ልጆች! በየአካባቢያችሁ ችግኞችን እየተከላችሁ እንደሆነ እገምታለው። ችግኞችን መትከል ብዙ ጥቅሞችን ስለሚያስገኝ ትከሉ፤ ተንከባከቡ። አሁን ያለንበት ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ የሚተከልበት ነው። እናንተም ከኮሮና ቫይረስ እየተጠነቀቃችሁ አረንጓዴ አሻራችሁን በየግቢያችሁ እና በየሠፈራችሁ አሳርፉ። እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር በመሆን ከአካባቢያችሁ ራቅ ወደ አለ ቦታ በመሄድ መትከል ትችላላችሁ። ነገር ግን ከቤት ስትወጡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረጋችሁን እርግጠኞች መሆን አለባችሁ።
ዛሬ የማቀርብላችሁ ልጅ ሰኔ 13 ቀን ሰሚት አካባቢ ለሥራ በሄድኩበት ወቅት ችግኝ ሲተክል ያገኘሁትን ተማሪ ነው። ተማሪ ካሌብ ዮሴፍ ይባላል። የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ወደፊት ኢንጅነር የመሆን ከፍተኛ
ፍላጎት አለው።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤት ቢዘጋም በቤት ውስጥ በመዋል ተገቢውን
ጥንቃቄ በማድረግ ከትምህርት ቤት የሚላክለትን ያነባል፤ በቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችንም እሠራለሁ ብሏል። ሁሉም ተማሪዎች መጽሐፎችን የማንበብ ልምድ ማዳበር እንዳለባቸው ይናገራል።
ተማሪ ዮሴፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤት ውስጥ የተለያዩ አይነት ችግኞችን እየተከለ ነው። ልጆች በሚመቻቸው ቦታ ሁሉ ጥንቃቄ በማድረግ ችግኝ ቢተክሉ ለሀገራቸው የተፈጥሮነ አየር ንብረት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይቆጠራል ብሏል።
ኮሮና እስኪጠፋ ድረስ በቤታቸው ሆነው እያነበቡና እየተጫወቱ ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ ጥሩ ነው። እንዲሁም ችግኝ አስገዝተው ወይም በራሳቸው አፍልተው በቤታቸው ውስጥ መትከል ይችላሉ። ችግኝ መትከል ለሀገራችን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በተለይ ደግሞ ንፁህ አየር ለማግኘት ይረዳል። እንደ ገቢ ምንጭነትም ያገለግላል። የአየር ፀባዩ
የተስተካከለ እንዲሆንና በየወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ይረዳል። ይሄ ደግሞ ሀገራችንም ሆነች እኛ የኢኮኖሚ ጥቅም እናገኛል። ጤናችንም የተጠበቀ ይሆናል። ‹‹ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኜ በግቢያችን ውስጥ ማንጎ፣ ሸንኮራና ሙዝ የመሳሰሉ ተክሎችን ተክያለሁ። ጠዋት ጠዋት ውሃ በማጠጣት እንከባከባቸዋለሁ። ከተክሎች ጋር ረጅም ሰዓት በማሳለፍ ሳይደብረኝ እንድውል አድርጎኛል ሲል የእፅዋትን ጥቅም ይገልፃል።
ልጆች! እናንተም እንደ ተማሪ ካሌብ ዮሴፍ ጊዜያችሁን በማንበብና ችግኝ በመትከል ማሳለፍ አለባችሁ። ችግኞችን መትከል ብቻም ሳይሆን መንከባከብም ይጠበቅባችኋል። ኮሮና ከማንበብ ስለማያግድ ማንበብም አለባችሁ። ችግኞችን በቀላሉ በግቢና በሰፈር ውስጥ መትከል ትችላላችሁ። አንብቡ፤ ችግኝ ትከሉ መልዕክታችን ነው። መልካም ቀን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ሞገስ ፀጋዬ