በአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ምልክቶች አንዱ ችጋር ነው፡፡ የአየር ንብረት ሲዛባ፤ መሬት ጦም ሲያድር፤ ገበሬው በፖሊቲካ መሪዎች ሲወጠር ወይም መሬቱ ሲሸነሽንበት፤ የእርሻ ወቅት ሲያልፍበትና፤ በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አለመኖር፤ በግብርና ባለሙያዎች አለመታገዝና በሌላም ምክንያት የግብርና ምርት እጥረት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ኃላፊነት የማይሰማው መንግሥት የእርሻ መሬት አለፈቃዱ በመቀማትና ከግብርና ውጪ ለሌላ ጥቅም በማዋል የምግብ እህል ምርትን ያስቀንሳል፡፡ የምግብ እህል ምርት ስለቀነሰ ሕዝቡ ቢራብ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችን ተጠያቂ በማድረግ እህል ከውጭ እንዲገባ ወይም እህል የሚገዛበትን ገንዘብ ድርጅቶቹ እንዲሰጡት የመንግሥት ባለሥልጣኖች ዓይናቸውን በጨው ታጥበው አለአንዳች ሀፍረት ቢጠይቁ አይገርምም፡፡
በሕዝብ መራብ ምክንያት ዓለም አቀፍ ውግዘት ከደረሰባቸውና ከሥልጣን ከተወገዱት መካከል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አንዱ ነበር፡፡ በደርግ ከተገደሉ ከፍተኛ በለሥልጣናት ውስጥ የወሎን ረሃብ ደብቀዋል የተባሉ ባለሥልጣናትም ይገኙበታል፡፡ የተደበቀው የሕዝብ ረሃብ ቂመኛና ስውር ፈንጂ ሆነ፡፡ አንዳንድ የሰው ጅቦች በሕዝቡ ረሃብ ያተርፉ እንደነበር ተነግሯል፡፡ ለምሳሌ ከሚጫነው የዕርዳታ እህል ላይ ማጉደል፤ አቅጣጫውን ማስቀየር፤ እስከጭራሹ እህሉን መሸጥና ገንዘቡን ማሸሽ፤ ለግል ጥቅም ማዋል ኅሊናን ያቆሰለ ነበር፡፡
በዚህ የሕዝብ ረሃብ ሰቆቃ የሚነግዱ አሁንም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ታሪክን አውቆ መርሳት የተለመደ ማወናበጃ ነውና ረሃብ በኢትዮጵያ መከሰቱን ማስታወስ የማይፈልጉ ሌቦች በየዘመኑ ይፈጠራሉ፡፡ ከንጉሡ መውደቅ በኋላ ረሃቡ ለደርግ የሥልጣን መደላድል የፈጠረ መስሎ ነበር፡፡ በደርግም ዘመን ድርቅ ተከስቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አልቋል፡፡ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋያ ኮሚሽን ተፈጥሮና ተጠናክሮ እንዲሠራ ቢደረግም ረሃብን ከሥሩ መንቀል አልተቻለም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ምንም እንኳን የመሬት ላራሹ ሕግ ቢወጣም በተግባር ግን መንግሥት የመሬት ባለቤት መሆኑና ገበሬው መሬት አልባ ሆኖ መቅረቱ ነበር፡፡
ደርግ በፈለገ ቁጥር ገበሬውን ፀረ-አብዮተኛ በሚል መሬቱን ሊቀማው ይችል ነበር፡፡ ገበሬው ከአዋጁ በፊት የግል ባለመሬት ፊውዳሎች ጭሰኛ አዋጁ ከወጣ በኋላ ደግሞ የመንግሥት ጭሰኛ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ጭሰኛ ማለት በማንኛውም ጊዜ ከመሬቱ የሚወገድ አርሶአደር ማለት ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ዓይነቱ የመሬት ይዞታ ገበሬውን እንደልቡ እንዲያርስ አላደረገውም፡፡ የምግብ አህልም የቻለውን ያህል ማምረት አልቻለም፡፡ ለረሃብ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም መንግሥት የመሬት ባለቤት በመሆን ገበሬውን እንደፈለገው ማሽከርከር ጀመረ፡፡
ኢሕአዴግ ገበሬውን በአንደ ለአምስት ጠርንፎና አሰባስቦ በማንጫጫት አጣዳፊ የግብርና ጊዜውን በከንቱ እንዲያሳልፍ አስገድዶታል፡፡ ከግብርና ጋር ግንኙነት በሌላቸው ፍሬቢስ ሁካታ አርሶአደሩ ተወዛግቧል፡፡ ከግብርና ተግባር እንዲዘናጋና እርስበራሱ ከጉርብትና ይልቅ በጠላትነት እንዲተያይ ተደርጓል፡፡ አንዱ በአንዱ እንዲያሳብቅና ራሱን እንዲገመግም በማድረግ በአጥፊነት ስሜት እንዲወጠር ተደርጎ ነበር፡፡ በተፈጥሮው አፈንጋጭ የሆነ ሰው አይጠፋምና አንዳንድ አርሶአደር ሆድ ሲብሰው ብሶቱን ለቅርብ ወዳጁ እንኳን ማካፈል ሲፈራ ነበር፡፡ ሊፈነዳ ሲደርስ ይተነፍስ ነበር፡፡
አንዳንድ አርሶአደሮች በጥቆማና በግምገማ ብዛት ሥራ መሥራት ይሳናቸው ጀመር፡፡ በመጨረሻም የምግብ እህል በበቂ መጠን ማምረት ያቅታቸው ነበር፡፡ ረሃብ ሰተት ብሎ ቤታቸው ይገባ ጀመር፡፡ ይህም የአርሶ አደሮችን ሞራል ሳይጎዳው አልቀረም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በመራባቸው የመንግሥት ምፅዋተኞች እንዲሆኑ መገደዳቸው ነበር፡፡ የገበሬው ካድሬም በዚህ ውጤት ይሸለምበታል፡፡ ካድሬው አርሶአደሩን በስብሰባና በጥርነፋ ወጥሮ የምግብ እህል ምርት እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ካድሬ አለቃውን ከማስደሰት በቀር በአርሶአደሩ ላይ ያስከተለውን ሰቆቃ ያልተገነዘበ ሮቦት/መሣሪያ ነበር ሊባል ይችላል፡፡
የምግብ እህል ምርት መቀነስ የሚያስከትለው ችግርና ሰቆቃ በገጠር ብቻ ተወስኖ የሚቀር አልነበረም፡፡ ከፍጆታ የተረፈውን የምግብ እህል በእህል ደላሎች አማካኝነት ለከተማው ሕዝብ ፍጆታ ማቅርብ የተለመደ ነበር፡፡ በጣም ከተትረፈረፈም ለጎረቤት አገሮች ማቅረብና የውጭ ምንዛሪ ማግኘትም ይቻል ነበር፡፡ አርሶአደሩን ለመቆጣጠርና ለማስገበር መንግሥት የምግብ እህል ምርት እጥረትን እንደመሣሪያ መጠቀም ነበረበት፡፡
በደላሎች አማካኝነት ለከተማው ሕዝብ የሚቀርበው የምግብ እህል መጠኑ በማነሱ ዋጋው በጣም የናረና ከሸማቹ ገቢ በላይ ሆኗል፡፡ ብልጣብልጥ ተለጣፊ አርሶአደሮች ብዙ ሳያመርቱ ብዙ የእህል ሽያጭ ገቢ በማግኘታቸው ለጊዜው ከተፋለሰ የእህል ገበያ ተጠቅመዋል፡፡ ሰፊው ገበሬ ግን በምግብ እህል እጥረት እየተራበ ባለበት ጊዜ የመንግሥት ራዲዮና ቲቪ ግን መንግሥት ለሰፊው አርሶአደር የቆመ በመሆኑ ገቢውን አሳድጎለታል በማለት ይለፍፉ ነበር፡፡ አብዛኛው አርሶአደር በድህነት እየማቀቀ ባለበት ወቅት የካድሬው ቀልድ አሳዛኝ ነበር፡፡ የገበሬው ካድሬ ለመንግሥት የተሳሳተ ሪፖርት ያቀርብ ነበር፡፡ በእንቅርት ላይ ጆር ደግፍ እንዲሉ መንግሥትም የካድሬውን ሪፖርት ሳያጣራ ተቀብሎ አስተጋባ፤ የገበሬ ሚሊየነሮችንም ፈጥሮ ሸለመ፡፡
የከተማው ለፍቶአደር ሕዝብ የለመዳቸውን የምግብ እህል ዓይነቶች ከገበያ ለመግዛት አቅሙ አልቻለም ነበር፡፡ ከጤፍ ወደ ማሽላ፤ ከማሽላ ወደ በቆሎ ከበቆሎ ወደ ዳጉሣ የእህል ግዢውን በገቢው መጠን ማስተካከል ነበረበት፡፡ ነጭ ወይም ሠርገኛ ጤፍ መሸመት ድሮ ቀረ፡፡ የከተማው ድሃ ሠርቶ አደር ወደ ዳጉሣው አመራ፡፡ አነስተኛ ገቢ ያለው ወንደላጤ የቢሮ ሠራተኛ የሆቴል ትርፍራፊ ገዝቶ በፌስታል ይዞ ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ የቀረው ለምሳው አንድ ጉርሻ በአንድ ብር ጎርሶ ሆዱን ይደልላል፤ ጉርሻውን ልድገም አልድገም እያለ ኪሱን እየዳበሰ ራሱን በራሱ ይሞግታል፡፡
ባለትዳር ከሆነ ደግሞ የቤተሰብ አባላት ቁርስ፤ ምሳ፤ እራት በየተራ ይመገባሉ፤ ሦስቱንም መሳተፍ ግን አይቻልም፡፡ ተማሪዎች ከሆኑ ምሳን ዘለው ቁርስና እራት ይበላሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ተማሪዎች በትምህርት ሰዓት ክፍላቸው ውስጥ ጠኔ ይጥላቸዋል፡፡ ያንዳንድ ትምህርት ቤቶች በመምህራን እነዚህን ተማሪዎች ምሳ በማብላት ይታደጓቸዋል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ያካል ብቃት ስለሚያንሳቸው አንጎላቸውም ትምህርት የመቀበሉ ብቃት አነስተኛ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት የከተማውን ሕዝብ አደህይቶና አስርቦ የመግዛት ዓላማውን መንግሥት በሚገባ አሳክቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
መንግሥት የልማት ፐሮጀክቶቹ ብዛት ከአቅሙ ጋር ያላተገናዘበ በመሆኑ ሕዝብን ለድነትና ለረሃብ ዳርጎታል፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ስለሚያስፈልጋቸው አርሶአደሮችን ለፕሮጀክቶቹ ሲባል ከእርሻቸው ማፈናቀልና በምትኩ ለእርሻ የማያመች መሬት እንዲሰጣቸው ማድረግ የተለመደ የማስራብ ዓላማ ማስፈጸሚያ ተግባር ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል የመንግሥትን የስኳር ፐሮጀክት በአንዳንድ ሸለቆዎች በተለይም በጣና በለስ ሸለቆ ውስጥ ለማካሄድ ታቅዶ በሺህ ለሚቆጠሩ ተፈናቃይ አርሶአደሮችም በተወሰደባቸው መሬት ምትክ ከሚኖሩበት መንደር 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መሬት ተከልሎላቸዋል ተብለው በርቀቱ ምክንያት እርሻ ማረስ እንዳልቻሉ በሚዲያ ተገልጿል፡፡ በቅርቡ በሚዲያ እንደተናገሩት አርሶአደሮቹ በልማት ፕሮጀክቱ እንደሚሳተፉ የተገባላቸው ቃል ፈርሶ፤ የልማት ሥራውም ተሰናክሎ፤ የስኳር ፋብሪካው ባለመጠናቀቁ የደረሰባቸውን ችግር አስረድተዋል፡፡ ደርሶ የነበረው የሸንኮራ አገዳ መባከኑ ለዚህም ተጠያቂ አካል አለመኖሩ አስቆጪ ተግባር ሆኗል፡፡ በአገሪቱ የመሬት፤ የሰው ኃይልና የገንዘብ አጠቃቀም ችግር በሕዝብ ላይ ሥራ አጥነትንና የዕለት ጉርስን ማጣትን አስከትሏል፡፡
ከመንግሥት ሌላ የችጋር ወኪሎች የነበሩት የእህል ንግድ ደላሎች ናቸው፡፡ ከገበሬው በርካሽ ገዝተው ለከተሜው በውድ ዋጋ በመሸጥ ትርፍ የሚያካብቱና ለዚህም የምግብ እህል ዕጥረትን የፈጠረው አካል ለዘለዓለም ይኑርልን የሚሉ የእህል ደላሎች ናቸው፡፡ ከገበሬው እህል ሲገዙ ዋጋውን የሚያጣጥሉበትን ዘዴዎች በየቀኑ ይፈጥራሉ፡፡ ዋናው ግን የትራንስፖርት ወይም የጭነት መኪና አርሶአደሩ ጎተራ ድረስ ለመግባት ከፍ ያለ ወጪ መጠየቁ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት እህሉ አፈርና እብቅ የተሞላበት ነው በሚል ዋጋውን ማጣጣል ነው፡፡ ሌሎችም ምክንያቶች በመፍጠር የአርሶአደሩን ምርት መሸጫ ዋጋ ማውረድ የእህል ደላሎች ተግባር ነው፡፡ የእህል ቅብብሎሹ ሰንሰለት ከገበሬው ጎተራ እስከ እህል በረንዳ እየረዘመ ሲሄድ የከተሜው ሸማች የዋጋ ጫና ገቢውን እያመነመነበት ይሄዳል፡፡
ከእህል ሸማቹ ይበልጥ የእህል ዋጋ ንረት የሚጎዳው ሆቴል የሚመገቡ ከተሜዎችን ነው፡፡ ባለሆቴሎች እህል በውድ ዋጋ ሸምተው፤ አስፈጭተው፤ እንጀራ ጋግረው ወይም ገዝተው ለደንበኞቻቸው ምግብ ሲያቀርቡ ወጪያቸውን በተመጋቢው ላይ ከነትርፋቸው በምግብ ዋጋ ላይ ማስተላላፋቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም ያገር ውስጥ ገቢ የቫት ገቢው ከዋጋ ንረቱ ጋር ከፍ ይልለታል፡፡ ባለሆቴሎች ከምግብ ጋር አብረው ከሚሄዱ የታሸጉ መጠጦችና ከቡናና ሻይ ከሚገኘው ቫት ታክስ ጋር ላገር ውስጥ ገቢ ማስተላለፋቸው የማይቀር ሲሆን፤ ለዚህም ሐቀኛ ግብር ከፋዮች ተብለው ይመሰገናሉ፡፡ ምንቸገራቸው፡፡ የሚከፍለው ያው የወር ገቢ ወይም ደመወዝና ጡረታ ጠብቆ የሚኖረው የሆቴል ተመጋቢ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ሕዝብን የማስራብ ስልት ብዛቱ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡
ከበላተኛው ጋር ፊት ለፊት የሚጋጠመው ባለሆቴሉ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በተራው የሚጫንበትን የቤት ኪራይ፤ የገቢ ግብር፤ በተዘዋዋሪ የሚጫንበትን የመንገድ ፈንድ፤ የስኳር ፈንድና ልዩ ልዩ ፈንዶችን በበላተኛው ላይ ካልጫነ በቀር ትርፍ ማግኘትና ድርጅቱን መምራት አይቻለውም፡፡ በተለይም የሆቴሉ ሠራተኞች እጀ መናኛ ከሆኑ ደግሞ በበላተኛው ላይ የሚጫነው የዋጋ ጫና ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ የማታ የማታ በላተኛው ገቢው እየተሸረሸረ ሂዶ በቀን ሦስት ጊዜ መመገቡ ቀርቶ ወደ ሁለት ብሎም ወደ አንድ ሊወርድ ይችላል፡፡ በመጨረሻም አንድ ጉርሻ በአንድ ብር ለመጉረስ ተገዶ የከተማው ጦም-አዳሪ ሠርቶ አደር ይሆናል፡፡ ይህም በከተማ ውስጥ የረሃብ ገፅታው ብዙ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ይህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡
በረሃብ ሕዝቡን ማሰቃየት ቢቻለውም ዓለም አቀፉን የመንግሥት ገፅታ ግንባታ ስለአፈረሰበት የከተማውን ሕዝብ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር በኩል እህል እንዲቀርብለት ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ግን አብዛኞቹ የሕብረት ሱቆች ኃላፊዎች የፓርቲ ካድሬ በመሆናቸው ከሱቁ የሚገኘውን ገቢና ትርፍ የት እንደሚያደርሱት ላይታወቅ ይችላል፡፡ ሱቆቹ እንደተቋቋሙ የቀበሌ ነዋሪዎችን ለይስሙላ ስብሰባ እየጠሩ ሪፖርት ያቀርቡ ነበር፡፡ ይህም ሪፖርት ባንዳንድ ቀበሌዎች ቀርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የሕብረት ሱቁን ገቢ መነሻና መድረሻ ለማጥፋት ነበር፡፡ ጭራሹን እህል ለከተሜው ሕዝብ ማቅረቡ ቀርቶ ዘይት፣ ስኳር፣ ቡና፣ ሸቀጣሸቀጥ፣ ቢራና ድራፍት በመሸጥ ተልዕኮውን በከፊል ሲወጣ የጤፍን ጉዳይ ወደጎን ትቶታል፡፡
የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ኃላፊዎችም ለዘመናት ከሥልጣናቸው ሳይነሱ ለነዋሪው ያተረፉለትን አትርፈው ወደየቤታቸው መግባት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የተለመደ ነበር፡፡ የከተማዋ ከንቲባ ኦዲተር ቢልኩለት የቀበሌው ሕዝብ እፎይታ ገደብ የለሽ ይሆናል፡፡ እህሉም በርካሽ እየቀረበለት ከስውር ረሃቡም ተላቆ የለውጥ ኃይሉን እያመሰገነ የሚያድርበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡ በተለይም የገጠሩ አርሶአደርና የከተማው በላተኛ ቀጥታ የግብይት ስንሰለት የፈጠሩ ዕለት የምግብ እህል ሽያጭና ሸመታ ለሁለቱም ወገኖች የገቢ ድጋፍ ያደርግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የለውጡ መንግሥት የሌሎች አገር ልምዶችን በጥንቃቄ ማስጠናትና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚከተሉትን የመፍትሔ ሃሳቦችንም አቀርባለሁ፡፡
1. አርሶአደሩ የሚያርሰውን ማሣውን በራሱ ባለቤትነትና ፈቃድ ብቻ እንደፈለገው በነፃነት አለካድሬ ጣልቃ ገብነት እንዲያርስ ማድረግ ለምርታማነትና ለምርት ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ በመንግሥትና በፓርቲ አካላት ሁሉ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡
2. መንግሥት ተፈጥሯዊ የረሃብ መንስዔ ምልክቶች እንደተከሰቱ አስቸኳይ ዕርምጃ በመውስድ በዕርዳታም ሆነ በግዥ እህል ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እህሉ ድርቅና ረሃብ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ደርሶ እንዲከፋፈል አስፈለጊው የሎጂስቲክስ ዝግጅት በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
3. በማንኛውም ደረጃ ያሉ በሕዝቡ ረሃብ ሲነግዱ የተገኙ ያገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ሰዎች ወይም ድርጅቶች አለአንዳች ምህረት ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ይሆናል፡፡
4. የእህል ግዥውን በወቅቱ ለማከናወን የሚያስችል በቂ ዝግጅት ድርቅና ረሃብ ከመከሰቱ ቀደም ሲል በሚገኝ ቅድመ – ማስጠንቀቂያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ምደባና የሎጂስቲክስ ዝግጅት ማድረግ ረሃብተኞችን ለመታደግ አስፈላጊ ነው፡፡
5. ረሃብተኞች ሠፈራቸውን ነቅለው ዕርዳታ ፍለጋ ሄደው ከተገኙ ተጠያቂው በሁሉም ደረጃ የሚገኝ መንግሥታዊ አካል ብቻ መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በራሳችን ችግር የውጭ ዕርዳታ ሰጪን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢነት የለውም፡፡
6. ለረሃቡ በተጠያቂነት የሚያዘው ድርጅታዊ ተቋም ሳይሆን መሪው ግለሰብ ባለሥልጣንና ግብረ አበሮቹ መሆናቸው ሊደነገግ የገባዋል፡፡
በመጨረሻም ፌዘኞች ረሃብ በታላቋ ብሪታንያም ገብቷል እንኳን በኢትዮጵያ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን ይህ ሌላ ያ ሌላ ሊባሉ ይገባል፡፡ በረሃብተኛው ከእንግዲህ መቀለድ አይቻልም፡፡
አመሰግናለሁ
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከበረች ቀን ትሁን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ጌታቸው ሚናስ