በኦሮሚያ ክልል ያሉ የኦሮሞ ፓርቲዎች መሰረታዊ በሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎቶች ላይ የሚታይ ልዩነት የላቸውም፡፡ ይህ ባልሆነበት በክልሉ ያለው የፓርቲዎች ሽኩቻ ከቡድኖች የስልጣን ፍላጎትና ከግለሰብ ጥቅም የዘለለ እንደማይሆን የሕግና የፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ ተናገሩ፡፡ አሁን ያለው ለውጥም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊና መጠበቅ ያለበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የሀግና ፖሊሲ ምሁር የሆኑት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኦሮሞ ፖለቲካ የዳር ፖለቲካ ነበር፤ አሁን ግን የመሃል ፖለቲካ መሆን ችሏል፡፡ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ይሄንን ነገር ከመደገፍ ይልቅ እርሱን ተሳፍረን ስልጣን እንይዛለን በሚል ቅዠት የህዝብን ትግል ማደናቀፍ የለባቸውም፡፡ ስለዚህ በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ በህዝብ ደረጃ በኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች ላይ የፖለቲካ ልዩነት የለም፡፡ ለምን ቢባል፣ ከኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች አንዱ የቋንቋ ጥያቄ ሲሆን፤ ይሄም የኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ ይሁን የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተዘግቶ የነበረው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ በር በጥቅሉ በዚህች አገር ውስጥ ለመገልገልም ሆነ ለማገልገል በኦሮሞ ላይ በር የዘጋው አንዱ የቋንቋ ፖሊሲ እንደመሆኑ ይህ ፖሊሲ እንዲለወጥ ነው፡፡
ይሄንን እንቃወማለን የሚል የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገር እንዳይሆን ለማደናቀፍና ኦሮሞን ለመከፋፈል ብሎም ትኩረቱን በሌላ ነገር ላይ እንዲያደርግ የሚያደርጉ ሰዎችና ድርጅቶች ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው የኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ፣ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት ኦሮሞ መሬቱ ሲዘረፍና ከቦታው ሲነቀል ነው የነበረው፡፡ እናም የመሬት ጉዳይ ትልቅ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ነው፡፡
ሦስተኛ፣ ኦሮሞ ህዝብ የሚፈልገው ራሱን በራሱ ማስተዳደር እና እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህችን አገር ከውጭ ወራሪ ሲከላከልና መስዋዕትነት ሲከፍል የቆየ እንደመሆኑ እርሱም ሆኑ ሌሎች ህዝቦች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአገር ባለቤት መሆንን የሚመለከት ነው፡፡ በእነዚህ ዙሪያም የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ፣ የአከባቢና ሃይማኖት ክፍፍል የለውም፡፡
እንደ ዶክተር ብርሃነ መስቀል ገለጻ፤ ቢያንስ በእነዚህ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በኦሮሞ ውስጥ የፖለቲካና ሌላ ልዩነት ከሌለ ምንድን ነው የሚያጣላቸው የሚለው ሲታይ፤ ከቡድኖች የስልጣን ፍላጎትና ከግለሰቦች ጥቅም የዘለለ ነው የሚል እምነት የላቸውም፡፡ ከዚህም ውጪ ነው የሚል ግንዛቤ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ለውጥ መምጣት ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ የዘመናት ትግል ውጤት ያገኘበት ነውአግኝቷል፡፡ የትግሉም ዋነኛ ግብ በዚህ አገር እኩልነትን፣ ነጻነትንና የህዝብ መንግስት ማረጋገጥ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካም ሆነ የአከባቢና የሃይማኖት ክፍፍል የለውም፡፡ ይሄንን ህዝብ አታግለው እዚህ ያደረሱት ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ ህዝቡ እራሱ ታግሎና እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ተናብቦ ነው ለዚህ የደረሰው፡፡
እናም ስልጣንም የሚፍልጉትም ሆኑ ሌላ ነገር የሚፈልጉት በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች፤ ክልሉን በእውቀትና በእውነት መምራት ኢትዮጵያን በእውቀትና በእምነት ወደ መምራት መሸጋገር መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም አቅምና ችሎታው ላለው በሁሉም ሥፍራ ቦታ አለው፡፡ የኢትዮጵያን ድንበር የሚገድበው ደግሞ መጠን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከኢኮኖሚ አኳያ አስፍቶ ማየት ከተቻለ እንኳን ምስራቅ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቻይቻውያን አፍሪካን፤ አሜሪካውያንም ዓለምን መኖሪያቸው አድርገው እየኖሩ መሆናቸውን መመልከት ተገቢ ነው፡፡
ይህ የሆነው ስለተባበሩና አንድ ድምጽ ሆነው ስለወጡ፤ እንደ ፖለቲካ ማህበረሰብና እንደ አገር ማሰብ ስለቻሉ ነው፡፡ እናም በየቦታው ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ይሄንን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ፣ አሁን ያለው ለውጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መሳካትና አለመሳካት ላይ የሚያተኩር እንደመሆኑ ለውጡ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊና መጠበቅ ያለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በዚህ ጉዳይ ግልጽ አቋም መያዝ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ ግራና ቀኝ እያለ በድንዛዜ መቀመጥ የለበትም፡፡ ምክንያቱም እንደ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሶማሊያና ኢራቅን የመሳሰሉ አገሮች የፈረሱት የተወሰነው ቡድን ነገሮችን እያጦዘ ሲያሳብድ፤ ሌላው ወገን ደግሞ ደንዝዞ ሲቀመጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሚደነዝዝ ወይም ዝም የሚል ቡድን ደንዝዞ መቀመጡን ከቀጠለና በአንጻሩ ነገሮችን እንደፈለጉ የሚያጦዙና የሚያሳብዱ ሰዎች ከቀጠሉ ይህች አገር እንደ አገር ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ በሃላፊነት ይሄንን ለውጥ መደገፍ ይኖርበታል፡፡
በወንድወሰን ሽመልስ