የድሮ ሰዎች አንድ ነገር አልጥም ሲላቸው አንድ አባባል አለቻቸው። ‹‹ወሬን አዳምጦ ምግብን አላምጦ›› የሚል። ያልተደመጠ ወሬ ሰው ይጎዳል፤ አገር ያምሳልና በነፋስ የተለቀቀን ወሬ ሁሉ መሰማት ሳይሆን መደመጥ አለበት ይላሉ። ነገርን አድምጦ ሲሆን ለማመዛዘን፣ ለማንሰላሰል ጊዜ ይኖራል። ታስቦና ታልሞ የተደረገ ነገር ደግሞ ውጤቱ ጎጂ ሳይሆን በተቃራኒው መሆኑ አይቀሬ ነው።
እንዲህ እንደ ሰሞኑ የተንቀዠቀዠ ነገር ሲገጥማቸውም ‹‹እህን ጨምርበት›› ይላሉ ። እውነት ነው። ለማንኛውም ወሬና አሉባልታ፣ የፖለቲካ ቅስቀሳ እህ ማለት ይጠቅም ይሆናል እንጂ አይጎዳም፤ እህ ያለ ያተርፋል። እንዴት ቢሉ እንዲህ እንላለን። እህ ማለት ነገሮችን ከግራ ከቀኝ ማድመጥ ነው። ማድመጥ ብቻ ሳይሆን ማሰላሰል ወደፊት የሚሆነውንና ወደኋላ የሆነውን ለማወቅና ለመረዳት ታሪክንም ለመመርመር ያስችላል። እህን ያልጨመረ ግን ትነስ መንገድ ዝጋ ሲባል ሲዘጋ፤ እህን ሳይጨምር አቃጥል ሲባል ክብሪትና ነዳጅ ይዞ ሲወጣ፤ ግደል ሲባል ወገኑ ላይ የጭካኔ እጁን ሲሰነዝር ወገንና ሀገሩን ያቆስላል።
ችኩል እህን ሳይጨምር በተሰጠው የመኪና ታርጋ ማንን እንደሚገል ሳያውቅ ለነጻነቴ የቆመ ጀግናዬ የሚለው ዝነኛ ወገኑን ደመከልብ ያደርጋል። የከፋ የታሪክ ጠባሳ ያሳርፋል። ታዲያ እነዛ አያቶቻችን እህን ጨምርበት ቢሉ አይገባም፤ እህን ጨምርበት ማለትማ ይሄኔ ነው።
መንገድ ዝጋ፣ ግደል ፣አቃጥል የሚል ቀስቃሽ ሲነሳ ማንን ፣ ለምን ውጤቱስ ምንድነው ብሎ ማሰብ። በስሜት የሚሆን ምክንያታዊነት የሌለው የኋላኋላ የሚጎዳው እኛኑ ነው። ራሳችንን፤ እህት ወንድማችንን። የተቃጠለው ሆቴል፣ ክሊኒክ እና ትምህርት ቤት… የማን ነው? የራሳችን፣ የሀገራችን ሀብት፣ ወገኖቻችንን ሰርተው የሚበሉበት፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት፣ ሲታመሙ ታክመው የሚድኑበት ተቋም። እና ይሄ ሁሉ ተቃጠለ ማን ተጎዳ? ይሄን ላቁምና ሌላ ላንሳ። በተሰራው የጥፋት ናዳ፣ በደረሰው ኪሳራ ማን ተጠቀመ? ትርፉ እማን ኪስ ገባ? ብቻ አንድ እውነት አለ ፤የተጎዳ ሰማይ የተደፋበት የክፉ አሳቢዎች በላንጣ ንጹሀን ዜጋ።
መንግሥትማ ዛሬ አለ፤ ነገ ይለወጣል። ሲኖርም ሲለወጥም አይተናልና ይሄ እውነት አለ። ፓርቲ ይኖራል ይከስማል። ይሄንንም በየዘመናቶቻችን አስተውለናል። ባለሀብት ይኖራል ዕድሜ ዘመኑን ሲጨርስ ማንም ሰው እንደሚያልፈው እሱም ያልፋል። ይሄ እዚህም እዛ ማዶም የነበረ፣ የሆነ፣ ወደፊትም የሚሆን እውነታ ነው። በሀገር ላይ የተሰራ ሀብት ንብረት ግን የህዝብ ሆኖ ይቀራል። አንዱ ሲጠቀምበት እሱም አልፎ ሌላው ሲተካ ሲገለገልበት ይኖራል። እናስ አሁን ማን ምን ሆነ? እጠይቃለሁ መልሱ ግን ይቆየን። ማንም ሰው በተለይ ወጣቱ ለሚሰራው ስራ እህ አለማለት ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። አንድን ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት እህን መጨመር። ማን ነው ያለው? ምንድነው ያለው? ለምንድነው ያለው? የኋላ ውጤቱስ ምን ይሆናል ብሎ ማሰብ ይገባል።
በቅናትና በምቀኝነት ላይ ተመስርቶ የሚደረጉ የሴራ ፖለቲካ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚጎዳው ህዝብን ነው። በየቦታው የወደመው ኢንቨስትመንት ጉዳቱ ለባለሀብቱ ብቻ አይደለም። በውስጡ ለሚሰሩ ዜጎች፣ ለሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች፣ ለከተማው ዕድገት፣ ለአላፊ አግዳሚው ከሁሉም በላይ ግን ለክልሉ ነዋሪዎች መሆኑን ማንም የሚመሰክረው ነው። በመቃጠሉ ዛሬ የተራቡ፣ የስራ ያለህ የሚሉ ዜጎች ከየትኛውም አካባቢ የመጡ አይደሉም፤ በወገናቸው ግፍ የተፈጸመባቸው የክልሉ ነዋሪዎች እንጂ። ከሴራኛው ለመጣው መልዕክት እህን ጨምረን አስተውለንና አገናዝበን ቢሆን ኖሮ ለወገኖቻችን መራብ፣ ለራስም የህሊና ስቃይና ጸጸት መዳረግ አይኖርም ነበር ። ቀደምቶቹ አዋቂ አያት ቅድመ አያቶቻችን እንዳሉት ለማንኛውም ነገር እህን ጨምሩበት። ከ‹‹እህን ጨምሩበት ››ብዙ ይተረፋል እና እህ ብለን እናድምጥ! አድምጠን እንመርምር!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
አልማዝ አያሌው