደረገ።
ይህ እጅግ በጣም ኢፍትሐዊና አሳፋሪ ስምምነት ነበር። ለይስሙላ ስምምነቱ በግብጽና በሱዳን ስም የተፈረመ ይሁን እንጂ ጠምዛዧም ተጠቃሚዋም እንግሊዝ ነበረች። በውሃ ክፍፍሉ መሰረት እንግሊዝ በበረሃማው የግብጽ ቅኝ አገሯ የምታለማውን ምርት በተለይም የጥጥ አዝመራዋን እንዳሻት እንድታዘምር አድርጓታል።
እንዲህ ያለውን ፍጹም ኢፍትሐዊ ስምምነት ነው እንግዲህ ግብጽ ዛሬም ድረስ ዛር ውላጇ አለቃት ብሎ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሟገቻ መሰረት የምታደርገው። ይሁንና ስምምነቱ ልክ እንደ 1929ኙ ሁሉ የዓለም አቀፍ የስምምነት መርሆዎችን የጣሰና አሁን ላለንበት ድህረ-ቅኝ አገዛዝ የነጻነት ዘመን የማይስማማ በመሆኑ በሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ዘንድ ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም።
ሁለቱም ስምምነቶች የኢትዮጵያውያንንና የሌሎቹንም የዓባይ ጥቁር ልጆች የመልማት መብት በፍጹም የመገደብ ሕጋዊ መሰረት ሊሆኑም አይችሉም።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2012
በገብረክርስቶስ