አዲስ አበባ፡- ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እየጎላ መምጣቱ ይታወቃል። በዚሁ ችግር ምክንያትም በርካታ ጉዳቶች በሰዎችና በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ሲደርሱ ክለቦች ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብና ነጥብ ተቀጥተዋል። በመሆኑም ይህንን ችግር ስር ሳይሰድ በቁጥጥር ስር መዋል ስላለበት በሚመለከታቸው አካላት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ጥረቶቹ ሙሉ ለሙሉ ፍሬ አፍርተዋል ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰቶች አሁንም እየተስተዋሉ መሆኑ ነው።
ስፖርታዊ ጨዋነት በስታዲየሞች ውስጥ ብጥብጥና ሁከት መፍጠር ብቻም ሳይሆን የተከለከሉ ድርጊቶችን መፈጸምንም ጭምር ያካትታል። ለአብነት ያህል የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ጉዳይ በስፖርት ሜዳዎች ላይ ማንጸባረቅ የተወገዘ ነው። ዓለም አቀፉን እግር ኳስ የሚመራው ፊፋም እንዲህ ዓይነት ጥፋቶች ሲፈጸሙ ቅጣት ከማስተላለፍ ወደኃላ አይልም። ነገር ግን የተከለከሉት እንቅስቃሴዎች አሁንም በውድድሮች ላይ መታየታቸው አልቀረም፤ ከትናንት በስቲያ በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የታየው ክስተትም ይኸው ነው።
ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ በመቀሌ ስታድየም በተገናኙበት ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ 1-0 በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። በጨዋታው ላይም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጂራ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተው ጨዋታውን እንዳስጀመሩ ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል።
በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ሶስት እጅግ ለጎል የቀረቡ ዕድሎችንም አምክነዋል። ዘግይተው ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት መቐለዎች በ36ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል በቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ አሸናፊ ሆነው ጨዋታውን ማጠናቀቅ ችለዋል። ሰላማዊ በነበረው በዚህ ጨዋታ ላይ ግን የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ያሳዩት ያልተገባ ድርጊት(ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ባነር ይዞ መገኘት) ስፖርታዊ ጨዋነት አሁንም ድረስ አለመስፈኑን የሚያሳይ ነበር።
በተለይ ሁለቱ ክለቦች ጨዋታው ከመካሄዱ አስቀድሞ ትኩረቱን በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ያደረገ ውይይት ማድረጋቸው ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል። ቀደም ሲል ሁለቱ ክለቦች በአዲስ አበባ ስታዲየሞች በደጋፊዎች መካከል የተከሰተውን ሁከት ለመፍታት ብሎም የእግር ኳሱን የሰላም መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚዎች መቐለ ድረስ በመጓዝ የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ከመቐለ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከክለቡ አመራሮች እንዲሁም ከደጋፊ ማህበራቱ ተወካዮች ጋርም ውይይቱ ተካሂዷል።
በወቅቱም የተከሰተውን ችግር በማጣራት መፍትሄ እየተሰጠ እንዲኬድ፤ ባለድርሻ አካላትም ለስፖርት ሰላም በጋራ መስራትና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ተገቢው ጥንቃቄ በማድረግ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር። ከዚህ ባሻገር ሁለቱ ክለቦች ችግሩን ብቻ ከመዘርዘር በይቅርታ ወደ ሰላማዊው መንገድ በመጓዝ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው በሚለው ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሮ ነበር።
ይሁን እንጂ በጨዋታው ወቅት የታየው፤ ምናልባትም ደጋፊዎችን ለጠብ የሚያነሳሳና ከመግባባት ላይ የተደረሰበትን ጉዳይም የሚያፈርስ ድርጊት ነበር። በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነት ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን ወደ ስታዲየም እንዲገቡ መፍቀድ ተገቢነት እንዲሁም ኃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው። ፖለቲካዊ ጉዳይ በሜዳ ውስጥ መንጸባረቁም በስፖርት ህግ መሰረት የሚያስጠይቅ ይሆናል። በተለይ የስፖርቱ አመራሮች በተገኙበት መድረክ ይህ ዓይነቱ ክስተት መስተዋሉ በቀጣይስ ምን ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት የሚያሳድር ነው።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን፤ «ስፓርታዊ ጨዋነት ችግሮች፣ መንስኤዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች» በሚል የማስፈጸሚያ ሰነድ ማዘጋጀቱ ይታወቃል። በሰነዱ ላይም በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ የስፖርታዊ ጨዋነት አቀጣጣይ ምክንያቶች በሚል ዘርዝሯል። አልኮል ጠጥቶ ወደ ስታዲየም መግባት፣ የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ፣ ስሜት ቀስቃሽ መረጃዎችን ማቅረብ እንዲሁም ዳኞችና ኮሚሽነሮች ከሜዳ ውጪ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት አቀጣጣይ ምክንያቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ አቀጣጣይ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሰውንና ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ፖለቲካዊ መልዕክት ከስታዲየም ተሰቅሎ ጨዋታው ተካሂዷል። ይህም የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰትን ከሁከት ጋር ብቻ የማያያዝ ዝንባሌ መኖሩን የሚያሳይ ነው። ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ ላይም ያለውን ክፍተት በግልጽ የሚያመላክት ነው። ነገሮች ከሆኑ በኃላ ማውገዝና ቅጣት መጣል ብቻውን መፍትሄ ባለመሆኑ በቅድሚያ አዋኪ ነገሮችን ማስወገድ የየትኛውም አካል ኃላፊነት ሆኖ ሳለ የታየው ግን አመራሮቹንም ጭምር የሚያስወቅስ ነው።
በመሆኑም በፌዴሬሽኑ እንዲሁም በክለቦች በኩል በርካታ የሚቀሩ የቤት ስራዎች መኖራቸው ሊታሰብበት ይገባል። ክለቦች እንዲሁም የደጋፊ ማህበራት ለአባላቶቻቸው ክለቦች በባላንጣነት እንዳይተያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እና ማሳወቅ ተገቢ ነው። ፌዴሬሽኑም በአንደኛው ሜዳ ላይ የታየውን ጥሰት ለመድገም በክለቦች መካከል የሚደረገውን ፉክክር አስተማሪ በሆነ መልኩ የሚያስታግስ እርምጃ መውሰድ አለበት። ከዚህ ባሻገር ስፖርታዊ ጨዋነትን አስመልክቶ በተሰራው ጥናት ላይ የተመለከቱትን ማስፈጸሚያ የመፍትሄ ሃሳቦች በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ብርሃን ፈይሳ