የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ኢትዮጵያ የከፋ የሙስና ተጋላጭ እንደሆነች ይገልጻል፡፡ እንደሪፖርቱ ገለጻ ከመቶ ፐርሰንት የመከላከል አቅሟ 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አገሪቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደምታጣ ያትታል፡፡
የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ለሌብነት ተገላጭነት ሪፖርት ባያወጣም በኮንስትራክሽን፣ በግብር አሰባሰብ፣ በማዕድንና ማውጣትና በሌሎች ዘርፎች በተለያየ ጊዜ ያወጣቸው ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ለሙስና ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ባለው የሌብነት ችግርም መጠን የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ አለመሆኑንም ያብራራል፡፡
ከኮሚሽኑ ሪፖርት በላይ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርቶች ይህን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም ካደረጋቸው 620 የሚሆኑት የኦዲት ግኝቶች አለመስተካከላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ የእንደራሲዎች ምክር ቤትም ሀላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡
ከ2002 እስከ 2006 በተደረጉ ኦዲቶች ከደንብና መመሪያ ውጭ ክፍያዎች ያላግባብ በመፈጸማቸው እንዲመለስና በቅጣት እንዲሰበሰብ ከተባለው 656 ሚሊዮን 155 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ውስጥ የተመለሰውና የተሰበሰበው 17 ሚሊዮን 472 ሺህ አካባቢ ወይንም ሁለት ነጥብ 66 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ የተቋም ሪፖርት አስደማሚ ብቻ ሳይሆኑ አስደንጋጭም ነው። ከብዙዎቹ ሪፖርቶቹ የተወሰኑ አመታትን መለስ ብዬ መመልከት ፈቀድኩ።
ሚያዝያ 25 ቀን 2004 ዓ.ም
ዋናው ኦዲተር የ2003 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን ሂሣብ ኦዲት በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ዓመተ ምህረት ባቀረበው ሪፖርት፤ የጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ትክክለኛነት አያያዝና አጠባበቅ ለማረጋገጥ ኦዲት አድርጎ በአራት መስሪያ ቤቶች ብቻ አንድ ሚሊዮን 66 ሺህ 524 ብር የት እንደገባ ደብዛውን ማግኘት አልቻልኩም ብሏል። በ59 መስሪያ ቤቶች ደግሞ አንድ ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር በወቅቱና በህጉ መሰረት ሳይወራረድ ተገኝቷል ብሎናል። በ16 መስሪያ ቤቶች ደግሞ 952 ሚሊዮን ብር በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሰበሰብ ተገኝቷል ሲል ገልጾ ነበር፡፡ ዋናው ኦዲተር ይኽን ይበል እንጂ ሪፖርቱን ያዳመጠው ምክር ቤት እስካሁን ምን እርምጃ ወሰደ? ምንም።
ሚያዝያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም
ከላይ በቀረበው ሪፖርት ሁላችንም ተደምመን፤ ከንፈራችንንም መጥጠን ሳናበቃ ይሄው ዋናው ኦዲተር፤ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የሂሳብ ገበና አሁንም በ2004 በጀት ዓመት ሂሣብ ኦዲት ውጤት አቀረበ።
በዚህ ወቅትም በሶስት መስሪያ ቤቶች ብቻ 247 ሚሊዮን 210 ሺህ ብር ጉድለት መገኘቱ፤ በ57 መስሪያ ቤቶች አንድ ቢሊዮን 369 ሚሊዮን 377 ሺህ 900 ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ስለመገኘቱ፤ በተጨማሪም አራት መስሪያ ቤቶችና በስድስት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በድምሩ ብር 29 ሚሊዮን 205 ሺህ 484 ብር በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች መሠረት ያልተሰበሰበ የገቢ ሂሣብ መኖሩ ለተከበረው ምክር ቤት ሪፖርት አቀረበ። በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤትና በስሩ ባሉ ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከውዝፍ ግብር፣ ወለድና ቅጣት መሰብሰብ የሚገባው 866 ሚሊዮን 171 ሺህ 112 ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፤ ምክር ቤቱም ሪፖርቱን አዳምጧል።
ምን እርምጃ ወሰደ? እስካሁን ምንም። ሌላም አለ።
ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም
ይሄው ዋናው ኦዲተር የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶችን የ2005 በጀት ዓመት ሂሣብ ኦዲት በተመሳሳይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም አቅርቧል። በወቅቱም አነጋጋሪ ግኝቶችን ይፋ አድርጎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በአምስት መስሪያ ቤቶች ብቻ አንድ ሚሊዮን 272 ሺህ 93 ብር እምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም። በዋናው ኦዲተር አገላለጽ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል። በዲፕሎማሲ ቃል ማለት ነው። የዚህ በጀት ዓመት ሪፖርት አያይዞም፤ በ77 መስሪያ ቤቶች 877 ሚሊዮን 45 ሺህ 264 ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱን አርድቷል፡፡ አዎን ዋናው ኦዲተር ይፋ አድርጓል።
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤትና በስሩ ባሉ አምስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከውዝፍ ግብር፣ ከቅጣት መሰብሰብ የሚገባው 326 ሚሊዮን 674 ሺህ 939 ብር ሳይሰበሰብ ቀርቷል ሲልም ይሄው ዋናው ኦዲተር ለተከበረው ምክር ቤት አስታውቋል። ምክር ቤቱ ምን አለ? ምን እርምጃስ ወሰደ? ምንም። ሌላም አለ።
ግንቦት 2008
አሁንም ይሄው ዋናው ኦዲተር፤ የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶችን የ2007 በጀት ዓመት ሂሣብ ኦዲት ሪፖርት ለተከበረው ምክር ቤት አቅርቦ፤ በሶስት መስሪያ ቤቶች 196 ሚሊዮን 544 ሺ ብር ጉድለት ተገኝቷል በቅንፍ ውስጥ ብሩ የት እንደገባ አልታወቀም። በ94 መስሪያ ቤቶች እና በ11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ደግሞ ሁለት ነጥብ 078 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡ ልብ ይበሉ! ሁለት ቢሊዮን ብር ነው።
በ34 መስሪያ ቤቶችና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ስር ባሉ አስራ አራት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በድምሩ ያልተሰበሰበ 118 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንዳለ ታውቋል። አሁንስ ምክር ቤቱ ምን እርምጃ ወሰደ? ምንም። በመጨረሻም
ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም
የተከበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተቋማትን የ2008 በጀት ዓመት የሂሳብ ሪፖርት ግንቦት 22 ቀን 2009 ዓ.ም አድምጧል። በዚህ ሪፖርት፤ በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ብር 144 ሚሊዮን 716 ብር ጉድለት ተገኝቷል። ያው “ጉድለት” ማለት የባለሙያ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የት እንደገባ አይታወቅም፤ ወይንም ማን እንደወሰደው አልታወቀም ማለት እንደሆነ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ይሰማዋል። ስለሚሰማውም በዚህ መንግድ ተርጉሞታል።
አሁንም ሪፖርቱ በ113 መስሪያ ቤቶችና በ28 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አምስት ቢሊዮን 262 ሚሊዮን 275 ሺህ 550 ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል ብሏል። አምስት ቢሊዮን ብር። በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤት እና በስሩ ባሉ አስራ አምስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በ30 መስሪያ ቤቶች በድምሩ አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ሣይሰበስቡ ተገኝቷል፡፡
መቼ ይሄ ብቻ፤ በግብር ከፋዮች ለቀረበው የቅሬታ አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴው በወቅቱ ውሳኔ ባለመስጠቱ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መስሪያ ቤትና በሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በወቅቱ ያልተሰበሰበ በድምሩ ብር ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በድምሩ በአንድ የበጀት ዓመት ብቻ በተወሰኑ ተቋማት ከስምንት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ አልተሰበሰበም።
የተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድብን ለመገንባት አራት ቢሊዮን ብር፣ የርብ የመስኖና የውሃ ግድብን ለመገንባት ያውም ከነችግሩ የፈጀው አራት ቢሊዮን ብር መሆኑን ስናስብ የዚህ ገንዘብ ጉዳይ ያሳስበናል። ተሰብስቦ ቢሆን ኖሮ ስንት ተከዜ ስንት ርብ፤ ስንት ሌላም ሌላም ፕሮጀክቶችን መገንባት በቻልን ነበር።
ምክር ቤቱ ጅብ ከሄድ…ምን አለ?
የዋና ኦዲተር ሪፖርት በየዓመቱ እየመጣ የምክር ቤቱን ጠረጴዛ አጨናነቀው፡፡ የአገሪቱን ከፍተኛ የስልጣን ማማ ተቆጣጥሮ በየጊዜው የኦዲት ግኝቱን እንደባለስልጣን ከማስተካከል ይልቅ እንደህዝብ ከንፈሩን ሲመጥ ነበር ምክር ቤቱ፤ በጊዜው የኦዲት ግኝቱ እንዲታረም ማድረግ ሲገባው አለደረገም፡፡ ለጉድለቱና ለጥፋቱ ተጠያቂዎችን በወቅቱ መጠየቅ ሲገባው ብዙዎቹ ሳይጠየቁና ግኝቱን ሳይስተካከል ከሀላፊነት ሲለቁ ዝም አለ፡፡
ሀላፊነቱን በወቅቱ ሳይወጣ ‹‹ጀብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ቢሆንም ምክር ቤቱ ባለስልጣንነቱ ተገልጾለታል፡፡ የባለፉትን ዓመታት የኦዲት ግኝቶች ሊያስተካክል፤ አጉዳዮቹን ሊጠይቅ ከአራት ወር በፊት ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ከፍተኛ የኦዲት መጓደል አዙሪት ውስጥ ገቡ ያላቸውን 58 ተቋማት ለይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም በልዩ ሁኔታ ለማስተካከልም ሲሰራ ነበር፡፡ የኦዲት አጓዳዮችንም ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የኦዲት አዙሪት ወስጥ ያሉትን የአራት ተቋማት ያለፉት አራት ወራት የኦዲት ማስተካካያ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የኦዲት ግኝቱን የማስተካከል ፍላጎት የለውም
የኦዲት ማስተካከያ አፈጻጸም ግምገማ ከተደረገባቸው አንዱ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ፤ የተገኙባቸው ሰባት የኦዲት ግኝቶች መሆኑን ያነሳሉ፡፡ እነሱም ከህግ ውጭ የጨረታ፣ የሰው ሀይል መጓደል፣ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ፣ የ15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የወጭ ደረሰኝ፣ ተግባር ላይ ያልዋለ በጀት፣ የንብረት አጠቃቀምና ሌሎች ጉድለቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ የኦዲት ግኝቶቹ ከሞላ ጎደል ተስተካክለዋል፡፡ የጨረታ ግዥውን አስተካክለነዋል፡፡ የተጓደሉ ሰራተኞችም በጊዜዊነት ተሟልተዋል፡፡ ተግባር ላይ ያልዋለ በጀትም ስራ ላይ ማዋል ጀምሯል፡፡ ለስልጠና ወደውጭ ወጥተው የቀሩ ሰራተኞች ክፍያም በህግ ተይዟል፡፡ ሌሎችም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አውስተው ለተለያዩ ተቋማት ያስተላለፉት 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግን በወጭ ደረሰኝ ተቋማት ማረጋገጫ ሊሰጧቸው እናዳልሰጧቸውና መ/ቤታቸውም ግኝቱን ለማስተካከል አለመቻሉን ለልዩ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡
የልዩ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ፤ ኢንስቲትዩቱ የወሰደው እርምጃ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ያደረገው ማሻሻያም ውስን ነው፡፡ ዋናው የኦዲት ጉድለት ግኝት 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር አልተስተካከለም፡፡ ለማስተካከልም ፍላጎት ያለው አይመስልም ብለዋል፡፡ ሌላኛው የኮሚቴ አባል አቶ ጫኔ ሽመካም፤ ኮሚቴው ስራውን ለማጠናቀቅ የሁለት ወር ጊዜ ነው ያለው፤ ይህ ኮሚቴ የተቋቋመው ተቋማቱን ተጠያቂ ከማድረግ በፊት ችግሩ እንዲፈታ ነው፡፡ ከኢንስቲትዩቱ በግኝቱ ላይ ስንገናኝ ሶስተኛ መድረኩ ቢሆንም የቀረበው ሪፖርት ገላጭም በቂም አይደለም፡፡ ይህ ካልሆነ ወደ መጠየቅ ነው የሚኬደው በማለት በቀረው ጊዜ የኦዲት ግኝቱን የግድ እንዲያስተካክሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ኦዲት መማሪያ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም ያደርጋል
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፤ የኦዲት ግኝቶቹን ለመፍታት መርሃ ግብር በመዘርጋት ብዙዎቹን መፍታታቸውን ገልጸዋል፡፡ የተቀሩትንም ግኝቶች ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በጋራ ሲሰራ ቁፋሮ በሚካሄድበት አካባቢ አደጋ ቢደርስ የሚከፈል ገንዘብ ፈሰስ ስለአለመደረጉ የተገኘው ኦዲት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ፈሰስ አለማድረጉ እንዲቀጥል ተስማምተናል፡፡ በግዥ መመሪያው መሰረት ያልተፈጸመ ግዥ ላይ ሁለተኛ እንዳይፈጸም አርመናል፡፡ ለስልጠናዎች የሚወጣውንም ወጭ የተሰጠውን አስተያየት መሰረት በማድረግ አቋርጠናል፡፡ የአላቂና የቋሚ ንብረትም ተመዝግቦ አልቋል፡፡ በእርዳታ የተሰጡ መኪኖች የታክስ ጉዳይ ስላለባቸው እስካሁን ማስለቀቅ ባለመቻሉ የኦዲት አስተያየቱን ማስተካከል አልተቻለም፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም የግንባታ ፈቃድ የኦዲት ግኝት ተስተካክሎ ወደ ግንባታ ተገብቷል፡፡ እንዲሁም፤ ለክልሎች የተላለፈ ገንዘብ የገቢ ደረሰኝ እየተሰበሰበ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ የሺእመቤት፤ የቅርስ ጥበቃ በትክክል ግኝቱን ፈትቶ ነጻ ከማድረግ ይልቅ መከላከል ነው የተያዘው፤ ያጠፋውን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ተምረንበታል፡፡ በቀጣይ እንዳይፈጸም አድርገናል ይላል፡፡ የኦዲት ግኝት መማሪያ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል እያወቀ ይህን አላደረግም፡፡ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ለክልሎች ተሰጠ በሚል ለማን እንደተሰጠ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ማንም ተጠያቂ አይደለም፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ በመሆኑም የኦዲት ግኝቱን ማስተካከል አለበት፡፡ ተጠያቂ መሆን የሚገባውንም ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
አቶ ጫኔ፤ በበኩላቸው ኦዲተር ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ያጠፋንም ያስጠይቃል፡፡ በጠፋው ገንዘብ ህዝብ ተጎድቷል፡፡ ባለስልጣኑ መጠየቅ አለበት፡፡ እስካሁን መውሰድ የሚገባችሁን እርምጃ አልወሰዳችሁም፤ ይህን ተረባርባችሁ ካልፈታችሁ ተጠያቂዎች እንደምትሆኑ እወቁ በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡
የኤጀንሲው የሽግግር ውዝግብ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሆልቲካልቸር አጀንሲ ስራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ሙላት፤ ግኝቱን ለማስተካከል መርሃ ገብር ተዘርግቶ እስከጥቅምት 2011 ድረስ 85 በመቶ ተስተካክሏል፡፡ ቀሪው ሳይስተካከል ተቋሙ በመፍረሱ ከዚያ በኋላ ብዙም አለመሰራቱን አመላክተዋል፡፡
ከኦዲቱ ግኝቶች መካከል የተሰጠውን ድጋፍ አለመጠቀም፡፡ ከእዳ ነጻ መሆናቸው ሳይረጋገጥ የጠፉ ሰራተኞች በህግ ክትትል እየተደረግ ነው፡፡ የጡረታ ክፍያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ሳይመጣ ይከፈል የነበረው የኦዲት ግኝት ተስተካክሏል፡፡ ለድጎማ ያልተከፈለ ክፍያም በመከፈል ግኝቱ ታርሟል፡፡ የንብረት አስተዳደርም በመስተካከል ላይ ነው፡፡
ችግር ሆኖ ያልተፈታው ገንዘብ ሚኒስቴር በፈቀደው መሰረት ተቋሙ ሲዋሀድ የተደረገው የሂሳብ አያያዝ በዋና ኦዲተር ተቀባይነት አለማግኘቱ ነው ሲሉ ለልዩ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡
የልዩ ኮሚቴው ሰብሳቢና ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታየ ምናለ፤ ኤጀንሲው የቀሩትን ስራዎች በአስቸኳይ በማስተካከል ማጠናቀቅ አለበት፡፡ በሽግግር ወቅት የተፈጠረውን ችግር ከዋና ኦዲተር ጋር በመሆን ግኝቱ እንዲስተካከል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ከዕድርና ዕቁብ ያልተሻለው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጃይሉ ኡመር፤ ዩኒቨርሲቲው ከ2002 ዓ.ም በፊት ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፡፡ የመነሻ ኦዲት ችግር አለ፡፡ ኦዲት መደረግ ከጀመረ በኋላም ዩኒቨርሲቲው በርካታ ግኝቶችም አሉበት፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ኦዲት የሚያደርግ ድርጅት ቀጥሮ እያስራ ነው ብለዋል፡፡
የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማቲዎስ ኢንሳሞ፤ የዩኒቨርሲቲው የመነሻ ሂሳብ ስላልታወቀ የኦዲት ግኝቱ የተበላሸ ነው ወይም አይደለም ለማለት አልተቻለም፡፡ ችግሩን ለመፍታት በ2007 ዓ.ም ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅተን ወደ ስራ ገብተናል፡፡ በ2008 ዓ.ም ዝርዝሩን አቅርበን የሚጠየቀው እንዲጠይቅም አድርገናል፡፡ ከግንባታ ጋር በተያያዘ የ5 ሚሊዮን ብር መቀጮ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ከግብር ጋር በተያያዝ የተገኘ የኦዲት ግኝት ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍሏል፡፡ ለኢንተርፕራይዝ የተሰጠ ገንዘብ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲመለስ ማኔጅመንቱ ወስኗል፡፡ ተከፋይን ለመክፈልና ተሰብሳቢውንም ለመሰብሰብ እየሰራን ነው፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ያሉበትን 217 ግኝቶች ለማስተካከል እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የልዩ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት፤ ከ183 በላይ ተቋማት የወሰዱት ከዕድርና እቁብ የማይለዩ በመንግስት ህግና አሠራር የማይመሩ አሉ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የዚህ አካል ነው፡፡ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የኦዲት ግኝቱን ማስተካከል አለበት፡፡ ይሻሻላል በሚል እንጂ ሁልጊዜ እንደለፈለፍን መኖር የለብንም፡፡ በተቋማት ውስጥ ያለውን ችግር እየሰራሁ ነው ቢልም ተጨባጭ ለውጥ አልመጣም፡፡ ሌሎች ያደረጉትን እኛ ማድረግ ያልቻልነው መምራት ስለማንችል፤ ህግ ስሌለን ወይስ ሌላ ምንድን ነው ችግሬ ብሎ መፍታት አለበት፡፡ ምክር ቤቱ መስጠት ከሚገባው በላይ ዕድል ሰጥቷል በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡
‹‹የግኝቱ መዝጊያ ካልጠየቅን እኛም እንጠየቃለን››
የልዩ ኮሚቴው አባል አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት፤ ምክር ቤቱ ያለፉትን የኦዲት ግኝት ችግሮች በመፍታት ከዚህ በኋላ ዘመናዊ አሰራር ዘርግቶ ችግር እንዳይፈጠር ለመስራት አቅዶ ነው ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ የገባው፡፡ አሁንም ግን እናንተ ከችግሩ ለመውጣት ዝግጁ ስላልሆናችሁ ተቸግረናል፡፡ አብዛኞቹ ችግር ከመፍታት ይልቅ ሂደቶች ናቸው፡፡ ጅምር ነው፡፡ ይህን እድል ካልተጠቀማችሁ ከዚህ በኋላ ምክር ቤቱ የሚሄደው የመጨረሻው አማራጭ ወደሆነው ህጋዊ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ ነው፡፡ ለቀጣይ ትውልድ ችግርና የአሰራር ጉድለት አናስረክብም ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ሌላው የኮሚቴ አባል አቶ ደረጃ ሀይሉ፤ ከአራቱ ተቋማት በቀጣይ እርምጃ እንወስዳለን ከማለት ያለፈ ተጠያቂ አላደረጉም፡፡
ተጠያቂዎችን ለህግ ያቀረበ አንድም የለም፡፡ የህዝብን ሀብት እያባከኑ አለመጠየቅ አይቻልም፡፡ ኮሚቴውም ተቋማቱን ለመርዳት ቢቋቋም እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ በማንሳት ምክር ቤቱ ተቋማቱንና ሀላፊዎቹን ተጠያቂ ወደማድረግ እንደሚሸጋገር አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ፤ የአብዛኞቹ ተቋማት ማስተካከያዎች አመርቂ አለመሆናቸውን አመላክተው ያረሙትን የኦዲት ግኝት በቀጣይ በማየት ለመስተካከሉ ማረጋገጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ምክትል አፈጉባዔዋ ወይዘሮ ሽታየም፤ ልዩ ኮሚቴው የተቋቋሙ ከመጠያየቅ በፊት ችግሩን በማረም ለመደጋፍ ነው፡፡ ስራችሁ አስጨናቂ ቢሆንም ማረም ካልቻላችሁ ከተጠያቂነት አታመልጡም፡፡ ምክር ቤቱም በህዝብ ስለሚጠየቅ ስማችንን ለመጠበቅ እኛም እናንትን ቀጥ አድረገን እንጠየቃለን፡፡ በመሆኑም እንደድሮው ወደ ኋላ አይባልም፡፡ ምክር ቤቱ መጠየቅ ከመጀመሩ በፊት ዕድሉን ተጠቅማችሁ የማስተካከል ስር መስራት አለባችሁ፡፡ ከሚመለ ከታቸሁ አካላት ጋር ተቀራረቦ መስራትም ይገባል፡፡ እንደባለፈው ስምንት ዓመታት ምንም ለውጥ ሳናመጣ መቀጠል አንችልም ሲሉ የኦዲት ግኝቱን ማረም የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ