ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ታላላቅ የሚባሉና አንቱታን ያተረፉ በርካታ ሰዎችን ተቀብላ ሸኝታለች። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ እንደነ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሊቆች ይገኙበታል። ለዛሬ ማውሳት የፈለግኩት የደራሲውን የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን አይደለም። ነገር ግን ፀሐፊው ካበረከቷቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ፤ ላለንበት ዘመን አስፈላጊ ነው ብዬ ያመንኩትን፤ ያመንኩትን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ ትውልድም ሊማርበት ይገባል ብዬ ከራሴ ጋር የተስማማሁበትን «ፋኖስና ብርጭቆ» የተሰኘውን የግጥም ሥራቸውን ነው።
ይህንን ግጥም ያነበብኩት በልጅነቴ ቢሆንም፤ ጥቂት ማሻሻያና ግጥሙ ጎልቶ እንዲወጣ ካለኝ ምኞት የተነሳ፤ የተወሰኑ ስንኞችን ከመጨመር ውጪ፤ ግጥሙ ከነሙሉ ወዙ በውስጤ ተተክሎ ይገኛል። ይህ እንግዲህ የሚያሳየው፤ የደራሲው ከበደ ሚካኤል በወቅቱ ያልሙት የነበረውን ትውልድን የመቅረጽ ምኞትና ርዕይ ነው።
በዚህ የግጥም ሥራ ውስጥ ፀሐፊው ሦስት ግዑዛን ገጸ ባህርያትን ተጠቅመዋል። ፋኖስ፣ ብርጭቆና ነፋስ። በመልእክታቸውም የመደመርን ቀመር /በኅብረት ውስጥ ያለውን አዎንታዊ ተጽእኖ/ በተቃራኒው ደግሞ ማን አለብኝነት የሚፈጥረውን የእኔነት ስሜትና አፍራሽ የሆነ ጎኑን በማመላከት፤ ኅብረት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተውበታል። በእርግጥ ገጣሚውን አመላክተውበታል የሚለውን ቃል ብቻ በመጠቀም ልንገልጻቸው ባንችልም፤ የደራሲውን ሥራዎች እንደገና በማጥናት የሚቀጥለውን ትውልድ እንደገና ማሳወቅና ማስተማር እንደሚገባ መንገድ የሚያሳይ ነው።
በዚህ የ«ፋኖስ እና ብርጭቆ» የግጥም ሥራ የምንመለከተው የፋኖሱን የዜሮ ብዜት ውጤት ነው። በዓለም ላይ የየዋሁን ፋኖስ ቀመር የተከተሉ ብዙዎች ምኞታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። እንደውም ከዚህ ይልቅ በትልቅ ኪሳራና ውድቀት ውስጥ ሲዘፈቁ ማየት የተለመደ ነው። ምንም እንኳን ዘግይቶ እንደነቃው ብልህ ፋኖስ፤ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም፤ ከብዙ ጥፋት በኋላ በመሆኑ በርካቶች ብዙ ዋጋ ሲከፍሉ ይስተዋላል። እናም የአገራችን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይህንን እውነት በመቀበል፤ ብርሃናቸው ደምቆ ይታይ ዘንድ «በአንድነት ለአንዲት አገር» እድገት እንዲተጉ ደራሲው መልዕክታቸው ነው። ስጋ ቢፈርስ አጽም ይናገራል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ተስፋዬ በለጠ