በኢትዮጵያ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት /ፓስተር/ ቀጥሎ አንጋፋውና የመጀመሪያው የግል ህክምና ላብራቶሪ ነው። የህክምና ምርመራዎች በአብዛኛው በላብራቶሪ አማካኝነት የሚከናወኑ በመሆናቸው ይህንኑ አገልግሎት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በብዛትና በስፋት በመስጠትም ይታወቃል።
ከመንግስት ጤና ተቋማት ውጪ በሃገሪቱ የኤች አይቪ ምርመራን ሲያደርግ የነበረና በአሜሪካ ኤምባሲም የኤች አይቪ ምርመራ ማእከል በመክፈት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ብቸኛው የግል ህክምና ተቋም ነው። – አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ።
የአርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለድርሻ ወይዘሮ ዘላለም ፍሰሃ እንደሚሉት፤አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ የአርመን ተወላጅ በሆኑት በዶክተር አርሻቬር ቴርዚያን በ1965 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተቋቋመ የመጀመሪያው የግል ህክምና ላብራቶሪ ነው። ስያሜውንም ያገኘው ከኚሁ መስራች ዶክተር አርሻቬር ቴርዚያን ነው። ላለፉት 47 ዓመታት በመዲናዋ የላብራቶሪ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። ላብራቶሪው እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ በዶክተር አርሻቬር ቴርዚያን ስም ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ወደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተሸጋግሯል።
አርሾ ስራውን የጀመረው በመስራቹ ዶክተር አርሻቬር አማካኝነት በአንዲት አነስተኛ ክፍል ውስጥ በአዲስ አበባ ፒያሳ በተለምዶ ሰራተኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሽንትና ሰገራ ምርመራ በማድረግ ነበር። መነሻ ካፒታሉም እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በሂደትም የደም ምርመራዎችን ማድረግ ጀመረ። በኋላ ላይ ግን የደም ምርመራዎቹ በአይነት እየሰፉ መጡ። በ1990 ዓ.ም በቴዎድሮስ አደባባይ ተጨማሪ ቅርንጫፍ በመክፈት ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን ጥረት አድርጓል።
ዶክተር አርሻቬር በሀገሪቱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ የዳበረ አለመሆን፣ የላብራቶሪ አገልግሎት ውስንነትና ሞያቸው ዶክተር አርሻቬርን ወደዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንዲገቡ ገፋፍቷቸዋል።
በወቅቱ ለምርመራ የሚያግዙና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ቀዳሚው የነበሩ ሲሆን፣ ይህም አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪን እንዲገንና ረጅም አመታትን በአገልግሎት እንዲዘልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳል። ከዛሬ ሃያ አመታት በፊት ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በከፈቱት ሁለተኛ ቅርንጫፋቸው ያስተዋወቋቸው ትላልቅና አዳዲስ የላብራቶሪ መሳሪያዎችም የዚህ ማሳያ ናቸው።
እንደ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ከአርሻቬር ህልፈት በኋላም ሁለቱ ልጆቻቸው ከውጪ ሃገር በመመለስ የጀመሩትን የላብራቶሪ አገልግሎት ለማስቀጠል ሞክረዋል። ለሁለት ዓመታት እንደሰሩም በቅድሚያ ሴት ልጃቸው በኩባንያው ያላቸውን ድርሻ ለሌላ ሰው አዘዋውረው ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። በዚሁ ጊዜም ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ገብተው ኩባንያውን ተረከቡ።
ሁለተኛው ወንድ ልጃቸውም ከነዚሁ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጋር ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ። እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያን ባለሃብቶች በኩባንያው ውስጥ ገብተው ያለውን ክፍተት በመረዳት ኩባንያው ቅርንጫፉን በመጨመር አገልግሎቱን እንዲያሰፋ ጥረት ማድረጋቸውን ይያያዙታል። ከላብራቶሪ አገልግሎት በተጨማሪ ሁለት ክሊኒኮችም ይከፍ ታሉ። የላብራቶሪውን አቅም ለማሳደግም ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል።
አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ በአሁኑ ወቅት 213 ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቋሚ የስራ አድል የፈጠረ ሲሆን፣18 ሚሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታልም አለው። ቅርንጫፎቹንም ወደ ስምንት በማሳደግ በላብራቶሪ አገልግሎት ዘርፍ ለህብረተሰቡ፣ ለሆስፒታሎች፣ ለክሊኒኮች፣ ለጤና ተቋማትና ለግለሰቦች ያለውን ተደራሽነት አሳድጓል።
በአብዛኛው ሁሉንም አይነት የላብራቶሪ አገልግሎቶችን እየሰጠም ይገኛል። አንዳንድ በሀገር ውስጥ የማይሰሩ ምርመራዎች ሲያጋጥሙም ናሙናዎችን ወደ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ዱባይ ለሚገኙ እውቅና ላላቸው ላብራቶሪዎች በመላክ ውጤቶችን
አረጋግጦ ለተመርማሪዎች ያስረክባል። ለሚሰጠው አገልግሎትም ተመጣጣኝ ዋጋ ያስከፍላል። በሃያ ሁለትና መገናኛ በሚገኙ ሁለቱ ቅርንጫፎቹ ክሊኒኮችን በመክፈትም ልዩ ልዩ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው። በመገናኛ ዓመታዊ የጤና ምርመራና አነስተኛ የህክምና ክትትል ለሚፈልጉ አገልግሎት ይሰጣል። በሃያ ሁለት አክሱም ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ቅርንጫፉም ለማህበረሰቡ ሁሉንም አይነት የህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪም በውስጥ ደዌ ክሊኒክ ለስራ ወደ ባህረ ሰላጤው አረብ ሃገራት ለሚጓጓዙ ዜጎች የጤንነት ሁኔታ ለማረጋገጥ በባህረ ሰላጤው አረብ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች ማህበር ከተመረጡ ክሊኒኮች ውስጥ አንዱ ለመሆንም በቅቷል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም ኩባንያው የአንቲ ቦዲ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ በመያዝ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚያወጡት መመሪያና ፕሮግራም መሰረት የላብራቶሪ ምርመራ ለማካሄድ ሲፈቅዱ በማንኛውም ጊዜ ለመጀመር ዝግጁ ሆኖ እየተጠባበቀ ይገኛል። በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ አካባቢም ራሱን የቻለ ትልቅ ባለአራት ፎቅ ህንፃ የሪፈራል ላብራቶሪ ማእከል ግንባታ አጠናቆ ለላብራቶሪ ምርመራና ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን በማስገባት ሂደት ላይ ይገኛል።
‹‹በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ገና ያልተሰራበትና ብዙ የሚቀረው ነው›› የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክ ተሯ፤ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የህክምና ምርመራዎች የሚከናወኑት በላብራቶሪ አማካኝነት በመሆኑ የተሻለና ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት በስፋት ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ። ኩባንያው በቀጣይ የሚከፍተው የላብራቶሪ ማእከልም ይህንን ክፍተት ከመሙላት አኳያ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚበረክትም ነው የሚጠቁሙት። በሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችም ናሙናቸውን ወደዚህ ማእከል በመላክ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት እንደሚስችላቸው ይጠቅሳሉ።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እንደሚገልፁት፤ኩባንያው ከሚሰጣቸው የህክምናና የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶ ችንም እየተወጣ ነው። ላለፉት አስራ አምስት አመታት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የነፃ ምርመራ አገልግሎት ሰጥቷል። መንግስታዊ ላልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶችም በቋሚነት እርዳታ በማድረግና በዓመቱ ውስጥ በሚዘጋጁ የተለያዩ ጤናን አስመልክቶ በሚከበሩ ቀናት /ለአብነትም የኩላሊት ቀን/ በዓመት በትንሹ ለ አንድ ሺ ሰዎች ነፃ ምርመራ ያደርጋል።
በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የግል ጤና ተቋማት ማህበር በተዘጋጀው ‹‹አፍሪካ ፈርስት›› የጤና ኤግዚቢሽን ላይ ከ1ሺ ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ነፃ የጤና ምርመራ አድርጓል። ይህም በምርመራ አይነት 2 ሺ 500 የሚጠጋና በገንዘብም ሲገመት ከ250 ሺ ብር በላይ የሚሆን ነው። ከጤና ሚኒስቴር በቀረበለት ጥሪ መሰረትም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጨቅላ ህፃናት የህክምና መስጫን በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳት አድርጎ ለሆስፒታሉ አስረክቧል። ይህም በጤና ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል እውቅናና ምስጋና አስገኝቶለታል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቋቋም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለይም ከጤና ሚኒስቴር የቀረበለትንም ጥሪ በመቀበል የህክምናውን ዘርፍ ለማገዝ እየሰራ ይገኛል።
‹‹በህክምናው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ እምብዛም የሚቸግር ነገር የለም›› የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፤ የህክምናው ዘርፍ አትራፊ ባለመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ እንደማያበድሩና ይህም የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ህጉ ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚበረታቱ መሆኑንም ገልፀው፤ ይሁን እንጂ ለማህበረሰብ የህክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ጤና ተቋማት በመሬት አስተዳደር በኩል የሚደረገው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የመሰሉ ተቋማት ለነዚሁ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማት ቅድሚያ ሰጥተው እንደማያገለግሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ያመለክታሉ። ለነዚህ ተቋማት የተለየ ትኩረት መስጠትና ማበረታታት እንደሚገባና በዚህ ዘርፍ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅም
ያሰምራሉ። ሁሉም ሰው እኩል ከኪሱ አውጥቶ ለህክምና መክፈል የማይችል በመሆኑ በሃገሪቱ የጤና ኢንሹራንስ ስርአት መዘርጋት እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የጤና ሚኒስቴር ለመንግስት ጤና ተቋማት የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለግሉም ሊሰጥ እንደሚገባ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ተናግረው፤ ስራዎችን ለብቻ መስራት እንደማይችልና አርሾን ለመሳሰሉ የግል ጤና ተቋማት ስራዎችን ማካፈል እንደሚገባው ያመለክታሉ። የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ከግሉ ሴክተር ጋር አብሮ የመስራትን ጉዳይ አፅኖኦት ሊሰጡት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ እየገነባ ያለውን ትልቅ ማእከላዊ ሪፈራል ላብራቶሪ በማጠናቀቅ በመላው ሃገሪቷ ተደራሽነቱን ያሰፋል። በአዲስ አበባና በድሬዳዋ እንዲሁም በአስሩም ክልሎች ላይ የናሙና መሰብሰቢያ ቦታዎችን ያዘጋጃል። በአንዳንድ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚታዩ የላብራቶሪ ክፍተቶችን ለመሙላትም ይሰራል። በኩባንያው ውስጥ የሚሰሩና ከኩባንያው ውጪ ያሉ የጤና ባለሞያዎች ስልጠና ለመስጠትም ፕሮግራም ይዟል። በሂደትም ምስራቅ አፍሪካ ላይ የመስራት ዕቅድ ይዟል።
ሜኔጂንግ ዳይሬክተሯ ‹‹አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ላለፉት 47 ዓመታት በገበያ ላይ የመቆየቱና የላቀ አገልግሎት ምሳሌ የመሆኑ ሚስጥር በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ያቆየው ተአማኒነት ነው›› ይላሉ። በህብረተሰቡ ውስጥ ያሰረጸው እምነት፣ጥራትና ተቀባይነት ያለው የላብራቶሪ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻለው ጠቅሰው፣በሀገሪቱ ‹‹አርሾ›› የሚለው ስያሜ የላብራቶሪ ገላጭ ቃል እስከመሆን ደርሷልም ሲሉ ይናገራሉ።
በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የምርመራ አገልግሎት መስጠቱም የስኬቱ ማሳያ መሆኑን ይመሰክራሉ። ለዚህ ሁሉ ስኬት ታዲያ የትጉህ ሰራተኞቹ አስተዋፅኦ እንዳለበትም ይናገራሉ።
እንደ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ጤና የሁሉ መሰረት በመሆኑ በርካታ ሀገራት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና ዘርፉን በመደገፍ የዜጎቻቸውን ጤንነት ይጠብቃሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለዚሁ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶና ፖሊሲ ቀርፆ እየሰራ ይገኛል። ይሁንና ለጤናው ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አሁንም በቂ ባለመሆኑ በተለይ የግል ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ለህብረተሰቡ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ መንግስት የተለያዩ ማበረታቻዎችንና ድጋፎችን ሊያደርግ፤ አብሮም ሊሰራ ይገባል።
እኛም የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት በአሁኑ ወቅት መንግስት አርሾን ከመሳሰሉና በላብራቶሪ ምርመራ ዘርፍ ረጅም አመታት ከቆዩ የጤና ተቋማት ጋር ቢሰራ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል እየጠቆምን አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል ህብረተሰቡን በይበልጥ ሊያገለግል እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
አስናቀ ፀጋዬ