እውነት ዝም ካለ ዛሬ ላይ እንደበቱ የሰላው ውሸት ጎልቶ ይሰማል። ፍቅር ፀጥ ማለትን ካዘወተረ ጥላቻ ቦታውን ወርሶ ይገናል። በዝምታ ምክንያት እውነትን የያዙ ብዙሀን ሀሰት በያዙ ጥቂቶች ይበለጣሉ። ዛሬ የበጎዎች ዝምታ አገራችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል።ከብዙ የፍቅርና የአንድነት ድምፆች ዝም ማለት ያነሱ የጥላቻና የልዩነት ድምፆች ለመጉላት ምክንያት ሆኗል። በጎዎች ምንም ያህል ቁጥራቸው ከፍ ቢል የጥቂት ክፉዎች ኮቴ ገዝፎ ተድጧል።
እርግጥም ለምናየውና ለምንሰማው እኩይ ተግባር የኛ ምላሽ ዝምታ መሆኑ ያሳስባል። እውነትን በጊዜው እውነት ካላሉት ሲያድር የውሸት ያህል አገርና ህዝብ ይጎዳል። ትክክል መስሎ የታየን ጉዳይ ላይ ትክክል ነው ይቀጥል፤ የተሳሳተው ደግሞ ስንመለከት አይ ይህ ለአገርም ለህዝብም በጎ አይደለምና ሊገታ ይገባዋል ማለት እንዴት ተሳነን።እውነት ባልነውና ባመንበት ጉዳይ ዝም ብንል እውነቱ መሻሩ ሀቁ መቀፍደዱ አይቀርም። እርግጥ ክፉ ነገርን የሚሰብኩ መልካም የሆነን የሚያሰርፁ ቁጥራቸው በዝቶ አይደለም። ይልቁንም የሰላም አምባሳደሮች ዝምታ ያነሱት ጥላቻ ዘቦች የበዙ አስመሰላቸው እንጂ።
ወገን ስለ አገር መፅናት ማውራት ፍቅርና አንድነት መስበክ ለምን ተውን። ቢያንስ ጥላቻን የሚሰብኩት መለያየትን የሚነዙትን ያህል መጮህ እንዴት አቃተን። እነሱ ስለ ክፉ ተግባር ደጋግመው ሲያወሩ እየሰማን እኛ ስለፍቅር መስበክ ለምን ተሳነን? የራሳችን ጉዳይ ላይ እኛው ዝም ጭጭ ማለታችን ለምን ይሆን?
ወገን የምንሰማውና የምናየው ግራ እስኪገባን ድረስ ከጫፍ ደርሶ የኛ ለዘብተኛ መሆን አሳስቦኛል። ፍቅርንማንገስ ሰላምን መስበክ ላይ መስነፋችን ነጋችንን በመጥፎ ገፅታው እንድናስበው እያደረገን ይገኛል። ዘመን ፍቅርን የጠላ መዋደድን የሰለቸው ይመስል መነጣጠል ላይ ዘምቷል። ለምን እኛ በዝምታችን የተጠላውን ጥላቻ እንዲቀርብ ፈቀድንለት።
ዛሬ ዝም ማለታችን ስለ ፍቅር መለዘባችን ትውልድ አገር ከመስፋት ይልቅ መቅደድ የተሻለ መስሎ ታይቶታል። ሀገር ከማነፅ ይልቅ አገር ማፍረስ ያለ ምክንያት ተላምዶታል። መቅደድ የመስፋትን ያህል ስላልከበደ፤ መስፋትን የመቅደድን ያህል ስላልቀለለ የቀለለው ላይ ተዘምቷል። ፍሬ የሚታየው በዘሩት ልክ ነው።ፍቅር ካስተማሩት ፍቅርን ጥላቻ ከሰበኩት ክፋትን ማግኘት አይከብድም።
ዛሬ እንደ አገር ፍቅርን የሚያፀና አንድነትን የሚሰብክ መዋደድን የሚያውጅ ተወዷል፤ ሰላምን የሚሰብክ ቅዳጁን የሚሰፋ ተናፍቋል። ኧረ ወገን ሀገርን እንስፋ ሀገርን ከሚነጣጥሉ አገርን ከሚያፈርሱ አንድነትን ከሚቀዱት በላይ ፍቅርን እንስበክ ፍቅርን እናፅና ጥላቻ ሲሰበክ ዝም ብለን ፍቅርን አንግፋ። በጎነትን ከፍ አድርገን እንንገር ፍቅርን አጉልተን እንስበክ። ስለ እውነት መናገርን ዝም አንበል።
ስለ ፍቅር ዝም በማለታችን ስለ እውነት ባለማውራታችን ስለ አንድነት ባለመናገራችን ከመስፋት ይልቅ መቅደድ፤ ከአንደነት ይልቅ መነጠል የተሻለ መስሎ ገዝፏል። ወገን በዝምታችን ምክንያት ስህተታችን ገዝፏል።እውነት ማለዘቡ እናቁም ያገር ሰው በጥላቻ የተቀደደው አንድነታችን እውነትና በፍቅር ኑ እንስፋ።በእርግጥ ቅዳጅ አንድ ጥቅም አለው የተሻለ አድርጎ ለመስፋት ከሆነ። የጋራ የሆነ ውብ እሴታችንን መቅደድ ያበዛነው መልሰን አሳምረን ልንሰፋው ይሆን እንዴ?
አዎ! ዝም ማለት ዋጋ ያስከፍላል የያዙት ነገር መልካምነት ከተፃረሩት ክፉ ነገር ቢገዝፍም የሚዋጥበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እርግጥ መልካም ነገሮች መገኛቸው ይርቃል። እነዚያ ጥሩ ትሩፋቶች በወቅቱ ካልተጠቀምንባቸው ምንም ናቸው። እናም የሰፊዎች መበራከት ባነሱት ቀዳጆች ቢዋጥ ወይም ደግሞ የሚሰፋ ከሚቀደው ቁጥሩ ቢበዛም የቀዳጁ ድምፅ ስለጎላ ሰፊው ተውጧል።በዚህም ምክንያት ስለ ፍቅር ዝም ካሉት ይልቅ ስለ ጥላቻ የተነፈሱት ድምፅ ጎላ። ብዙዎች ዝም ካሉ ያነሱ ድምጸኞች ይገዝፋሉ።እርግጥ ዝም ያለ ውሀ ጥልቀት አለ እሙን ነው ነገር ግን ውብ የሚስለው የሚንፋፋን የውሀ አይነት ነው።
በአደባባይ ያላንዳች እፍረት ኩፍስ ብሎ “እኔ ፍላጎቴ መነጠል ነው።” ቀዳጅነቱን እራሱ ላይ በሚመሰክርባት ሀገር አይ እኔ ሰፊው እያለሁ አታደርገውም የሚል ይጥፋ።እርግጥ ቁጥሩ ያነሰው ቀዳጅ ድምፁ ከፍ ተብሎ እንዲሰማ ያደረገው የሰፊው ዝምታ ነው።ዝም ያለ ዝምታ ይውጠዋል እንጂ በዝምታው ዘላቂ ዝምታን እንዳያገኝ እንደሚችል አያስበውም።
ጥላቻን የሚሰብክ አንድነትን የሚንድ ቀዳጅ በዝቷል ዝምታን ሰብረን ፍቅርን የሚፀድቅ አንድነትን የሚያፀና ሰፊን እናበርክት፤ ለትውልዱ ፍቅርን እናውረስ። ውዶቼ በጥላቻ አገር እንቅደድ ከሚሉት በላይ ጮኸን በፍቅር አገር እንስፋ፤ አገር እንገንባ ማህበረሰብ እናድን ስለ ፍቅር ዝም ማለት እናቁም። ሰፊንት እኮ እርባናው ከፍ ይላል።የመቅደድ በጎነት ያለው ስፌትን ለመጠገን ሲያስቡ በጎደለ ለመሙላት ሲያስቡ ነው። ውዶቼ ከጉድለት ላይ መቀነስ እኮ ነው ክፉው መቅደድ።
በዝምታችን የምናጣው አገር ነው። ጥቂቶች ጥላቻን በአደባባይ ሲያውጁ እያየን ስለ ፍቅር ግን ብዙዎቻችን መተንፈስ ተሳነን። እንዴት ግን ጥላቻ ሰባኪው ከፍቅር አንጋሹ በጩኸት ያይላል? የጥላቻ ሰባኪውን ያህል ፍቅር አንጋሹን ብናበዛ የሚያበላሸውን ያህል አልሚ ቢበረክት ዛሬ የምናየው በጥባጭ ጎልቶ ይሰማ ነበር? በፍፁም።እንደውም ፍቅርና አንድነት በትንሹ ቢጪሁትም ከጥላቻ ገዝፎ ይሰማል።
ግን ደግሞ ፍቅር ለጥላቻ ቦታን ለቆ ጥላቻ የቀደደውን በመስፋት ጊዜውን ይፈጃል። ጥላቻ ሀይ ባይ አጥቶ ተሰፍቶ የቆየውን ሀገር ካልቀደድኩ ብሎ አደባባይ ላይ ዘራፍ ማለትን ተላምዷል። የፍቅር ሰባኪው ሚና ያልጎላበት ዋንኛ ምክንያት ይሄ ነው።
ወገን በፍቅር ተሳስረን ዘመናትን ተሻግረናል። አንድነት በመስበክ መዋደድን ማፅናት ችለንበትም ቆይተናል። ዛሬም የፍቅር ዝማሬያችንን ከፍ አድርገን ያለዘብነውን ድምፃችንን አጉልተን ሰላምን እንዘምር ሰላም መሆንን እንስበክ ያኔ በእርግጥም ሀገር በአንድነት ማቆም ማህበረሰብ ማስተሳሰር ጀመርን እንላለን።ስለ ፍቅር ዝም ካልን ስለ ጥላቻ ብዙ እንሰማለን።አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2012
ተገኝ ብሩ