አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያላትን ስምና ዝና እንዲሁም ውጤት ለማስቀጠል ሲባል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ለማድረግ ቅድመ ማጣሪያ ውድድሮችን ማድረግ የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በየዓመቱ ከሚደረጉ ቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ይጠቀሳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ላይ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች አትሌቶች ክለቦቻቸውን በመወከል ያላቸውን አቅም ማሳየት ከጀመሩ ሰባተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄደው ሻምፒዮናው በትናንትናው እለት በአሰላ አረንጓዴው ስታዲየም በይፋ ተጀምሯል።
የውድድሩ ውጤታማ አትሌቶች የውድድሩ ዓላማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄዱ የወጣቶች ውድድር አገራቸውን ወክለው የሚካፈሉ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ፤ቀጣይ ለአገሪቱ አትሌቲክስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሆነም ጭምር መሆኑን ተነግሯል። የሻምፒዮናው አላማ ይሄንን መልክ የያዘ ቢሆንም ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማግኘት ያለመ ቢሆንም ፤የዕድሜ ተገቢነት ችግር አሁንም ሊፈታ ያልቻለ ጉዳይ እንደሆነ የተለያዩ ባለሙያዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።
ፌዴሬሽኑም ይህን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነበትና ክልሎችና ክለቦች ሲጠየቁ ክለብ ሲገባ ዕድሜውን እንዲቀንስ ተደርጎ የተመዘገበበትን ሀሰተኛ የሆነ ማስረጃ እንደሚያቀርቡ በተደጋጋሚ ሲነገር ነበር። በዚህ ምክንያት ዕድሜያቸውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑ ይነሳል። ከዚህ በመነሳትም የዘንድሮው የሰባተኛው ከ20 ዓመት በታች የታዳጊዎች ሻምፒዮና ከዚህ ችግር የጸዳ በሆነ መልኩ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ስለመሆኑ ጥያቄን አስነስቷል። ሻምፒዮናው ከትናንት ማለዳ ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል።
በእለቱ ከተካሄዱ ውድድሮች የስሉስ ዝላይ ሴቶች ከኦሮሚያ ክልል እንደቴ ሮቤ 11.67 ሜትር በመወርወር አንደኛ ስትሆን ፣ ኡጁሉ ኦዶላ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 11.64 በመወርወር ሁለተኛ ፣ ኩለኒ ድሪባ ከኦሮሚያ ክልል 14.54 በመወርወር ሶስተኛ ሆነዋል። ዲስከስ ውርወራ ወንዶች የሲዳማ ቡና ለማ ከተማ 47.44 በመወርወር አንደኛ ሲሆን፣ የመከላከያው ጌታቸው ተመስገን እና የአማራ ክልሉ አየነው ኮሴ 47.23 እና 42.80 በመወርወር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በሴቶች ዲስከስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ መሪያምመዊት ፀሀዬ 38 .73 ሜትር በመወርወር አንደኛ ሆናለች። ማርታ በቀለ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 34.99 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ፣ ትንጓደድ ተሰማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከንግድ ባንክ 32.89 በመወርወር ሶስተኛ ሆናለች። የወንዶች 10 ሺ ሜትር ሌላው በትናንትናው እለት የተካሄደ ውድደር ሲሆን ጸጋዬ ኪዳኑ 29፡34፡27 ሰዓት በመግባት ከመስፍን ኢንጂነሪንግ አሸናፊ ሲሆን እርሱን ተከትሎ ሚልኬሳ መንገሻ ከሰበታ ከነማ ክለብ 29 ፡35፡65 ሁለተኛ እንዲሁም ወርቅነህ ታደሰ ከኦሮሚያ ክልል 29፡39፡98 ሰዓት አስመዝግቧል።
በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም የሚካሄደው ሻምፒዮናው ለቀጣይ አራት ቀናት በድምቀት የሚቀጥል መሆኑን ታውቋል። ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድሩ 9 ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 34 የተለያዩ_ ክለቦችና ተቋማት ተካፋይ ሆነዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ዳንኤል ዘነበ