በፍራጃ የተካነ ማህበረሰብ እየተፈጠረ ነው እንዲህ ያለ ልኬት በራሱ አተያይ የሚፈርጅ እታች ሰፈር እንዲ ተባለ፤ እላይ ሰፈር ደግሞ እንዲህ ሆነ ማለት የተለመደ ሆኗል እራስን ከሰፈርተኞች በማውጣት ሌሎችን አቅጣጫ ሰጥቶ ማቧደንን ተያይዘነዋል መዳቢነት ተፀናውቶናል እኛ ማን ነንና ነው መሀል ላይ እራሳችንን አስፍረን የላይና የታች ሰፈር እያልን ፍረጃን የተካንን?
እኔ የሚለውን ባለቤትነት ስበን ከመሀል አስቀርተን እነሱ እነዚያ ማለት አዘውትረናል እራሳችን ለማንፃት ሌሎችን ኮንነናል በራሳችን መለኪያ መስፈት ቀምረን፣ ድንበር አበጅተን፣ መደብ አውጥተን ሰፍረን ስናበቃ የላይና የታች ሰፈር የመሀልና የጥግ ልየታን ስራዬ ብለን ተያይዘነዋል በፍረጃ ላይ በርትተናል እኛ ማን መዳቢ እነሱ ማን ተመዳቢ እንዳደረገን ግን ማወቁ ነው ችግሩ
የኛን ተግባር ሰናይ ከኛ አርቀን መድበናቸው ስናበቃ እነሱ ያልናቸው ምግባረ ብልሹ አድረገን የላይና የታች ሰፈርተኞች እራሳችን ያልተነካ መሀለኞች ማድረግ ተክነናል እኛ ኢትጵያን የምንወድ እነሱ ለማጥፋት የሚታትሩ፤እኛ ወገንን የምንደግፍ እነሱ ህዝብን የሚጨቁኑ፤እኛ መልካም ነገር ላይ ዘውታሪ እነሱ ሴራን የሚጎነጉን አድረገን ስለናል የእነሱን በጎነት ከመመልከት ይልቅ የእኛን ተገቢነት የሌለው ምግባር በመልካም ማወደስ ቀሎናል
እርግጥ የዳበረ የፖለቲካ ባህልና ነፃ የሆነ የሀሳብ ሙግት ባህል ባልዳበረበት ማህበረሰብ ይሄ የሚጠበቅ ነው ግን ደግሞ ባህል ተኮር የሆነ ለዘመናት የቆየ በስርዓት ብንጠቀምበት ለሌላው ይተርፋል እያልን ብዙ የምናወራለት የራሳችን የሆነው ውብ የመከባበር እሴታችን ማን ነጥቆን ነው? ስናሳዝን
ይችን ሀገር ያቆዩዋት አባቶች በራሳቸው መንገድ ባልነጠፈ ፍቅር ዘመናትን ተሻግረው ድንቅ የሆነ ባህል ከጥበብ ጋር አውርሰውናል ያ ጥበብ እኛ ጋር ሲደርስ ተንኮታኩቶ ሚዛን አልባ ፈራጅ ምክንያት አልባ ኮናኝ አድርጎን አርፏል ጉድ ነው ተነጋግሮ በመግባባት አማራጮችን አቅርቦ የተሻለውን መምረጥ ተሟግቶ የነጠረውን መለየት እንደ ልማድ ብናዳብር ኖሮ አሁን እየተከተበ ያለው ታሪካችን ነገ ላይ በሌሎች ሲገለፅ
የተሻለ ገፅታ ይኖረው ነበር
ከሀገር የላቀ ሀሳብ ከወገን የከበደ ጉዳይ ያለ ይመስል አተያያችን የተዛባ መሆኑ አልገባ ያለን ሃሳባችን ሀገር ካላካለለ እሳቤያችን ስለ ወገን ካልቆመ የኛ መክበድና ታላቅነት ምኑ ላይ ሊሆን ይችላል? እነሱ እንዲህ ናቸው የሚል ፍረጃ እኛ እንደዚያ ነን የማለትን ልማድ ከየትኛው ወገን ወርሰን ከየትስ ተላምደን ይሆን መደበኛ ተግባር ያደረግነው
እኛ መሀለኛ ሌሎችን ዳርና ዳር አስቀምጦ ስለ ሀገር እኛ ብቻ ተቆርቋሪ ስለ ወገን እኛ ብቻ አሳቢ ነን ብለን ወስነናል የእኛን መወርወር እንጂ የሌላው የማንሰማ ሌላውን መናቅና ማጥላላት እንጂ የራሳችንን ስህተት የማናርም ልማደኞች ሆነናል እራስን አሸንፎ ስለ ወገን የተሻለን ሀሳብ መሰንዘር ቢከብድ የተሻለውን አማራጭ ማመልከት ቢሳን እንዴት በሌላ የቀረበን በጎ እሳቤ ማጤን ያቅታል?
ደረጃ መዳቢዎቹ እኛ ግትር ሆነን የኔን ስሙኝ እንጂ ስለሌላ ሀሳብ አይገደኝም፤ አልያም የሌላው ፍላጎት አይጨንቀኝም የሚል ልማድ ተፀናውቶናል በእብሪት ተሞልቶ ማን ደፍሮኝ የሚል ሀሳብ ፈፅሞ ቢነጣጥለን እንጂ አያቀራርበንም እርግጥ አውርቶ መግባባትና ገዢ የሆነ ሀሳብ በማቅረብ በሀሳብ ብቻ ሞግቶ መርታት የላቀ ስልጣኔ ነው በትክክለኛ ሚዛን የመለካት፤ በሀሳብ ሙግት የመርታት ስልጣኔ ላይ መድረስ እንዴት ተሳነን
ሀገራዊ ታላቅ ጉዳይን የግል አድርጎ ሌላው ስለዚያ ያለው እሳቤ የተዛባ ምን አልባትም ከኛ በተቃራኒ የቆመ ያንን ጉዳይ አጥብቆ የሚጠላ ስለ ሀገሩም ግድ የሌለው ይመስለናል ነገር ግን እኛ የእርሱን ተፃራሪ ተግባር ፈፃሚዎች የፈረጅነው ደግሞ የእኛን በጎ ሀሳብ ላይ አለመገኘቱ አልገለጥ ቢለንስ? አዎ እኛ ቀድመን ፈርጀን ሌሎችን የምናየው በጠለሸ መነፅር ሆንስ መጀመሪያ አተያያችንን እናፅዳ፤ ምልከታችን በበጎነት የተቃኘ ሚዛናችንም ያልሳተ ይሁን እስኪ
በፍረጃና የላይና የታች ሰፈር በሚሉት ቡደና አልያም ደግሞ አግዝፈው በሚየሳዩት አለመግባባት የሚወለደው መፍትሄ ሳይሆን ልዩነት ነው እነሱና እኛ እነዚያና እነዚህ በመባባል ማቀራረብም ሆነ መቅረብ ይከብዳል ሀሳብ አይደል ችግራችን፤ ሙግት አይደል ልዩነታችን የሚያገዝፍብን ታዲያ ሀሳቡ ተጣርሶና ተጋግሎ ከሌላው ጋር አልጣጣም ብሎ ሀገር ከሚያፋጅ፤
ወገን ከሚጎዳ ቢጣልስ? በሚያፋቅር ፍረጃን አስቀርቶ በሚያቀራርብ ሀሳብ ቢተካስ ጎበዝ
እራስን መሀል በማስፈር የላይና የታች ሰፈር እያሉ ሌሎችን በመፈረጅ እራስን ከኩነኔ የማራቅ የተንሸዋረረ እይታን መግራት ቀዳሚ ተግባር ነውበነገራችን ላይ እኛ መሀል ላይ ሆነን የላይ ሰፈርተኞች ለምንላቸው እኛ ለእነሱ የታች ሰፈርተኞች ነን በሌላኛው እይታ ደግሞ እኛ መሀል ሆነን የታችኞቹ የምንላቸው ለእነሱ የላይ ሰፈርተኞች መሆናችን መዘንጋት ፈፅሞ አይኖርብንም
አስታራቂ የሆነ ለሁሉም ምቹ ለሌላኛው ሀሳብም ግራ ያልሆነ ሃሳብ መውለድ ለድርድርም ማቅረብ ሲገባ እዚያ ላይ ተራርሞ ማለፍ ሲኖርብን ያለ እኔ ሀሳብ ያለእኔ ውሳኔ የማንም አይሆንም ማለት ደስ አይልም እንደ ሀገር ታስቦ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ተተግብሮ መዝለቅ ፈፅሞ አይሞከር ነገር መቻቻሉ ግድ ይላል
የእኛን መፈራረጅ ወዲያ ጥለነው ለሀገር ጠበቃና የገዘፈ ሀሳብ መለኪያው መሬት ላይ ሰፍሮ የላቀ ፋይዳ ሊፈጥር የሚችል መሆኑ ላይ ነው ሀገር አስቀድሞ እኔ ከማለት መራቅ፣ ህዝብን አክብሮ እኛ ማለትን ማዘውተር፣ ሀሳብን ሰጥቶ መቀበል መግባባትን አዘውትሮ በቀናነት መቀጠል የታላቅነት ጅማሮ ነው
ፍረጃን በመግታት እኔ ብቻ ያልኩት ይፈፀም፤ የኔ ብቻ ይደመጥ የሚለውን ሀሳብ ትተን አንተስ ምን አልከን ብንለምድ ስንቱ ሀገራዊ ችግር በተፈታ ነበር ሀሳባችን በእኛው ዙሪያ ብቻ አጥረን በሩን ዘግተን የሌላን ወደእኛ አናቅርብ የኛንም በግድ ተግብሩ መፈክራችን ባይሆን ምንኛ ባማረብን ነበር ሀሳብ መሰንዘር የመውደዳችን ያህል መቀበልን ብንለምድ ስለ ሌላው አይመለከተንም፤ አያገባንምን ትተን በግልፅነት በመተሳሰብ ብንነጋገር ምን ይጎለን ነበር ? ምንም
እኔ ብሎ እራሱን አጥርቶ ሌላውን ከመኮነን እኛ ወደሚል አብሮነት የተሸጋገረ ምክንያታዊ መሆን ይገባናል ህዝብ አንድ አድረጎ መብትና ፍላጎቱ ተጠብቆ እንደ ሀገር ወደፊት ማራመድ እንዲቻል ዋንኛ መንገዱ ይህ ነው አገር ታላቅ የማድረግ ምኞታችንን ወደ ተግባር ለመለወጥ ትልልቅ ሀሳቦች መነሻ አድርጎ ተቀራርቦና ተነጋግሮ መግባባት ይጠይቃል ችግሮችን ከራሳችን አርቀን የሌላ ከማድረግ ይልቅ የእኛ የሆኑ ችግሮች የራሳችን የሆኑ መፍትሄ ብናስቀምጥ መልካም ነው አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ተገኝ ብሩ