በሀገረ አሜሪካን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ሩሲያ በሌሎችም የዓለም ሀገራት የሀገራቸውንና ብሔራዊ ጥቅምን አስከብረው ተፈርተው የኖሩ መሪዎች ሁሉ አምባገነኖች ቢሆኑም በሀገራቸው ሰላም በሕዝባቸው ደህንነት ላይ የማይደራደሩ፡፡ በብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ እሰጥ አገባ የማይገቡ ነበሩ፡፡ ሕግና ሥርዓትን የሚያፈርሱትን እያፈረሱ ሀገርን የሚያስከብሩ ኮስተር ኮምጨጭያ ሉ መሪዎች ነበሩ፡፡ ሀገር ቀውስ ውስጥ ስትገባ ሕግና ሥርዓት ሲጣስ ሁሉም ነገር ከሕግና ከሥርዓት ውጪ ወደ መሆን ሲያመራ ሀገርን የማዳን ብቸኛው መንገድ ኮስተርና ቆፍጠን ብሎ ህግን ማስከበር ብቻ ነው፡፡ በአምባው ላይ መግነን፡፡ ሀገሬ ቆሜ ክፉሽን ውድቀትሽን አልይ ማለት ይሄኔ ነው፡፡
ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መግነን፡፡ የሀገርና የሕዝብን ሰላም ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሥርዓተ አልበኞች ላይ አምባገነን መሆን፡፡ ግድያን ዘረፋን ልቅነትን የመንደርና የሰፈር አዋኪውን አደብ ለማስገዛት ኮስተርና ቆፍጠን ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ዴሞክራሲ ሊከበርና ሊታወቅ አይችልም፡፡ የመንግስትን ትእግስትና ሆደ ሰፊነት ከአቅም ማጣትና ለመሪነት ብቁ ካለመሆን ጋር የሚያያዙት ጸረ ሰላም ኃይሎችን፤ አዋኪና አሸባሪ ቡድኖችን አደብ ለማስያዝ ብቸኛው መንገድ ለሰላም ሲባል ኮስተርና ቆፍጠን ማለት ነው፡፡ የሚገባን ቋንቋ እሱው ብቻ ከሆነ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡
የሀገር ግድግዳው ጣሪያና ማገሩ ጥንትም ተከብሮ የኖረው ዛሬም ወደፊትም ጸንቶ የሚዘልቀው ልቅነትን በመፍቀድ አይደለም፡፡ ሕግና ሥርዓትን በሕጋዊ መንገድ እንደ ብረት ጸንቶ በማስከበር ብቻ እንጂ፡፡ ነጻነት ሲገኝ በቅጡ መያዝ ካልተቻለ ነጻነት የሀገርን ሰላም የሚያደፈርስና የሚያጠፋ ከሆነ ለሕዝብና ለሀገር ሰላም ሲባል የግድ ስራ ላይ የሚውለው ኮስተርና ቆፍጠን ማለቱ ብቻ ነው፡፡ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡ አለም እኮ እንዲሁ ነች፡፡
ነጻነትና ዴሞክራሲን በቅጡና በአግባቡ ለመያዝ ካልተቻለ ነጻነት ማለትም ልቅነትና ሥርዓተ አልበኝት ፣ ሰው መግደል፣ቤት መዝረፍ፣ ዜጎችን ማፈናቀል ከሆነ መቼስ ምን ይደረጋል ህግና ሥርዓትን ለማስከበር ብቸኛው መንገድ ኮስተርና ቆፍጠን ማለቱ ነው፡፡
በሁሉም መስከ ያለው እሹሩሩ ማብቂያው ጫፍ ላይ ደርሷልና ያብቃ፡፡ እንኮኮውም አንቀልባውም አልችል ብሎ ሰልስሎ ሊበጠስ ተቃርቧልና ማዘሉ ይብቃ! ከዚ በኋላ ቢጮሁ እሪታው ቢቀልጥ ፋይዳ የለውም፡፡ ያገኘነውን መልካም እድልና አጋጣሚ በሥርዓት መጠቀም ስላልቻልን ሀገርን ለማዳን ብቸኛው አማራጭ ሳይወደድ በግድ የሚገባበት ምርጫ ያለማወላውል ህግን ማስከበር ብቻ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ኃያልና ገናና ሁና ታፍራና ተከብራ ትኖር ዘንድ ሊያፈርሱዋት የሚሹትን ሁሉ በኃያል ክንድዋ ማድቀቅም ማሽመድመድም እንደ ጥንቱ ሁሉ ዛሬም ትችልበታለች፡፡ ጉንጭ አልፋ ማባበል ከመገመት ውጪ መላ አያበጅም፡፡ ሰላምና መረጋጋት አያመጣም፡፡ የኃይል ሚዛን መኖር ነው ዓለምን አከባብሮ የዘለቀው፡፡ መንግስት ሀገራዊውን ሁኔታ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመቀየር በታሪክ ያልታየ ሰፊ ትእግስት አሳይቷል፡፡ ለሰላም ሲል ረዥም ርቀት ሄዷል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ውስጥ ያልተለመደና እንግዳ ነው፡፡ ለዚህ ዘመኑን ለባጀ ዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ አካሄድም ኮፍያችንን ከፍ አድርገን እጅ እንነሳለን፡፡
የሀገርን ሰላምና መረጋጋት ለሚያናጉት አውቆ አበዶች ወታደራዊ እርምጃ እንድንወስድ አታስገድዱን፤ ትእግስታችን አልቋል አይደለም የሚባለው፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላምና ለሕዝቧ ስንል ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ጀምረናል የሚለው አዋጅ ነው መሰማት ያለበት፡፡ ዴሞክራሲ መብትህን በአግባቡ ተጠቀም ሲባል አውሬነትን ምርጫው ላደረገ ብሎም ሀገሪቱን የሥርዓተ አልበኞች መናሃሪያ ለማድረግ ለሚንቀሳቀስ መድሃኒቱ ኮስተርና ቆፍጠን ማለት ነው፡፡ ይልሀል የሀገሬ ሰው “አርፎ ተቀምጦ የተኛውን በሬ – ቆስቁሰው ቆስቁሰው አደረጉት አውሬ” ማለት ነው፡፡
መልካምና ደግ ነገሮች ሁሉ የማይጥሙን፣ ሰላም ሲባል ጦርነት የሚናፍቀን፣ በአጉል ከንቱነትና ጀብደኝነት ስሜት ውስጥ የምንዋጥ ነን፡፡ ከእኛ በላይ ለሀገር አሳቢ ተቆርቋሪ የለም የምንል ትናንትን እያወገዝን ዛሬም ተመሳሳይ ታሪክ የምንደግም፤ ይህች ሀገር የተዋቀረችበትን የአባቶችና የእናቶች የታላቅነትና የጀግንነት ታሪክና መስዋእትነት የረሳን ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን የምናገዝፍ፤በጥላቻ ባሕር ውስጥ ሰምጠን ነፍሳችን የምትቃትት ሆነናል፡፡
ለሀገር ተቆርቋሪ መስሎ ሀገርን ማቁሰል ማድማት የህዝቡን ሰላምና ልጆቹን መግደል የጀግንነት መለያ ተደርጎ እየተወሰደ እንደምን ሀገር ይቀናል? እንደምንስ ከድህነት ይወጣል? መደማመጥ ጠፍቶ ሁሉም በየጎራው አካኪ ዘራፍ የሚልበት የእብደት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ ሕግና ሥርዓትን እያንዳንዱ በሥርዓቱ አውቆ ሊጠብቀው ካልቻለ ለልቅነት ለሥርዓተ አልበኝነት ካጨበጨበ፤ ሌብነት ዝርፊያ፤ ንጥቂያ፤ ሴቶችና ሕጻናት መድፈር፣ቤት መስበር፣ መኪናና ንብረት በአደባባይ መስረቅን፣ማጅራት መቺነትን ሁሉም የሚያበረታታ ከሆነ በእርግጥም መንግስት ቢኖርም የለም፡፡ ሕግና ሥርዓት የለም ማለት ነው፡፡ ውሃ ሲወስድ- አሳስቆ አሳስቆ…እንዲሉ ሌሎች ሀገራትም ሲጠፉ አጀማመራቸው የእኛኑ አይነት ሆኖ የፖለቲካ እብደትና ስካር ሰፍኖ ነበር፡፡ በሂደት ወደ ጦርነት ውስጥ ተገባ፤ ሀገራቸውን አፈራርሰው እነሱም ፈረሱ፡፡ ዴሞክራሲን አውቀን ለመጠቀም እጅግ ብዙ ርቀት ይቀረናል፡፡ ብዙ መለወጥን ይጠይቃል፡፡
ተሰንገን ስንያዝ እሪታና ኡኡታ ለቅሶና ማማረር የመብዛቱን ያህል፤ ትንሽ ነጻነት ስናገኝ ደግም የትናንቱ እየናፈቀን ጋጠ ወጦችና ሥርዓተ አልበኞች ዘራፊና ቀማኛዎች የተደራጀ የማጅራት መቺ ቡድን አደራጅተን ሀገርና ሕዝብ እናምሳለን፡፡ ሰላም እንነሳለን፡፡ ዛሬ ምን ያህል ለዘረፋ፤ ለነፍሰ ገዳይነት የተዘጋጀ ቡድን በየከተማው ተደራጅቶ ስምሪት እንደሚጠብቅ ለመናገር ነቢይ መሆን አይጠይቅም፡፡ ምልክቶቹ በገሀድ እየታዩ ስለሆነ፡፡ ስለዚህም ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ የሚበጀው ብቸኛው አማራጭ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የመፍቻው ቁልፉ ኮስተርና ቆፍጠን ማለት ብቻ ነው፡፡
ለሁሉም የሚበጀው በሰላምና በዴሞክራሲ ማመን በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ ተቻችሎ መኖር ነበር፡፡ እሹሩሩ ማሞ እሹሩሩ ቢባሉም የልጅ ነገር በጄ አላሉም፡፡ ኦነግን ከመገፋት አውጥቶ በሀገሩ ምድር በሰላማዊ መንገድ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ ያስቻለው የህዝብ ትግልና በኢሕአዴግ ውስጥ የመጣው ለውጥ ነው፡፡ ሌሎቹንም ያንቀላፉትንም በምትሀት አስነስቶ ነፍስ ኡፍ ብሎ የዘራባቸው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ቅንነቱ ኑ አብረን እንስራ ማለቱ ባልከፋ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ጭራሹን በሰላም በሚኖረው ሕዝብ ላይ ከአስመራና ከአውሮፓ የመጡ ቅምጥሎች ደም ናፋቂና ባሩድ አሽታች ሆነውት አረፉ፡፡
በነጻነትና በዴሞክራሲ አንኖርም ሀገርን ሰላም ነስተን ነው መኖር ያለብን ላሉትም መድሃኒታቸው የህግ የበላይነትን ማስከበሩ ላይ ጠንከር ብሎ መስራት ነው፡፡ ሀገርን ከአደጋ ለማዳን፤የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ፤ ከትርምስና ከቀውስ ማእከልነት ለማውጣት ሲባል የህግ የበላይነት ለዘለአለም ይኑር፡፡ ይሄው ነው ሊባል የሚችለው፡፡ ሌላ ምን ይባላል፡፡
ኢትዮጵያ በሴረኞች ሴራ ዱለታና ሽረባ አትፈርሰም፡፡ አትጠፋም፡፡ ይልቁንም ጠላቶቿ ሁሉ ተጠራርገው ይጠፋሉ፡፡ ሕግና ሥርዓት የለም ማለት መንግስት የለም ሀገር የለም ማለት ነው፡፡ እኛ ዴሞክራሲ ከቃላት ውጪ በተግባር በማይታወቅበት ባልተዘራበት ዴሞክራሲን ስለተመኘነው ብቻ ማምጣት አይቻልም፡፡ ሊሰፍንም አይችልም፡፡ ዴሞክራሲን በመጽሀፍት እንጂ በተግባር የማናውቀውን የግድ እወቁ ብሎ ማስጨነቅ ያልነበረውን አምጡ ውለዱ የማለት ያህል ነው፡፡ ዴሞክራሲ በዘመን ፍሰት ውስጥ ከእውቀት ማደግና መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንጂ በጡሩንባ ስለተለፈፈ በቴሌቪዥንና በሬድዮ ስለተለፈፈ አይመጣም፡፡ ኧረ ወዴት ወዴት አሉ ሰውየው፡፡ እኛም ሀገራችንም የምንገርም ሆነናል፡፡
ጥፋት ማድረስ፣ የሰውን ልጅ መብት መድፈቅ፣ መሳደብ፣ ልዩነትን አልቀበልም እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብሎ ማመን፣ባሕላችን አድርገን የቆጠር ነን፡፡ ስልጣኔም አድርገን ወስደነዋል፡፡ ሰውየው እንዳሉት በትክክልም ከዴሞክራሲ ጋር ትውውቅ የለንም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አመራር በትእግስቱ ይደነቃል፡፡ በመቻል ችሎታው ጫንቃው ደንዳና ነው፡፡ ስለሆነም ሊወደስ ይገባዋል፡፡ ፈጣሪም ሰው መስሎ በመሃላችን ቢገኝ የሚፈተንባት ጉደኞች የተፈጠሩባት ያሉባት ሀገር ነች ያለችን፡፡
ፍላጎታችን ብዙ ሺህ ነው፡፡ በቅጡ አይታወቅም፡፡ እሱ ሲነካ የሚጮህ ፣የሌላውን መብትና ነጻነት መርገጥ መድፈቅ የዴሞክራሲ መብቴ ነው የሚል እሳቤ በበዛበት ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን በሂደት እየተማረው እየተለማመደው ካልመጣ አያውቀውም፡፡ ሁሉን አማራሪዎች ስለሆንን ተደፍቆና ተረግጦ መያዝ ነው የሚመቸን፡፡ እንደ ቦይ ውሃ በተገኘው ቀዳዳ መፍሰስ እንወዳለን፡፡ በስሜት እንደግፋለን፡፡ በስሜት እንጠላለን፡፡ታላቅ እብደት ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ማመዛዘን የለም፡፡ ለሀገር የሚሞት እንጂ ሀገር ገዳይ ጀግና አይሆንም፡፡ እንይዘው እንጨብጠው ጠፍቶናል፡፡
ሕግና ሥርዓትን ደፍቆ የሚያስከብር፣ ሀገርን ከጥፋት የሚታደግ ፣የሕዝብን ሰላም በብርቱ ክንዱ የሚያስከብር፣ የመንደር ጎረምሳና ቀማኛውን ዘመናዊውንም ሌባ ጸጥ እረጭ አድርጎ የሚደፍቀው ለሀገር ሰላም የሚያመጣው ዴሞክራሲ ሳይሆን የህግ የበላይነት መስፈን ብቻ ነው፡፡
ባይበዛም አምባገነንነት መድሀኒት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሲስሟት ቀርቶ ሲስቧት ሆነና ረዥሙን እንደልብ የሚያስጋልበውን ገመድ አጥብቀን አንገታችን ላይ ማድረግን የወደድን ይመስለኛል። በቅሎ መጫኛዋን በጠሰች ቢሉ ለእራስዋ አሳጠረች አሉ፡፡ የእኛም ነገር ይሄው ሆኗል፡፡ ነጻነትን ዴሞክራሲን በአግባቡ መጠቀም አልቻልንበትም፡፡ የለመድነው አልሆነም፡፡ ዝምታው ጥፋትን የሀገር ሀብት ውድመትን የዜጎችን መፈናቀል አስከተለ፡፡ ይህ አካሄድ ለካስ ወደው አይደለም መሪዎች አምባገነን የሚሆኑት ያስብላል፡፡ ኢትዮጵያን ሊያጠፏት ጥርሣቸውን እያፋጩ ካሉት ስመ ብዙ አውሬዎች ለማዳን ኮስተርና ቆፍጠን ብሎ ህግን ማስከበር ግድ ይላል፡፡ እዛ ላይ ጨዋታው በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚደረገው ቀልድ ሁሉ ያበቃል፡፡ ለእዚህም ነው በጽሁፉ እሹሩሩው ሊያበቃ ይገባል የተባለው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
መሐመድ አማን