የጽንሰ ሃሳብ ማስታወሻ፤
ሰብአዊነት ፍቺው ጥልቅ፤ ትርጉሙም ከ እስከ ተብሎ ተተንትኖ የሚያበቃ አይደለም። ጥንታዊያን ፈላስፎችም ሆኑ ዘመናዊዎቹ ብጤዎቻቸው ሰብአዊነትን “የሰው ልጆች አስተሳሰብ፣ ስሜትና ተግባር መገለጫ ተፈጥሯዊ ምንነት ነው” የሚለውን ጥቅል ጽንሰ ሃሳብ ከሰጡ በኋላ እፎይ ብለው ተደላድለው አልተቀመጡም። የሃይማኖት መምህራንም ቢሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍታቸው እያጣቀሱ ወይንም በሥልጣነ ክህነታቸው ብቃት የሰብአዊነትን ምሥጢራት በሙሉ ለመተንተን መሞከራቸው እንዳለ ሆኖ ከእንቆቅልሹ ዳርቻ ለመዳረስና ምሉእ በኩለሄ ወደ ሆነ ማጠቃለያ ለመድረስ አልቻሉም።
ሰብአዊነት፤ “የፈጣሪ አምሳል መገለጫ ነው” የሚለው መንፈሳዊ ብያኔ እጅግ ከመርቀቁ የተነሳ ፍጥረተ አዳም መለኮታዊ እውነታውን የተቀበለው በይሁንታና በአሜንታ ተቀብሎትና አፅድቆት እንጂ በምርምር ግኝት ተጎናጽፎት አይደለም። ከቅዱሳት መጻሕፍት አናቅጽ መካከል ይህንን ጸሐፊ እጅግ ከሚያስደንቁትና ከሚያስገርሙት ሰብአዊ ነክ ሃሳቦች መካከል አንዱን ለመረዳት እጅግ እንደጠጠረበት ሳልገልጽ አላልፍም። ሃሳቡን በመዝሙር መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈረው ቅዱስ ዳዊት ነው። መዝሙረኛው ስለተከበረው የሰው ልጅ ሰብእና ምንነት ፈጣሪን በመሞገት መልሱን ራሱ የሰጠበት ሃሳብ በእጅጉ “ኦሆሆ!” አሰኝቶ እጅን በአፍ ላይ በሚያስጭን አስገራሚ ገለጻ የተዋበ ነው። እንዲህ በማለት ነው በመዝሙር መጽሐፉ ምዕራፍ 8 ውስጥ ሰብአዊ ፍጡርን ያስተዋወቀን፤
“ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
ትጎበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?
ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስከው፣
በክብርና በምሥጋና ዘውድ ከለልኸው።
በእጆችህም ሥራዎች ሁሉ ላይ ሾምኸው፤
ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት።”
ፈላስፎችም ሆኑ ጠቢባን፣ የሃይማኖት መምህራንም ሆኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ወይንም የኪነ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ልህቀቱ የመጠቀውንና የረቀቀውን ይህንን ሃሳብ ተንትነው ከማጠቃለያ ላይ ለመድረስ በእጅጉ ሳይቸገሩ የቀሩ አይመስለኝም። ለመሆኑ የሰው ልጅ በሰብእናው ብቃት ከመላእክት ጥቂት ያነሰው እስከ ምን ደረጃ ነው? የተቀዳጀውስ የክብርና የምስጋና ዘውድ ሞገሱና ሥልጣኑ እስከ ምን ድረስ የተረጋገጠ ነው? በፈጣሪ የእጆች ሥራ መሾሙና ሁሉን እንዲገዛና እንዲያስተዳድር ከመለኮት የተጎናጸፈው መብት እስከ የት ይዘረጋል? ሥልጣኑን የሚተገብርበት የአጥናፈ ዓለሙ ወርድና ስፋትስ እስከ ምን ይለጠጣል? እነዚህን አንኳርና እጅግ አስደማሚ ጥያቄዎች ለመመለስ የጸሐፊው ብዕር አቅም ስለሌለው “ይገርማል!” ከማለት ውጭ ለመተንተን አይሞክርም።
በቋንቋችን የተጻፉት መዛግብተ ቃላትም ቢሆኑ ይህንን የሰብአዊነት ረቂቅ ምሥጢር ለመተንተን ስላልቻሉ ለድንጋጌው የሰጡት ማብራሪያ በነካ ነካ የታለፈ ይመስላል። ባህሩ ዘርጋው ባዘጋጁት መዝገበ ቃላት ውስጥ ሰብዊነትን የደነገጉት “ሰዎች ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ አደጋ ለደረሰባቸው፣ የሚያሳዩት ሀዘኔታና የሚፈጽሙት ተግባር ነው” የሚሉ ገራገር “የርህራሄ” ቃላትን በመሰደር ነው።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ለሰብእ (ሰብአዊነት) የሰጡት ዝርዝር ፍቺ እጅግ የተወሳሰበና ለመረዳት አዳጋች ቢመስልም ጠቅሶ ማለፉ ግን ለማነጻጸሪያነት ይበጅ ይመስለኛል፤ “ዘር ኹሉ፣ ነፍስና ሥጋ ያለው፤ ከነፍስ ከሥጋ አንድ የኾነ፣ በነፍስ አካልነት የቆመ፤ የተፈጸመ፤ ሥጋ ብቻ ወይንም ነፍስ ብቻ ያይዶለ፤ ፍፀመ ሥጋ ወነፍስ፤ ፍፀመ ጸጋ፣ ምሉእ ጸጋ” የመዛግብተ ቃላቱ አሰናጅ ጠቢብ ከዚህን መሰሉ ጥልፍልፍ ድንጋጌ በላይ ተጉዘው ሰብአዊነትን ሊተነትኑ እንዳዳገታቸው ከአቀራረባቸው መገንዘብ ይቻላል።
ስለዚህም ነው የሰብአዊነት ምንነትና የከበረ ሥፍራ በፍልስፍና እውቀትም ሆነ በሃይማኖት ትምህርቶች ተሰልቆ ስላልተጠናቀቀ ከድምዳሜ ላይ ለመድረስ አዳጋች ነው ለማለት ጸሐፊው የደፈረው። አጠቃላይ እውነታው ይህንን ይምሰል እንጂ የጋራ መስማሚያ ሃሳቦች የሉም ማለት ግን አይደለም። ሰብአዊነት የፍጥረታት ሁሉ ቁንጮነት፣ ከፈጣሪ የተሰጠ ጸጋና በክብር እየተኖረ በክብር የሚታለፍበት ልዩ የሰው ሰውነት መለኪያ፣ ከእንስሳት ከፍ ያለ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ፣ በደመ ነፍስ ሳይሆን በማስተዋል ለመኖር የሚረዳ ብቃት ጭምር ነው። እንደ አንዳንድ አራዊቶች የራስን ዘር በማጥፋት ማግሳት የሰብአዊነት መገለጫ አይደለም። የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን በተግባርም፣ በዕለት ተዕለት ውሎም ማረጋገጥና በአብሮ የመኖር ጸጋ ውስጥ አንዱ ካላንዱ መኖር እንደማይችል የመረዳት ልዩ ባህርይ የተሰጠው ለዚሁ ክቡር የሰው ልጅ ብቻ ነው። ሰብአዊነት ሲነሳ ርህራሄ፣ ፍቅር፣ መተጋገዝ፣ መከባበር፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳት፣ መደናነቅ፣ መዋደድና ለነገው ትውልድ ማሰብን የመሳሰሉ የፍጥረታችን ቅመሞች ሊዘነጉ አይገባም።
ተሐድሶ፤ እንደገና ታርሞና ተስተካክሎ ወደ መነሻና ነባር አቋም መመለስ እንደሆነ መዛግብተ ቃላት በዝርዝር ይደነግጉልናል። መታደስ መቀየር ነው። መታደስ ጥፋትን፣ ድክመትን፣ ስህተትን፣ መተላለፍን በመረዳት ዳግም ስህተትን ላለመድገም ተፀፅቶ በንስሃ “መታጠብ” ላይ ትኩረት ያደርጋል። ተሐድሶ ራስን ለተሻለ ነገር ማብቃትም ሊሆን ይቻላል። ዓለማችንና ተፈጥሮ በተለያዩ የተሐድሶ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳለፉና እያለፉ እንዳሉ ታሪክንና አሁናዊ ዐውዶችን በማጣቀስ በበርካታ ማስረጃዎች ማስረዳቱ አይገድም። ከዋነኛው የጽሑፌ ሃሳብ ላለማፈንገጥ በማሰብ ብቻ አንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮችን እየነቀስኩ ለመፈተሽ እሞክራለሁ።
ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ተግባሩ እንኳን ቢቀር ቢያንስ ተሐድሶ የሚለውን ቃል እስኪሰለቸን ድረስ እያላመጥነው ኖረናል። በተለይም ባለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ በፈነጨው የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ “ተሐድሶ፣ ዳግም ተሐድሶ፣ ጥልቅ ተሐድሶ” ወዘተ. የሚሉትን ግራ ገብ ቃላትና ሀረጋት ፖለቲካውን ሲዘውሩና ሲያዘውሩ በነበሩ መሪዎችና ግለሰቦች አንደበት እሲኪያቅረን ድረስ ስንጋት መኖራችን አይዘነጋም። በአማላይ ቅጽሎች ሲጎላመስ የኖረው ሀጋራዊ የፖለቲካ ተሐድሶ ነገረ ጉዳይ እንኳን በተግባር ሊተረጎም ቀርቶ ከድጡ ወደ ማጡ እየተጨማለቀ ቁልቁል በመዝቀጥ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ተብዬውን የራሱን የፖለቲካ የእስትንፋስ ሻማ እፍ ብሎ እንዳጠፋው ሕያው ምስክሮች ነን።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚም ቢሆን ከተተበተበበት የፓርቲና የግለሰቦች የግላጭ ዘረፋ አረንቋ ዘሎ በመውጣት ታድሶና ተለውጦ በብዙኃን ዜጎች ሕይወት ውስጥ ለውጥ ማምጣት ተስኖት የቢቸግር የተስፋ ዳቦ ስንገምጥ ብንኖርም ለራበው ሆዳችን ጉርሻ መሆን ስላልቻለ ዛሬም ድረስ የእኛ የተራ ዜጎች ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ከነበረበት ደረጃ ዝቅ ብሎ በባዶ መሶብ ላይ እስከ ማፍጠጥ ደርሰናል። ሀገራዊ የልማት ትኩረትን የሚያደናቅፉ እጅግ በርካታ ተግዳሮቶች መልካም የለውጥ ጅምሮችን እያሰነካከሉ ከዕለት ወደ ዕለት እየሟሸሽን መሄዳችን የምስራች ዜና ሳይሆን የጥፋት መርዶ ሆኖብን እንዳለን አለን። የሰው ሕይወት ጠፋ፣ ተቋማት ወደሙ፣ ንብረቶች የዶግ አመድ ሆኑ፣ የኢንቬስትመንት ትሩፋቶች ጋዩ፣ ፋብሪካዎች ተቃጠሉ ወዘተ. የሚሉት ዘገባዎች የሚዲያዎቻችን የዕለት ዜና መክፈቻዎች መሆናቸው ዜጎችን ብቻም ሳይሆን ሀገሪቱን ራሷን አንገት አስደፍቶ የሚያስነባ እኩይ ጥፋት ከሆነ ውሎ አድሯል።
በሃይማኖት ጎራም ቢሆን የተሐድሶ ድምጾች እየጎሉና እየደመቁ ሲነገሩ ብንሰማም ብዙዎቹ እንቅስቃሴዎች “ከእጅ አይሻል ዶማ” እየሆኑ እንኳን ሊታደሱ ቀርቶ ከሚቃወሟቸው መሠረቶቻቸው እጅጉን በማነስ ግራ ተጋብተው ግራ ሲያጋቡን እያስተዋልን ነው። “ሃይማኖት ይታደሳል? ወይንስ አይታደስም?” የሚለው መሟገቻ በዘመናት ውስጥ በእጅጉ አከራካሪ ብቻ ሳይሆን ደም አፋሳሽ የመሆኑ ታሪክ ሳይዘነጋ፤ ታድሰናል የሚል የእምነት እንቅስቃሴ የሚያካሂዱ ቡድኖች እንወክለዋለን የሚሉትን ምእመን ሕይወት ለበጎነትና “ለጽድቅ ሥራ” ከማደስ ይልቅ ራሳቸው ዘርፈ ብዙ የሀገራዊ ችግሮች ቋት ሲሆኑ መመልከቱንም ተላምደነዋል።
በማሕበራዊው የዕለት ተዕለት ኑሯችን ውስጥም ተሐድሶ የሚጠቀስላቸው ጉዳዮች እጅግ በርካታ ቢሆኑም የለውጡ ትሩፋት ግን “ይህንንና ያንን የመሰለ መልካም ፍሬ አፍርቶልናል” ብሎ ለመመስከር እየተቸገርን ነው። ተሐድሶ “አድርገንባቸዋል” እያልን የምንፎክርባቸው በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮቻችንም ቅኝት አልባ ሆነው ትሩፋቱን ማየት የተሳነን ምናልባትም ዋነኛውና መታደስ የሚገባው ጉዳይ ችላ ስለተባለና ስላልተነካ ይሆንን? ብሎ መጠየቁ አግባብና ወቅቱም ራሱ የሚያስገድድ ይመስለኛል።
በዓይናችን ፊት የተጋደመውን ምሰሶ ችላ ብለን፤ ጥቃቅን ጉድፎችን ከብሌኖቻችን ውስጥ ለመጥረግ እየሞከርን ይሆንን ብሎ ማሰላሰሉም አይከፋም። በስመ ተሐድሶ ተጀምረው የከሸፉት ሀገራዊ ጉድፎችን የማጥራት ዘመቻዎች ምርኮ አልባ በመሆን መና ቀርተው መና ያስቀሩን ምናልባት ዋነኛው ዒላማ ላይ ማነጣጠሩ ስለተሳነን እንደሆነስ? በጸሐፊው ምልከታ “ዋና” ባልኩትና የምር ተሐድሶ በሚያስፈልገን የሰብእና ተሐድሶ ጉዳይ ላይ ጥቂት ቁዘማ ማድረጉ ይበጅ ስለመሰለኝ እነሆ የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አጋራለሁ።
ጊዜ የማይሰጠው የሰብአዊ ተሐድሶ አስፈላጊነት፤
ከፖለቲካው፣ ከኢኮኖሚው፣ ከማኅበራዊውና ከቴክኖሎጂው የተሐድሶ ጥማት ጎን ለጎን በዜጎች የሰብአዊነት ተሐድሶ ላይ ትኩረት በመስጠት መሥራቱ ለነገ ይደር ወደማንልበት ደረጃ ላይ የተሸጋገር ይመስላል። ሰብእና የሚገራና የሚታረም እንጂ ልጓሙ የተለቀቀ እንስሳዊ ተፈጥሮ አይደለም። የሰውነት ክብር በራሱ ፈጣሪና ፍጥረት ያከበሩት ጸጋ እንጂ እንዳሻን እየፈነጨን የምንኖረው ኑሮም አይደለም። የሰብአዊነት ተቀዳሚ መገለጫ ራስን ማክበርና ከራስ ጋር መታረቅ ነው። ሰው ራሱን አክብሮ ለራሱ የከበረ ሥፍራ እስካልሰጠ ድረስና ለሌላው ወገን በረከት ለመሆን፣ ከፈጣሪ በጎ ሃሳብ ጋር ለመስማማትና ከተፈጥሮ ጋር ታርቆ በሰላም ለመኖር አቅምም ይሁን ራእይ ወይንም ምኞት እስካልተጎናጸፈ ድረስ ሰውነቱ ከንቱ፤ በሕይወት መኖሩም ትርጉመ ቢስነት ነው። ሰብአዊነት በግለሰቦች ውስጥ መሻገትና መዛግ ሲጀምር በማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ በሽታ የሚያዛምት የጥፋት ቫይረስ ሆኖ ስለመስፋፋቱ አሌ የሚባል አይደለም።
ሰሞንኛ ማመላከቻዎች፤
ከጥቂት ዓመታት ወዲህና ሰሞኑን በመላው ሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉት አንዳንድ አሰቃቂ ድርጊቶችና ትራዢዲያዊ ትዕይንቶች በብዙኃን ዜጎቻችን የሰብአዊነት አቋም ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዱናል። ደፍረን ማሳያዎቹን እናመላክት። ለመሆኑ የሰብአዊነትን የክብር አክሊል ከፈጣሪ የተቸረው የሰው ፍጡር እንደምን በዓላማ ቢስ መነሳሳት ታውሮ የራሱን ወገን ይጨፈጭፋል? እንደምንስ ደሙን በገፍ አፍስሶ ሕይወቱን በቀጠፈው የግለሰብ በድን ላይ እየተሳለቀ ይዘባበታል? ይህንን መሰሉን ሰይጣናዊና የአራዊት ተግባር ከማውገዝ በዘለለ እንደ መንጋ ሆ! ብሎ በመሰባሰብ የጭካኔ ተግባር የፈጸሙትን ግለሰቦች ሰብአዊነት መፈተሽና በአግባቡ መመርመሩ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል።
የሀገርና የወገን ንብረቶችን በጠራራ ፀሐይ ነዳጅ እያርከፈከፉ በማቃጥል፣ በማውደምና በመዝረፍ ጮቤ መርገጥ በእርግጡ የጤነኛ ሰብአዊነት መገለጫ ናቸውን? በፈቃድ ያልተወለዱበትን ዘር፣ ብሔርና ቋንቋ እንደ ዋስትና በማውለብለብ የሌላን ብሔርና ቋንቋ ማዋረድና ማራከስስ ህሊናው ከሚሠራ የሰው ፍጡር የሚጠብቅ ነውን?
የሰብአዊነትን ክቡር ስጦታ እንደ ርካሽ ሸቀጥ ቆጥሮ በምክንያተ ቢስ ጀብደኝነት ከራስ መጣላት፣ ከወንድምና ከእህት መፋለም፣ ከፈጣሪ መጋጨት፣ ከተፈጥሮ ጋር መቃረን የአረዌነት ባህርይ እንጂ ሌላ ትርጉም የሚሠጠው አይደለም። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተዘረዘሩትን የሰብአዊነት ቅመሞች ማራከስና ራስን በደመ ነፍስ ጎራ መመደብ፣ የሰብእና መዝቀጥ ምልክት ተደርጎ የሚታይ ብቻ ሳይሆን ከህሊና ክብር ዝቅ ብሎ መዋረድ ጭምር ነው።
በሀገራዊ የዜጎች የሰብእና ተሐድሶና ግንባታ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ምድራዊ ስልጣንም ሆነ ወይንም “ሰማያዊ ክህነት” እና የባለድርሻነት ሚና አለን የሚሉ ተቋማት በጋራ ተቀናጅተው መሥራት የሚገባቸው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጊዜው ዛሬ ይመስላል። የፖለቲካውን ሥርዓት የሚዘውሩ ቡድኖችና መሪዎቻቸው የአባሎቻቸውን የሰብአዊነት አቋም ጤንነት ሊፈትሹና በተሐድሶ ላይ ትኩረት ሊያድርጉ ይገባል የሚባለውም ሰለዚሁ ነው።
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና መምህራን የምእመናቸውን ቁጥር ከማግዘፍ ይልቅ የአስተምህሯቸውን ጥራት በመፈተሽ በክበባቸው ውስጥ ለታቀፉት ዜጎች ጤነኛ የሰብእና ግንባታ ላይ ሊሠሩ ይገባል። የኪነ ጥበባት ቡድኖችና ባለተሰጥኦ ነን ባዮች በክፉዎቹ የሰው ልጆች አፀያፊ ባህርያት ላይ ብቻ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ወደ በጎነትና መልካምነት ሊያሸጋግሩ በሚችሉ ጭብጦች ላይ የጥበብ ሥራዎቻቸውን ደግሰው ቢመግቡን መልካም ይሆናል።
ልጆቻችን በሥነ ምግባር ትምህርቶች ታንፀው እንዳያድጉ ሆን ተብሎ ሲሰራበት የኖረው የትምህርት ካሪኩለም ሥር ነቀል ለውጥ ተደርጎበት ጊዜ ሳይሰጠው በዜጎች መልካም ሰብእና ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተደጋግሞ ተነግሯል። ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሕብረተሰብና የሚዲያ ተቋማት በጋራና በተቀናጀ ስትራቴጂ እየተመሩ በዜጎች መልካም ሰብእና ተሐድሶ ላይ በትጋትና በንቃት እንዲሰሩ የመንግሥት ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን ይገባል። ብልጭ ድርግም እያሉ ሀገራዊ ጥፋት የሚፈጸምባቸው የዛሬዎቹ የኢሰብአዊያን እንቅስቃሴዎች በጊዜው ካልተቀጩና በቁጥጥር ሥር መዋል እስካልቻሉ ድረስ ነገና ተነገወዲያ ብልጭታዎቹ ወደ ነበልባል እሳት ተለውጠው ወደ አልተፈለገና ልናርመው ወደማንችለው ጫፍ እንዳያደርሱን በዜጎች የሰብእና ተሐድሶ ሥራ ላይ ልንረባረብ ይገባል። ሰላም ይሁን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com