አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ብሄራዊ ቡድን በጀርመን ለሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሳቦም ዮሴፍ ገለታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገለጹ። ከሚያዝያ 20 እስከ 30 ለሚካሄደው በጀርመን አዘጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ቴኳንዶ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ የምትሳተፍ መሆኑን ገልጸው፤ በሻምፒዮናው 6 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።
ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡት ተጫዋቾች የተመለመሉበት መስፈርት በአገር አቀፍ ውድድር የወርቅና የብር ሜዳሊያ ያመጡት መሆናቸውን የገለጹት ኢንስትራክተር፤ሜዳሊያው የመጀመሪያው መስፈርት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ መስፈርቶች እንደነበሩም ተናግረዋል። ኢንተርናሽናል ቴክዋንዶ አምስት አይነት የመወዳደሪያ ዘርፎች አሉት፤ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ ሶስቱን መሳተፍ መቻል ሌላ መስፈርት እንደነበር አስረድተዋል።
በዚህ መሰረት የነበረው የብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ ዝግጅቱን የጀመረው ከአንድ ወር በፊት ሲሆን ለሁለት ወራት ያህል የሚዘልቅ መሆኑንና በሻምፒዮናው ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ከብሄራዊ ቡድኑ አባላት አንዷ የሆነችውና ከአዲስ አበባ የተመረጠችው ሳምራዊት ዘርጋው እንደተናገረችው፤ ለብሄራዊ ቡድን የተመለመሉት በዚህ ዓመት ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ብርና ወርቅ ያመጡ ተወዳዳሪዎች ፓተርን፣ ፋይትና ሰበራ ካታጎሪዎች መሰረት በማድረግ ምርጫ ተደርጎ ስድስት ተጫዋቾች ለብሄራዊ ቡድን ተመርጠዋል፡፡ በሻምፒዮናው ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን በሳምንት ሶስት ጊዜ ልምምድ እያደረጉ ዝግጅታቸውን እያደረጉ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ‹‹ለሻምፒዮናው እኔም ሆንኩኝ ጓደኞቼ ልዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥተነዋል። በመሆኑም በሻምፒዮናው ለወከልናት አገራችንን ሜዳሊያ በማምጣት ሰንደቃላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እናደርጋለን›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች ።
ከአዳማ ከተማ የተመረጠው ጥሩ ሰው በልሁ በበኩሉ፤ የአፍሪካ ወርልድ ቴክዋንዶ ሻምፒዮን ሺፕ በመሳተፍ ወርቅ ያመጡት ከተመለመሉ በኋላ ማጣሪያውን ያለፉት ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ መመረጣቸውን ተናግሯል። ‹‹ዓለም ሻምፒዮና በጣም ፈታኝ ውድድር መሆኑ ይታወቃል ፤በአሰልጣኞቻችንም እየተሰጠን ያለው የስልጠና ዝግጅት ይሄንኑ መሰረት ያደረገ ነው። ዝግጅታችንን ከጀመርን አንድ በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት እናመጣለን ብለን›› እናስባለን ሲል ተናግሯል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ዳንኤል ዘነበ