ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። ይህ ለውጥ ደግሞ በመላ ኢትዮጵያውያን፤ በተለይም በወጣቶች እና በለውጥ አመራሩ የጋራ ትግል የተገኘ ነው። ለውጡ ደግሞ ለብዙዎች የወደፊት ብሩህ ተስፋን ያጫረ ፤ በተለይ ለዴሞክራሲ ለታገሉና ለአገራችን መፃኢ እድል ተስፋን ለሰነቁ ዜጎች ተስፋ ብቻ ሳይሆን ለሥራ ያነሳሳ ጭምር ነው ። በተጻራሪው ለውጡ ጥቅማቸውን ያሳጣቸው ኃይሎች ደግሞ ገና ከጅምሩ ለውጡን ለማደናቀፍ ተግዳሮት ሆነው ተሰልፈዋል። ለውጡን ለማደናቀፍም ሌት ቀን እየሰሩ ይገኛሉ ።
የመጀመሪያው ለውጡን የማደናቀፍ ሙከራ መሰረት ያደረገው ዜጎችን ማፈናቀልና ህብረተሰቡን እርስ በርሱ በማጋጨት በአገሪቱ አለመረጋጋትን መፍጠር ነበር ። በዚህም በሀገሪቱ ታሪክ ባልታየ መልኩ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። ሀገርም ብዙ ዋጋ እንድትከፍል ሆናለች ።ያም ሆኖ ግን ይህ አካሄድ ብዙ አላራመዳቸውም ። ዜጎች ይህንን ሴራ በመረዳታቸው የታሰበው እና የታቀደው ሳይሆን ቀረ ።
ይህ አካሄድ አለመሳካቱን የተረዱት እነዚህ ኃይሎች ሀገር የማተራመስ ስልታቸውን በመቀየር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በመግደል ለውጡን ማጨናገፍ ሁለተኛው አማራጫቸው አደረጉት። ይህ ድርጊት አሳዛኝ ቢሆንም አለመሳካቱ ግን የነዚህ ሰዎች እጅ ረጅም መሆኑን ያሳየ ነበር ። ይህም ቢሆን ድርጊታቸውን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳው የተሻለ እድል መፍጠር የቻለ ነበር ። የድፍረታቸው ጉዳይ ግን ለብዙዎች መነጋገሪ ከመሆኑ ባለፈ የቱን ያህል በለውጡና በለውጡ አስተሳሰቦች ላይ ጥርስ የነከሱ ስለመሆናቸው ተጨባጭ ማስረጃ ሆኗል ።
በመቀጠልም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም እና ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙት ግድያ በአገሪቱ ውስጥ ትልቅ ቀውስ በመፍጠር አገሪቱን የማፍረስ ሴራ ነበር። በቅርቡ ሰኔ 22 የተፈጸመው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን የመግደል ተግባር ደግሞ ለውጡን በማይቀበሉ የውስጥ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች ጭምር የተደገፈና አጠቃላይ አገሪቱን የማፈራረስ ትልቅ ሴራ የተቀነባበረበት ነበር። ድርጊቱ ከ250 በላይ ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍና በቢሊዮን የሚገመት ሃብትና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። የዚህ ድርጊት (የጥፋቱ አቀናባሪዎች) ሴራ እንዳለ ሆኖ በነዚህ ኃይሎች ተንኮልና ሴራ ተጠልፎ ለጥፋት የተሰለፈው ወጣት ጉዳይ ግን ቆም ብሎ ሊታሰቡባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ስለመኖራቸው ያመላከተ ነው ።
በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ መንግሥትን መቃወም ያለና የተለመደ የፖለቲካ መብት ነው። ተቃውሞዎች ትላንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ወደፊትም ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ሁከት በተነሳ ቁጥር ተነስቶ ህይወት ለማጥፋትና ሃብት ለማውደም መንቀሳቀስ ለሴረኞች መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ አንዳችም የሚፈይደው ነገር አይኖረውም። ይልቁንም ከድርጊቱ በኋላ ለህሊና ጸፀት ከመዳረግ ፤ ከዚያም አልፎ ድህነትን ከማባባስ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የአረብ አገራት በተነሱ ቀውሶች የፈረሱ አገራት ዜጎች የደረሰባቸውን አስከፊ ማህበራዊ ቀውስ መመልከቱ ለዚህ ትልቅ ትምህርት ነው። በነዚህ አገራት የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት መንስኤው መንግሥትን ከመቃወም የመነጨ ቢሆንም የተቃውሞ መንገዱ ግን መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚደረግ እና ከበስተጀርባው የሌሎች ድብቅ አካላት ጣልቃ ገብነት ያለበት የቀለም አብዮት እንደሆነ ምሁራን ሲተነትኑ ይደመጣል።
መንግሥትም ለተነሳው የህዝብ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ የሰለጠነ አለመሆኑ ደግሞ አገራቱን ለቀውስ ዳርጓል። በሁሉም አካላት የተሄደበት መንገድ ግጭቱ የሚያስከትለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ባለማስገባት የተፈጠረ በመሆኑ ውጤቱ እንደታየው አስከፊና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በዘግናኝነታቸው ከተመዘገቡ ጦርነቶች ሁሉ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል።
በነዚህ አገራት የተፈጠረው ቀውስ በህይወትና በንብረት ላይ ካስከተለው ጉዳትም ባሻገር የፈጠረው ስነልቦናዊ ቀውስ ዘግናኝና በሰው ልጅ ላይ እንዲፈጠር የማይመኙት ነው። በፈራረሰ ከተማ ውስጥ ከላይ የሚወርድባቸውን የጥይት ናዳ ተሸሽገው በጉድጓድ ውስጥ ጠብታ ውሃ እየናፈቃቸው የሚያለቅሱ ህጻናትን በቴሌቪዥን መስኮት መመልከት የጦርነትን አስከፊነት ሳንወድ በግድ እንድንረዳና ጦርነትን እንድናወግዝ ያደርገናል። ከዚህ አይነት አስከፊ የእርስ በርስ ግጭትም ትምህርት ወስደን “ሰላም” ለሚለው ሰላማዊ ሃሳብ የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናበረክት ያስገድደናል።
ሰላም እንደቃሉ አጭር ሳይሆን ዘመናትን የሚሻገር፣ የሰው ልጅ ከሚያስበው በላይ አስፈላጊ የሆነ ስጦታ መሆኑንም እንገነዘባለን።ሰላም ከሌለ እናት ልጇን ማዳን ቀርቶ አልቅሳ ለመቅበር እንኳን እድል እንደማታገኝ ስንገነዘብ ቆም ብለን እንድናስብ እንገደዳለን።
አሁን አሁን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እያየን ያለነው የፀጥታ ችግር ወዴት ይወስደን ይሆን ብለን ማሰባችን አይቀርም። በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን በሚሰሩ የውስጥ ኃይሎችና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ በሚጥሩ የውጭ ጠላቶች አማካኝነት በሚፈጠሩ ሴራዎች አብዛኛው ጊዜ ወጣቱ በቀላሉ ሲነዳና የጥፋቱ አካል ሲሆን ይስተዋላል።
ይህ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ምንም እንኳን ጊዜያዊ ችግር ቢሆንም ብልህ የሆነ አመራርና የህዝባችንን የኖረ ባህላዊ እሴት በአግባቡ መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። የሰላም እጦት በተንኮል ኃይሎች የሚፈጠሩ ሴራዎችን እየተከተሉ ነገ ራሳችን፣ ቤተሰባችንና የኛው ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸው ንብረቶች ማውደም አገርን ከመግደል የሚተናነስ አይደለም። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለጠላቶቻችን መሳሪያ በመሆን ራሳችንን በራሳችን ለማጥፋት የምንሄድበት መንገድ ቆም ብለን ልናስብበት የሚገባ ትልቁ የቤት ሥራችን ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው ጠላቶቻችንን መክተን በመመለስ እንጂ ለጠላት መሳሪያ በመሆን አይደለም። የውስጥ ጥያቄዎች እንኳ ቢኖሩ በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ እንጂ ንብረት በማውደም እና የራስ ወንድምና እህትን በመግደል አይደለም። እኛ የምንታወቀው የራሳችንን ሰላም ብቻ ሳይሆን የጎረቤት አገራትን ሰላም በማስጠበቅ ጭምር ነው። እናም የራሷ አርሮባት የሰው ታማስላለች እንዳይሆንብን ስለራሳችን ሰላም አጥብቀን እንጨነቅ።
ሰላም የሚጀምረው ከቤት ነው። በቅድሚያ ለቤተሰቡ ፍቅር የማያሳይ ሰው ከፍ ብሎ ለማህበረሰቡ ወይም ለአገሩ ፍቅር ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ ቤተሰባችንን ማሰብ ተገቢ ነው። ይህም ሲባል በቅርቡ ከወላጆቻችን፤ ከልጆቻችን ወይም በቅርባችን ያሉንን ጓደኞቻችንን በማሰብ እነዚህን የቅርብ ሰዎች ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ከመፈለግ ይጀምራል። የሚወደው ወይም የሚንከባከበው የቤተሰብ አካል ያለው ዜጋ ለሰላም ቦታ ይሰጣል። የሌሎች ሰላምም እንዳይደፈርስ የራሱን ድርሻ ይወጣል። ስለዚህ ቤተሰብ በልጆቹ ውስጥ ፍቅርን መዝራት ይጠበቅበታል። ከዚያም አልፎ ስለአገሩና ስለቀጣዩ ትውልድ ማስተማርና መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ እንዲፈጠር ማድረግ ይኖርበታል።
ከሁሉ በላይ ግን ህብረተሰቡ በተለይ ከውጭ ሆነው እዚህ የእሳት ነበልባል የሚረጩ ሚዲያዎችን ሴራ ሊገነዘብ ይገባል። አገራችን አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ መፍታት የሚችለው እዚሁ ያለው አካል እንጂ ከባህር ማዶ ሆኖ እዚህ እሳት የሚጭረው አካል አይደለም። እንዲህ አይነት ሰዎች ዓላማቸው እሳት መለኮስና ከዳር ቆሞ ማየት ነው። ስለዚህ የነዚህን አካላት ሴራ በአግባቡ መረዳት ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። ካልሆነም እንዲህ ብለን እንምከራቸው፤”ኑ አብረን የጋራ መፍትሄ እናፈላልግ”። ይህ ካልሆነ ግን እንደፈሪ ዱላ ከርቀት ሲመች እየገረፉ ሳይመች ደግሞ እየሸሹ ማጥቃት የፈሪ ዱላ ነውና ተው ማለት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ውቤ ከልደታ