ጥቂት የማይባሉ በአፍሪካ የሚገኙ ሰባኪያን በሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን የተንደላቀቀ ህይወትን በመምራት ላይ ናቸው፡፡ አንድ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ እንደውም ሃይለኛ የዋጋ ተደራዳሪዎች ናቸው ተብሎ ይነገርላቸዋል፡፡ የግል ጀቶችን እስከመግዛትም ደርሰዋል፡፡ ናይጄሪያውያን ሰባኪዎች በዚህ ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡
አብዛኞቹ ባልተገባ መንገድ ከተከታዮቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በመሰብሰብ ነው ሀብት የሚያፈሩት እየተባሉ ይታማሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ አፍሪካዊ ሰባኪ “የመንግስተ ሰማያት መግቢያ ነው” የሚለውን ነጠላ ቲኬት እስከ ሃያ ሺ የአሜሪካን ዶላር ሲሸጥ ቆይቶ በቅርቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ ተከታዮቹ እኛ ወደንና ፈቅደን ገንዘባችንን በሰጠነው መንፈሳዊ አባታችን ምን በወጣው ይታሰራል ሲሉ የተቃውሞ ሰልፍ መውጣታቸው ነው፡፡
በቅርቡ በአዲስ አባባ ዳርቻ ከተገነቡ የኮንደሚንየም መንደሮች በአንዱ የሚገኝ የሃይማኖት ተቋም ሲነገር የሰማሁትን ላካፍላችሁ፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቤተ እምነቱ የሚወስደውን መንገድ እንዲያሰሩ የሚቀሰቅስ ስብከት ነው እየተደረገ ያለው፡፡ ሰባኪው ይናገራሉ “ይህ መንገድ ከተሰራ የእምነታችን ተከታዮች ወደዚህ ይጎርፋሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የቤተ እምነታችን ገቢ ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ ሰባኪዎች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙና ህይወታቸው እንዲሻሻል ያደርጋል፡፡ ወገኖቼ እውነቴን ነው የምላችሁ ኑሮ እጅግ ተወዷል በአሁኑ ወቅት ሰባኪያን የሚኖሩት ኑሮ ኑሮ እንዳይመስላችሁ” እንግዲህ ሰባኪዎች ለስለድህነት መጨነቃቸውን እርግፍ አድርገው ስለ ድህነት (ማጣት) መጨነቅ መጀመራቸውን ተመልከቱ፡፡
በፈረንጆቹ የ2018 ዓ.ም ፎርብስ መጽሔት ባወጣው የሰባኪ ሀብታሞች ዝርዝር ከዓለም በሀብታቸው ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ ከያዙ ሰባኪዎች ውስጥ አራቱ አፍሪካውያን ናቸው። አንደኛ፣ ሶስተኛ፣ አምስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል። አንደኛው 150_ሚሊዮን ዶላር ሲኖረው፣ ሶስተኛው 59 ሚሊዮን፣ አምስተኛው 39 ሚሊዮን እና ሰባተኛው 10 ሚሊዮን ዶላር ሀብት አላቸው።
ፎርብስ ዘለለው እንጂ፣ የማላዊው ተወላጅና ሰባኪ ቡሹሪ፣ 150 ሚሊዮን ዶላር ሀብት እንዳለው በሌላ ዘገባ ላይ ተጽፏል። እሱምን ካከልን በዓለም ላይ ካሉ አስር ሀብታም ሰባኪያን አምስቱ የሚገኙት በርካታ ነዋሪዎቿ በድህነት ውስጥ በሚገኙት አፍሪካ ይሆናል ማለት ነው። እንደ አፍሪካ ባለ ድሃ አህጉር ሰባኪ መሆን ይህን ይህል የናጠጡ ሀብታም ማድረጉ እጀግ በጣም አስገራሚ ነው።
አፍሪካውያን ሰባኪዎች አነጋጋሪ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸምም ይታወቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተከታዮቻቸው ወደ ቤተ እምነቶቻቸው ሲመጡ አንድ አሊያም ሁለት ቢራ ይዘው እንዲመጡ ያዛሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተከታዮቻቸው የሆኑ ሴቶችን ከንፈር ምጥጥ አድርገው በመሳም የፈውስ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከቅንጡ መኪናዎቻቸው ሲወርዱ እግራቸው መሬት እንዳይነካ ተከታዮቻቸው መሬት ላይ ተነጥፈውላቸው በእነርሱ ላይ እየተረማመዱ የሚያልፉ ሰባኪያንም አልታጡም፡፡ በእጃቸው የያዙት ሃይማኖታዊ መጽሐፍ ከሚያስተምረው በተጻራሪ ደጋግመው በማግባት የበርካታ ሚስቶች ባለቤት የሆኑ ሰባኪያንም አሉ፡፡ ተከታዮች ፊት እባብ ታቅፎ ረጅም ስብከት የሚሰብክ ሰባኪም በአፍሪካ ምድር ታይቷል፡፡
ከአንዳድዶቹ ደግሞ አጅግ በጣም አስቂኝ ሃሳቦችን ልታደምጡ ትችላለችሁ፡፡ ለምሳሌ አንድ አፍሪካዊ ሰባኪ በአንድ ወቅት በሞባይል ስልኩ በቀጥታ ከመንግስተ ሰማየት እንደተደወለለት ለተከታዮቹ በኩራት አብስሯል፡፡ ከዚያን እለት አንስቶም ባሻው ጊዜ ወደ መንግስተ ሰማያት እየደወለ ከፈጣሪ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ይናገራል፤ ተከታዮችም በፍጹም ልባቸው ያምኑታል፡፡
በሀገራችንም እጅን በአፍ የሚያስጭኑ “መንፈሳዊ መልዕክት አድራሾች ነን” የሚሉ ሰዎችን በስፋት መመልከት ጀምረናል፡፡ ” እዛ አጥሩ ጥግ ያለሽው ወየውልሽ ዛሬ ነጭ ለብሰሻል ነገ ጥቁር ትለብሻለሽ” እያሉ ተከታዮቻቸውን የሚያሸብሩ ሰበኪያን ብቅ እያሉ ነው፡፡ በየመንገዱም ራሳቸውን በተለየ አለባበስና ገጽታ በማቅረብ ያገኙትን ሰው እንዲህ ካላደረግህ መአት ይወርድብሃል የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ ከፈጣሪ እንደተላከች የምትናገር አንዲት ሴትም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የታዋቂ ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ስትገጽስ፣ ስታስጠነቅቅና ስትወርፍ ተሰምቷል፡፡
በሀገራችን አንድ ሰባኪ “ወ/ሮ አዜብ መስፍን የመለስ መቃብር እንዲቆፈር ከፈቀደች ካለምንም ክፍያ መለስ ዜናዊን ከሞት አስነሳዋለሁ፤ በርግጠኝነትም ከመቃብሩ ተነስቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር “ይደመራል” ማለቱን ተከትሎ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ብዙ ተብሏል፡፡ በንግግሩ የተበሳጨ “አንድ አስተያየት ሰጪ እንኳን መለስን ሊያስነሳ ራሱ በአላርም ነው የሚነሳው” ማለቱ ትዝ ይለኛል፡፡
በወለጋ ቄለም ወረዳም ከሞተ አራት ቀን የሆነውን ሰው አስነሳለው ብሎ መቃብሩን እስከማስቆፈር የደረሰ ሰባኪ ተመልከተናል፡፡ ነገር ግን ያሰበው አልተሳካለትም፡፡ ጉድጓድ ውስጥ ግብቶ ሳጥኑን በመክፈት በስሙ እየጠራው ብዙ ቢጮህም መልስ አላገኘም፡፡ በኋላም በፖሊሶች ቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል፡፡
ቀደም ብሎም እንዲሁ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይጠለፋል ብሎ አንድ ሰባኪ ትንቢት ተናገረ፡፡ ነገር ግን በተባለው ዓመት የተባለው ሳይሆን ቀረ ፤ የአየር መንገዱ አውሮፕላን አልተጠለፈም፡፡ ሰባኪው ግን ዝም አላለም ትንቢቴን አራዝሜዋለሁ ሲል ተደመጠ፡፡
አውሮፕላን ይጠለፋል ብለው ትንቢት የሚነግሩን ሰባኪዎችና የሃይማኖት ተቋማት ራሳቸው በፖለቲከኞች ተጠልፈው ሰማያዊ ተልዕኳቸውን ወደጎን ብለው ምድራዊ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሆነው ነበር፡፡ በእኔ እይታ በዶክተር አብይ ዘመን ነጻ ከወጡ እስረኞች መካከል የሀገራችን የሃይማኖት ተቋማት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በሀገራችን የሚገኙ የተለያዩ የእምነት ተቋማት ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት በሚያከብሩበት ዕለት የሚያደርጉት ንግግር ግርም ይለኛል፡፡ እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሳችሁ ካሉ በኋላ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንዲሳካ እያንዳንዱ ምዕመን ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ሰማያዊውን መንግስት ትተው ምድራዊውን መንግስት ያገለግላሉ፡፡ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች ምን ሰርተው ይብሉ? ድርጊቱ መደጋገሙን ሳይ አንዳንድ ጊዜ ለረጅም ዘመናት አንድ ለናቱ ሆኖ የከረመው የቴሌቪዥን ጣቢያ መልዕክታቸውን እየቆራረጠ ይሆን እንዴ ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
በቀጥታ ሃይማኖታዊ ስብከት ማድረግ በራሱ መንግስትን ማገዝ ነው፡፡ እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም ተከታዮቹ ላይ የቤት ስራውን በሚገባ ቢሰራ ዜጎች ፈጣሪያቸውን የሚፈሩና ግብረገብ ያላቸው ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ዜጎች ደግሞ ለልማት እንጂ ለጥፋት የሚሰማሩ አይሆኑም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት ተቋማት ከተከታዮቻቸው የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እየተቀበሉ ክትትል በማድረግ ከመሰረታዊ አስተምሯቸው ውጭ የሚንቀሳቀሱ ሰባኪያን ላይ እገዳ ሲጥሉ እየተመለከትን ነው፡፡ በሀገራችን የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትክክለኛ ሚናቸውን እየተጫወቱ ያሉት አሁን ይመስለኛል፡፡ በአማራና ትግራይ ክልል መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን የሰሩት ስራ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀው እንዲህ ያለ ተግባር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
የትናየት ፈሩ