የአሁኑን ድህረ ዘመናዊነት ዘመንን ከቀድሞዎቹ የሚለየው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር ስለ ቋንቋ ከሚባሉት፣ ከሚነገሩት፣ ከሚወሩትም ሆነ ከሚጠኑት ጉዳዮች ሁሉ በላይ እያነጋገረ፣ እያወያየ፣ እያመራመረ ያለው በፖለቲካው ዘርፍ የቋንቋ ሚና፤ በተለይም ከማንነት ጋር በተያያዘ የግጭቶች ሁሉ ቁንጮ የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን፤ በመስኩ ተመራማሪዎች በኩል ይህ “ፍፁም ስህተትና ያለ አውዱ የተተረጎመ” ነው፡፡ በፖለቲከኞች በኩል ግን አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ እየተሰራባቸው ይገኛል። ህይወት እየጠፋም ቢሆን፣ ደም እየፈሰሰም ቢሆን፣ ንብረት እየጋየም ቢሆን፣ ሀብት እየወደመም ቢሆን፣ ቢሆን … ቢሆን … ቢሆን … ቢሆን … በፖለቲካው ዓለም ቋንቋን ከማንነት ጋር አያይዞ የማጫረሱ ጉዳይ ላፍታም አልተቋረጠም።
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ቋንቋን ከመግባቢያ መሳሪያነቱ፤ በተለይም ከጽሑፋዊ ተግባቦት አንፃር ያለውን ሚና መነካካት ነው። በመነካካቱ ሂደትም (“አ”ንም ሆነ “ኮማ”ን አይነት) ማሳያዎችን በመጥቀስ ነው።
ችግሩ በመልእክት ማቀበልና መቀበል ሂደት መካከል እራሱ “የጽሑፍ ክሂል” የሚባል ነገር አለና ጉዳዩን እንዳያወሳስብብን ክሂሉ ከፍተኛ ችሎታ፣ እውቀትንና ጥንቃቄን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰን እንለፈው።
ይህ “መዘዝ” ስለጽሑፍ እያወራን ስለሆነ በጽሑፍ ብቻ እንዳይመስል፤ በንግግርም እንዳለ እናሳይ። ለማሳየትም ከራሳችን እንጀምር። አማርኛ መነሻው ግእዝ ነውና ይህንን ታሳቢ አድርገን ነገሩን እንመልከተው። ማሳያችንን የተለመደውን ለማድረግ “ስም”ን እንውሰድ፤ “ሠረቀ”ን።
የባለ ስሙ ትክክለኛ ስም “ሠረቀ” ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ሲጠሯቸው በሁለቱም መግባቢያ መንገዶች
(በቃልም፤ በጽሑፍም) ብዙ ጊዜ ስህተት ሲፈጥሩና የስያሜውን ትርጉም ሲያዛቡት በማጋጠሙ በተሰያሚው በኩል የማንነት ጥያቄን ያስነሳል። በቃል ሲጠራ “ሠ” (SZA) ላልቶ መነገር ሲገባው ጠብቆ መነገሩ ትርጉሙን ሙሉ ለሙሉ መቀየሩ ሲሆን፤ በጽሑፍ ደግሞ “ሰረቀ” ተብሎ እየተፃፈ ማጋጠሙ ነው (“ሰ” – SA)። ይህም ብዙ ጊዜ አወዛግቦ እንደነበር በወቅቱ ከተጻፉት ተረድተናል። ከዚህ ቃላዊ ተግባቦት ሂደት ወቅት ከሚፈጠር ክስተት ሳንወጣ አንድ ማስረጃ እንጨምር። ለዚህም የእውቁ ደራሲ አቤ ጉበኛን አባት ስም “በ”ን በማጥበቅ የተከበሩትን ሰውዬ ባንዴ “ሙሰኛ” የሚያደርጓቸው መኖራቸው ነው።
የዚህ የቋንቋ መዘዝና የፊደል/ሆሄ ጉዳይ ከተነሳ የሚስተዋሉት ስህተቶች በርካታ ናቸው። ለምን ቢሉ አንድን ቋንቋ ያሳድጋሉ፤ ያበለፅጋሉ የሚባሉት ጋዜጠኞችና ደራሲያን ሳይቀሩ የስህተቱ ቀዳሚ ጀልባ ቀዛፊዎች ሆነው መገኘታቸው ነው። ልብ ካልን ዛሬ በ”ዉ” እና “ው”፤ በ”ዩ” እና “ዪ” ወዘተ መካከል ልዩነት የጠፋ እስኪመስለን ድረስ ተሳክረው የምናገኛቸው እነዚሁ ባለሙያዎች ዘንድ ነውና ያሳስባል። በተለይ በተለይ “ከሁሉም ይልቃሉ፤ ቋንቋውን አገላብጠው ይጠቀሙበታል” በሚባሉት ገጣሚያን ዘንድ የዚህ አይነቱ ስህተት ሲታይ ይሰቀጥጣል፤ “የቋንቋ ጥናት” እያሉ የሚደክሙ ሰዎች ድካምም ያሳዝናል።
ይህን ስህተት አጉልቶ ለማሳየት ቢያስፈልግ፤ “ምሁር”ና “ምሑር”ን፤ “ሰአሊ”ና “ሠዓሊ”፣ “ቴድሮስ” እና “ቴዎድሮስ”፤ “ሚኒሊክ”፣ “ምንሊክ”፣ “ምኒልክ”፤ “ዐባይ”፣ “ዓባይ”፣ “አባይ”፤ “አብይ”፣ “ዐቢይ”፣ “አቢይ”፤ “ነብይ”ና “ነቢይ”፤ (ጥላሁን) “ገሠሠ”፣ “ገሠሰ”፣ “ገሰሠ”፣ “ገሰሰ”፤ “ክሂሎት”፣ “ክህሎት”፤ “መጻሕፍት”፣ “መጽሐፍት” ዝርዝሩ ብዙ ነው።
እዚህ ላይ የፊደልና የቁጥርን ዝምድና፣ የAstrology (Zodiacal sign), Numerology እና የመሳሰሉትን የጥናት መስኮች ለሚገነዘብ አንባቢ እነዚህ የጠቀስናቸው ስህተቶችም ሆኑ ሌሎች ምን ያህል አደገኛና ሰብአዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መዘዝን እንደሚያስከትሉ ይገነዘባል። በተለይ በስሙ ፊደላት መቀያየር ብቻ እጁ የገባውን የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ስኮላርሺፕ ያጣውን (በፎርጅድም የተጠረጠረውን) ወንድማችንን ስናስብ የመዘዙ ጉዳትና ክብደት ይሰማናል።
ወደ እንግሊዝኛውም ስንመጣ ችግሩ ያው ነው። “ሚሌኒየም”ን ስንጽፍ በትንሹ “m”፤ ሕገመንግሥትን ስንጽፍ በትንሹ “c” የምንጽፍ እንጂ በትልቁ ከሚፃፈው በምን እንደሚለይ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? የቱስ ነው ትክክሉ? (እናንተ ተደናቂውን የAyi Kwei Armah (1968)ን “The Beautyful Ones Are Not Yet Born” ስራ “…Beautiful…” ስራ አይኑን ደንቁላችሁ፤ በለመዳችሁት ብቻ ያሄሳችሁ ወዳጆቼ ሰላም ነው? ቤተሰብስ?)
የዚህ አይነቱን ከእውቀትና ከደራሲው ፍልስፍና ጋር የተጋጨ የቋንቋ አጠቃቀም እንደ ቀልድ የሚያዩ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይህ ፀሀፊ አሳምሮ ያውቃል። ይሁንና እነሱን አስቦ ስህተትን መዝለል አይፈቀድምና ዝም አይባልም። ለምን ቢባል፤ የስህተቱ መዘዝ ግዙፍ በመሆኑ። ለዚህ ምሳሌያችን በ2017 አንድ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት የአንድን ኩባንያ ስም በአንዲት ፊደል በማሳሳቱ ብቻ ዘጠኝ ሚሊዮን ፓወንድ ቅጣት መከናነቡ ነውና መዘዝ አለው ያልነው ለዚህ ነው።
ወደ ሃያሲዎቻችንም ስንመጣ ያው ነው። “ሃያሲ” ነኝ ብለውን ሂሳቸውን እየጠበቅን ከሂሳቸው ግን የምንረዳው ራሱ ስራቸው ሂስ የሚያስፈልገው መሆኑን ነው። የ”ፍትህ” ሃያሲና አምደኞች ለጉዳያችን በቂ ማስረጃዎች ናቸው። የፕሮፌሰር መስፍንን “አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ”ን አስደማሚ ስራ “ችግር አለበት” ባይ ሃያሲያኑ አንዱ
“ያንዣበበት” በሚል ርእስ ፅፎ የተቸ ሲሆን፤ ሌላውና የባሰበት ደግሞ “ያንዛበበበት” በማለት አሂሷል። አሪፍ አይደሉም? “ይህም አለ” ለማለት ያህል እንጂ የ”አ ሰው ገደለ”ንና “ኮማ”ን ጉዳይ ረስተነው አይደለም።
አንድ ሰው ባጠፋው ጥፋት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር ይባላል። ያው የማይቀረው የፍርድ ሂደትም ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ ይቆያል። በመጨረሻም ጉዳዩ “ይሙት/አይሙት”፤ “ይገደል/አይገደል” ውሳኔ ነበርና የሚጠበቀው ክቡር ዳኛ “አይገደል” በማለት ፍርድ ይሰጡና እንዲለቀቅ ይወስናሉ። ለመለቀቅ ተፈቺው መውጫ ደብዳቤ ያስፈልገው ነበርና ጸሐፊት “አ”ን ገድፋ “ይገደል”ን አፅድቃ ለፖሊስ ትሰጣለች። በተሰጠው ፍርድና በደረሰው ደብዳቤ መሰረት ተፈቺን ይለቀዋል ተብሎ የሚጠበቀው ፖሊስ እስረኛውን ከታሰረበት አውጥቶ ወደ “መግደያ ወረዳ” በመውሰድ በጥይት ደብድቦ ገደለው ይባላል፤ እነሆ “አ ሰው ገደለ”ም ለዚህ በቃ። ይህ ብቻም አይደለም፤ ከዛ በፊትም በሌላ ያገራችን አካባቢ “አይሙት” የተበየነለት ፍርደኛ በጸሐፊት አመካኝነት “አ” ተገድፋ “ይሙት” ተጽፎ በመውጣቱ ምክንያት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የደረሰው ሰው መኖሩ ይነገራል። ወደ “ኮማ”፤ አብዝተው ከሚጠቀሱና ከሚታወቁት አንዱ “a coma killed a person.” እንሂድ።
“A coma killed a person.” የአሁን ዘመን፤ ወይም የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም። በ18ኛው ክ/ዘ የተከሰተና ከዛን ጊዜ ጀምሮ እንደ አንድ ማስተማሪያ አባባል ተቆጥሮና እውቅናን አግኝቶ እዚህ የደረሰ ዘመን ተሻጋሪ አባባል ነው። “kill him not, let him go.” የሚለውን የዳኛ ውሳኔ ጸሐፊት ስለ “ኮማ” ያላት እውቀት “የላቀ” በመሆኑ “kill him, not let him go.” አደረገችው። ያው ከላይ “አ ሰው ገደለ” እንዳልነው አይነት አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ። አላማችን ይህ እንዳይደገም ነውና ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ግርማ መንግሥቴ