የፍቅር እስከመቃብሮቹ በዛብህና ሰብለወንጌል የልቦለድ ገፀባህርያት ቢሆኑም በገሐዱ ዓለም የምናውቃቸውን ያህል በየአጋጣሚው አብረውን ይኖራሉ:: ከየትኛው የገሐዱ ዓለም ሰው ይልቅ ነፍስ ዘርተው በዓይነ ህሊና ይታዩናል:: ማንነታቸው ግዝፍ ነስቶ፤ አስተሳሰባቸው ደርጅቶ ሰርክ ይመላለስብናል:: ኑሯችንን ይኖራሉ፤ መከራችንንና ደስታችንንም ይካፈላሉ::
በዛብህ ሰብለን በማፍቀሩ የተነሳ ከአባቷ ከፊታውራሪ መሸሻ የሚደርስበትን ጥቃት በመፍራት እንደነፍሱ የሚወዳትንና የሚሳሳላትን ፍቅረኛውን ሰብለወንጌልን ትቶ ወደማያውቀው አገር ይሰደዳል:: ስደቱም አዲስ አበባ አድርሶት ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ቢጥለውም የፍቅር ጥማቱን ማስታገስ አልቻለምና አዲስ አበባንም የሩፋኤል ደብርንም ተሰናብቶ ይመለሳል:: ሆኖም ግን የሰው ልጅ ሁልጊዜም ከአሰበበት አይደርስምና ዓባይ በርሃ ላይ ሲደርስ በሽፍቶች ተደብድቦ እንዳይሆን ይሆናል::
የበዛብህ መጥፋት ያሳሰባት ፍቅረኛው ስብለወንጌልም ተወልዳ ባደገችበት ቀዬ መቀመጥ ተሳናት:: ሰርክ እየመጣ ፊቷ ላይ ድቅን የሚለውን በዛብህን ለማግኘትና የፍቅር ጥማቷን ለመወጣት መነኩሴ መስላና በአባለምለምእኔ ተመስላ ከእሾህና አሜካለው ጋር ተጋፈጠች:: ቆሰለች፤ ተራበች፤ ተጠማች:: ፍቅር ሃያል ነውና መከራና ችግር አያሸንፈውም:: መነኩሴዋ ሰብለም በፍቅር ጎዳና ተመርታ ዓባይ በርሃ ደረሰች:: የበረሃው መውጫ ላይም ደመነፍሷ ነግሯት በሽፍቶች የተደበደበውን የዓይን ርሃቧን አገኘችው:: በዓባይ በርሃ፤ በዓባይ መንገድ፤ በዓባይ ጎዳና ሁለቱ ርሃብተኞች ከመከራና ከደስታ ጋር፤ ከስቃይና ከተስፋ ጋር ናኙ:: በዓባይ በርሃ፤ በዓባይ ወበቅ፤ በዓባይ ሐሩር ተንገላቱ:: በዓባይ ሽፍቶች ተፈተኑ:: ፍቅር መከራን የመቋቋን ሃይል አለውና ፍቅር የተራቡት፤ ፍቅር የተጠሙት ሁለቱ መከረኞች በዓባይ በርሃ ተገናንተው የፍቅርን ውሃ ጠጡ:: ጥማቸውን አረኩ::እስከወዲያኛውም ፍቅራቸውን ዘላለማዊ አደረጉት::
ዓባይ ሚስጢር ነው:: ልክ እንደበዛብህና ሰብለወንጌል እኛም የአሁን ዘመኖቹ ኢትዮጵያውያን በዓባይ እንፈተናለን፤ በዓባይ እንንገላታለን፤ በዓባይ እንታመሳለን:: ሆኖም ግን በጽናትና ብርታታችን መከራና ስቃዩን አልፈን፤ መታመስና መንገላላቱን አሸንፈን የዓባይን ውሃ እንጠጣለን፤ ችግርና መከራችንን አውልቀን እንጥላለን፤ ድህነትን እናራግፋለን:: ሽፍቶቹንም አሸንፈን ወደ ብልጽግና ጎዳና እናመራለን:: የኢትዮጵያውንም አንድነትና አብሮነት ዘላለማዊ ይሆናል::
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት ናት:: ከእነዚህ ፀጋዎች አንዱ የሆነው ዓባይ ከስም በዘለለ ትርጉም ሳይኖረው ቢቆይም ዘመኑ ደርሶ የዚህ ትውልድ ምርኮኛ ሆኗል:: የአንድነታችን ማህተም፤ የአብሮነታችን ቋሚ ሐውልት የሆነው ዓባይ የእናቱን ማህፀን ለማርጠብ ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሯል::
የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው እንደሚባለው እኛ የዓባይ ልጆች ውሃ ላይ ተቀምጠን ውሃ ጠምቶናል:: በርሃብ ስማችን ገኖ በዓለም መድረክ በጥቁር መዝገብ ሰፍሯል:: በ21ኛው ክፍለ ዘመን መብራት ናፍቆን ኩራዝ ለኩሰናል:: የእናቶቻችን ወገብ በእንጨት ለቀማ ጎብጧል:: ወጣቶቻችን ሥራ አጥተው በስደት የበረሃ ሲሳይ ሆነዋል:: የዛሬው ትውልድ ግን ይህ ሁሉ ስቃይና መከራ እንዲቀጥል አይፈቅድም:: የተከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ ተፈጥሮ ከለገሰችው ሀብቱ መጠቀምን ምርጫው አድርጓል::
የዓባይ ገፀ በረከት ዋነኛ ተቋዳሽ ሆና ለሺ ዘመናት የኖረችው ግብጽ ይህ ሃቅ ተዋጠላትም ፤ አልተዋጠላትም የአሁኑ ትውልድ ዓባይን ይገድባል፤ ዕውቀቱን፤ ገንዘቡን፤ ጉልበቱን አልፎም ህይወቱን ገብሮ ዓባይ በኢትዮጵያ ቤቱን እንዲሠራ ያደርጋል:: ፍትሐዊና ጎረቤት ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዓባይን ከጎረቤቶቹ ጋር ተካፍሎ ማደግ ይፈልጋል:: የዓባይ ገፀ በረክት ሰፊነውና የዓባይ ውሃ ለሁሉም እንደሚበቃ የኢትዮጵያ ህዝብ ያምናል:: ግብጽን የመሰሉ ጎረቤቶች ኢትዮጵያውያን በርሃብ ሲረግፉ መሳቅያና መሳለቂያ ከማድረግ ባለፈ የችግራቸው ተጋሪ ባይሆኑም ያንን መከራና ግፍ አስታውሰው ኢትዮጵያውያን ለበቀል ተነሳስተው አያውቁም:: ይልቁንም ግብጾች የኢትዮጵያውያን መከራና ስቃይ፤ ርሃብና ቸነፈር ዘላለማዊ እንዲሆን በመሻት በተበደልኩ ባይነት ሲጮሁ ይደመጣሉ:: ይህ ጩኸታቸው ለሺ ዘመናት ቢያወጣቸውም ዛሬ ግን ግብዓተመሬቱ የተፈፀም ይመስላል::
ዛሬ ከግብጾች ባዶ ጩኸት ይልቅ የኢትዮጵያውያን ዝምታ ይሰማል:: ዛሬ ከግብጾች አስመሳይነትና ጀብደኝነት ይልቅ የኢትዮጵያውያን ፍትሃዊነትና ጨዋነት ገዝፎ ይደመጣል:: ዛሬ ከግብጾችና አሜሪካኖች ኢፍትሃዊ ብያኔ ይልቅ የሱማሊያና የጅቡቲ የፍትህ ድምጽ ጆሮ ያገኛል:: ዛሬ ከዓረብ ሊግ ውሳኔ ይልቅ የአፍሪካ ሕብረት ድምጽ ሚዛን ይደፋል::
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሚኒስቴር ም/ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት ዛሬ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ወንዞቻችንም ግብጽን ተዋግተው ማሸነፍ ይችላሉ:: ግብጽ ከተቻላት የፀጥታው ምክርቤትንም ሆነ የሃያላን አገራትን ድጋፍ በማግኘት የህዳሴወን ግድብ ለማስቆም አሊያም ከተሳሳተ ስሌት በመነሳት ኢትዮጵያውያን በዘርና በሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ብሎ በማመን እርስ በእርስ ለማተራመስ የምትሸርበው ሴራ ብዙርቀት የሚያስኬዳት አይደለም:: ኢትዮጵያውን በውስጥ ፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም በዓባይ ጉዳይ ግን አንድ ናቸው:: ኢትዮጵያውያን ዓባይን ሲነኩብን ልዩነታችን ጠፍቶ ሕብረትና አንድነታችን እንደሚጠነክር ለግብጾች ማን በነገራቸው:: እስላም ክርስቲያኑ፤ አማራ ኦሮሞው፤ ጉራጌ ሲዳማው፤ ትግሬ ወላይታው፤ ሶማሌ አፋሩ፤ ቅማንት ጉሙዙ ወ.ዘ.ተ ሁሉም በዓባይ ጉዳይ አንድ ነው:: ይህ ነው የዓባይ ሚስጢር::
ትንታጉ የመድረክ ሰው ጌትነት እንየው ‹‹ዓባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ›› በሚለው የስንኝ ቋጠሮው የዓባይን ጉዳይ እንዲህ ተቀኝቶበታል:: ከፊሉን እነሆ:-
እናም አደራህን እንግዲህ አገሬ
አማራ፤ ኦሮሞ፤ ሶማሌ፤ አደሬ፤ አፋር ሆንክ ትግሬ
ቤኒሻንጉል፤ ኮንሶ፤ ጋምቤላ ሐረሬ
የአንድ ወንዝ ልጅ ሁሉ፤ ይህን የዓባይ ሐረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ
ከጋራ አንገት መድፋት፤ ከጋራ መሳቀቅ፤ ከጋራ አፍረት ወጥተህ
በያለህበት ሁሉ፤ በየዓለማቱ ጥግ በአንተነትህ ኮርተህ
አንተ ማነህ ሲሉህ፤ ከወዴት ነህ ሲሉህ፤ በሙሉ ራስነት አንገትህን አቅንተህ
ድምጽህን ከፍ አድርገህ፤ ደረትህን ነፍተህ
የዓባይ ልጅ ነኝ እኔ፤ ጦቢያ ነች አገሬ፤ በል አፍህን ሞልተህ
ይህ ነው ከእንግዲህ ፀጋ በረከትህ፤ የትውልድ ኒሻን የዕድሜ ሽልማትህ
እራትና መብራት፤ ክብርና ኩራት፤ አበባና እርግብ ነው፤ የዘመን ስጦታህ
የዓባይ ምርቃትህ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
እስማኤል አረቦ