የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ ጡንቻው በርትቷል። አሜሪካም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳቱን ከሚያስተናዱ አገራት የመጀመሪያ ደረጃውን እንደያዘች ቀጥላለች። በዚህ የተነሳ ስህተቴ ምን ይሆን? መፍትሄውስ ከየት ይምጣ? በማለት ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ከሰሞኑ በመከላከል ተግባሯ ላይ ጥናት አካሂዳ ውጤቱን ይፋ አድርጋለች። የክትባት መድኃኒት ማምረት እንደጀመረችም ከአንድ ባለስልጣኗ ተሰምቷል።
በጥናቱ እንደተመለከተው የኮሮና ወረርሽኝን ከመከላከል አኳያ 24 በመቶ ዜጎች ራሳችንን ከሚገባው በላይ እየጠበቅን ነው ይላሉ። 39 በመቶዎቹ ቢያንስ አንድ የንጽህና መጠበቂያ እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል። 19 በመቶዎቹ ደግሞ የሚመገቧቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች በበረኪና ጭምር ያጥባሉ። 18 በመቶዎቹ ደግሞ በሳሙና ምትክ በጣም መርዛማነት ባላቸውና ሊጎዱ በሚችሉ አልኮሎች ጭምር እያጠቡ እንደሚጠቀሙ ጥናቱ ይፋ አድርጓል። በዚህ የተነሳም የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ያስፈልጋሉ፤ አትክልትና ፍራፍሬዎች በሽታን የመከላከል አቅም ያሳድጋሉ። ነገር ግን በኬሚካል እስካልተጎዱ ድረስ ነው። ወደ ሰውነት ሰርገው ሊገቡና ሊጎዱ የሚችሉትን የማጠቢያ ኬሚካሎች ተገልጋዮች መለየት ይኖርባቸዋል ሲል ምክር ለግሷቸዋል።
በኢትዮጵያስ የምግቦቻችንን ምድቦች፣ ጥቅሞች፣ በማጠብ ሂደቱ ሳንጎዳቸውና አስፈላጊነት ተረድተን የመከላከል አቅም እየፈጠርን ይሆን? ራሳችንን መዝነን ማስተካከል ይቻል ዘንድ ቀጥሎ በዝርዝር ይዳሰሳል። የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ለረጅም ጊዜያት ትኩረት ሳይሰጥ በቆየባቸው የምግብና የስርዓተ ምግብ ይዘቶች ዙሪያ ትኩረት መስጠት የጀመረበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የሰውነት የመከላከልን አቅም በማሳደግ ኮሮና ወረርሽኝን ድል ማድረግ ይቻላል።
አቶ ቢራራ መለሰ በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ ቅመማ ቅመሞችን መመገብ ‹‹ኢሚዩኒቲ›› የሚባለውን የበሽታ የመከላከል አቅም መገንባት ያስችላሉ። በመሆኑም ‹‹ኢንፌክሽን›› የሚከላከሉ ናቸው። ስለዚህ ከስጋና ከቅባት እህሎች ቀንሶ በአትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ በማተኮር አመጣጥኖ መመገብ ሰውነት በቂ የሆኑ ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን ማግኘት እንዲችል ይረዳል። የሰውነትን በሽታ በቀላሉ የመከላከል አቅም ያድጋል ይላሉ።
እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሕጻናትን በበቂ መጠን ጡት ማጥባት አለባቸው። በተጨማሪም ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ለሕጻናት ተጨማሪ ምግቦች ማቅረብ ያስፈልጋል። ተጨማሪ ምግቡ ምጥን መሆን ይኖርበታል። ሕጻናቱ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ያካተተ ምግብ ማግኘት አለባቸው። ስብጥሩን የያዘ፣ድግግሞሹን ያረጋገጠና ከፍ ሲሉም ሕጻናት በቂ ምግቦች ካገኙ በኮቪዲ 19 ኝም ሆነ በሌሎች በሽታዎች በቀላሉ አይጠቁም። ስለዚህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በንክኪዎች የሚተላለፍ እንደመሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከገበያ እንደመጡ በንጹህ ውሃ ማለቅለቅና ማጠብ ይገባል። ከቤትም ሲቀመጡ፣ ሲዘጋጁም ጭምር በተቻለ መጠን መበከል እንዳይፈጠር ማድረግ ይገባል። የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችም ንጽሕናቸው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እንዲጠበቁ አድርጎ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ይላሉ።
አትክልትና ፍራፍሬዎች በሚታጠቡበት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ‹‹ኒውትረንት›› በውስጡ ሊኖር ይችላል። በተቻለ መጠን የአትክልቱን ምንጭ ማረጋገጥ ተገቢነት አለው። አትክልቶቹ ከንጹህ ቦታ መምጣታቸውን በማረጋገጥ በንጹህ ውሃ አጥቦ መጠቀም ቢቻል ይመረጣል። ጎመን በሳሙና ማጠቡ የሚመከር አይደለም። በኬሚካል ማጠቡም ከኬሚካሎቹ ጋር በተያያዘ በረጅም ጊዜ የሚጎዱ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ካንሰር አይነት በሽታዎችን ያባብሳሉ። ፍራፍሬዎችን በተመለከተ በሳሙና በደንብ ማጠብ አስፈላጊ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለብ ባለ ውሃ ቢታጠቡ የኮቪዲ 19 ቫይረስን ጨምሮ ሌሎች በዓይን የማይታዩ በሽታ አምጪ ነገሮች ስለሚወገዱ ጥቅሙ ላቅ ያለ እንደሆነ አቶ ቢራራ ገልጸዋል። ሕብረተሰቡ በቶሎ የሚበላሹ ምግቦችን ገዝቶ በማከማቸት ለበሽታ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ። የተመጣጠኑ አመጋገቦች ለኮቪዲ 19 ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች በሕይወት ሲኖሩ በየእለቱ ከበሽታዎች ተጠብቀው መኖር ይችሉ ዘንድ የሚያስችሉ ናቸው።
የምግብ ምድቦች
የስርዓተ ምግብ አማካሪው አቶ ቢራራ እንዳሉት፤ ምግቦች ከሚሰጧቸው ፋይዳዎች አንጻር በተለያዩ ምድቦች ሊከፈሉ እንደሚችሉ የምግብ ጥናት ባለሙያዎችን አጣቅሰው ያስረዳሉ።
መደበኛ የምግብ ምድቦች ስር የሚካተቱት ኃይል ሰጪ የምግብ አይነቶች ሲሆኑ በይዘታቸው ደግሞ የካርቦ ሃይድሬት የምግብ ንጥረ ነገር የያዙ ናቸው። በአብዛኛው እንደ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ገብስ፣ ስንዴ ዓይነቶቹ ይካተታሉ። እነዚህ የምግብ ምድቦች በዋናነት ኃይል ሰጪ ከመሆናቸው አንጻር ያልተፈተጉትንና ያልተላጡትን መመገቡ ይመከራል። ያልተፈተጉት ማለት ሽፋናቸው ያልተወገደ፣ የድንቹንም ልጣጭ እንዳለ ሕብረተሰቡ መጠቀም ቢችል የንጥረ ነገር ይዘቶቹን ሙሉ ለሙሉ ማግኘት ይችላል ማለት ነው።
ሁለተኛው የጥራጥሬ የምግብ ምድቦች ይባላሉ። በዋናነት የገንቢ የምግብ አይነቶች ናቸው። እነዚህ ፕሮቲን የምግብ ንጥረነገር ይዘት ያላቸው ናቸው። እንደ ቦሎቄ (በቀዩም፣ በነጩም)፣ ደገራ (ማሾ)፣ ምስር፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽምብራና ሌሎችም ጥራጥሬዎች ይካተታሉ። በዋናነትም እነዚህ የምግብ ምድቦች ገንቢ ናቸው። በተለይም አብቅሎ መመገቡ በውስጣቸው የያዟቸው ንጥረ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ሰውነት እንዲጠቀምባቸው ይረዳል።
ሶስተኛው የፍራፍሬ የምግብ ምድቦች ናቸው። እነዚህ የምግብ ምድቦች ወሳኝ የሆኑ የቪታሚንና የማዕድናት እንዲሁም የአሰር የምግብ ንጥረነገሮች ይዘት ያላቸው ናቸው። በየእለቱ ከገበታችን መጥፋት የሌለባቸው የምግብ ይዘቶች ናቸው። ብርቱካን ፣ሙዝ፣ፓፓያ፣ማንጎ ወዘተ ይጠቀሳሉ።
አራተኛው የምግብ ምድብ የተለያዩ የአትክልት አይነቶች ናቸው። እንደ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ካሮት፣ ዱባ ወዘተ በዚህ ምድብ ይካተታሉ። ዱባ በየትኛውም አካባቢ በቅሎ ማደግ የሚችልና ለሰውነት በጣም ጠቃሚነት ያለው ነው። አንድ ቁራሽ(ፍንካች) መጠቀም ለሰውነት በየቀኑ(ለእለታዊ ፍላጎት የሚጠቅም) የሚጠቅም የቫይታሚን ንጥረ ነገር በመያዙ ከገበታ መገኘት ቢችል መልካም ነው።
አምስተኛው የተለያዩ የቅባት እህሎች ምድብ ነው። እንደ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ኑግ፣ የዱባ ፍሬ፣ ለውዝ፣ አኩሪ አተርና ሌሎችም የቅባት እህሎች ይካተታሉ። ቅባት እንደሚታወቀው ኃይል ሰጪ ሲሆን በተለይም ደግሞ ከካርቦሃይድሬትና ከፕሮቲን ንጥረነገሮች እጥፍ ያህል ኃይል ይሰጣሉ። እነዚህን የምግብ ምድቦች በየእለቱ ማግኘት ቢቻል ወሳኝ ጥቅም አላቸው። በተለይም በቅባት መልክ የሚሟሙ የቪታሚን አይነቶችን ሰውነት ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀምባቸው እነዚህ የቅባት እህሎች አስፈላጊ ናቸው።
በስድስተኛነት የሚጠቀሱት በእንስሳት ተዋጽኦ የሚመደቡት ናቸው። እንደ ወተት፣ እንቁላል፣ ስጋ፣ የዶሮ ስጋ፣ አሳ፣ እርጎ፣ አይብ የመሳሰሉት ይካተታሉ። እነዚህ የምግብ ምድቦች በኢትዮጵያ አጠቃቀማቸው ውስን መሆኑ ይነገራል። ለተለያዩ ልቃቅ የሆኑ (ማይክሮ ኒውትረንት) የምግብ እጥረት ሕብረተሰቡ በስፋት እንዲጋለጥ ያደርጋሉ። ስለዚህ አንድ ሕጻን ልጅ አንድ እንቁላል በቀን ማግኘት ይኖርበታል። ይህ መሆኑ የሕጻኑ አጠቃላይ አካላዊና አዕምሯዊ እድገት ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር በተለይም የስርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ከሚያስከትላቸው እንደ መቀንጨር ያሉትን ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል። ስለዚህ እንቁላልን ቀቅሎ በየእለቱ አንድ ለሕጻን መስጠቱ አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ እነዚህ የተለያዩ የምግብ ምድቦችን መመገብ የተለያዩ የተሰባጠሩና የተመጣጠኑ ምግቦችን መስጠት እንደሚችሉ አቶ ቢራራ ተናግረዋል። ስለዚህ ሕብረተሰቡ የራሱንና የቤተሰቦቹን ጤናማነት በአመጋገቡ የተነሳ መጠበቅ ይችላል። አመጋገብን ማስተካከሉ ከኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን ከየትኛውም በሽታ መጠበቅ የሚያስችሉ በመሆናቸው ሊለመዱ እንደሚገባቸው መክረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ሙሐመድ ሁሴን