‹‹ለኑሮ በማይመች ረግረጋማ መሬት ላይ እንድንሰፍር ተደርገናል፤ ቦታው ቤት ሠርቶ ለመኖር አይመችም፤ ለግብርና ሥራም አመቺ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ለበሽታና ለርሃብ ተጋልጠናል፡፡ ችግራችንን ለሚመለከታቸው አካላት ብናሳውቅም ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ከልማት ተነሺዎቹ መካከል ለህልፈት የተዳረጉም አሉ፡፡›› ሲሉ በምሬት የተናገሩት ለጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ከቀዬአቸው ተነስተው ፓዊ ከተማ ክስቶን በሚባል ቀጣና ላይ የሰፈሩ የ181 አባወራዎችና እማወራዎች ተወካይ አቶ ታደሰ ሎጵሶ ናቸው፡፡
በጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ምክንያት እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አባወራዎችና እማወራዎች በፓዊ ወረዳ መንደር 4 ቀጣና 1፣ መንደር 7 ቀጣና 1፣ መንደር 9ቀጣና 1 ይኖሩበት ከነበሩበት ያለፈቃዳቸው እንዲነሱ ተደርገው በፓዌ ወረዳ መንደር 30 ክስቶን በሚባል ጎጥ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ታደሰ አሁን ለተወሰደባቸው መሬት በምትክነት የተሰጠው መሬት ረግረጋማ ከመሆኑም ባሻገር ለልማት ከመነሳታቸው በፊት ከነበራቸው መሬት አንጸር ሲነጻጸር በምርታማነትም በስፋት አይመጣጠንም፡፡ በፊት 5 ሄክታር መሬት እንደነበራቸው የሚገልጹት አቶ ታደሰ፤ አሁን ግን አንድ ነጥብ 5 ሄክታር ብቻ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እሱም ቢሆን ለእርሻም ሆነ ለመኖሪያነት የማይመች በመሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውደቃቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ ታደሰ እንደሚያብራሩት፤ የሚያስተዳድሩት ሰባት ቤተሰብ አላቸው፡፡ ከቀዬአቸው ከመነሳታቸው በፊት ጥምር ግብርና በማካሄድ መልካም ኑሮ የሚኖሩ ፣ትርፍ በማምረት ምርት ለገበያ የሚያቀርቡ እና በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን በአግባቡ የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡ ከቀዬቸው ከተነሱ በኋላ ግን ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሎባቸዋል፡፡ የመንግሥትን ዕርዳታ ለመጠበቅም ተገደዋል፡፡ ልጆችን ማስተማር ባለመቻላቸው ልጆች ትምህርታቸውን አቋርጠው አልባሌ ቦታ እየዋሉ ነው፡፡ ይህ የእሳቸው ችግር ብቻ ሳይሆን ከሳቸው ጋር ክስቶን የሰፈሩት የልማት ተነሺዎች ሁሉ ችግር ነው፡፡
የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ለንብረት ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/1997 አንቀጽ 8 ላይ የመሬት ይዞታን በቋሚነት እንዲለቅ የሚደረግ የገጠር መሬት ባለይዞታ መሬቱን እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት ያገኘው አማካኝ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ ከሚከፈለው የመፈናቀያ ካሳ በተጨማሪ ካሳ ማግኘት እንዳለበት በአዋጁ ላይ የተመለከተ ቢሆንም በአዋጁ ላይ የተቀመጠው ተግባራዊ ባለመደረጉ ለአደጋ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ፤ የተፈናቃዮች ልጆች ትምህርት አቋርጠው፣ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ለፋብሪካው ግንባታ ትተው በስተእርጅናቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የወደቁትን በዕድሜ የገፉ እናትና አባት ለመንከባከብ ተገደዋል፡፡ ቅሬታቸውን ከወረዳ እስከ ፌዴራል ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም ላይ ከስኳር ኮርፖሬሽኑ ተቀንሶ ለልማት ተነሺዎች ይሰጥ ቢባልም እስከአሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ በመሆኑም 2011 ጥቅምት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ለተወካዮች ምክር ቤት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ከጽህፈት ቤቱ የሚሰጠውን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በፕሮጀክቱ ምክንያት ከፓዌ ወረዳ ቀጣና አንድ መንደር ሰባት ተነስተው አባይ በር ቀበሌ የሰፈሩ 450 አባወራዎችና እማወራዎች ተወካይ አቶ ዓሊ አደም እንደሚሉት፤ አርሶ አደሮቹ ከቀዬአቸው ለመነሳት ፈቃደኛ ስላልነበሩ በኃይልና ማስፈራሪያ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ የክልሉ መንግሥት የተሻለ መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ለ30 ዓመታት ከኖሩበት ቀዬአቸው እንዲነሱ የተደረገ ቢሆንም መንግሥት የገበውን ቃል አልፈጸመም፡፡
የንብረት ዋጋ ካሳ አከፋፈል ኢ- ፍትሐዊ ነበር የሚሉት አቶ ዓሊ፤ ያፈሯቸው ንብረቶች ተገቢው ካሳ አልተከፈለም ይላሉ፡፡ ለአንድ ማንጎ በሌሎች አካባቢዎች ላይ እስከ 60 ሺ ካሳ ሲከፈል እንደነበር ገልጸው፤ ለእነሱ ግን 12ሺህ ብር ብቻ እንደተከፈለ ነው የሚያብራሩት፡፡
እንደ አቶ ዓሊ ማብራሪያ፤በአባይ በር የሰፈሩት አብዛኞቹ ከ5 እስከ 10 ሄክታር መሬት የነበራቸው ናቸው፡፡ ለልማት ሲነሱ ግን ሁለት ሄክታር እንኳ አልተሰጣቸውም፡፡ እሳቸውም 1 ነጥብ 5 ሄክታር ነው የተሰጣቸው፡፡ ከዚያ ባሻገር የማፈናቀያና የመቋቋሚያ ገንዘብ ሊሰጥ እንደሚገባ ህጉ የሚያዝ ቢሆንም የማፈናቀያና የማቋቋም ገንዘብ አልተሰጠም፡፡ ጥያቄዎችን ሊያቀርቡ በሚሞክሩበት ወቅት የልማት አደናቃፊዎች ናችሁ በማለት ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር፡፡
የፓዌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ከድር እንደሚናገሩት፤ ለስኳር ኮርፖሬሽኑ ከወረዳው አንድ ሺህ 276 አባወራና እማወራ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ እነዚህ አባወራዎች በፓዌ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ክስቶን፣ አባይ በርና ህዳሴ በሚባሉ ቀበሌዎች እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡ በወቅቱ የልማት ተነሺዎቹ ተጎድተውም ቢሆን መላው ኢትዮጵያዊያንን ተጠቃሚ ለሚያደርግ ፕሮጀክት ቅድሚያ ይሰጥ ተብሎ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡ ሆኖም ተነሺዎቹ ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር፡፡ የተሰጣቸው ምትክ መሬት በስፋትም በጥራትም የሚመጣጠን አለመሆኑንና እንዲሰፍሩ የተደረገበት ቦታ መሰረተ ልማት ያልተሟለበት መሆኑን እንዲሁም ሌሎች ቅሬታዎችን ሲያነሱ ነበር፡፡ ነገር ግን ተገቢው ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡ ወረዳው መሰረተ ልማት ሊያሟላ ጥረት ቢያደርግም በበጀት እጥረት ምክንያት ከአቅሙ በላይ ሆኗል፡፡ አሁንም ቢሆን የተነሺዎቹ ጥያቄ መመለስ እንዳለበት ወረዳው ያምናል፡፡
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ታደሰ እንደተናገሩት፤በአንዳንድ አካባቢዎች የሰፈሩት የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት ተነሺዎች ያሉበት ቦታ አምርተው ለመመገብ አመቺ አይደለም፡፡
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ የልማት ተነሺዎቹ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግራቸውን እንዲያጣራ ተደርጓል፡፡ በተደረገው የማጣራት ሥራ አንዳንድ አርሶ አደሮች የሰፈሩባቸው ቦታዎች ችግር ያለባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይም ክስቶን የሚባል ቀጣና ያሉት የሰፈሩበት መሬት ረግረጋማ መሆኑን ከሰፈሩበት በኋላ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀድሞውኑ ተገቢው ጥናት ሳይከሄድ በቦታው እንዲሰፍሩ መደረጉ ስህተት መሆኑን ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም 2 ሺህ ሄክታር መሬት ለልማት ተነሺዎቹ እንደሚያስፈልጋቸው ዞኑ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በቃለ ጉበኤ አሳውቋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በበኩላቸው፤ከአርሶ አደሮቹ ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ከንብረታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ቅሬታቸውን እንዳያቀርቡ አፈና ያደረገባቸው አካልም የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የልማት ተነሺዎቹ የሰፈሩባቸው አንዳንድ ቦታዎች ለኑሮና ለእርሻ የማይመች መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፤ አንዳንድ የልማት ተነሺዎች አሳሳቢ ችግር ውስጥ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ላሉት የልማት ተነሺዎች ቅያሪ ቦታ ሊሰጥ እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ በዚህም መሰረት ቅያሪ ቦታ ለመስጠት ቦታ የማፈላለግ ሥራ ሲሠራ ነበር ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አድጎ ማብራሪያ ቅያሪ ቦታ በክልሉ ሊገኝ ባለመቻሉ፤ ለስኳር ፋብሪካ ከተለየውና ልማት ላይ ካልዋለው መሬት ውስጥ ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ለልማት ተነሺዎቹ እንዲሰጥ ክልሉ በደብዳቤ የጠየቀ ሲሆን፤ የደብዳቤው ግልባጭ የስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት እንዲያውቁ ተደርጓል፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታቸው እስከአሁን ድረስ ለልማት ተነሺዎቹ መሬት ማቅረብ አልተቻለም፡፡
የልማት ተነሺዎቹ በክልሉ ህግ መሰረት አንድ ግለሰብ እስከ 10 ሄክታር መሬት እንዲያገኝ ይፈቅዳል ቢሉም አቶ አድጎ የክልሉ ህግ ለየትኛው አካል የሚሰጥ መሬት ከ3 ሄክታር በላይ መሆን እንደሌለበት ተደንግጓል ይላሉ፡፡ ለልማት ተነሺዎቹም እስከ ሁለት ሄክታር መሬት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አድገህ መኩሪያ እንደሚሉት፤የክልሉ ካቢኔ አጽድቆ ለስኳር ኮርፖሬሽን ያቀረበው ካሳ ለተነሺዎቹ ተከፍሏል፡፡ ክልሉ አጽድቆ ከቀረበው ካሳ ውስጥ ሳይከፈል የቀረ የለም፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁለቱም ክልሎች የልማት ተነሺዎቹ በተነሱበት 13ሺህ 147 ሄክታር መሬት ላይ አገዳ መተከሉን የሚያነሱት አቶ አድገህ፣ለፕሮጀክቱ ከተያዘው መሬት ውስጥ የተወሰነው ለልማት ተነሺዎች ሊሰጥ ነው የሚል ጭምጭምታ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እስከአሁን ድረስ ለፕሮጀክቱ ከተያዘው መሬት ተቀንሶ ለልማት ተነሺዎች ይሰጥ የሚል ውሳኔ ለፕሮጀክቱ በደብዳቤ እንዳልደረሰው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
መላኩ ኤሮሴ
This is exactly what I needed to read today Your words have given me a new perspective and renewed hope Thank you
Your blog always puts a smile on my face and makes me feel better about the world Thank you for being a source of light and positivity
79king là nhà cái cá cược trực tuyến uy tín, nổi bật với kho trò chơi đa dạng như casino trực tuyến, cá cược thể thao, lô đề và slot game. Với giao diện hiện đại, tốc độ nạp rút tiền nhanh chóng và chính sách bảo mật cao, 79king cam kết mang lại sân chơi an toàn, minh bạch và đẳng cấp cho người chơi.
Link truy cập 79king mới nhất: https://79kingtop.me/