ህይወት ነዋሪዎቿን ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላኛው ክፍል ለማለፍ ሳይሆን ከቀን ቀንን ለማሸጋገር ስትከጅል “ማርክ” ሳትይዝ በራሷ መንገድ የምትፈትነን እልፍ ፈተና አለ። ባለታሪካችን የተመሰቃቀለ ህይወቷን ፈር ለማስያዝ የምትውተረተር የቀን ጎዶሎ ያጋጠማት ምስኪን ሴት ናት። ዛሬ ምንም የተጨበጠ ተስፋ በሌለበት ያመነችው ነገን አስባ ዝም ባለ ቀን ውስጥ የታመቀ ጩኸቷን እንዳትተነፍስለት ይሰማት ዘንድ ያለ ጆሮ ሰጪ ዘመድ ስለሌላት “ለእንዲህም ይኖራል” አምዳችንን ምስጢሯንና ብሶቷን አካፍላናለችና እኛም የህመሟን ጥልቀት በሷ ልክ ታመን ከሰፊው ህዝብ ዘንድ ይደርስላት ዘንድ እንዲህ ከትበነዋል።
የታሪኩ “አልፋ”…
ህይወት መለስ ትባላለች፤ የወጣትነት ዘመኗ እየጠለቀ የጉልምስናዋ ወራት መጣሁ መጣሁ እያለ ነው። ውልደቷ በአማራ ክልል ውስጥ ነው። የትውልድ ቀዬዋ “የነ ሸግዬ አገር የነ አይጠገቡ” ተብላ በምትሞካሸውና የውቦች መፍለቂያ በሆነችው ከተማ ነው።
የተወለደችባት ስፍራ በውቧ ኢትዮጵያ እስላም ክርስቲያኑ በፍቅር ላይለያዩ በተዛመዱባት፤ ላይላቀቁ በተጋመዱባት በፍቅር ጸዳሏ ከተማ ነው። በከተማዋ እስላሙ የክርስቲያኑን ማህተብ ሲገምድ ክርስቲያኑም የሙስሊሙን ቆብ ሲሰፋ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ሰው በሰውነቱ ብቻ ተከብሮ የሚኖርባት ህዝቡም አብሮ ለመኖር የሰው መሆንን መስፈርት ብቻ ሚዛኑ ያደረገ ነው፤ የሰውነት ትርጉም ከንግግር ባለፈ በመኖር የገባው ነው። ብዙ ታዋቂ ሰዎች ምሁራን ዘፋኞች ፖለቲከኞችንና ሌሎችንም ለሀገራችን ያበረከተችው የወሎ አብራክ ክፋይ የሆነችው ደሴ ከተማ!
ደሴ ለህይወት እልፍ ትርጉም አላት። ድሮስ ሰው የእድሜውን ጥንቅሽ ወራት ያሳለፈበትን ስፍራ ያውም በአይጠየፍ አዳራሽ ግብር የበሉ አያቶቹን ታሪክ ለማየት ያዳራሹን ውጪና ውስጥ ሲያልፍ ሲያገድም ሰላም ያለ፣ በአርዲቦ ሀይቅ ዋኝቶ በቦታው የፍቅር ወራቶቹን አሳልፎ፣ በድምፀ መረዋው አለማየሁ እሸቴ ጥኡም ሙዚቃ ውስጥ ዝንጀሮ አይወጣውም ከተባለው ከጦሳ አቀበት ጋር ቃል ኪዳን ለተገባባ ሰው እንዴት ደሴ ብዙ አትሆንለት?
ሥራና ህይወት…
ህይወት ለህይወት ፈተናን የጀመረችው ገና ከጅምሩ ነበር። ኀዘኗን በጉያዋ ፍቅሯን በልቧ ደስታዋን ባንጀቷ ሸሽጋ ብዙ ስቃይ የተሸለመ ዘመን ኖራለች። ከደሴ ከተማ እንደ ወጣች ወደ ሌላኛዋ ውብ ሀገር ከተመች። ሀገሪቷ የፀሐይ መውጫዋ የምስራቅ ፈርጥ ናት። ሰው ሁሉ ሲወድም ሲጠላም ፊት ለፊት ነው። ነገር ከኋላ አይጎነጉንም። ከነዋሪዎቿም አፍ ላይ አቦ የሚል ቃል ተከትቧል። የበረሀዋ ገነት ድሬዳዋ ።
የሆነ የህይወት አጋጣሚ ህይወትን ድሬዳዋ አስከትሟታል። ድሬዳዋ የሄደችበትን ትክክለኛ ወቅት ባታስታውሰውም ረጅም ዓመት ቆይታለች። ድሬዳዋ ህይወትን እጆቿን ዘርግታ ተቀበለቻት። ድሬዳዋ ቤተሰቦች ነበሯት። የቅርቤ የምትላቸው አያቷ የጡት ካንሰር ታማሚ ነበሩና ክፉ ሞት ህይወትን ካለ አያት አስቀራት። የድሬዳዋ ዘመዶቿ በቻሉት መጠን ይረዷትም ነበር። አያቷን በሞት ስትነጠቅ ግን ሁሉም ነገር አከተመ። እሷ ስትሞት ህይወትን የሚረዳ ሰው ታጣ። መኖር ግድ ነውና ህይወት ቀጠለ።
ኑሮዋን ለማቅናት የተገኘውን ሥራ በመስራት ትተዳደር ነበር። ሥራ ከተባለ ህይወት ፅዳትም ሆነ ያገኘችውን ሥራ ሳትመርጥ ትሰራው ነበር። ስትታይ ትታመንና የእጇም ንፅህና አሰሪዎችን ይማርክ ነበርና ድሬዳዋ ውስጥ በአንድ ኢንተርናሽናል ሆቴል ውስጥ የመስራት ዕድል አጋጥሟታል።
ፍቅርና ህይወት…
ህይወት ፈተናዋ ቢበረታም እጅ አልሰጠችም ። አንዱን ሁለት ለማድረግ ጥቂቱን ለማበርከት ትታትር ነበር። በድሬዳዋ ከተማ ላይ በሚገኘው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስትሰራ ያገኘችው የሱማሌ ጉብል ልቧን ረታው። ጠየም ባለ መልኩ ላይ ሉጫና በአንድ ጎን የበቀለ ሽበት ያለበት ፀጉሩ ውበትን ሸልመውታል። ጉብሉ በዩኒቨርሲቲው በቆየባቸው ወራት ከወጣቱ ጋር ጥሩ የሚባል የፍቅር ህይወት ነበራት። ነገሩ እንዲህ ነው። በሥራ ቦታዋ እግር አበዛ፤ ተለማመዱ። ወደድኩሽ አላት። ላትጠረጥር አምና ላትጠላ ወደደችው። በዛም ቀድማ የወደደችው ልቧን ሰጠችው።
ወጣቱ ፌዴራል ፖሊስ ነበር። መቆም የማይችሉት ቀናት ተመሙ። ፍቅራቸውም ብዙ ርቆ ሄደ። ሥራ መስራቷም ቀጥሎ ነበር። በዚም መሀል ህይወት አረገዘች። ነገር የመጣው አሁን ነው። ከእርግዝናዋ መከሰት በኋላ የነገሮች አቅጣጫ ተቀያየሩ። ልቧን የሰጠችው ሰው ቀድሞም ቀልቡ ከሷ አልነበረምና ስታረግዝ ልቡን ነሳት።
ድሬዳዋ ከተማ በተለምዶ አሸዋ የሚባለው ሰፈር መሄጃ ላይ ባለ መከላከያ ካምፕ ውስጥ አየር ወለድ የሚባል ስፍራ ላይ ሁለት ወር እንደሰራች በእርግዝናዋ ምክንያት ከባድ ማቅለሽለሽ ስላለው ሥራ መስራት ያቅታታል።
የሚገርመው ነገር እሷ ያላወቀችውን የእርግዝና ወቅት ወጣቱ ቀኑን ቆጥሮ መጥፋቱ ነበር። ወደ ኡጋዴንና ሌላም ይኖርበታል ብላ ተስፋ የጣለችበት ስፍራ ድረስ እሱን ፍለጋ እግሯ ኳተነ፤ አለ ባለችበት ሁሉ ተጓዘች። አውቆ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም ሆነና ፍለጋዋ መና ሆነ። ፍቅሯን የበላው ጅብ ትንፍሽ ሊል አልፈለገም።
እስካሁን ድረስ ማርገዟን አላወቀችም ነበር። የማስታወክና ሌላም ስሜት ሲሰማት ወቅቱ በድሬዳዋ ላይ ደንጌና ኮሼ የሚባል በሽታ ገብቶ የነበረበት ወቅት ስለነበር ያንን በመጠራጠር ወደ ህክምና ሄደች። ሽንት ስጪ ተብላ ውጤቱ እርግዝናዋን ያረዳት ነበር።
ልቧንም ሴትነቷንም አሳልፋ የሰጠችው ሰው ከሷ ውጪ የራሱ የሚለው ሌላ የትዳር ህይወት ያለው ያውም የልጅ አባት አዲስ አበባ ውስጥ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ከፍቶ በዛ መተዳደሪውን ያደረገ ሆኖ ተገኘ።
መከዳት፤ መጣል፤ መረሳት፤ መታለል ሌሎችም የህይወትን ልብ ያደከሙ መጥፎ ስሜቶች ነበሩ። ቢሆንም ማርገዟን አውቆ የራቃትን ሰው ልትረሳ ግን አልቻለችም ነበር።
ከወራት በኋላ መጥፎ ትዝታዎቿንም፤ ድሬዳዋንም ተሰናብታ ወደ አዲስ አበባ መጣች። መጎዳት ላጎበጠው የህይወት ትክሻ ሌላ ከባድ ወራት መጡባት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ከገጠሟት መጥፎ ነገሮች ጋር ታግላ ልጇን ለማሳደግ አቅዳ ብትወልደውም ውጤቱ ግን ሌላ መከራ ይዞባት ከተፍ አለ።
በስቃይ የተሞሉ የእርግዝና ጊዜያትን አሳልፋ ወንድ ልጅ ተገላገለች። የአራስነት ግዜዋ ኀዘን ያረበበበት
ትካዜን የተሸለመም ነበር። ማንም አጠገቧ ያልነበረበት የህይወቷም ከባድ ጊዜ ስትል ታወሳዋለች። አብሯት ማንም ካለመኖሩ የተነሳ በአካባቢው የነበሩ ያዘኑላት ፖሊሶች ነበሩ በምጧ ሰዓት ወደ ሆስፒታል ወስደዋት የነበሩት። ሶስት ቀናትን ያስቆጠረ ከባድ ምጥም ነበር።
በከባዱና ፈታኝ በሆነው ምጧ ሰበብም በህይወት ትተርፋለች ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም። እጣ ፈንታና ፈጣሪ ሙቺ ብለው ያልፈረዱባት ነፍስ ነበረችና በህይወት ተረፈች።
ከማስወረድ መውለድ ይሻላል ብላ የወለደችው ልጇ ግን ሌላ ጉዳት ይዞ ተወለደ። በእርግዝናዋ ወራት በነበራት ምርመራ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደነበር ነው የተነገራት። ስትወልደው ግን ብወልደውም ሰርቼ ልጄን አሳድገዋለሁ የሚል ተስፋዋን ያመነመነ ክስተት ተፈጠረ። ብዙ ፈተና ያየችበት ኀዘኗን ዋጥ አድርጋ የወለደችው ልጇ እግሩ ችግር ነበረበት። የልጇ ሁለት እግሮች ዞረው ነበር የተወለደው። እግሮቹን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለማዞር የሚደረገው ጥረትም እጅግ አድካሚ ነው። ማንም ረዳት በሌለበት ሁኔታ ዞረው የተወለዱ የልጇን እግሮች ትታ ሥራ አትወጣ ነገር እንዴት ተብሎ። ሥራዋን አቁማ አትኖር ነገር ምን በልታ ትኑር?
ህይወት ህይወትን መንታ መንገድ ላይ ጥላታለች። በልቶ ለማደር ልጇን መተው ወይ ልጇን ለማኖር ሳይበሉ ማደር የሚሉ መንታ መንገዶች ላይ ህይወት ተገኘች።
የምስጋና እጅ መንሻ…
ሰው ባልነበራት እንዲሁም የሰው ረሀብ በፈጃት ወቅት አለሁልሽ ያላትም አልታጣም። በአካባቢው የኮሮና ቫይረስን በሚመለከት የተቸገሩትን ለመርዳት የተቋቋመው 31 ማዞሪያ የበጎ አድራጎት ማህበር አለሁልሽ ብሎኛል ትላለች። ምሳና ራቴን ችሎ ለእርዳታ ከሰበሰበው አስቤዛ ላይ የእለት ጉርሴን አልነሳኝምና ምስጋና ይቸረው ትላለች። በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ልጇን ለማከም ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ ታታሪ ዶክተሮችም የምስጋና ቃሎቿ የተሰውላቸው ናቸው። ልጇን በማከም ሂደቱ ላይ ከነበራቸው አስተዋፅኦ ባልተናነሰ የቤት ኪራይ እስከ መክፈል ድረስ የሰብአዊነት ሥራን ሲከውኑ ነበርና።
የታሪኩ “ኦሜጋ”…
ዛሬ የልጇ የዞሩ እግሮች በሀኪሞች እርዳታ ለውጥ ቢያሳዩም ያለ ሰው እርዳታ ግን ልጁ ምንም ማድረግ አይችልም። ሁለቱ እግሮቹ መሀል ላይ በተሰካ ቱቦ ታግዞ እየኖረ ነው። ምስኪኗ ህይወትም ሰሚ ያጣ ጩኸቷን ለመስማት ብሎም አባሽ ያጣ እምባዋን ለማበስ የሚችልን ፍቃደኛ ሰው እየተጠባበቀች ነገን በቀቢጸ ተስፋ ተሞልታ ነገን ደጋጎችን ያመጣላት ዘንድ እየፀለየች ዛሬን በመከራ እየኖረች ነው። ለጊዜው ህይወት በበጎ ፍቃደኞች መጥፎ ቀናቶቿን እያሳለፈች ነው።
ህይወት ስለነገ ህይወቷ ስታስብ ከተራበው ሆዷ በላይ ካለሰው መንቀሳቀስ የማይችል የልጇ ጉዳይ ያስፈራታል። በተሰበረው እጇ የተሰበረ ተስፋን ታቅፋ ኑሮን ለመግፋት ተገዳለች። ‹‹ማን ያውቃል ቀጣይ ከሚነጋው ፀሐይ አብሮ የሚነጋ ተስፋ ይኖራል፤ ልጄንም ልቤንም የሚጠግን ቀን ይመጣል›› እያለች በህይወት ተስፋ ላለመቁረጥ መልካም መልካሙን ታስባለች።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
ዳግማዊት ግርማ