ውሎና አዳሩን ጎዳና ካደረገ ሁለት አመት ሆኖታል ታዴ እብዱ ። እናቱ ታደለ ብላ ስም አውጥታለት ነበር። ነገር ግን ይሄ ስም ማህበረሰቡ እብዱ ታዴ በሚል ቀይሮለታል። በእርግጥ እሱ አላበድኩም ብሎ ሞግቶ ነበር እብድ የተባለ ሰሞን። እንደውም “ከሁሉም ጤነኛው እኔ ነኝ። እውነት ስል እውነት የሚጠላ እብድ ብሎኝ እነጂ እኔ አላበድኩም” ቢልም “አይ አብድህ” አሉት።
መጀመሪያ ላይ የሰው አስተያየትና እይታ አንድ ሲሆንበት “እውነት አብጄ ይሆን እንዴ?” ብሎ እራሱን ተጠራጠረና ያበደ መስሎት ነበር። ነገር ግን ውሎ ሲያድር እብድ መሰኘቱን እንጂ እብድ መሆኑን ካደ። አለማበዱን እብድ ለሚሉት ሁሉ አስረዳ። ነገር ግን ፈፅሞ እብድ አለመሆኑን የሚያምነው ጤነኛ ነህ የሚለው ሲያጣ ማስረዳቱን ተወው።
አሁን አሁንማ “ታዴ እብዱ” ሲሉት ድምፁን ከፍ አድርጎ “አቤት” በማለት ምላሽ መስጠት ጀምሯል። የሚኖርበት አካባቢ ሰዎች ሲቸገሩ መልዕክት ይልኩታል። በእብደቱ እስኪጠራጠሩ ድረስ የላኩትን እቃ ወይም መልዕክት በትክክል ይዞላቸው አልያም አድርሶላቸው ይመለሳል። “ታዴ የ10 ብር ከሰል ገዝተህልኝ ና”፣ “ታዴ ሞባይል ካርድ አምጣልኝ”፣ ”ታዴ ጉሊት ሄደህ ድንች ገዝተህልኝ” እያሉ የሰፈሩ ሰዎች ይልኩታል። የላኩት ሰዎች ሳንቲሞችን ይሰጡታል። እሱም በላይ ሱቅ ሄዶ ሲጋራ ይገዛበታል።
ለታዴ እብዱ ምግብ የማይሰጠው የሰፈሩ ነዋሪ ጥቂት ነው። ተኮማትሮ ከሚያርበት አንድ ሱቅ ጎን ካለው ላስቲክ ዳሱ በጠዋት ይነሳል። ከማደሪያ ፊት ለፊት ያለ ጠፍጣፋ ድንጋይ አዘውትሮ የሚቀመጥበት ማረፊያው ነው። ታዴ እብዱ ካልተላከና ምግብ ፍለጋ ካልሄደ ከድንጋዩ ላይ አይጠፋም። ብርድና ፀሐይ እየተፈራረቁ መልኩን ወደ ጥቁረትና ግርጣት ሳይለውጡት በፊት መልከ ቀና የሚባል ዓይነት ሰው ነበር ታዴ እብዱ።
ደህና ሥራና ገቢ አግኝቶ ለዓመታት በድሎት ይኖር ነበር። እንደ ዛሬ እብድ ተብሎ በንግግሩ ከመሳሳቃቸው በፊት። የሚ ያውቁት ቀርበውም ብዙ አማክረውት በምክሩም ተጠቅመዋል። አንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ጥሩ የወር ገቢ ያገኝ ነበር። ታዴ እብድ የተባለበት እውነት እሱና እብድ ያሉት ያሰኙት ያውቁታል። የሚሠራበት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ሙስና መሥራት የሥራ መደባቸው ያህል መደበኛ ተግባራቸው ነበር።
ታዴ እዚህ መስሪያ ቤት ተመደበ። ሥራውን ጀምሮ ሁለት ወር ሳይሞላው አገልግሎት ሰጥቷቸው ከሚሸኛቸው ግለሰቦች ጥያቄ ይቀርብለት ጀመር። “የባንክ ሂሳብ ደብተር ቁጥርህን ንገረኝ፣ ሌላ ቦታ ሻይ ቡና እያልን እናውራ ስልክህን ስጠኝ” የሚሉት ሲበዙ ግራ ገብቶት አንድ ባልደረባውን አማከረ።
ቀድሞ እዚያው መስሪያ ቤት ለሥራ የቆየ ባልደረባው ታዴ በነገረው ጉዳይ ተገርሞ ሳቀና። “ቆይ ታዴ እንዴት አይገባህም? እንዴት ዝም ብለህ ትሸኛቸዋለህ። እሺ ብለህ የሰጡህን ላፍ ነው እንጂ። እኔ በደሞዝ ልትኖር ፈለክ እንዴ። ፍሬንድ በጊዜ ከተፍ ከተፍ አድርጊና የድርሻሽን ይዘሽ ላሽ ነው እንጂ፤ ስማ እዚህ ቤት ገብቶ እራሱን ዲታ ለማድረግ የማይመኝ ሠራተኛ የለም። አንተ ዕድለኛ ነህ ። ”በማለት ስለ ሥራና ሴራው አስረዳው፤ ደነገጠ። ፈጽሞ ያልጠበቀው በመሆኑ አዘነ። በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው የተበላሸ አሠራር እጅግ እስጠላው።
“ሰዎች አገልግሎት ለማግኘት መጥተው በትክክል የፈለጉትን አገልግሎት የማግኘት መብት እያላቸው ለምን ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ይጠየቃሉ? ለምን በትክክለኛ መንገድ ብቻ አይስተናገዱም? ለምን ሠራተኛው ደሞዝ እያለው ሌላ ክፍያ ከተገልጋዮች ያላግባብ ይቀበላል? ለምን የመንግሥትና የህዝብ ገቢ ያላግባብ ይመዘብራል?” ብሎ ተከራከረ። የረባ እርምጃ በአሠራሩም ሆነ ከሥራቸው ውጪ ግልፅ በሆነ መልኩ ከተገልጋይ ገንዘብ የተቀበሉ ሠራተኞች ላይ ምንም እርምጃ አለመወሰዱን ሲያይ ተስፋ ቆረጠ።
ስለ ተቋሙ የአሠራር ግድፈት ብዙ ተናገረ የሚሰማው ግን አልነበረውም። የሚሳለቅበትና ገርምሞት የሚተወው እንጂ። ይባስ ብሎ ሠራተኛው በሙሉ አደመበት። ሠራተኞች እንዳያጋልጠን በሚል አሰጋቸውና ተንኮል ሸረቡበት። በተለይ የሱ የቅርብ አለቃው ታዴን ክፉኛ ጠላው። እንጀራው ላይ የመጣ መሰናልክ አድርጎ ገመተው። በመጨረሻም ከሌሎች የተቋሙ ሠራተኞች ጋር በመሆን ያጠመዱለት ወጥመድ ጠልፎ ጣለው።
እለቱ ደንበኞች የሚበዙበት ሰኞ ጠዋት ነበር። ታዴ የቀረበለትን ሰነድ አገላብጦ እያየ ፈርሞ ወደሌላ ፈፃሚ ያስተላልፋል። ከብዙ ሰነዶች ውስጥ አንድ ወረቀት ላይ ያረፈው አንዱ የታዴ ፊርማ ግን ዛሬ ለሚገኝበት ሁኔታ ምክንያት ሆነው። ከሱ በፊት ሰነዶችን እየመረመረች ለታዴ ለፊርማ የምታቀርብለት ባልደረባው ተማምኖ በቅርፅ ተመሳስሎበት ይዘቱን ሳይመረምር ፊርማውን ያኖረበት አንድ ወረቀት ብዙ ዋጋ አስከፈለው። ያንን ፊርማ አኑሮ ለበላዩ የላከው ሰነድ ዋጋዋ ከፍ ያለ ስለነበረች ታዴ ላይ ሲያፋጭ የነበረው ሁሉ ጥርሱን ለንክሻ አዘጋጅቶ ቀረበው።
በንጋታው ቢሮው ሲገኝ ፖሊስ ተቀብሎ እጁን በካቴና አስሮ ከተቋሙ አስወጥቶ ወደ እስር ቤት ወሰደው። ፖሊስ የተከሰሰበት ጉዳይ ሲነግረው ደነገጠ። መርማሪው “በተደጋጋሚ በሰነድ ማጭበርበርና ከተገልገይ ገንዘብ ተደራድሮ መንግሥት ሊያገኘው የነበረ የ50 ሚሊዮን ብር ገቢ ግለሰብ ጋር እንዲቀር ሙከራ በማድረግ ተከሰዋል” አለው።
ታዴ ይህን አለማድረጉን ቢያስረዳም የቀረቡበት የሰነድ ማስረጃዎች ግን ከእርሱ የእውነት የሚለው ቃሉ በቀር ምንም ማስተባበያ የሚሆን ማስረጃ አጣ። ይባስ ብሎ በሥራው ላይ እያለ ተፅፎለታል የተባሉ ተዳጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች የማያውቃቸውና ፈፅሞ ያልፈፀማቸው የስነ ምግባር ግድፈቶችና ለወንጀሉ ማጠንከሪያነት ሲቀርቡበት ግራ ተጋባ።
ፍርድ ቤት ማስረጃዎቹን ተመልክቶ አምስት ዓመት ፅኑ እስራትና ሰባት ዓመታት ከማህበራዊ መብት አገልግሎት ከማግኘት እንዲገለል ወሰነበት። አምስት ዓመታት ሳያውቅና ሆን ተብሎ በተሠራበት ደባ እስር ላይ ቆየ። እስር ቤትም እያለ እውነት ብሎ ያመነበት ጉዳይ ላይ ሙግቱን አላቆመም። ያየውን እውነት ሁሉ ፊት ለፊት የሚናገር ፅኑ ሰው ሆኖ ቀጠለ። ከእስር ሲወጣ ሥራ የመቀጠር ዕድል አልገጠመውም። የኑሮ ጫናን እየታገለ ለወራት ቆይቶ በፊት ያለምግባሩ እስር ቤት ያሰገቡትን ወንጀለኞች ፊት ለፊት ተጋፈጠ።
መንገድ እየተከተለ ሥራቸውን ህዝብ እንዲሰማ በጩኸት ያስረዳ ጀመር። ከመታሰሩ በፊት ይሠራበት የነበረው ተቋም አካባቢ መዋያው አድርጎ ሠራተኞቹን መኮነን ሥራቸውን ለህዝብ ጮክ ብሎ መንገር አዘወተረ። ይሄን ጊዜ የተቋሙ ሠራተኞች አብዷል ብለው አወሩበት። ወንጀላቸውን በድፍረት ሲናገር ታማኝነቱን ለማሳጣት በህብረት አብረው እብድ ነው ብለው ደጋግመው ነገሩበት። እብድ ለማሰኘት ብዙ አደረጉት።
የውስጡን ለመናገር ጮኾ ማውራቱ፣ በችግር ምክንያት ጎዳና መውጣቱና ያደፈ ልብስ ለብሶ አምንበት ያለው እውነት ደጋግሞ ማውራቱ አበደ ለማለት ማረጋገጫ ሆኖላቸው ታዴን “ታዴ እብዱ” አሰኙት። እውነት እንጂ እብደት ውስጡ የሌለው ታዴ እብድ ተሰኘ። ተፈፀመ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
ተገኝ ብሩ