ቄራ አካባቢ መንገድ በመዘጋጋቱ ምክንያት እኔና ጓደኛዬ የተሳፈርንበት 54 ቁጥር አውቶቡስ፤ በቄራ አጥንት መጣያ ትይዩ በግምት ከ5-10 ደቂቃዎች ያህል ለመቆም ተገዷል። ይሄኔ ነው ታድያ! «ዓለም ቴአትር ናት፤ ሕዝቦቿ ተዋናዮች ናቸው» የሚለውን አባባል ያስታወሰኝን ትዕይንት የተመለከትኩት። በዚህ አባባል የምስማማ ቢሆንም ሌሎች ተዋናዮች መኖራቸውን አለማካተቱ ግን ቅር አሰኝቶኛል። በቄራ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተመለከትኩት ትዕይንትም ለዚህ ቅሬታዬ ማስረጃ ይሆንልኛል ብዬ እገምታለሁ።
በግቢው ውስጥ አንድ በሰው ቅርጽ የተሠራና በእጁ ዱላ ጨብጦ የቆመ የሚመስል፤ ብቻ «ሰው መሳይ በቄራ!» ልበለው? ሰሌን ኮፍያውን ደፍቶ ግትር ብሎ ቆሟል። እንደምገምተው ይህ ሰው ተብዬ ሰው፤ አሞራዎችን ለማባረር የተመደበ የእድሜ ልክ ተረኛ ዘብ መሆኑ ነው። ዘመኑ ሆነና! ምንም እንኳ ፈርቶ የሚሸሽለት አሞራ ለማግኘት ባይታደልም፤ ለቆመለት ዓላማ ግን «ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ» መሆኑን፤ ያየው ሰው ሁሉ ሊመሰክርለት ይችላል።
ዛሬ ግን አንድ ደፋርና ዐይን አውጣ ጆፌ አሞራ ይባስ ብሎ አናቱ ላይ ቂብ ብሎበታል። አንገቱን ቁልቁል አስግጎ ወደ ግራም ወደ ቀኝም በማድረግ ሲመለከት ላስተዋለው ሰው፤ ይህ ጆፌ አሞራ የሆነ ጥናትና ምርምር እያደረገ ለመሆኑ እርግጠኛ ይሆናል። ምናልባትም ባልተሟላ እግር ሚዛኑን ጠብቆ መቆሙ አስደንቆትስ ቢሆን? ማን ያውቃል! በትዕይንቱ እየተደመምን አውቶቡሳችን ጉዞውን ቀጠለ።
ስለ ህልም ምንነት ጥናትና ምርምር የተደረገባቸውን የምርምር መጽሐፍቶች አግኝቼ የማንበብ እድሉ ባይገጥመኝም፤ የህልም ምንነትና ባልተጠበቀ ጊዜ መከሰቱ ግን ያስደንቀኛል። በቅርቡ የተመለከትኩት ህልምም፤ ይህንኑ ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ምንም እንኳን በገሃዱ ዓለም የተመለከትኩት የቁራው እውነተኛ ትዕይንት ከረዥም ጊዜ በፊትና ፈጽሞ የረሳሁት ጉዳይ ቢሆንም፤ ህልሜ ግን ይህንኑ ገሃዳዊ ትዕይንት ቀጥሎ በማቀርበው ሁኔታ አሳይቶኝ ላስታውሰው ችያለሁ።
በዚህ በቄራ ቅጥር ግቢ ውስጥ በዛ በተመለከትኩት ሰው ቢጤ ምትክ በተመሳሳይ ሁኔታና አቋቋም ዘብ ተመድቤ የቆምኩ ይመስለኛል። ወዲያውኑ አንድ ጆፌ አሞራ የአውሮፕላን ጎማ የሚመስሉ እግሮቹን ዘርግቶ አናቴ ላይ ያርፋል። «እህህህ…!» በማለት ጎሮሮውን ከጠራረገ በኋላ አንገቱን ቁልቁል አስግጎ፤ «አይ አቋምና አቋቋም! ከሆነ አይቀር እንዲህ ነው» በማለት አሞካሸኝ።
ወዲያውኑ ውስጤን ሞቅታ ተሰማው። ሰውነቴ ተንቀሳቃሽ ባለመሆኑ ሳልችል ቀረሁኝ እንጂ፤ ደስታዬን በወታደራዊ ሰላምታ ብገልጽለት ደስ ባለኝም ነበር። በድጋሚ ቁልቁል ተመለከተኝና «እኔ ግን ከሁሉም በላይ የማረከኝ የእግርና የእጅህህህህ…» ብሎ ጥቂት ጸጥ ካለ በኋላ «…አይ እግርና እጅ!» በማለት አከለበት። አሁን! በመጀመሪያ ሙገሳው የፈጠረብኝን ሙቀት በሦስት እና በአራት እጥፍ አሳደገው። ማለቴ! በቃ ደስታዬ እንደ ኤርታሌ አሳተ ገሞራ ወደ ላይ ሲፍለቀለቅ ተሰማኝ። ምን አለፋችሁ ዛሬ እድለኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ሥራ ተመድቤ ከጀመርኩባት ደቂቃ ጀምሮ እንኳን ሊያሞካሸኝ ይቅርና ሰላምታ እንኳ ሊሰጠኝ የወደደ ከዚህ ከባለውለታዬ ጆፌ አሞራ በስተቀር ማንም የለም።
ይህ ጆፌ አሞራ በዚህ አላበቃም። ዙሪያ ገባዬን እየተሽከረከረ በፉጨት ከቃኘኝ በኋላ፤ «ስማ!» አለኝ፤ «አቤት!» አልኩት፤ «ለመሆኑ እግርህንና እጅህንእእእ…» ብሎ ፀጥ አለ። በጣም ተበሳጨኹ፤ ምክንያቱም ደግሞ ደጋግሞ እንዲያሞካሸኝ መፈለጌን መደበቅ አልፈልግም። ይህም ብቻ ሳይሆን የዚህ ባለውለታዬ ጆፌ አሞራ ድምጽ ለስለስ ብሎ እንደሚንቆረቆር የጃፓን ክላሲካል ሙዚቃ የማይጠገብ ከመሆኑም በላይ፤ በቀጣይ ሊነግረኝ ያሰበውን የተመረጠ የሙገሳ ቃሉን ለመስማት ቸኩያለሁ።
እንደውም እንድናገር ከተፈቀደልኝ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ቤቶች ቅር ሊሰኙ ይችላሉ ይሆናል እንጂ፤ ይህ ጆፌ አሞራ ከፈጠረብኝ ተደራራቢ ሙቀት የተነሳ፤ ለአንዲት ቀን በግቢው ውስጥ ስልጣን ማግኘት ቢቻለኝ፤ ለእርድ የገባውን የከብርይ ስጋ በሙሉ ምናምንቲ ሳይቀር ለዚሁ አድናቂዬና ባለውለታዬ ለሆነው ጆፌ አሞራ በሽልማት መልክ ባበረክትለት ለዓመት ቀለቡ ቢያንሰው እንጂ መቼም አይበዛበትም።
ዳሩ ምን ያደርጋል! እንዴት እንደምገልጸው ባላውቅም፤ በቃ! ይሄ አስቀያሚ የሆነ ጆፌ አሞራ ጉድ ሠራኝ። እኔ ለውለታው ስለማበረክትለት የሽልማት መጠንና ዓይነት፤ በሃሳቤ ሳወጣና ሳወርድ ሳለሁ፤ ምን የተሲያት በኋላ ልክፍት እንዳገኘው ባላውቅም፤ በሬክተር ስኬል 4.5 ሊለካ የሚችል ነውጥ በውስጤ ፈጥሮ አረፈው።
ይኸውም፤ ለሁለት ደቂቃ ያህል ጸጥ ብሎ ዙሪያ ገባዬን በፉጨት ከተመለከተኝ በኋላ፤ «ስማ!» አለኝ። «አቤት!» አልኩት። «እኔ ካንተ የምደብቀው ነገር የለም። ለመሆኑ እግርህን በስንት ነው ያከራየኸው?» አለኝ። «አልገባኝም» አልኩት።
«ድሮስ መች ይገባሃል! አንተ ምቀኛ» አለና፤ በዛ የአውሮፕላን ጎማ በሚመስለው እግሩ ቁልቁል ሶምሶማ ደቀደቀኝ። ቀጠለና ደግሞ «ባንተ ቤት እኛን ማስፈራራት ነው አይደለ? አንተ ምቀኛ! አልተሳካልህም እንጂ ቢሳካልህ ኖሮማ አንተን ፈርተን ከዚህ አካባቢ ድራሻችን እንዲጠፋ፤ ቀን ከሌሊት ጥረት ማድረግህን ደርሰንበታል።…ስማ! ደግሞ እጅ እንዳለው ሰው ዱላ መጨበጥም ያምርሃል?» ብሎ ከሳቀ በኋላ፤ የሆነ የፉጨት በሚመስል ድምጽ ጓደኞቹን ጠራቸው።
ምድረ ማቲ ጆፌ አሞራ ከያለበት ተጠራርቶ እስኪሰበሰብ ድረስ በደንብ አድርጎ ወቀጠኝ። ደግነቱ የሠራኝ ያ የሠራተኞች ቱታ አጣቢ ኢንጅነር ምስጋና ይግባውና፤ እንዳላስፎግር ብሎ ሰሌን ኮፍያ አናቴ ላይ ጣለ ባያደርግልኝ ኖሮ፤ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ሊቅ መሆን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም።
አሁን ታላቅ የሆነ የአሞራዎች ስብሰባ በዙሪያዬ ሆነ። ከዚህ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ባልችልም፤ አናቴ ላይ የቆመብኝን ጆፌ አሞራ ግን ለቅኝት ተልኮ የመጣ መሆኑን ደርሼበታለሁ። በዚህ ጆፌ አሞራ «ፀጥታ» የሚል ድምጽ ከመሰማቱ በፊት ግማሹ ይስቃል፤ አንዳንዱ ፊቴን ለማየት ይንጠራራል፤ ሌላው ነቃንበት በማለት እርስ በእርሱ ይጠቃቀሳል። ከማዶ ደግሞ «ይሄ ምቀኛ!» የሚል ድምጽ በርከት ብሎ ይሰማል።
ኧረ ምኑ ቅጡ! ከወደ ኋላዬ ደግሞ «ዱላውን ንጠቀው! ንጠቀው!» የሚሉ ጆፌ አሞራዎች፤ ይኼ የግቢው አሸባሪ ነው ይወገድ! ይወገድ! በማለት አክለው ይናገራሉ። ብቻ! ግቢው በጩኸት ድብልቅልቁ ወጣ። «ፀጥታ! ፀጥታ! ሁላችሁም በዚህ ጅላጅል ሰውዬ ላይ ምን ልንወስን እንደምንችል ክንፍ በማውጣት ሃሳባችሁን ልታቀርቡ ትችላላችሁ» አለ፤ ቃኚው።
ወይ እድሌ! ምድረ ማቲ አንዳንድ ክንፉን ከፍ አደረገ። «አንተ! አዎን አንተ! ክንፍህ ላይ ነጭ ጣል ያደረገብህ» ቀጠለ፤ «እኔ በበኩሌ…» አለ አንድ ሰጋጋ ጆፌ አሞራ፤ «አዎ እኔ በበኩሌ ይህ ሰው ከምቀኝነት ምን ትርፍ ሊያገኝ እንደሚችል አስቀድሞ ቢነግረንና፤ ጥርሳችንን ከነቀልንበት ሰፈር ወዴት ሂዱ እንደሚለን ቢያስረዳል» አለ። «አይ! አይ! ይህን የጅል ሃሳብ መስማት ለእኛ ጥቅም የለውም። በዚህ ሰው ላይ ስለምንወስነው ተመጣጣኝ ቅጣት መናገር ብቻ በቂ ይሆናል» አለ ቃኚው።
ከዚህ በኋላ አንድ አራት የሚሆኑ ጆፌ አሞራዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ሰጡ። በመጨረሻ አንድ በእድሜ ከሁሉም አነስ የሚል ጆፌ አሞራ የሰጠው አስተያየት ግን፤ አምርሬ ያንን ያበጃጀኝን የሠራተኞች ቱታ አጣቢ እንድረግመው ያስገደደኝ ነበር። ይህ ቱታ አጣቢ መሃንዲስ የሠራተኞችን ቱታና ሽርጥ አስጥቶ ዞር ሲል እነዚህን ተንኮለኛ የሆኑ ጆፌ አሞራዎች በኩሳቸው ስለሚያበላሹት ነበር መፍትሄ ቢያመጣልኝ ብሎ በማሰብ እኔን ያበጃጀኝ፣ ድንቄም መፍትሄ! ገና ዘብ ተመድቤ በቆምኩ በሦስተኛው ቀኔ ነበር የነቁብኝ።
አሁን፤ ያ ፈልፈላ ጆፌ አሞራ፤ «እኔ የምሰጠው አስተያየት አለ፤ አዎ እኔ የምሰጠው አስተያየት…ይኼ በህልውናችን ላይ የተቃጣ አደገኛ ሴራ በመሆኑ፤ ይህንን ጅላጅል ተሸክመን ደመናው ጋር ካደረስነው በኋላ፤ ከላይ ወደታች ብንለቀው ቅጣቱ ተመጣጣኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ» አለ። በዚህ ጊዜ በመንቆሩ ቅንቅኑን እያራገፈ ያዳምጥ የነበረ ያ ሁሉ! ማቲ ጆፌ አሞራ በሰጠው የቅጣት ሃሳብ አንጀቱ ቅቤ መጠጣቱን ለመግለጽ፤ ክንፉን በማርገፍገፍ ደስታውን ገለጸ። ይሄም ብቻ ሳይሆን «ይገባዋል! ይገባዋል!» በማለት በአንድ ድምጽ በቀረበው የቅጣት ሃሳብ መስማማታቸውን ከመግለጻቸውም በላይ፤ ሃሳብ አመንጪውን ጆፌ አሞራ አጮልቀው በማየት፤ ብስለት በተሞላበት ሃሳብ አመንጪነት ያቺ የመንገድ ዳር ሳንቡሳ የምታህል ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ አድናቆታቸውን ገለጹለት።
በጣም ተበሳጨኹ። ደግነቱ መጨበጫ የለኝም እንጂ የምይዝ የምጨብጠው ጠፋኝ። ድንገት ግን «አንተ ጥንብ አንሳ ሁሉ! ቆይ አገኝሃለሁ» የሚል ድምጽ ከውስጤ ተፈትልኮ ወጣ። እንደው በደመ ነፍስ ተናገርኩኝ እንጂ አሁንስ አጠገቤ አይደሉ? ምነው ባልተናገርኩ! እንደውም ቁጣቸውን አባባስኩት። ድንገት ግን አንድ ሰጋጋ ጆፌ አሞራ ኮፍያው ይውለቅና ፊቱን እንመልከት የሚል ሃሳብ አቀረበ። «አዎ! ይውለቅ! ይውለቅ!» አሉ። እስከዚያች ሰዓት ድረስ ሰሌን ኮፍያዬ ወደ ፊቴ ዘንበል ብሎ ፊቴን ከልሎት ስለነበር ምን እንደምመስል እንኳን ያወቀ አልነበረም።
አሁን ያ ቃኚ ጆፌ አሞራ ሰሌን ኮፍያዬን በጥፍሮቹ ቆንጥጦ ወደ ላይ ውልቅ አደረገው። በዚህ ጊዜ ግን በጆፌ አሞራዎች ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ታላቅ የሆነ የዓለማችን የሳቅ ፌሽታ በዚህ ስፍራ ተካሄደ። በተፈጠረው አጋጣሚ በጣም ተደሰትኩ። ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ በእድሜ የገፉ ጆፌ አሞራዎች፤ ብዙ ከመሳቃቸው የተነሳ እዚህም እዚያም ተንደፋደፉ። በተለይም ደግሞ ከእነዚህ ውስጥ ያ ሰጋጋ ጆፌ አሞራ መካተቱ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አደረገው።
ድንገት ግን፤ «እንደው ባልጠፋ እቃ ጀበና? የሚል ድምጽ የዛን ሁሉ ማቲ ጥንብ አንሳ ሳቅ ገታው። አሁን ሁሉም መሳቁን አቆመና «ጀበና! ጀበና!» እያለ ማዜሙን ቀጠለ። አልተሳሳቱም፤ ያ ሰው አስመስሎ የሠራኝ ኢንጅነር፤ ጀበናውን ከየት እንዳገኘው ባላስታውስም፤ ነገር ግን ከአንገት በላይ ላለው አካሌ እንደ ግብዓት የተጠቀመው መጨበጫና ማንቆርቆሪያዋ የተቆረጠን አንዲት ጌጠኛ ጀበናን ነበር።
አሁን፤ ምድረ ማቲ በየት በኩል እንደተናገርኩ አወቁ። አገልግሎት ከጀመርኩበት ደቂቃ ጀምሮ የማወራው፣ የምተነፍሰውና የማነጥሰው በዚህችው ተቆርጣ በወደቀች የቡና ማንቆርቆሪያ ጡት በኩል ነው። በእርግጥ እንደ ሰው በደንብ አድርጌ መናገር እችላለሁ ብዬ ባልኩራራም፤ነገር ግን ማንኛውም ሰው በአፍንጫው የሚናገረውን ያህል ግን አቀላጥፌ መናገር እችላለሁ። የሆነው ሆነ ሁሉም ሳወራ ለመመልከት በመፈለጋቸው ምክንያት ጥያቄዎቹን ያከታትሉብኝ ጀመር። እኔ ግን ፀጥ አልኩ፤ ሁሉም ተናደዱ።
በዚህ ጊዜ ግን ከዚህ አስቀያሚ ህልም የገላገለኝ ክስተት ተፈጠረ። ቃኚው ከአናቴ ላይ በመውረድ ሁሉንም ወደ አንድ አቅጣጫ ከሰበሰባቸው በኋላ የሆነ ነገር ሹክ አላቸው። ሁሉም ከት ብለው ሳቁ።የሆነው ሆኖ ስቀው ካበቁ በኋላ ሹክ ባላቸው ሃሳብ መስማማታቸውን ለመግለጽ ክንፋቸውን በማርገፍገፍ ድጋፋቸውን ሰጡ። ወዲያውኑ ኦፕሬሽን ሹክሹክታ ተጀመረ።
ሁሉም የሰውነት ማሟሟቂያ ዓይነት ስፖርት ዱብ ዱብ ካሉ በኋላ፤ ባለ በሌለ ኃይላቸው ወደ አፍሪካ ኅብረት አቅጣጫ ይነፍስ የነበረውን የአካባቢውን አደገኛ ሽታ በክንፎቻቸው ወደ እኔ አራገፉት። በቃ ምን ልሁን! እስኪበቃኘ ጋቱኝ፤ ወይ ጊዜ! ለካስ ህልምም እንዲህ መጫወቻ ያደርጋል! ያለማጋነን አምስት ጊዜ አስነጠሰኝ። መታገስ አልቻልኩም። እንደምንም ተፍጨርጭሬ እግሬ ተተክሎ ከነበረበት ቦታ ነቅዬ በመሮጥ ያንን አስቀያሚ ጆፌ አሞራ በያዝኩት ዱላ አንድ ጊዜ ጀርባውን በደንብ አድርጌ አቅምሼው፤ ቅልጥሙ ላይ ልደግመው ስንጠራራ ሳለሁ ከእንቅልፌ ነቃሁ። እሰይ! ተገላገልኩ!!
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ተስፋዬ በለጠ