አየሩ ከፍቶታል። አሻግሮ ወዲያ ማዶ ማየት የፈለገ እንኳን ርቆ በቅርብ ለማየት ተስኖታል። ምክንያቱ ጉሙ አጠገቡ ያለውን እንኳን በቅጡ እንዲያይ የፈቀደለት አይመስልም። ነጫጭ የሀገር ባህል የለበሱ ሰዎች በየአቅጣጫ ይታያሉ። ዕለቱ ህዳር 12 በመሆኑ የህዳር ሚካኤልን በዓል ለማክበር ወደ ቤተክርስቲያናት እየተመሙ መሆኑ ገብቶኛል። በየዓመቱ ይህን ቀን የሚያከብሩ ሴቶች፣ ወንዶች፣ አዛውንት፣ ወጣትና ህፃናት ጭምር ናቸው። ኃይማኖት፣ ባህል፣ አውደዓመት …የመሳሱሉት በዓላት በሚከበሩበት አካባቢ የሰዎች ብዛት የመንገድ ትራፊክ ላይ መጨናነቅ ያስከትላል። የትራንስፖርት እጥረትም ይኖራል። ይሄን አስቀድሞ የተረዳ ሰው ነጋዴ፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የግል ተቀጣሪ፣ ተማሪ፣ ጉዳይ ያለው ሁሉ ማልዶ በመውጣት የመንገድ ላይ ችግሩ እንዳይፈትነው ያደርጋል። ይሄን አስቀድሞ ያላሰበ፣ አስቦም ማልዶ ያልወጣ ግን ሊገጥመው የሚችለውን አስቡት። አሰበው ቦታ በስንት ሰዓት ሊደርስ እንደሚችል ገምቱ፤ ያውም ትራንስፖርት ከተገኘ አይደል!።
የአየሩ መክበድ የተራራቁትን አላተያይ ማለት ሚስጢሩ እንግዲህ በዕለቱ የሚደረገው ጭስ የማጨስ ስነ ሥርዓት ነው። ይሄ እንደ ባህል እየተለመደ የመጣው በዓመት አንድ ጊዜ አካባቢን ለማጽዳት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህን ብልም አንድን መንደር፣ ግቢ፣ ቤት በአንድ ቀን ጽዳት ማስዋብ ይቻላል እንዴ ወይስ በአንድ ጊዜ ጽዳት በሽታ እንዳይመጣ ማድረግ እንችላለን። አይመስለኝም በሽታ እንዳይመጣ ብን በቆሻሻ ክምር፣ በዝንብና በሌላውም ከተማችንን፣ አካባቢያችንን፣ ግቢና ቤታችንን መጽዳት የሚኖርብን በዓመት አንዴ ሳይሆን በየዕለቱ መሆን አለበት። ዋናው ጉዳይ ደግሞ መጽዳቱ ብቻ አይደለም፤ የሰበሰብነውን ቆሻሻ የምናስወግድበት መንገዱ ነው። ቤታችንን፣ ግቢያችንን አፅድተን ቆሻሻውን አሁን አንዳንድ ቦታ ላይ እንደምናየው መንገድ ዳር፣ አጥር ስር፣ አረንጓዴ በሚባሉ አካባቢዎች፣ ቦይ ውስጥ፣ በየወንዞቻችን ዳር የምንጥል ከሆነ አስቀድሞ ነገር ባናፀዳው ብል መዳፈር አይሆንም። ምክንያቱም ከቤት አውጥተን የጣልነው ቆሻሻ በዝንብም ሆነ በሌሎች ነፍሳት አማካይነት ለእኛው እቤታችን ይመለስ የለ። ያውም በምናየው መልኩ ሳይሆን ረቀቅ ብሎ በርካታ የበሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች ቫይረስ ሁሉ ተባብረው ጠንቅ መሆናቸው አይቀርም።
ባለፍን ባገደምን ቁጥር ያ እያወጣን የጣልነው ቆሻሻ በፀሐይና በዝናብ በስብሶና ወደ መጥፎ ጠረን ተቀይሮ የሚጠብቀን ራሳችንና ልጆቻችንን ነው። እና የእያንዳንዳችን የግል፣ የቤትና የግቢ ጽዳት ከምን አስጣለን? በዓመት አንዴ ማቃጠሉም ቢሆን የአካባቢ አየር በመበከል የሚያስከትለው ጉዳት እንዳለም ሆኖ ለአንድ ዓመት የንጽህና ዋስትና መሆን አይችልም። ስለዚህ የሚጎዳንን ሳይሆን የሚጠቅመን ላይ ብናተኩርስ?
ይህን ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ንግድ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እንዳው በትንሹም ቢሆን ያየሁት የስድስት ኪሎ የሰንበት ገበያ ነው። እዚህ ቦታ እና ሌሎችም የንግድ ስፍራዎች ዕቃዎች በካርቶን በላስቲክ ማሸጊያ አምረውና ተውበው ይቀርባሉ። ገዥና ሻጭ ከተገበያዩ በኋላ ግን እነዛ ማሸጊያዎች በየቦታው ይወድቃሉ። እኔ አካባቢዬን ካፀዳሁ፣ ሁሉም አካበቢውን ካፀዳ፣ ከተማችን ትፀዳለች የሚል ያለ አይመስለኝም። ኧረ እንዳውም ጸዳ አልጸዳ ብሎ የሚያስብ አለ እንዴ በሚያስብል መልኩ ነው ውዳቂው ለመዘጋጃ ቤት ጽዳት ሠራተኞች የሚተርፋቸው።
ይሄ ብቻም አይደለም፤ የፍራፍሬ ጭማቂ (ጁውስ ቤት) ያላቸው፣ ሻይ ቡና ከሚያስ ተናግዱ ንግድ ቤቶች የሚወጣው ተወጋጅ ቆሻሻ ብዙ ጊዜ በየመንገዱ ዳር ወንዝ አጠገብ ይታያል። በእርግጠኝነት ይሄን የሚያደርጉት ነጋዴዎቹ ናቸው ወይም አይደሉም ብሎ ለማለት ማስረጃና ማረጋገጫ የለም። ምክንያቱን አብዛኛውን ጥፋት የሚፈጸመው ጨለማን ተገን ተደርጎ ነው። እንደሰማነው ሥራቸውን አጠናቀው፣ ንግድ ቤታቸውን ዘግተው ሲወጡ በመኪና ይዘው በመውጣት መንገድ ዳር ይወረውራሉ፤ እኔ ግን አለየሁም። ሌላው ደግሞ ይሄንን ቆሻሻ እንዲያስወግ ዱላቸው የቀጠሯቸው ሰዎች ያወጡትን ቆሻሻ ቆሻሻ መጣያ ገንዳ ድረስ ይዘው ላለመሄድ ጥጋጥግ ላይ ጥለው የሚሄዱ እንዳሉም ይጠረጠራል። ሁሉንም በማስረጃ ባናረጋገጥም አይሆንም ብሎ ለማሰብ ግን ይከብዳል። እናም ለቤታችን የተፀየፍነው ለህዝብ፣ ለከተማው ነዋሪ ለእንግዶቻችን ይሄው ማለት ተገቢ ይሆናል? ብቻ መልሱን ለእናንተ ልተው።
እንዳው ነገርን ነገር ያነሳው የለ። አካባቢን በማጽዳት ጉዳይ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን ብለን እኩል አስበን፣ እኩል ተቆርቁረን እኮ አንሠራም። ከኢትዮጵያ ዋና ከተማነት ከፍ አድርገን የአፍሪካ መዲና ፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መኖሪያ …እያልን በምናሞካሻት ከተማ እንኳን የሚታየው የሚያስተዛዝብ ነው። እንዳውም ያውቃል /ታውቃለች፣ ተምራለች/ ተምሯል ወይም ሰልጥነዋል በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ላይ መዘናጋቱ ሳይብስ እንዳልቀረ ይሰማኛል። ያን ሰሞን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው የሩጫው ተሳታፊ «የሰለጠነ» የሚመስል መስሎኝ ነበር። አብዛኛውም ወጣት ነው፤ ከተለያዩ ተቋማት የተሰባሰቡ …ብቻ እውቀት ቀመስ ናቸው ብል ይሆናል። ግን በድርጊት እንደእዛ ሆኖ አልተገኙማ።
ሳስበው ሳስበው «የሰለጠነ» የሚባለው የሰለጠነው ለስድብ፣ ለትችት፣ ለተረብ እንጂ እንዳው አካባቢን ለማጽዳት አይሆንም። አስቦ ለመናገር፤ ከስሜት ወጥቶ በስሌት መንቀሳቀስ አይችልም እንዴ? አንዳንዱ የታላቁን ሩጫን መድረክ የፖለቲካ መድረክ ይመስለዋል። አንዳንዱ ደግሞ ጥላቻን መንዣ፣ መሳደቢያ፣ መዛቻ … ብዙ ደስ የማይሉ ከ«ሰለጠነ» ከሚባለው ወጣትም ሆነ ጎልማሳ የማይጠበቅ ነው። ለስድብም ባይሆን እኮ ሀሳብን፣ ተቃውሞንም ሆነ ድጋፍ ለማድረግ ጊዜው መድረኩም እንዳለ ባይዘነጋስ። ነገርን ነገር ያነሳው ሆነና መስመሬን ሳትኩ መሰለኝ ልመለስ።
የጠጡበትን የውሃ መያዣ ላስቲክ ቆሻሻ ለመጣያ በተዘጋጀው ቦታ፣ በየመንገድ ዳር ባሉት የብረት የቆሻሻ መጣያ ውስጥ መክተት ምን ይጎዳል? ማንን ይጎዳል? ብቻ ሁሉም ባይሆንም (ስልጡኑን አላልኩም) የጠጡበትን በየቦታው እየጣሉ ከተማውን የውዳቂ አውድ አስመስለውት ውለዋል። ይሄም እነዛ ለፈረደባቸው፣ እነሱም ፈረደብን «ለእኛም ድካም ለከተማውም ፅዳት የማይጨነቁ» ብለው ለሚንቁን የማዘጋጃ ቤት የጽዳት ሠራተኞች እንደሚቆይ አስባለሁ። በማንኛውም የአደባባይ ፕሮግራም በማግስቱ የሚተርፋቸው ልፋት ይታየኛል። ይሄን ስል ግን ለበዓለ ጥምቀት መንገዱን ሁሉ በቄጤማ የሚያደምቁትን ወጣቶች አይመለከትም። እነሱ በማግስቱ ሳይሆን በዕለቱ አመሻሽ ላይ ሲያጸዱ ስላየሁ እነሱን ከመኮንን ተርፌያለሁ።
የውሃ ፕላስቲኩን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራሁ ነው የሚለው ፋብሪካ ለጥሬ ዕቃነት የሚያውለው የጥሬ ዕቃ እጥረት እንዳለበት ሲናገር የሰማሁ መሰለኝ። ጆሮዬ ካላሳለፈ። ይሄን በየመንገዱ የወዳደቀውን ታዝቤ እንዴት የዕለቱ የገቢ ማስገኛ ይሆን ነበር አልኩ። አንድ ሥራ ፈጣሪ ተነስቶ ለዛሬው የሥራ ፈጠራዬ የወዳደቁትን በመልቀምና በመሸጥ የዕለቱን ወጪዬን መሸፈን ነው ብሎ ቢነሳ። ከዛም የታላቁ ሩጫ ከሚካሄድባቸው የመሮጫ ቦታዎች ላይ የሰበሰብኩትን ፕላስቲክ ሸጬ የሆነ ገንዘብ አገኘሁ ወይም ደግሞ ይሄንን እየሰበሰብኩ ባለሁበት ቦታ የከተማውን ንፅህና በመጠበቅ አርአያ በመሆን ብሎ ይሄን ሸለመኝ የሚል ቢፈጠርና ይሄ ሆኖ ብናየው እርግጠኛ ሆኜ ለቀጣዩ ዓመት ይሄ ሀሳብ በብዙዎች ዘንድ ይሸመታል። ብዙዎች ሀሳቡን ገዝተው ለነገ ለራሳቸው ያደርጋሉ። እንዳው የቅርቡን ብዬ ታላቁን ሩጫ አነሳሁ እንጂ በተለያየ ጊዜ በሚካሄዱ የጤና ሩጫዎችም ላይ የተመለከትኩት እንዲሁ አካበቢን የሚያቆሽሽ እንጂ የሚያጸዳ አይደለም።
ሩጫቸውን አጠናቀው ለገቡ ሯጮች ብስኩት ባለ ፕላስቲካ ለስላሳ መጠጥና ውሃ ይታደላል። አዳዩም ሰዎቹ ከተጠቀሙ በኋላ ቆሻሻው አካባቢ እንዳይበክል በአንድ በታ ይሰብሰብ ብሎ በቆሻሻ መጠያ አያጠራቅምም። እንዲያጠራቅሙትም አያሳስብም። ተጠቃሚውም ቢያንስ እቤቴ ወስጄ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ እከተዋለሁ ብሎ አይነሳም ። በሁለቱም ጥፋት ልበለው ስህተት ብቻ አካባቢው በብስኩት ማሸጊያም በሌላውም ይደምቃል። ደፋሩ ንፋስም አንዱን ወዲያ ሌላውን ወዲህ እያደረገ የአንዱን ቦታ በሌሎች በርካታ ቦታዎች ለማቆሸሽ ይራዳል። በዚህ መልኩ ድሮም ያላማረበት ይባስ ብሎ ይበላሻል። ይሄ ከየት መጣ? ለምን መጣ? እንዴት መጣ? ብሎ ጠያቂም ተጠያቂም የለማ፤ አሁን በድሮው፣ ባለፈው መወቃቀሱ ይብቃ። ሁላችንም እንጽዳ፣ እናጽዳ። ታዲያ ህዳር 12 ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቀን መሆኑን እንዳንረሳ።
አልማዝ አያሌው