የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ከሲራራ ንግዱ ዘመን ጀምሮ የነበረ ሲሆን ከደብዳቤ መፃፃፍ፣ መልእክተኛ መላላክ፣ እርዳታና ትብብር ከመጠያየቅ እስከ ግዥና ስጦታዎች ድረስ፤ ጥበብን ፍለጋ ጨምሮ የውጭ ግንኙነት አካል ሆነው ተመዝግበዋል፤ ይህም እስከ ዘመናዊው የአገራችን የውጭ ግንኙነት ድረስ ዘልቋል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ የውጭ ግንኙነትን በአዲስና ዘመናዊ መልክ የጀመረችው በአፄ ቴዎድሮስ (1847 እስከ 1860 ዓ.ም) ዘመነ መንግስት ነው። አፄ ቴዎድሮስ የአገሪቱን ነባር ዳር ድንበር ለማስከበር፣ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ፤ ከሁሉም በላይ አገሪቱን አንድ በማድረግ ከነበረችበት የኋላ ቀርነት ዘመን (ዘመነ መሳፍንት) ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ያላቸውን አላማ ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ ከውጪው አለም (በተለይም ከእንግሊዝና እየሩሳሌም) ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በተሻለ መልኩ ሲያኬዱት የነበረ በመሆኑ ነው።
በእስካሁኖቹ የአገራችን መሪዎች የተደበላለቀና የተቃረነ አመጣጥ ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ምናልባትም አንድ ጠንካራና ያልተዛነፈ አካሄድ ቢኖር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ሲሆን፤ እስካሁኑም ድረስ አብሮነትን፣ የሰው ያለመፈለግን፣ ትብብርን፣ ጣልቃ አለመግባትን፤ በተለይ አፍሪካዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን ከማጠናከር አኳያ ቀጥ ብሎ መምጣቱ ላይ የጋራ ስምምነት አለ። ከዚህ ውስጥ በአፍሪካ ወንድማማችነትን ከመፍጠርና አፍሪካዊ አንድነትን ከማምጣት አኳያ የመሪነት ሚናውን እየተጫወተች የምትገኘው ኢትዮጵያ ስትሆን፤ ከሌሎች አፍሪካ አገራት ባፈነገጠ መልኩ የአረብ ብሔርተኝነትን ከመፍጠርና ማጠናከር አኳያ ግብፅ የእንቅስቃሴው አስኳል መሆኗ ይታወቃል። በተለይም አረቢኛ ተናጋሪነቷን፣ ከሌላው የአረብ አገራት በተሻለ የምሁራን ቁጥሯና በመሳሰሉት ምክንያቶች ተሰሚነትን በማግኘት በቀጠናው የፈለጋትን በማድረግ ሌሎችን በቀየሰችላቸው ቦይ እንዲፈሱ ስታደርግ መቆየቷ ይታወቃል። ከ75 አመታት በፊት የተመሠረተው እና በግብፃዊው አሕመድ አቡ ጋይት ዋና ጸሐፊነት የሚመራው የአረብ ሊግ የያዘው አቋምም ከዚሁ ከግብፅ የአረቡ አለም ተሰሚነትና ተቀባይነት የመነጨ ሲሆን ያለችውን የሚሆነውና የሚያደርገውም ከዚሁ የመነጨ መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና የመን ከማንም በላይ ያላቸው ግንኙነትም ሆነ ትስስር ሰፊና ጠንካራ መሰረት ያለው የሚጀምረውም ከመፅሀፍ ቅዱስ ነው። ይህንኑ ተከትሎም ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ መተሳሰራቸው፤ በሀይማኖት (ኮፕቲክ) በኩል ያላቸው ቅርርብ፤ መተጋገዝና መረዳዳት (ከነችግሮቹም ቢሆን) በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ይህ በተለይ ግብፅ በኢትዮጵያ ይፋዊ ኤምባሲዋን ካቋቋመች 1927 ጀምሮ ብቻ ሳይሆን ጥንታዊነት ያለው ግንኙነት ነው ያላቸው። ይሀን እንጂ እነዚህ ሁሉ ዘመናት ለሁለቱ አገራት አልጋ ባልጋ አልነበሩም፤ እስካሁንም አይደሉም። ከታሪክ እንደምንረዳው ደግሞ የዚህ ሁሉ መነሾ ምክንያት ግብፅ እንጂ ሌላ አይደለም።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በ”The Modern History of Ethiopia 1855-1991” ጥሩ አድርገው እንዳሳዩት በሁለቱ አገራት ግንኙነትም ሆነ አጠቃላይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በተመለከተ እንደ ግብፅና ኢትዮጵያ ጉልህ ስፍራን የያዘ የለም። ይሁን እንጂ እንደ ግብፅ ደግሞ አስቸጋሪና የሥርዓት ጥሰት ፈፃሚ የለም። በይኩኖ አምላክ (1272) ሳይቀር የአባይ ጉዳይ ያሳስባት የነበረች አገር ነች።
ከባህሩ ተነስተን ወደ ኋላ ስንሄድም የምናገኘው የኢትዮ-ግብፅ ግንኙነት በግብፅ ምክንያት ሁሌም ሲደፈርስ ነው የሚታየው። በዚህም ምክንያት 4ኛውም በ14ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያም በተከታታይ ስትፈፅም በነበረው ሴራና በፈፀመችው ኢሰብአዊ ድርጊት የየወቅቱ መሪዎች የአባይን ወንዝ አቅጣጫውን እንደሚያስቀይሱና አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጧት እያስጠነቀቋት፤ ለጊዜው አንገቷን ስትደፋና ሽማግሌዎችን በመላክ ስትታረቅ ነበር ኑሮዋ። አፄ ዘርዓ ያዕቆብም “ላቆመው ነው” በማለት ለሱልጣን ጋቅማቅ ደብዳቤ በመላካቸው ደንግጣ ስርአት ያዘች እንጂ በወቅቱ አካሄዷ ሁሉ አደገኛ ነበር። በምኒሊክም ተመሳሳይ ተግሳፅና የማስተካከያ እርምጃ ሲደርሳት ነው የነበረው።
ግብፅ ይህን ሁሉ ሴራ፣ ሸርና ደባ በኢትዮጵያ ላይ ስትፈፅም የኖረችው ሰክራ ወይም አመል ሆኖባት አይደለም። ኢትዮጵያን ማዳከምና አባይን መቆጣጠር የሚለውን ስትፈጠር ጀምሮ በልቧ የቋጠረችውን እቅድ ለማሳካት እንጂ። ያ አልሳካ ቢላት በእንግሊዝና ሌሎች ሙሉ ድጋፍ ኢትዮጵያን ያላካተቱ ውሎችን ፈፀመች።
የግብፅ አላማ ከላይ እንደጠቀስነው ነው፤ በውጭ ጉዳይ ስትራቴጂዋ ረጅም እቅድን ቀይሶ ሳያሰልሱ መስራት፤ ለዛ ስኬትም እስከ ደም ጠብታ ድረስ መጓዝ። ይህ ካልተሳካ መለማመጥ፤ ፈሪ ከተገኘ ደግሞ ማስፈራራት።
አሁናዊውን ሁኔታ ስንመለከት የምናገኘው “ኢትዮጵያ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ጎን ለጎን ውኃ ለመሙላት የደረሰችበትን ውሳኔ እንደማትቀበል” እየገለፀች መሆኑን ነው። ይህ ያሁኑ ሲሆን ግድቡን ለመገንባት የመጀመሪያዋ ጠጠር ካረፈችበት ጊዜ ጀምሮ ግንባታውን ለማስቆም ያልበጠሰችው ቅጠል የለም። ስትፈልግ ክስ ትሄዳለች፤ ስትፈልግ ትለማመጣለች፤ ስትፈልግ ታስፈራራለች። ከሁሉም ግን በቋሚነት የያዘችው የዲፕሎማሲ ፍልስፍናዋ “ሲቂሎ ሲቂሎ” (ማሳቀል) ይሉት አይነት “Naming and shaming” ስትራቴጂ ነው። ስራዋ ሁሉ በየግዜው “ኢትዮጵያ …” እያሉ፤ ስምን እየጠሩ በየመድረኩና ተቋማት እየዞሩ ማልቀስ፤ መውቀስ … የዚሁ የ”Naming and shaming” ዲፕሎማሲያዊ ፍልስፍና አካል ነው። ትራምፕ ቻይናን በኮሮና ጉዳይ ነክሰው እንደያዙት ማለት ነው። ማሳቀልና ማሳፈር፤ ከዛም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተሰሚነትን፣ ተቀባይነትን፣ ‘ትክክል ነው’ አይነት አስተያየትን ለመሸመት፤ በፍርድ ሰጪዎች ዘንድ ስነ ልቦናዊ ጫና ለማሳደር በከፍተኛ ደረጃ ስትንቀሳቀስ እንደ ቆየችው ሁሉ ዛሬም አጠናክራው ትገኛለች።
ግብፅ “Naming and shaming” ስራቴጂዋን በእቅዷ መሰረት እያስኬደች ሳለ የእኛ እየተከተሉ መሳፈጥን ምን አመጣው ነው። ባስፈራራችን ቁጥር እንደማንፈራው ሁሉ በጠራችን ቁጥር “ወይ”ን ምን አመጣው የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው።
እርግጥ ነው «የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውኃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ ነው» በማለት አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለሶስቱ አገራት የሥምምነት ሰነድ ማዘጋጀታቸውን ባለመቀበል እንዳሽቀነጠረችው ሁሉ እራሷን ግብፅንም “እባክሽ እንዳንቺ የአስዋን ግድብ ወቅት ሁሉ እኔም ስራ ላይ ነኝ” ብላ ልትነግራት ይገባል። ይህን አልቀበልም ካለችና “ካልተኮስኩ” የምትልም ከሆነ ጉዳዩን በ”ምከረው ምከረው፤ እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” ማለፍ እንጂ አብሮ መሟዘዙ የትም አያደርስም። እኛ እኮ እሷ በ”Naming and shaming” የውጭ ግንኙነት ፍልስፍናዋን እዚህ ድረስ ስትቆዝም ነው የአባይን ወንዝ 74 እጅ እያገባደድነው ያለነው። አሁንም “ወግድ ይሁዳ” ልንላት ይገባል።
በተለይም “ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላ ኢትዮጵያ ትስፈነጠራለች” በማለት ከየአቅጣጫው የሚሰራጭ ዜና ራስ ምታት የሆነባት ግብፅ ተኝታ በተነሳች ቁጥር በውጭ ጉዳዩዋ አማካኝነት የምትተነፍሰው “አየር” የሚጠቅማትን ሳይሆን ለዘለቄታዋ የሚጎዳትን፤ የሚያጋጭትንና ከወዳጆቿ የሚያለያያትን ነው። ለምሳሌ ያህል ነጋ ጠባ “ኢትዮጵያ ግድቡ ከ12 እስከ 21 አመት ባለው ጊዜ ነው መሞላት ያለባት”፤ “ታሪካዊ መብቴ (የ1929 እና የ1959 ውሎች) ንክች አይደረግም” እያሉ ማላዘን ትዝብት ላይ ከመጣል ሌላ ምን ይፈይዳል? “አንዲት ጠብታ ውሃ ትነኩና ደማችሁን ነው የማፈሰው” ማለትስ የቱ ጋር ነው ጥቅሙ? “በአንድ በተን (የኮምፑተር ቁልፍ ጠቅታ) ነው ድራሻችሁን የማጠፋው” ሲባል ምን ለማለት ነው? አታውቀንምን? ሌላው ቢቀር አሉላ አባ ነጋን እረሳችው?
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ከእንደዚህ አይነቱ መደዴነት መቆጠቡና ለዛሬዋ ቀን መብቃቱ ያስመሰግነዋል። ይሁንና “እሹሩሩ”ን ለማታውቀው ግብፅ “እስከመቼ?” ብለን ብንጠይቅ ስህተቱ የቱም ጋር ሊሆን አይችልም። ይህን ስንል ከታሪክ፣ ልምድና እንደ አገር ከገጠመን ተነስተን ሲሆን ለዚህም ማስረጃችን ከጉንዲት፤ ከዛም ቀጥሎ ከጉራእ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አፄ የሆንስ በእንግሊዞች ቢያስለምኗትም “ወይ ንክች ወይ ፍንክች …” ነበር መልሷ። ያው ከላይ እንዳልነው “ምከረው …” ሆነና መከራ መክሯት ተመለሰች። ዛሬስ? በብዙ አቋሟ እዛው 19ኛው ክ/ዘ መግቢያ ላይ ስለሆነች በዚህ ጉዳይ ተለውጣለች ማለት ይቸግራልና ማገዶ ከመፍጀት ልንቆጠብ ይገባል።
የአሜሪካንን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲን በተመለከተ እንደ ሰነድ ወስዶ መንቀፍ/መደገፍ ባይቻልም ኢትዮጵያና ግብፅን በተመለከተ ከምትሰራው ስራ ተነስቶ አንድ ድምዳሜ ላይ መድረስ ግን ይቻላል። ግብፅ አስዋን በምትገነባበት ወቅት በ1954 አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አይዘንሃወር (Dwight Eisenhower) ዘንድ ብቅ ብለው ምነው ለእኛ ለፀጥታና ደህንነት ስራ ማስኬጃ ትደግፉን የነበረውን ትንሽ ገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አቆማችሁ? በማለት ጠይቀው በቅሬታ ተመልሰዋል። በወቅቱ አሜሪካ ለግብፅ አስዋን ግድብ ግንባታ ድጋፍ ታደርግ ነበርና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አቆመች። ይህ ያላስደሰታቸው ንጉስ ኃይለ ስላሴ በቀጥታ ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ህብረት፣ ኢንዶኔዥያና ቼኮስላቫኪያ አዞሩ። በጊዜያዊነትም መንግስታዊ ሶሻሊዝም (state socialism)ን አወጁ። ይህን የሚለን Sabeed A. Adejumobi (2007፣ ገፅ 93 – 94) ነው።
በደርግ ወቅትም አሜሪካ ቃል የገባችውን የመሳሪያ ሽያጭና ሌሎች ድጋፎችን ጦርነቱ ሲፋፋም ቃሏን አጥፋ ለኢትዮጵያ የታሰበውን ለዜአድባሬ አውላዋለች። አሁንም ኑ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ላነጋግራችሁ ከማለትም አልፋ ውል ማርቀቅ ድረስ መሄዷ ቀደም ሲል ከጠቀስናቸው ጉዳዮች ጋር ያውና አንድ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም ግብፅ በአፄ ዮሀንስ ዘመነ መንግስት ጉንደት፤ ተመልሳ በመምጣትም ጉርአ ላይ ስትዋጋን ከኋላ የነበሩት እኮ የአሜሪካ ከፍተኛ መኮንኖች ነበሩ። ይህንን ሁሉ በማወቅ ነው አንዳንድ ፀሀፊዎች አምርረው “ኢትዮጵያ በጠላት የተከበበች አገር በመሆኗ የውስጥ አንድነትና ጠንካራ መንግስት ያስፈልጋታል” በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ/ሲመክሩ የሚሰሙት። ስለዚህ ከአሜሪካ ኢትዮጵያን ታሳቢ ያደረገ መፍትሄ መጠበቅ ከእባብ የእርግብ እንቁላል እንደመጠበቅ ይቆጠራል የሚባለው። የኒዮ ሊበራሊዝም አስቀያሚ ገፅታም በዚሁ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በምትሰራው ሴራ ይገለፃል።
ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ተመሥርቶ የአገሪቱን አንድነት መልሶ የመገንባቱን ተግባር ተያይዘውት የነበሩትን አፄ ቴዎድሮስ ህልማቸውን ካጨናገፉት ጨካኞች መካከል በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ስትሰራ የነበረችው ግብፅ ትንኮሳና በወቅቱ የፈጠረው ተጨማሪ አለመረጋጋት መሆኑንም መርሳት አይገባም፤ በኢትዮ-ሶማሌ ጦርነትም የተጫወተችውን ፀረ-ኢትዮጵያ ሚና መታለፍ የለበትም። በኢህአዴግ ዘመንም እስካሁኗ ሰአት ድረስ ያለ እረፍት የማሳቀል (Naming and shaming) ስራዋን እየሰራች ሲሆን፤ ሌላውና ብዙም ያልታወቀላትን ኢትዮጵያን የማተራመስ ሴራ ለመረዳት የጊሬጎሪ አር. ኮፕሌይን “Analysis: Energy and Security in the Red Sea” ጥናት መመልከት ግብፅን ይገልፃታልና ይህንን ጥቆማ መጠቀሙ ይመከራል።
ለቁጥር የታከቱ ሚዲያዎቿና ምሁሮቿ ሳይቀሩ የግብፅ የ”Naming and shaming” ስትራቴጂ ማራመጃዎች መሆናቸው ሁሉ እስካሁን በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ የፈጠረው አንዳች ነገር ባይኖርም ኢትዮጵያን በአረቡ አለም እንደ አንድ የግብፅን ህዝብ ለመበደል እንደ ተነሳ አገር በመቁጠር በጠላትነት እንድትታይ እያደረጉት ያለው ጥረት በከፊል ፍሬ አላፈራም ማለት አይቻልም። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሚዲያና ሌሎች ሁሉ እዚህ የግብፅን “Naming and shaming” ስትራቴጂክ የሆነ ፕሮጀክት ማፍረሱ ላይ በርትተው መስራት ያለባቸው መሆኑ እየተነገረ ያለው።
የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተካፈሉበትን 4ኛ ዙር የቴክኒክ ውይይት ሲያጠናቅቅ ከግብፅ የቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች ውይይቱ ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ እንዳደረገው በተገለፀ ጊዜ የግብፅ ግትርነት፤ የ”Naming and shaming” ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ አራማጅነት ፍጥጥ ብሎ ወጥቷል።
“ግብፅ የህዳሴ ግድብ ድርድርን ወደ መንግስታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት መውሰዷን አስታወቀች፤ ምክር ቤቱም ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀች”፤ “ግብፅ የውሀ ሙሌቱ ጉዳይ ያሳስበኛል አለች”፣ “ያለ ሶስቱ ሃገራት ስምምነት ኢትዮጵያ በተናጥላዊ ውሳኔ ግድቡን ውሃ ልትሞላ ነው ስትል ለፀጥታው ምክር ቤት አቤት አለች” የሚሉት የየቀን ዜናዎች የሚነግሩን ቢኖር ይህንኑ የግብፅን በማሳቀል ላይ የተንጠለጠለ የ”Naming and shaming” ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂን ነው።
አሁን አሁን ረጋ ብሎ ላሰበው ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር “ማገዶ መጨረስ” ካልሆነ በስተቀር ይለወጣሉ፤ ይቀበሉታል … ብሎ ማሰብ ዘመኑን፤ በተለይም የግብፅን የኋላ ታሪክ ያላገናዘበ የዋህነት ነው። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን እንደ አዲስ “እየተካሔደ በሚገኘው ድርድር ስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ የለኝም” በማለት የእስከ ዛሬውን ሁሉ ወደ ኋላ የመለሰው የግብጽ የውኃ ሐብትና መስኖ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መሐመድ አል-ሴባይ ንግግር ሌላውና የቅርቡ ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን ለግብፅ ችኮና ግትር አቋም ማሳያ፤ ላላቋረጠ “Naming and shaming” ዲፕሎማሲያዊ ተግባራቸው መገለጫ ነውና ኢትዮጵያ ማገዶ መፍጀት የለባትም ስንል በምክንያት ነው።
በጉዳዩ የተሰላቸውም ሆነ ወደ ግብፅ ያደላው የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት በዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቂ አህመድ ነጋሽ በኩል “የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ልዩነት በአጭር ጊዜ ይጠባል ማለት አስቸጋሪ ነው።” ማለቱም የዚሁ የግብፅ ግትርነትና የኢትዮጵያ እሹሩሩ ባይነት ውጤት ነው። ተወያዮቹም “ስምንት ዓመት ሙሉ ስንወያይበት፤ ስንደራደርበት የነበረ ነው ግብጽ ግን አንዴ የግድቡን ቁመት ቀንሱ፤ አንዴ የውኃ መጠኑን ቀንሱ አንዴ ግንባታውን ቀንሱ እያለች ለማጨናገፍ እየጣረች” መሆኗን በብስጭት የገለፁትና የጀርመኑ ዶቼ ቬሌ ድምፃቸውን ላየር ያበቃላቸው ተወያዮች ስሜትም ይህንኑ የዚህን ፀሀፊ አቋም የሚጋሩ እንጂ የሚፃረሩ አይደሉም። በዚህ በተወያዮቹ አስተያየት ውስጥ የተደጋገመው “አንዴ …” ግብፅ ምን ያህል በማሳቀል ላይ ባተኮረው “Naming and shaming” ስትራቴጂዋ እንደዘለቀችበት ከበቂ በላይ ማሳያ ነውና ኢትዮጵያ ማገዶ መፍጀቷን ታቁም ስንል በምክንያት ነው ያልነው ይህንን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ እንጂ ለፌዝ አይደለም።
የግብፅ ጉዳይ አስቴር አወቀ፤
“እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ፣
ባሉባልታ ፈረስ አገር አደረሰ” እንዳለችው ነው። “Naming and shaming”ም ይሄው ሲሆን ጥያቄው “ያዋጣል ወይ?” የሚለው ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ግርማ መንግሥቴ