ወዳጄ መቆጨት ካለብህ አሁን ነው መቆጨት ያለብህ። እንደ ቀልድ ዓይናችን እያየ ያጣናቸው የተፈጥሮ ሀብቶቻችን በርክተው ለመቁጠር እየተቸገርን ነው። ላፍታ ጢስ አባይ ፏፏቴን በህሊናህ ሳለው። እውነቱን ልንገርህ ጢስ አባይ ፏፏቴ ዓይናችን እያየ ነው መቼም ልንመልሰው በማንችለው ሁኔታ ያጣነው። ያ ግርማ ሞገሳሙ ፏፏቴ ዛሬ ብታየው ታነባለታለህ። ከራማውን ተግፎ፤ጉልበቱ መንምኖ በሰለለ ትንፋሽ ነው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚንገታገተው።
ጢስ እሳትነቱን በታሪክ አተላዎች ተገፎ ‹‹እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው›› ሆነና ነገሩ ያ ግርማ ሞገሱና ነጎድጓዳማው ድምጹ ተነጥቆ ትናንሽና ቀጫጭን መስመሮች ሆነው በቁጭት ሲወርዱ ታያቸዋለህ። ያኔ በነጎድጓዳማው ድምጹ፤ እንደጉም በሚትጎለጎለው የውሃ ነጠብጣቡ ከሩቅ እየተጣራ፤ በውበቱ እያማለለ፤ ሳትወድ በግድህ እዚች ቅድስት ምድር ላይ በመፈጠርህ በሀሴት እንድትኮፈስ ያደርግህ ነበር። አንተ ባትንቀባረር እንኳን ውቅያኖስ አቋርጠው የሚመጡት ሀገር ጎብኝዎች ባንተ እነሱ ይኮሩና ስለዕድለኝነትህ ደጋግመው ሲነግሩህ በርግጥም በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመወለድህ የተቀደስክ ያህል ይሰማህ ነበር።
ልብ በል «ነበር» እያልኩ ነው የማወራህ፣ እመነኝ የሰማሁትን ሳይሆን በዓይኔ በብረቱ ያየሁትን ነው የምነገርህ። በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ ጢስ አባይ ፏፏቴ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተብሎ በሸፍጥ ከራማውን በተገፈፈበት ሰሞን ነው። በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ያዩትን ነገር ለማመን ጉልበት አጥተው ይጨቃጨቃሉ። በመጽሐፍ ያነበቡት፤ በመረጃ መረብ ያገኙት መረጃና በፎቶግራፍና በፖስተር ያዩት እንደተጋነነ አምነው እንደተሸወዱ ነበር እርግጠኛ የሆኑት። አብሯቸው የነበረው አስጎብኚ በምንም ቋንቋ አውርቶ እነሱን
ሊያሳምናቸው አልቻለም ነበር። አስጎብኚው አንድ የማምለጫ ዘዴ ፈለገና እንዲህ አላቸው።
‹‹አያችሁ እንደእናንተ ዕድለኛ የለም፤ አስተውላችኋል እዚህ ቦታ የረገጠ ጎብኚ ሁሉ ያየው ነገር ቢኖር ያን ባለግርማ ሞገስ ውሃ ብቻ ነበር። እናንተ ግን ለዘመናት በውሃ ተሸፍኖ የነበረውንና ማንም አይቶት የማያውቀውን ጥቁር ድንጋይ እያያችሁ ነው። ይህ ደግሞ መታደል ነው። እነርሱ ስለፋፋቴው አስደናቂነት ጽፈው ሊሆን ይችላል። እናንተ ግን ለዘመናት በውሃ ተሸፍኖ ስለነበረው ጥቁር ድንጋይ ውበት መጻፍ ትችላላችሁ›› በእርግጥም አማራጭ አልነበረውምና የማምለጫ መንገድ ሰራለት ጎብኚዎቹ በነገራቸው ነገር ተመሥጠው በጠቆረውና ለዘመናት ተደብቆ በነበረው ድንጋይ ላይ ታሪክ ማስፈር ጀመሩ።
ወዳጄ እውነቱ ግን ሌላ ነበር። ያንን የኃይል ማመንጫ የቀየሰው መሐንዲስ ከግብጽ የመጣ ወይም የታሪክ ዝቃጭ ካልሆነ በቀር በታሪክ፣ በቅርስና በውበት ላይ ባልቀለደ ነበር። ግን ማንም ይሁን ማን በታሪክ ወንፊት ሲንጠፈጠፍ በዝቃጭነት መመዝገቡ የማይቀር እውነታ ሆነና ይኸው እያማነው ነው። የሸፍጠኛውን መሐንዲስ ሀሳብ እንደወረደ ተቀብለው ያስተገበሩት ጊዜ የሰቀላቸው የክልሉ ባለሥልጣናትም በታሪክ ተወቃሽነት መጠቀሳቸው አይቀርም።
ወዳጄ ሌላ እውነት ልንገርህ! ብታምንም ባታምንም በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነልህ። ታማኙ አባይ በጣና ላይ ምንም ጉዳት ላለማድረስ ለራሱ የተማማለበት ቦታ ላይ ትልልቅ ድንጋዮች ተፈጥሮ መገደቢያ አድርጋ ተክላቸው ነበር። አባይ በጣና ላይ በኩራት ሲገማሸር የተለየ ድምጽ ሳያሰማ መሰሰስስስስስ ብሎ ምንም ቅንጣት ውሃ ሳይወስድ ነበር የሚያለፈው። በዚህ ሁናቴ ጣናና አባይ ላይከዳዱ ተማምለው ተዋደውና ተፋቅረው ነበር የኖሩት።
ወዳጄ አሁንም «ነበር» እንዳልኩህ ነው ልብ
በለኝማ። በአንድ ወቅት አባይ ከጣና በሚወጣበት ድምበር ላይ የተፈጥሮን ቃልኪዳን አፍርሰው የመገደቢያ ድንጋዩን ናዱት። እነማን እንዳትለኝ ወዳጀ እንደኔ ግምት የታሪክ ዝቃጮች መሆናቸውን ብቻ ነው የምነግርህ። ምክንያቱም በጣና ላይ የክፋት እጁን የሚያነሳ ሁሉ እርሱ ለእኔ ክፉ የክህደት መንፈስ የተጸናወተው ዝቃጭ ነውና። እናም ታማኙ አባይ ለዘመናት ጠብቆት የኖረውን ቃልኪዳን ክፉዎች አስከዳውና የጣና ውሃ ተቀላቅሎ መጓዙን ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ ጣና ለጠላት እጅ ሰጠ፤ ወዘናው ተሟጠጠ፤አጥንቱ ገጠጠ፤በላዩ ላይ ለዘመናት በኩራት የሚርመሰመሱት ጀልባዎችን ሁሉ አሳቀቀ፤ አድናቂዎቹን ሁሉ አንገት አስደፋ።
ከክፉዎች መሃል አንዳንድ ቅኖች አይጠፉምና በብዙ ጩኸት ያንን የጣናና የአባይን ተፈጥሯዊ የቃልኪዳን ማህተም ወደነበረበት በመመለስ ጣናና ከመንጠፍጠፍ ታደጉት።
ወዳጄ ጣና የራሱ አምላክ እንዳለው ስነግርህ በልበሙሉነት ነው፤ ጣናን ለማድረቅ ያሴሩ፣ የተገበሩ ብዙ ክፉና ለሆዳቸው ያደሩ ነበሩ። ሆኖም የጣና አምላክ አያንቀላፋምና እነርሱን አጥፍቶ በጥፋታቸው ልክ እንደሚቀጣቸው አምናለሁ። አሁንም የእምቦጭ ጉዳይ ከዚህ አያለፍም።
ወዳጄ ልብ ብለህ አድምጠኝ ሌላ እውነት ልንግርህ! እንዲህ እንደ ዛሬው እምቦጭ ሳይስፋፋ ከአስርና አስራአምስት ዓመት በፊት ገና ምልክቱ ሲታይ ‹‹ጣና ባዕድ አረም እየወረረው ነው፤ ካሁኑ ይታሰብበት›› ያሉ እንደ ጥፋተኛ ተቆጥረዋል፤ ምናልባትም ተወቅሰዋል! ተቀጥተዋል።
ለዚህ ነው ጣና የተፈጥሮ ጉዳት ሳይሆን የሸፍጥ ውጤት ነው የምልህ በብዙ ማሳያ ነው። ጣና ላይ በቅለው፤ የጣናን ውሃ ጠጥተው ያደጉ በስሙ የሚምሉ አስመሳዮች የማያውቁት እውነት ቢኖር ጣና ከውሃ ያለፈና የገዘፈ ምስጢር መሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ደጉ ከማዶ ሰፈር