እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
አንድ ሰው በውል ውስጥ የገባውን ግዴታ በአግባቡ ካልፈጸመ የድርሻውን ግዴታ የተወጣው ሌላኛው አካል ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ሕግ ያስገድዳል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ማስጠንቀቂያ የደረሰው ወገን አንድም እንደውሉ ግዴታውን ሊወጣ ይችላል፤ አልያም ግዴታውን ሳይወጣ የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል።
ይህንን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ወገን መብቱን ለማስከበር የሚሄድባቸው መንገዶች ምን ምን እንደሆኑ በሕጉ በግልጽ ተቀምጠዋል።
እኛም በዚህ ጽሁፋችን የማስጠንቀቂያ አሰጣጥና ውጤቱን እንዳስሳለን። ማስጠንቀቂያ ለምን እና መቼ እንደሚሰጥ እንዲሁም ማስጠንቀቂያ በመስጠትና በመቀበል ምክንያት በሕጉ የተቀመጡ ውጤቶች ምን ምን እንደሆኑ እንመለከታለን።
በማያያዝም ማስጠንቀቂያ አለመስጠት ምን ያስገኛል ምንስ ያሳጣል የሚሉትን ጉዳዮች በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጋችንን ማዕቀፎች እንቃኛለን።
የውል አለመፈጸም የሚያስከትለው ውጤት በጠቅላላው
ውል የተዋዋዮች ፈቃድ በተግባር የሚገለጽበት ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ለአፈጻጸሙም ሕግ ዋስትና የሚሰጠው ስምምነት ነው።
በዚሁ መነሻ በሕጉ መሰረት የአንዱ ተዋዋይ ወገን ግዴታውን በአግባቡ አለመወጣት የበኩሉን ግዴታ ለተወጣው ወይም ለመወጣት ዝግጁነቱን ላሳየው ለሌላው ተዋዋይ የተለያዩ መብቶችን ያስገኝለታል።
በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1771 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው ውሉ እንዲፈጸም መብት ያለው ባለገንዘብ ሶስት አማራጭ መብቶች አሉት። እነዚህም የውል አለመፈጸም የሚያስከትላቸው ውጤቶች ናቸው።
ከባለገንዘቡ መብቶች ውስጥ የመጀመሪያው ውሉ እንደነገሩ ሁኔታ በባለዕዳው ወይም በሌላ ሰው እንዲፈጸምለት የማስገደድ መብት ነው።
ይህም በውሉ ባለዕዳ የሆነው ወገን በአካል ተገዶ በውሉ የተመለከተውን ተግባር እንዲያከናውን ወይም ንብረት እንዲያስረክብ ወይም ገንዘብ እንዲከፍል ወይም የውሉን ቃል በመጻረር የሰራውን ሥራ እንዲያፈርስ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሕግ አስከባሪ ተቋሞች አማካኝነት የሚገደድበት የውል አለመፈጸም ውጤት ነው።
ውልን በግድ ማስፈጸም የሚቻለው ሁለት ቅድመ-ሁኔታዎች በጣምራ ተሟልተው ሲገኙ ብቻ ነው – እንደ ውሉ ይፈጸምልኝ ብሎ ለሚጠይቀው ተዋዋይ የተለየ ጥቅም የሚሰጠው ከሆነ (የመብራት ወይም የውሃ መስመር ያለአግባብ ቢቆረጥ) እና አፈጻጸሙም በባለዕዳው ነጻነት ላይ ምንም መሰናክል የማይፈጥር ከሆነ (ሊታሰር ወይም ሊታገት አይገባውም) ነው።
ውሉን መሰረዝ ሁለተኛው የውል አለመፈጸም ውጤት ነው። ሁለቱም ተዋዋዮች ወይም አንደኛው ወገን ማድረግ የሚገባውን ካላደረገ፣ ማድረግ የማይገባውን ካልፈጸመ ሌላው ወገን ከሕግ ወይም ከውሉ ከራሱ ካገኘው መብት ተጠቅሞ ውሉን የመሰረዝ መብት አለው።
ይህም ማለት እንደውሉ ያልተፈጸመለት ተዋዋይ ወገን ውጤት ሊኖረው የሚችለውን ውል ውጤት አልባ የሚያደርግበት መንገድ ነው።
ውል የሚሰረዝ ከሆነ ውሉን የሚሰርዝ ወገን ለውሉ ያወጣውን ወጪ ብቻ ሳይሆን ውሉ ባይሰረዝና ቢፈጸም ኖሮ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም የሚሸፍን ኪሳራ የማግኘት መብት አለው። ስለዚህ የውል መሰረዝ ውጤት ከውሉ በኋላም ያለውን ጊዜ አሻግሮ የሚመለከት ነው ማለት ነው።
ሶስተኛው የውል አለመፈጸም ውጤት ውሉ በአግባቡ ባለመፈጸሙ የተነሳ ለደረሰ ጉዳት ኪሣራ የመጠየቅ መብት ነው። የጉዳት ኪሳራ አጠያየቅን መሰረተ-ሃሳብ የሚያስቀምጠው የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1790 እንደሚያመለክተው የኪሳራ ጥያቄ ውሉ
በግዴታ እንዲፈጸም ወይም እንዲሰረዝ ከሚቀርብ ጥያቄ ጋር ተጣምሮ ሊቀርብ ይችላል።
በውል ግዴታ ውስጥ የጉዳት ኪሳራ የሚመዘነው የተጎጂው ኢኮኖሚያዊ አቅምና ውሉ በአግባቡ ቢፈጸም ኖሮ ሰውየው ሊገኝበት ይችል የነበረው ኢኖኮሚያዊ አቋም እየተገናዘበ ሊሆን ይገባዋል።
እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ታዲያ ተጎጂው ማስረዳት የሚ ጠበቅበት የውሉን በአ ግባቡ አለመፈጸም ብቻ ሳይሆን በዚህም የተነሳ የደረሰበትንና በእርግጠኝነት ሊደርስበት የሚችለውን የጥቅም መቋረጥ ነው።
በመሆኑም ውል ያልተፈጸ መለት ወገን እንደሁኔታዎቹ እነዚህን ሶስት መብቶች በተናጠል የመጠቀም መብት አለው። ይህ ብቻም ሳይሆን የጉዳት ኪሳራን ከሌሎቹ ከሁለቱ የተናጠል መብቶች ጋር በማዳበልም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል መገንዘብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ውሉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ወገን ጉዳት ደርሶበት ከሆነ ኪሣራንም የመጠየቅ መብት አለው።
የሆነው ሆኖ እነዚህ የውል አለመፈጸም ውጤቶች የሚመነጩት ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነው። ይህም ማለት የሌላኛውን ወገን ውል አለማክበር ማረጋገጥ የሚቻለው ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነው ማለት ነው።
እናም የውል አለመፈጸም የሚያስከትላቸውን መብቶች ለመጠቀም ዓይነተኛው ቅድመ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ነው።
ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?
“እንደ ውሉ ሳይፈጸምልኝ ቀርቷል በማለት ክርክር ለማቅረብ የሚፈልገው አንደኛው ተዋዋይ ወገን የተዋዋለው ሰው ግዴታውን እንዲፈጽምለት ለማድረግ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ያስፈልጋል” ይላል ሕጉ የማስጠንቀቂያን አስፈላጊነት ሲደነግግ።
ከዚህ የሕጉ ድንጋጌ በግርድፉ እንደምንረዳው ማስጠንቀቂያ ማለት የውል ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኝነቱን ለማያሳይ ዳተኛ ባለዕዳ ባለገንዘቡ ተገድቦ በተቀመጠ ጊዜ ውስጥ ውሉን እንዲፈጽምለት የሚያቀርበው ጥያቄ ነው።
እናም የባለዕዳው ውል አለማክበር ከሁሉም በፊት የሚረጋገጠው ከባለገንዘቡ ለሚደርሰው ማስጠንቀቂያ በሚሰጠው ምላሽ ነው። ባለዕዳው ለማስጠንቀቂያው ምላሽ ካልሰጠ ወይም አሉታዊ የሆነ ምላሽ ከሰጠ ባለገንዘቡ ሕግ በሰጠው መብት ይገለገላል።
በማስጠንቀቂያ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ልሂቃንን ሥራዎች ዋቢ የሚያደርጉ ጸሀፍት እንደሚገልጹት ከሆነ የኢትዮጵያን ዓይነት የሕግ ሥርዓት (ሲቪል ሎው የሚባለውን ዓይነት) ባላቸው አገራት ማስጠንቀቂያ ሁለት ዓበይት ዓላማዎች አሉት።
እነዚህም የባለዕዳውን ግዴታ ያለመወጣት በማረጋገጥ የጉዳት ኪሣራ የመጠየቅ መብትን ማግኘትና በተለይም የማስረከብ ግዴታ ባለበት ውል ውስጥ በዕቃዎቹ ላይ የሚደርሰው ድንገተኛና ያልተጠበቀ አደጋ የሚደርሰውን የጉዳት ኪሣራ ኃላፊነት ወደባለዕዳው ማሸጋገር ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕግም ቢሆን የማስጠንቀቂያ ደንቦችን ሲደነግግ ከእነዚህ ሁለት ዓላማዎች ያልራቁ አራት አመክንዮዎችን በማንገብ ስለመሆኑ ሕጉን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ሬኒ ዴቪድ በሕጉ ዙሪያ በጻፉት ማስታወሻ እንዲሁም ፕሮፌሰር ጆርጅ ቺቺኖቪች “Formation and Effects of Contracts in Ethiopian Law”
በሚል ባሰናዱት መጽሐፋቸው አስፍረውታል።
ከአጠቃላይ ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ ማስጠንቀቂያ ባለዕዳ ውሉን ባለመፈጸሙ የሚደርስበትን ውጤት እንዲገነዘብ ያደርገዋል። በፍርድ ቤት ሊነሱ የሚችሉ የውል አፈጻጸም ክርክሮችንም ለመቀነስ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑ አይቀርም።
ለማሳያነት ውሉን ባለ መፈጸሙ የተነሳ ባለገን ዘቡ ሊከሰው እየተሰናዳ መሆኑን ከደረሰው ማስጠንቀቂያ የተረዳ ባለዕዳ ለተጨማሪ ኪሣራ ከመዳረጉ በፊት ግዴታውን ለመወጣት እንደሚጣጣር እሙን ነው። ከተሳካለት ታዲያ ተጨማሪ ወጪን፣ ኪሣራንና ድካምን ከሚያመጣው የፍርድ ቤት ሙግት ይድናል ማለት ነው።
ማስጠንቀቂያ ሌሎች ጥቅሞ ችም አሉት። የማስረከብ ግዴታ ባለበት ውል ውስጥ ማስጠንቀቂያ የጉዳት ኃላፊነትን ከአስረካቢው ወደተረካቢው ያስተላልፋል። ገንዘብ የመክፈል ግዴታ ባለበት ውል ውስጥ ደግሞ ለባለገንዘቡ ወለድ የሚጠይቅበትን መብት ያጎናጽፈዋል።
የማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ሥርዓት (ፎርም)
የፍትሐብሔር ሕጉ እንደሚገልጸው የማስጠንቀቂያ መስጠት ጉዳይ የሚደረገው ይህን እንድትፈጽም የሚል እንደመጨረሻ ትዕዛዝ በሆነ ማስታወቂያ ወይም በሌላ አድራጎት የባለገንዘቡን ሃሳብ በሚገልጽ ዓይነት የሚቀርብ ነው።
ከዚህ የምንረዳው በሕጉ በግልጽ የተለየ የማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ሥርዓት (ፎርም) አለመኖሩን ነው። ያም ሆኖ ብዙውን ጊዜ የተለመደው የማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ሥርዓት በጽሁፍ ነው።
ይሁንና ባለገንዘቡ የባለዕዳው የውል መፈጸሚያ ጊዜ እንደደረሰ ጥያቄውን ሲያሻው በጽሁፍ፣ ሲፈልግ በቃል ወይም በሌላ ልማዳዊ መንገድ ማድረስ ይችላል።
በዚህም ሆነ በዚያ ዋናው ቁም ነገር ባለገንዘቡ ውሉ እንዲፈጸምለት ያለውን ቁርጥ ፍላጎት በማያሻማ አኳኋን ለባለዕዳው መግለጹ ላይ ነው።
የማስጠንቀቂያ አሰጣጥ ሥርዓት ሌላኛው ዓይነተኛ መገለጫ የጊዜ ጉዳይ ነው። ከማስጠንቀቂያ ጋር “ጊዜ” ሲባል ደግሞ አንድም “ማስጠንቀቂያ መቼ ይሰጣል?” የሚለውን ያመለክታል።
በዚሁ መሰረት ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበትን ጊዜ በተመለከተ የውሉ መፈጸሚያ ጊዜ ከደረሰ (ዕዳው ከበሰለ) ማስጠንቀቂያ መሰጠት እንደሚገባው ነው ሕጉ የሚገልጸው። ይህ ማለት ዕዳው ሳይበስል ወይም በውሉ የተቀመጠው የግዴታው መፈጸሚያ ጊዜ ከመድረሱ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ መስጠት አይቻልም ማለት ነው።
በሌላ በኩል “የማስጠንቀቂያው የጊዜ ርዝመት ምን ያክል መሆን ይገባዋል?” የሚለውም ቁልፍ ጉዳይ ነው። ባለገንዘቡ ለባለዕዳው ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ለግዴታው መፈጸሚያ የሚሆን የተወሰነ ጊዜ ገድቦ ይሰጠዋል። ይህ ጊዜ ካለፈ ታዲያ ባለገንዘቡ ከላይ የጠቀስናቸውን ሶስቱን መብቶቹን ወደመጠቀም ይሸጋገራል።
ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበትን የጊዜ ርዝመትን በተመለከተም ሕጉ የተለየ ደንብ አላስቀመጠም። ይልቁንም ውሉ እንዲፈጸም በማስጠንቀቂያው ተገድቦ የሚቀመጠው ጊዜ የሚወሰነው ከጉዳዩ ዓይነትና ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ በቂ በሆነ መጠን ሊሰጥ እንደሚገባው ነው ።
ያም ሆኖ “በቂ” የሚለው የሕጉ አነጋገር አብዝቶ ያከራክራል። በተለይም ከጉዳዩ ዓይነትና ከነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት “ምክንያታዊ” የሚባል ጊዜ ለግዴታው መፈጸሚያ መስጠት እንደሚገባ መስማማት ይቻላል።
ለማሳያነት ከባለዕዳው የሚጠበቀው ገንዘብ ወይም ንብረት በእጁ ሳይሆን በሌላ አካል ይዞታ ሥር ከሆነ አልያም ገና ወደፊት ተመርቶ የሚገኝ እንደሆነ ባለዕዳው ግዴታውን እንዲፈጽም ከሁኔታው በመነሳት የሚሰጠው ጊዜ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል።
በሌላ በኩል ገንዘብ ከካዝና፣ ከኪስ ወይም ከባንክ አውጥቶ በመስጠት ለሚፈጸም የውል ግዴታ ረዥም ጊዜ እንዲሰጥ መጠበቅ ከሕጉ ዓላማ ጋር ይጋጫል።
ማስጠንቀቂያ መስጠት የማያስፈልግባቸው ሁኔታዎች
በመርህ ደረጃ እንደውሉ ግዴታውን ላልፈጸመ ተዋዋይ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ ከውሉ ወይም ከግዴታው ባህርይ በመነሳት በተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች ማስጠንቀቂያ መስጠት እንደማያስፈልግ ሕጉ ይገልጻል።
በውሉ የተመለከተውን ግዴታ አለማድረግ ሲሆን፤ ማስጠንቀቂያ መስጠት ጠቃሚ አይደለም። በውሉ የተመለከተው የግዴታ መፈጸሚያ ጊዜ ካለፈም እንዲሁ።
ባለዕዳው ግዴታውን የማይወጣ መሆኑን ገልጾ በጽሁፍ ካስታወቀ እንዲሁም በውሉ ላይ ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልግም የሚል ቃል ከሰፈረም መስጠት አይጠበቅም።
በዚሁ መነሻ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ባለገንዘቡ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልገው በባለዕዳው የውል አለመፈጸም የሚያስገኙለትን መብቶች (ውልን መሰረዝ፣ አስገድዶ ማስፈጸም ወይም ኪሣራ መጠየቅን) አማርጦ መጠቀም ይችላል።
ማስጠንቀቂያ ያልሰጠ ባለገንዘብ ምን ያጣል?
በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ በውል አለመፈጸም ምክንያት የሚገኙትን ሶስቱን ፍሬዎች ለመቋደስ ማስጠንቀቂያ መስጠት ያስፈልጋል። ማስጠንቀቂያ መስጠት የማያስፈልግባቸውን ልዩ ሁኔታዎችም ተመልክተናል።
እዚህ ላይ ታዲያ የሚነሳው ቁልፍ ነጥብ ባለገንዘቡ ማስጠንቀቂያ ባይሰጥስ የውሉ ውጤትና በተዋዋዮቹ መካከል ሊፈጠር የሚችለው አለመግባባት መቋጫው ምን ሊሆን ይችላል የሚል ነው።
እርግጥ ነው ማስጠንቀቂያ መስጠት ውልን ለመሰረዝ ወይም በግዴታ እንዲፈጸም ለማድረግ ወይም ኪሣራም በተጨማሪነት ለማግኘት መልካም ቅድመ-ሁኔታ ነው።
ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ባለገንዘቡ ግዴታውን ላልፈጸመው ባለዕዳ ማስጠንቀቂያ ላይሰጥ ይችላል። ሰጥቶም ከሆነ አሟጋችና ምናልባትም ሕጉን ያላገናዘበ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ወቅት ታዲያ ማስጠንቀቂያ ያልሰጠው ይህ ባለገንዘብ ብልህ ሰው አልነበረምና ጉዳት ደርሶበት እንኳን ቢሆን ኪሣራው ቢቀርበት እንጂ ዋናውን ገንዘቡን ከሶ ለማስከፈል ሙሉ መብት አለው።
ማስጠንቀቂያ ባለመስጠቱ የጉዳት ኃላፊነቱ ወደ ባለዕዳው ሳይሸጋገር በገዛ እጁ ላይ ቀርቷል፤ ዋናው ገንዘብ ሊያስገኝለት የሚችለውን ወለድ በባለዕዳው ትከሻ ላይ የሚጣልበትን ዕድልም በራሱ ጊዜ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
እናም ለክሱ ያወጣውን ወጪ ወይም ባለዕዳው ግዴታውን ባለመወጣቱ የደረሰበትን የጉዳት ኪሣራ ወይም የወለድ ጥቅሞችን ይጣ እንጂ ዋናውን ገንዘብ እንዳያገኝ የሚከለክለው ሕግ የለም።
ለምሳሌ በአንድ የብድር ውል ውስጥ የመክፈያ ጊዜው ከደረሰ (ዕዳው ከበሰለ) አበዳሪው ያለማስጠንቀቂያ ክስ ቢመሰርት ያበደረውን ገንዘብ የማግኘት መብት አለው። ተበዳሪው ማስጠንቀቂያ አልሰጠኸኝምና ልከፍልህ አይገባኝም ብሎ ሊከራከረው አይችልም።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
በገብረክርስቶስ