በጥበብ ደስታና ሀዘን፣ እውቀትና ፍልስፍና፣ታሪክና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች በስፋት መዳሰስ ይቻላል። ዘርፏም ብዙ ነው። ስሜትን ቆንጥጦ ለመግለፅ የሚያስቸግር አንዳች ነገርን በጥሩ ቋንቋ በግጥም ማስፈር፣ በዜማ ማቀንቀን፣ በብሩሽ ሸራ ወጥሮ ማቅለምም ሆነ በስነ ፅሁፍ መተረክ ይቻላል። ይሄ መንገድ የሰው ልጅ የዘመናት እውነት ሆኖም እስካሁን ድረስ ቆይቷል።
በተለይ ሃያላን በጉልበታቸው የተጨቆኑ እውነቶችን የመጠምዘዝ አሊያም ደግሞ የጥበብ ድምፅን የማፈን አቅም የላቸውም። ለዚህ ነው እነዚህ ድምፆች በኪነ ጥበብ፣ ስነ ፅሁፍ እንዲሁም ስነ ጥበብ ውስጥ አንፀባርቀው ማህበረሰቡ ልቡና ውስጥ ገብተው ለውጥን የሚያመጡት።
ለዛሬ ከላይ ያነሳነውን እውነት የሚመሰክርልን አንድ የስነ ፅሁፍ ውጤት ይዘን ቀርበን ዳሰሳ ለማድረግ ወደናል። የታፈነ እውነቶችን በመረጃ ተደግፎ በማስረዳት በጥሩ ቋንቋና ስነ ፅሁፋዊ ውበት የሚዳስስ ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት ያለፈውን ስርአት ጭቆናና እንግልት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ጭምር። ከዚህ ባሻገር ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ስርዓቱን እንዴት መታገል እንደተቻለ አመላካች ሃሳቦች የያዘ ነው። ፅሁፉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ በሆኑት አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነማሪያም የተፃፈ ነው። ከዚህ እንደሚከተለው የመፅሃፉን ዳሰሳና የፀሃፊውን ሃሳቦች አዘጋጅተናል።
የመፅሃፉ ርእስ፦ የዋልድባና የህውሃት ፍጥጫ (የአባቶቼን ርስት አልሰጥም)
ፀሃፊ፦ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማሪያም
የገፅ ብዛት፦ 187
ጭብጥ፦ የገዳሙ ታሪክ፣ በመንግስት በተለይም ህወሃት ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ በነበረበት ያለፉት 27 ዓመታት በገዳሙ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖና የደረሰ ጉዳት ላይ የሚያጠነጥን።
ፀሐፊው ማን ናቸው?
መጋቢ ስርዓት አባ ገብረየሱስ ኪዳነ ማርያም ይባላሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት አሁን ማእከላዊ ጎንደር ተብሎ የሚጠራው ቀደም ሲል ደግሞ የሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት በመባል የሚታወቀው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች የገዳማት ክፍል ሃላፊ ነበሩ። በኋላም ላይ የዋልድባ ገዳም አብረንታንት ቤተ ሚናስ ተወካይ ሆነው ለዓመታት አገልግለዋል።
እኚህ አባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በታሪክ፣ ቅርስ፣ በስነ ፅሁፍ ሃብትና በልዩ ልዩ አገራዊ ሃብቶች በበለፀገው የዋልድባ ገዳም በመሄድ ምንኩስናቸውን ተቀብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ ዋልድባ ገዳም ቤተክርስቲያኗ አሏት ከሚባሉት ዋና ዋና ገዳማት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። ገዳሙ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ 485 ዓ.ም የተመሰረተ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናትን በመጥቀስ ይናገራሉ። የዚህን ታላቅ ገዳም ታሪክና ዝና በማወቃቸውም በስፍራው ስርዓተ ምንኩስናን ለመቀበል ችለዋል። በዚያም እምነቱና ስርዓቱ በሚፈቅደው መንገድ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ጥቂት ስለ ዋልድባ ገዳም
የመፅሃፉ ደራሲ አባ ገብረየሱስ ከ10 ሺህ ኮፒ በላይ አሳትመው ለአንባቢያን ይፋ ያደረጉት መፅሃፍ ላይ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ስለሚገባው ገዳም በተለያዩ ርእሶች ስር ሰፋ ያለ መረጃን ከጠንካራ ትንታኔ ጋር አስቀምጠዋል። ከዚህ ውጪ ገዳማዊ ህይወት ምን እንደሚመስል፤ ምንስ መሆን እንዳለበት ከማንሳታቸው ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉት መንግስታት በዚህ ታላቅ ስፍራ ላይ ያሳረፉትን በጎ አሻራ በማንሳት ለታሪክ ፍርድ ክፍት አድርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ ዘመን የዘመን ጥበብ አዘጋጆች ጋር በነበራቸው ቆይታም በፅሁፋቸው ያስቀመጡትን ሃሳብ አጠር ባለ መንገድ ከዚህ እንደሚከተለው ገልፀውልን ነበር።
የዋልድባ ገዳም በቀድሞው አጠራሩ በበጌ ምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ስር ነበር። በአሁኑ አወቃቀር ደግሞ የዋልድባ አበንታት በትግራይ ክልል ስር የሚገኝ ሲሆን ሌላኛው የገዳሙ ክፍሎችና የእምነት ስፍራዎች በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ
እንደተቀደሰ ስፍራ የሚወሰደው ይህ ስፍራ አራት ወንዞች ያዋስኑታል። እነዚህም በምስራቅ የእንስያ፣ በምእራብ የዛሬማ፣ በደቡብ የማይወይባ እንዲሁም በሰሜን የተከዜ ወንዞች ናቸው። በአጠቃላይ ስፋቱ ከ30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር፤ ርዝመቱ ደግሞ ከ80 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደሚሆን እርሳቸው በቃል ከሚነግሩን በላይ ለአንባብያን ይፋ የተደረገው የአባ ገብረየሱስ መፅሃፍ ይነግረናል።
የስነ ፅሁፍ፣ታሪክና ቅርስ በዋልድባ
በዓለም ላይ ሶስት የጌታ ገዳማት ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ የዋልድባ ገዳም አንዱ እንደሆነ አባ ገብረየሱስ በመፃሀፋቸው ይናገራሉ። ምክንያቱ ደግሞ እራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቋቋሙ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ የተነሳ እጅግ በርካታ ታሪካዊ የብራና ስነ ፅሁፍ ውጤቶች፣ ሚስጥራት፣ ድርሳናት፣ የኢትዮጵያ ታሪክን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ጥበባዊ ውጤቶች እንደሚገኙበትም ይናገራሉ። ከዚህ ውጪ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው አቋቋም በዚሁ ገዳም እንደሚሰጥ በዝርዝር በቃልም በፃፉት መፅሃፍትም ላይ አስፍረዋል። የተቀሩት ሁለት ገዳማት በእስራኤልና በግብፅ የሚገኙ ናቸው።
ዋልድባና የህውሃት ፍጥጫ ለምን?
አባ ገብረ ኢየሱስ በመፅሃፋቸው ላይ ‹‹ዋልድባ ገዳም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ እንዲሁም ብሄራዊ ኩራታችን ነው›› ይላሉ። ሆኖም ህውሃት በ1967 ዓ.ም የትግል አላማውን ሲቀርፅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የማጥፋት ዓላማ እንደነበረው ይገልፃሉ። በዚህም የዋልድባ ገዳምን የነፍጠኞች መጠራቀሚያ ነው በሚል ዋናው ኢላማው አድርጎት እንደተነሳም ይናገራሉ። ቦታውን ለልማት ይፈለጋል በማለት በውስጡ የሚገኙ ማእድናትን የማጥናትና ሃብት የመመዝበር ስራም እንደሰራ ይገልፃሉ። የወልቃይት የስኳር ፕሮጀክት በሚል የዛሬማ ወንዝን በመገደብ ቤተክርስቲያን፣ ቅርስ የአገር ታሪክና መሰል ሃብቶችን ለማጥፋት መንቀሳቀሳቸውንም ይገልፃሉ። ልማትን መቃወም ሳይሆን የገዳሙን ታሪክና ሃብት የሚያወድም በመሆኑ መቃወማቸውና በምላሹም ብዙ መከራ መቀበላቸውን ያነሳሉ።
በተለይ ታላላቅ የአብነት መፅሃፍት፣ ሰነዶችና
የገዳሙን ቅርሶች ለማውደምና ለማጥፋት አበክሮ መስራቱን ይገልፃሉ። ይህን እቅዱን ለማሳካትም ለብዙ ዓመታት የሰለጠኑ ሃይሎችን በማስገባት ለማስፈፀም ሲሞክር ቆይቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ስርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የተለያዩ ዓለማዊና ያልተገቡ ተግባራትን በተቀደሰው ስፍራ ለመፈፀም መንቀሳቀሳቸውን አንስተዋል። አባ ገብረ ኢየሱስም ይህን ጉዳይ በመፅሃፋቸው ላይ በመዘርዘር ተሰርቷል ያሉትን ሴራ በመረጃና በተለያዩ መንገዶች በትንታኔ አስቀምጠውታል። የገዳሙ አባቶችም ይህን ደባ ለመታገል የተጓዙትን እርቀትና ያገኙትን ውጤት ጨምረው አስፍረዋል።
ሃይማኖት፣ቅርስ ታሪክ እንዳይጠፋ አቤቱታ
‹‹የዋልድባና የህወሃት ፍጥጫ›› በሚል ርእስ 187 ገፆችን ይዞ ለአንባቢያን የበቃው መፅሃፍ አባ ገብረ ኢየሱስን ጨምሮ ሌሎች አባቶች ኮሚቴ በማዋቀር ሊደርስ የታሰበውን ጥፋት ለማስቆም በሚል ለመንግስት አቤቱታ ማቅረባቸውን የተለያዩ መረጃዎችን በመጥቀስ ብዙ ርቀት መጓዛቸውን ይዳስሳል። በዚህ መነሻ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በወቅቱ አገሪቷን ይመሩት የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ቢሮን ጨምሮ ይመለከታቸዋል ላሉት አካላት የገዳሙ አባቶች ደረሰብን ያሉትን በደል ለማሰማት መሞከራቸውን ይዳስሳል። የዚህ መፅሃፍ ፀሃፊም አቤቱታውን ካቀረቡት ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። በሂደቱ ያገኙትን መረጃዎች በመመዝገብና በመከታተልም ለታሪክ ፍርድ ይቅረብ ሲሉ ይህን መፅሃፍ ለአንባቢ እንዳቀረቡት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ ገልፀውልናል። አንባቢያን ሙሉ መፅሃፉን አግኝተው ሲያነቡት ዝርዝር ጉዳዩን እንደሚረዱት ብንገነዘብም፤ ለዳሰሳችን እንዲመቸን የፀሃፊውን ቃል በመጠቀም የተወሰኑትን እንደሚከተሉት እናነሳለን።
በመፅሃፉ ላይ እንደተጠቀሰውና ፀሃፊውም በቃል እንዳረጋገጡልን በ2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ድረስ ኮሚቴው በመሄድ ስለጉዳዩ አቤት ብሏል። በጊዜው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት ጉዳዩን ችላ ከማለት ባሻገር በአባላቱ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ያብራራል። ይህን ተከትሎ ስለ ጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው
በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የሚገኙ ጋዜጦችና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ሽፋን መስጠታቸው ሁኔታውን ወደ ህዝብ እንዲደርስ በማድረጉ ውዝግቡ መክረሩን ‹‹የዋልድባና የህውሃት ፍጥጫ›› የሚለው መፅሃፍ ይነግረናል። በተለይ የገዳሙን በተለይም የኢትዮጵያውያን የሆነውን ሃብት ለማጥፋት የህወሃት አባላት ከምንም በላይ ደግሞ የስርዓቱ መሪ ባለስልጣናት መሳተፋቸውን ይነግረናል። የእያንዳንዱን ማንነት ከመግለፁም ባሻገር ግብራቸውን ፍንትው አድርጎ ይገልፃል።
የገዳማቱ አባቶችና ምእመኑ ጆሮ ዳባ ልበሱ የተባሉት ጥፋቱን ከሚፈፅሙት የህወሃት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያኗ በተለያየ የስልጣን እርከን ላይ በነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ጭምር እንደነበርም ይገልፃሉ። ይህ የሆነበት ምክንያትም ህወሃት አባላቶቿን የበግ ለምድ በማልበስ በቤተክርስቲያኗ ላይ በመሰግሰጓ ነበር። በደላቸውን በሚያምኑት አምላካቸው ፊት በማቅረባቸውና በአካልም ከአጥፊዎቻቸው ጋር መታገል በመቻላቸው በተለያየ ጊዜ በጎ ምልክት ማየታቸውን መፅሃፉ ይዘረዝራል። ፀሃፊው እንደሚሉት በምድር ያጡትን ፍትህ ከሰማይ እንደሚያገኙ የሚያሳዩ ምልክቶች በተለያየ ጊዜ ተከስተዋል።
እስርና እንግልት
የዋልድባና የህወሃት ፍጥጫ የሚል ርእስ የተሰጠው መፅሃፍ ፀሀፊን ጨምሮ ሌሎች አባቶችና ምእመናን ለፍትህና ለእውነት በመታገላቸው ለዓመታት በእስርና ከአገር አገር በመባረር መከራን ማየታቸውን መፅሃፉ ይተርካል። ይህን ሃሳባቸውንም ከመፅሃፉ ባሻገር ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ቃል ላይ ያረጋግጣሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የዋልድባና የወቅቱ መንግስት እሰጣ ገባ በስፋት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
‹‹ልማት የሚቃወም አባትም ሆነ ምእመን የለም። አባይም ሆነ ሌሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወንዞች መገደብና ለተለያዩ ልማቶች መዋል አለባቸው›› የሚሉት አባ ገብረ ኢየሱስ ነገር ግን ሆን ተብሎ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ቅርስና መሰል ሃብቶችን የሚያጠፋ ሴራ ሊከሽፍ ይገባል በማለታቸው ለእስር፣ ድብደባና ያልተገባ እንግልት መዳረጋቸውን ይገልጻሉ። ለውጡ በመምጣቱ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ትዛዝ ለሁለት ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ ከተወረወሩበት ወህኒ ቤት መፈታታቸውን በመፅሃፋቸው ላይ አስፍረዋል።
እርሳቸው በቃላቸውም ሆነ በመፅሃፋቸው እንደከተቡት አሁንም ድረስ የዋልድባ ጉዳይ አልተቋጨም። ለጊዜው ይቁም እንጂ በግልፅ በአደባባይ ሴራው ቆሟል ተብሎ ማረጋገጫ እንዳልተሰጠ ይናገራሉ። ዝርዝር ጉዳዩንም በመፅሃፋቸው ይዳስሳሉ። ሆኖም ትልቁን ዳገት እና እንቅፋት መሻገር መቻላቸውን ከመግለፅ አልተቆጠቡም።
እንደ መውጫ
የዋልድባና የህውሃት ፍጥጫ በሚል ርእስ የተከተበው ታሪካዊ መፅሃፍ በስምንት ምእራፎች ተቀንብቦ በርከት ያሉ አገራዊ አጀንዳዎችን ከጠንካራ መረጃ ጋር እያዋዛ የሚያስቃኝ ነው። የመፅሃፉን ዓላማ አንብቦ ግንዛቤ ከመያዝ ባሻገር በታሪክ ሂደት ውስጥ ማመሳከሪያ ሰነድ የማግኘት እድልን ይከፍታል። በተለይ ሃሳብን በጠንካራ የስነ ፅሁፍ ብቃት በመረጃ ደግፎ ከማስቀመጥ አኳያ ሰፊ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደሌሎቹ ሃይማኖቶች ለአገር አንድነት፣ ለስነ ፅሁፍ እድገት፣ ለታሪክ፣ ቅርስ መጠበቅ ያላትን አበርክቶ በቀላሉ እንድንገነዘብ የሚያስችል አቅምን የያዘ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን በቁንፅል መረጃ ነጠላ ጉዳይ በማንሳት ጭብጥ የሚስት ጉንጭ አልፋ እሰጣ አገባ ውስጥ ለሚገባ የማህበራዊ ድረ ገፅ አንባቢ ሰፊ ትምህርት የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል። ፊቱን መለስ አድርጎም መፅሃፉን ማንበብ ቢችል በብዙ እንደሚያተርፍና ከያዘው እውነት በተሻለ የዳበረ ሃሳብ እንደሚገበይ ጥርጥር የለውም። ከዚህም ሌላ የዚህ መፅሃፍ ፀሃፊ የሚያነሱትን ሃሳብ በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ የማይቀበሉ ወገኖች ካሉ መሰል መረጃዎችን በማስደገፍ ተቃራኒ ሃሳቦችን እንዲያነሱ የሚያበረታታ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተለየ ሀሳብና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ካሉ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን። የዛሬውን ዳሰሳ በዚህ ቋጨን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
ዳግም ከበደ