አብሮ አደግ ባልንጀራዬ የነገረኝን ፈገግ የሚያሰኝ ወሬ አስቀደምኩ:: ነገሩ የሆነው በዘመነ ደርግ ነው:: ደርግ በመሰረተ ትምህርት ንቅናቄው ይመረቃልም፤ይረገማልም:: የዚህ ባልጀራዬ አባት የደርግን መሰረተ ትምህርት በወቅቱ ከሚረግሙት አንዱ ነበሩ:: የማሳቸው ነጭ ጤፍ ደረስኩ ደረስኩ፣እጨዱኝ እጨዱኝ እያለ በሚዘናፈልበት ወቅት መሰረተ ትምህርት ቤት ሂደው በመዋላቸው ይናደዳሉ:: መቅረትም ፈጽሞ አይቻልም:: እናቱ እሱን(ጓደኛዬን) ነፍሰጡር ሆነው በመታመማቸው መሰረተ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ ይቀራሉ:: በዚህም አባቱ ለሁለት ብር ቅጣት ተዳርገዋል:: ግን አይቀሩ ነገር ሆኖባቸው ይሄዳሉ:: በመቀጣታቸውም፣ ከማሳቸው ባለመዋላቸውም፣ ማንበብና መጻፍ ባለመቻላቸውም ተናድደውበታል::
በኋላም ልጁ(ጓደኛዬ) አድጎ ለአቅመ ትምህርት በቃ:: አባቱን ለእስክብሪቶ መግዣ ሁለት ብር ሲጠይቃቸው ‹‹አንተ እኮ ከእናትህ ሆድ ጀምረህ እኔን ገንዘብ ለማስወጣት አልቦዘንክም›› ይሉት እንደነበር እየሳቀ አጫውቶኛል::
ሕዳር 16 ቀን 1967 ዓ.ም የታወጀው የእድገት በሕብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ እንዲሁም በሐምሌ ወር 1971 ዓ.ም የተጀመረው የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ መሀይምነትን በመዋጋት ረገድ ስኬታማ እንደነበር ይነገርለታል::እነዚህ አዋጆች የደራሲያን የሥነጽሁፍ ሥራዎች በሰፊው መነበብ እንዲችሉ መልካም እድል መፈጠራቸውም ይነሳል::ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ለ12 ዓመታት ያህል በገጠርና በከተማ በ22 ዙሮች ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል:: የመሰረተ ትምህርት አስገዳጅነት ቢኖረውም በዘመቻው ላይ የተሳተፉት ወጣቶች እንደ እዳ አይወስዱትም ነበር::ይህም በመላው አገሪቱ ዜጎች በእውቀት በተለይም ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ የማድረግ አላማን ሰንቆ የተካሄደው ዘመቻ ነው:: ፍሬያማ እንደሆነ ይነገርለታል::
ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት ዓላማው ማርክሲስት ሌኒኒስት ሕብረተሰብን ለመገንባት በማሰብ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ካወጀ በኋላ ማንበብና
መጻፍ የማይችሉትን ጎልማሶች መታደግ በሚል ግብ በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የሚገኙ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶች ቁጥርን ወደ 24 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሎ ነበር::በዚህም ስኬት በመላው አገሪቱ ከሰባት ሺህ በላይ ቤተ መጽሐፍት ተገንብተው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ::ይህ መሆኑ የማንበብ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ቀላል የማይባል ፋይዳ አበርክቷል::
መሰረተ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲጀመር መሰረት የተጣለው በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የካቲት 21/ 1948 ነበር::በዚያ ወቅት የመሰረተ ትምህርትን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቅሮ ነበር:: ይህ ስለመሰረተ ትምህርት አመሰራረትና አሰራር ባጠና ኮሚቴ የተጠቃለለ ሐሳብ የወቅቱ ፍርድ ሚኒስቴር ለነበሩት ለብላታ መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ እንዲመለከቱት ቀርቧል:: ለምክትል ሚኒስቴሩ ተብራርቶ የቀረበላቸው ሐሳብ ስድስት ነጥቦች ላይ የሚያተኩር ነበር:: የመጀመሪያው መሰረተ ትምህርት እድሜያቸው ከ18 እስከ 50 ለሚሆኑ ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ የሚሰጥ ፕሮግራም መሆን እንደሚገባው ነው::ከማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን መሰረተ ትምህርት ለሚያስተምሩ መምህራን ጉርሻና ሽልማት መስጠት እንደሚገባም ተካትቷል::
ሥራውንም ለመቆጣጠር በ1948 ዓ.ም 28 ኢንስፔክተሮች እንዲጠሩ ተወስኗል:: በቀን ሙያተኛነትና በ”አሽከርነት” ቀን ሰርተው በፕሮግራሙ መካተት ለሚፈልጉ እድሜያቸው ከሰባት እስከ 18 ዓመት ከሆናቸው መሳተፍ ይችላሉ:: የካቲት 21/ 1948 ዓ.ም በወጣው ግምት መሰረት እያንዳንዱ ጠቅላይ ግዛት 10 ሺ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንዲችል ሐሳብ ቀርቦ ነበር:: በሐሳቡ መሰረትም በአጠቃላይ በአገሪቱ 140 ሺ ተማሪዎች በመሰረተ ትምህርት መርሐ ግብር ሊታቀፉ ይችላሉ በሚል ታሳቢ ተደርጓል:: በወቅቱ ለማስተማሪያነት ተመርጦና ታትሞ የነበረው መጽሐፍ ታሪክና ምሳሌ ይባል እንደነበር ሰነዶች ያረጋግጣሉ::
ኢትዮጵያ በዘመናዊ የመንግስት ስርዓቷ የጎልማሶችን ትምህርት ለማስፋፋት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን የፊደል ሰራዊት፣በደርግ ዘመን ደግሞ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ የተሰኘ ዓበይት ፕሮግራምን በመንደፍ በብቃት በመስራቷ በዩኒስኮ ለመሸለም አብቅቷታል::
የመሰረተ ትምህርት ንቅናቄ ለሕብረተሰብ ለውጥ ትላልቅ ተቋማት ከሰሯቸው ስራዎች በላይ ተጽዕኖ እንዳበረከተ በርካቶች ይናገራሉ:: ፊደል ማስቆጠሩ፣ ማንበብና መጻፉ ብቻ አልነበረም፤ ኑሮ ዘዴን ፣ አካባቢ እንክብካቤን ጭምር የሚያስተምር ነበር:: ዛሬ ትላልቅ ወረቀቶችን ለምሁራን ካስያዙት ተቋማት በላይ ሕብረተሰብን በማዘመንና በመለወጥ በኩል መሰረተ ትምህርት የነበረው ተጽዕኖ መቼም እንደማይረሳቸው የዘመቱ አባቶች ይናገራሉ::
ፍቅረስላሴ ወግደረስ ፡ እኛና አብዮቱ በሚል መጽሐፋቸው በገጽ 424 ላይ እንደገለጹት፣ ‹‹እኛ ስልጣን ስንይዝ በመላው አገሪቱ ማንበብና መጻፍ የሚችለው ሰባት በመቶ ብቻ ነበር::93 በመቶ የሚሆነው ማንበብም ሆነ መጻፍ አይችልም ነበር::በቅድሚያ ከመሀይምነት ጨለማ መውጣት ካልቻልን በስልጣኔ ጎዳና መራመድ ስለማንችል መሀይምነትን ለማጥፋት መላውን ሕዝብ የሚያንቀሳቅስ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ፕሮግራም ነደፍን:: ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ነው:: ሰፊ የትምህርት ልምድ ያላቸውን በርካታ ባለሙያዎች መደብን:: በመላው አገራችን በየመንደሩ መሰረተ ትምህርት እንዲሰጥ አስፈላጊው የግብዓት ቁሳቁስ ተዘጋጀ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየአካባቢያቸው መሰረተ ትምህርት እንዲያስተምሩ ተመለመሉ:: ትምህርት ቤቶች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ጎጆ ቤቶች፣ጥላ ያላቸው ዛፎች ለማስተማሪያነት ተዘጋጁ:: በሐምሌ ወር 1971 ዓ.ም የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ በይፋ መጀመሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ በይፋ ተገለጸ:: በዚህ አይነት አንደኛ፣ሁለተኛ እና ሶስተኛ እያልን የዘመቻውን ፕሮግራም ለአስር ዓመት ያክል አካሄድን። ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብም ከመሀይምነት ነጻ ወጣ:: ከመላው ሕዝባችን መካከል ማንበብና መጻፍ የሚችለው ከ68 በመቶ ከፍ አለ:: ይህ ታላቅ ውጤት ነበር:: ›› ሲሉም አስፍረውታል::
የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ብዙ ዜጎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ አድርጓል:: ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ገፊ ምክንያት ሆኗል:: የገጠሩ ማህበረሰብ በእርሻ ሥራ፣ በከብት ርባታና በመሳሰሉት ዘርፎች የተሻለ ክህሎት እንዲኖረው አግዟል:: ለመብትና ለነጻነቱ እንዲታገልና እንዲተጋ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮለታል::በወቅቱ በርካቶች ማንበብና መጻፍ በመቻላቸው በመደበኛ ትምህርት ራሳቸውን አሻሽለው ለከፍተኛ ትምህርት ደረጃ በቅተዋል:: አሁን ላይ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአገሪቱ ካሉ ጎልማሶች እድሜያቸው ከ15 እስከ 60 ካሉት ዜጎች 54 ነጥብ አራት በመቶ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ 46 በመቶ ደግሞ የማይችሉ ናቸው::
የዩኒስኮ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከዘመነ ደርግ ወዲህ ይህ ነው የሚባል የጎልማሶች ትምህርት እድገት አላስመዘገበችም::ለዘርፉ የመደበችው በጀትም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ይገለጻል::የጎልማሶች ትምህርት አለመስፋፋት ማለት በአብዛኛው ሕዝብ በግብርና በሚተዳደርባት አገር ውስጥ ሕዝቡ የተጻፈ ማስታወቂያ ማንበብ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የጤና ማስታወቂያዎች፣የመንግስት መመሪያዎች እና የመንገድ ላይ ማስታወቂያዎችንም አያነብም፤አይረዳማ ማለት ነው::
ትምህርት የእድገት መሰላል ነው:: ስለ እድገት ሲወራ ቁልፍ የሆነው የትምህርት መስፋፋት የሚያያዘው ከጎልማሶች ማንበብና መጻፍ ችሎታ ጋር ነው:: እንደ የዩኒስኮ የቅርብ ጊዜ መረጃ ከሆነ ማንበብና መጻፍ የማይችለው ጎልማሳ ቁጥር ከሰባት ሚሊዮን በላይ መጨመሩን ያመላክታል:: ከትምህርት ገበታ አቋርጠው ወደ ከተማ የሚፈልሱና በየጎዳናው የሚታዩ ሕጻናትና ወጣቶች የነገ ጎልማሶች ይሄን ቁጥር ከፍ ሊያደርጉትም ይችላሉ::
ዩኔስኮ በኢትዮጵያ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶች ቁጥርን ባሰፈረበት ሰንጠረዥ ላይ እ.ኤ.አ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ለማሳያ ያህል አልፎ አልፎ ብንጠቅስ፡- በ1994 ዓ.ም 27 በመቶ፣ በ2004 ዓ.ም 35 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ፣በ2005 ዓ.ም 29 ነጥብ ስምንት በመቶ፣ በ2007 ዓ.ም 39 በመቶ፣ በ2015 ዓ.ም 48 ነጥብ ስምንት በመቶ፣በ2018 ዓ.ም ደግሞ 46 በመቶ ጎልማሶች ማንበብና መጻፍ የማይችሉ እንደሆኑ ተመላክቷል:: መሀይምነት ለመለመ? ወይስ ከሰመ? በበጎ ተጽዕኖ የተገኙ ትሩፋቶች ይመስገኑ? ወይስ ይኮነኑ?
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ሙሐመድ ሁሴን