የተወሳሰበ ችግር ውስጥ የሚከተው የጥገኝነት ጉዳይ ሲነሳ፤ አሁን አሁን የተለመደው በቤተሰብ ቤት ትዳር መስርቶ የመኖር ጉዳይ ይጠቀሳል። በባል ቤተሰብ ወይም በሚስት ቤተሰብ ቤት ትዳር መስርቶ መኖር ለአንዳንዶች ከባድ ዕዳ ሲሆን፤ ለሌሎች ደግሞ የደህንነት ጉዳይ ሆኖ በመልካምነቱ ይነገራል። ብዙዎች የሚስማሙበት በቤተሰብ ቤት ትዳር መስርቶ መኖር ምንም እንኳ ከቤት ኪራይ ወጪ የሚገላግል ቢሆንም፤ በገንዘብ የማይለካ ነፃነትን ያሳጣ መሆኑ ላይ ነው።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ በባለቤታቸው ቤተሰቦች ግቢ ለስድስት ዓመታት የኖሩት ወይዘሮ አልማዝ ካሳ እንደሚናገሩት፤ በፍፁም ማንም ሊተገብረው የማይገባ ጉዳይ ቢኖር በቤተሰብ ቤት ትዳር መስርቶ መኖር ነው። ብዙዎች በባለቤታቸው ቤተሰብ ግቢ ቤት ሰርተውም ሆነ፤ የባለቤታቸው ቤተሰቦች በሰሩት ቤት የሚኖሩ ከሆነ ትዳራቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ሚስት እና ልጆች በከፍተኛ መጠን ይጎዳሉ።
‹‹ የባል ቤተሰቦች የወንድማቸው ወይም የልጃቸው ሚስት ምንም ባታጠፋም የእነርሱን ልጅ ስላገባች ብቻ እንደ ጥፋተኛ ያዩዋታል። ልጃቸው እርሷን ባያገባ ሌላ ማግባቱ እንደማይቀር አይረዱም። እርሱ ቢያጠፋ ‹እርሷ መክራው ነው› በማለት፤ መጥፎ ነገሮችን ሁሉ በሚስት ላይ ያላክካሉ።›› የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ በዚህ ሳቢያ ሚስት እና የባል ቤተሰቦች መሃል በሚፈጠረው ግጭት ልጆች ላይም የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑን ይህም በእርሳቸው ህይወት ውስጥ ያጋጠማቸው መሆኑን ያብራራሉ።
ከባል ቤተሰብ ጋር አብሮ መኖር በአጭር አገላለፅ ‹‹ሲኦል›› ማለት ይቀላል የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ ቤት እና መቃብር በግል ነው። የፈለገ ቢሆን በነፃነት ለመኖር፤ የሚፈለገውን ሁሉ ለማድረግ ከባልም ሆነ ከሚስት ቤተሰብ መራቅ የተሻለ መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹በልጅነቴ ወደ ባለቤቴ ቤተሰቦች ቤት መግባቴ አርቄ ባለማሰቤ የተከሰተ ነው። የእርሱ ቤተሰብ ለኔም ቤተሰብ ነው። የሚል እምነት ነበረኝ። ነገር ግን በኋላ ላይ ግን ቤተሰብነታቸው ለባለቤቴ እንጂ ለኔ ባዳ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ። ›› ካሉ በኋላ፤ ከትዳር አጋራቸው ጋር ተግባብተው እና ተስማምተው ያለምንም ፀብ መኖር ቢችሉም በቤተሰብ ቤት መኖራቸው በተለይ ከባለቤታቸው ወንድም ጋር የተፈጠረው ፀብ ከባለቤታቸው ጋር እስከመለያየት ሊያደርሳቸው ጥቂት ቀርቶት እንደነበር ያስረዳሉ።
ወይዘሮ አልማዝ ለብሰው ሲወጡ ይሳቀቃሉ። ጓደኞቻቸው ቤት ሊጠይቋቸው ሲመጡ ይጨነቃሉ። ምክንያቱም የባለቤታቸው እናት ‹‹የልጄን ገንዘብ ለማንም ወፍ ዘራሽ ትበትናለች›› ይሏቸዋል። ወይዘሮ አልማዝ ከደጅ ሳይገቡ በባለቤታቸው ከተቀደሙ አሽሙሩ ከባድ ነው። የባለቤትየው እናት እና ወይዘሮ አልማዝ ከተጣሉ ደግሞ ልጆች ይጨነቃሉ። እንደውም እንደወይዘሮ አልማዝ ገለፃ፤ አንዳንዴ የባል እናት፣ እህትም ሆነች ወንድም ወይዘሮ አልማዝ ላይ ያላቸውን ጥላቻ በወንድማቸው ልጆች ላይ አያትየውም በልጅ ልጆቻቸው ላይ ያንፀባርቃሉ። በዚህ ሳቢያ ልጆቹም ነፃነት እያጡ የአባታቸውን ቤተሰብ እየጠሉ ነው ይላሉ።
ወይዘሮ እስከዳር ተሰማም ለ11 ዓመታት በባለቤታቸው ቤተሰብ ግቢ ኖረዋል። እርሳቸው ግን ከወይዘሮ አልማዝ የተሻለ ኑሮን በባላቸው ቤተሰቦች ቤት ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። ‹‹በባል ቤተሰብ ቤት መኖር ሁል ጊዜ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም። እንደየሰው ይለያል፤ በኔ በኩል እስከአሁን ጥሩ ነው። የኔ ለየት የሚያደርገው ከልጅነት ጀምሮ ከእህት ወንድሞቹ ጋር አብረን ነው ያደግነው። በጣም ስለምንቀራረብ ብዙ ችግር አልገጠመኝም። ›› ይላሉ።
‹‹አንዳንዴ ከተለያየ አካባቢ ሲመጣ በፀባይም አለመተዋወቅ ስለሚኖር መጋጨት ያጋጥማል። እህቱም ጓደኛዬ ነበረች። ያደግነው አብረን ነው። የእኔ እናት እና የእርሱ እናት ጓደኛሞች ናቸው። እንደባል ቤተሰብ አርቄ አላያቸውም። ያገባሁት በጣም የሚወዱትን ልጃቸውን ነው። እኔም በቅርብ ስላደግኩኝ የሚያዩኝ እንደልጃቸው ነው። የወለድኩትም ሆነ የታረስኩት እዛው ቤት ሆኜ ነው። እንደውም ተከራይቼ ከምኖር ለሁለት ሴት ልጆቼም ሆነ ለራሴ ደህንነት እዛ መኖሩ የተሻለ ነው። ›› ይላሉ።
ወይዘሮ እስከዳር የባለቤታቸው እናት እጅግ አስተዋይ እና ጥሩ ሰው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቀሏቸው እንደሚኖሩና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመነጋገር እንደሚፈቱ ይገልፃሉ።
ሌላኛዋ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ መቅደስ ወልዴ ደግሞ ከአምስት አመት በላይ በራሳቸው ቤተሰብ ጊቢ ከትዳር አጋራቸው እና ከልጆቻቸው ጋር ኖረዋል። ከወይዘሮ እስከዳር ተቃርነው ከወይዘሮ አልማዝ ጋር ደግሞ ተስማምተው በቤተሰብ ቤት መኖር እጅግ ፈታኝ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹እህት ወንድሞቼ እኩል መብት ስላለኝ ምንም አይሉም። ከእናቴ ጋር ግን ብዙ ነገር ያገናኘናል። አንዳንዴ እናቴ እየተናገረች ታስከፋኛለች። በሌላ ጉዳይ ስትበሳጭ ‹ቤቴን በገዛ እጄ ሰጥቼ› ትላለች።›› የሚሉት ወይዘሮ መቅደስ፤ በቤተሰባቸው ግቢ መኖር ከጀመሩ ወዲህ ቀደም ሲል ከውጭ ለጥየቃ ወደ ቤተሰባቸው ሲመጡ ያገኙ የነበረው ክብር መቀነሱን ይገልፃሉ።
‹‹ለእኔ ቤት የገዛሁት ምግብም ሆነ ዕቃ ቤተሰቦቼ ቤት ከሌለ አስቸጋሪ ነው። ‹አንቺማ ሃብታም ነሽ› ይላሉ። ያሽሟጥጣሉ። እነርሱ ከሚጠቀሙት የተለየ ነገር መጠቀም አልችልም። ልርዳ ከተባለም በጣም ብዙ ገንዘብ እንዳለኝ ይገምታሉ የሚያልቅብኝ የምቸገር አይመስላቸውም። ›› ካሉ በኋላ፤ ራሳቸውን ችለው ከቤተሰቦቻቸው ርቀው አለመኖራቸው በባለቤታቸው ነፃነት ላይም ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ያብራራሉ።
እንደወይዘሮ መቅደስ ገለፃ፤ በቤተሰብ ቤት መኖር ጉዳትም ሆነ ጥቅም አለው። ነገር ግን በወንድ ቤተሰብ ቤት ከመኖር ሴት ቤተሰብ ቤት መኖር በተለይ ለሴቷ የተሻለ ነው። ሴቷ በባለቤቷ አትጠቃም። የሴት ቤተሰቦች ባልየውን ያከብሩታል። ሴቷም ለባለቤቷ ትጨነቃለች። በተቃራኒው ባል ቤተሰብ ቤት ሚስት ስትገባ የእርሱ ቤተሰቦች ሲያበሳጯት እርሱ አይጨነቅም።
ቤተሰቦቿ ቤት ተጠግታ የምትኖር ሴት በቤቷ ሥራ ስትደክም ቤተሰቦቿ ያግዟታል፤ ያዝኑላታል። የባል ቤተሰቦች ግን ‹‹ትስራ›› ብለው እንደግዴታ ይቆጥሩባታል። ይህም ለጉዳት ይዳርጋታል። ወንድ ቢያጠፋ እንኳ የሚስት ቤተሰብ ያጉተመትማል እንጂ አልፎ አይናገርም፤ ጠብ ውስጥ አይገባም። የሚስት ቤተሰብ ግን ሚስትን እስከመደብደብ ይደርሳሉ ይላሉ።
ነገር ግን ቤተሰብ ቤት መኖር ጉዳት ብቻ አይደለም በተለይ ልጆች ለማሳደግ ይጠቅማል። እርሷ ከስራ እስከምትመጣ ልጆቿ በሰራተኛ ሲያዙ ቤተሰቦች ክትትል ያደርጉላታል። ሰራተኛ መቅጠር ካልቻለችም ልጆቿ ይያዙላታል። ያደጉ ልጆችም ከትምህርት ቤት ሲመጡ በር ቢዘጋ አያታቸው ቤት ይገባሉ። ለሚስት ለራሷም ሆነ ለልጆቿ ደህንነት በቤተሰብ ቤት መኖር በጣም ጥሩ ነው። ስለዚህ ቤተሰብ ቤት መኖሩ በሌላ መልኩም የሚደገፍ ነው። ነገር ግን ዋናው የሚያስማማው ጉዳይ ነፃነት ከተባለ ከምንም በላይ ቤተሰብ ቤት ከመኖር ይልቅ በራስ ቤት መኖር የሚደገፍ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
ምህረት ሞገስ