በመንግስት የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚጠበቅባቸወን ያህል የውጭ ምንዛሬ እያመነጩ እንዳልሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
በግንባታ ላይ ያሉትም በተያዘላቸው ጊዜና በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ እየተሰሩ እንዳልሆነ ተገልጿል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር ጋር በመሆን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ2007 እሰከ 2000 ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ዛሬ ለኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎች በምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፤ በዚሁ መድረክ ላይ ኮሚቴው ተገንብተው ያለቁ የኢንዱሰትሪ ፓርኮችም መንግስት የፈለገውን አላማ እያሳኩ አይደለም ሲሉ ተናግሯል።
እንደ ቋሚ ኮሚቴው ገለጻ፤ ከቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ 130 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 16 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።
በተመሳሳይም ከዚሁ የኢንዱስትሪ ፓርክ በ2009 በጀት አመት 40 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማግኘት የተቻለው 23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
ከሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 50 ሚሊዮነ ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም የተገኘው አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ነው ቋሚ ኮሚቴው የገለጸው።
ለአፈጻጸሙ አነስተኛ መሆን ዋናው ምክንያት በተጠቀሱት አመታት በአገሪቷ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ አለመረጋጋት እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ለሊሴ ነሜ በሰጡት ማብራሪያም፤ የአዳማ߹ የድሬዳዋ߹ የጀማ߹ የቂሊንጦና የቦሌ ለሚ ቁጥር 2 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ደረጃ ከታቀደው አንፃር አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
መንግስት መሰረተ ልማት አለመዘርጋቱ߹ የበጀት ዕጥረትና የሰራተኛ ፍልሰት߹ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረ አለማረጋጋት እንደ እንቀፋት አንስተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ኮርፖሬሽኑ ክፍተቱን ለመሙላት ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ማሟላት ያለበት ነገሮችና የባለድርሻ አካላት ርብርብ ውስን መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱሰትሪ ፓርክ ልማት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አፈፃፀም (ከ2007-2010 ዓ/ም) የኦዲት ውጤትን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በማዕረግ ገ/እግዚአብሔር