በ120 ወረዳዎች የሚተገበረው የገጠር መንገዶች ግንባታና ጥገና ፕሮግራም

 

ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ የልማት ተምሳሌት ለመሆን በምታደርገው ጉዞዋ በሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ ትገኛለች። በተለይ በሀገሪቱ እድገትን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት እና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ከእነዚህ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መካከል የመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፉ ጉልህ ድርሻ አለው።

በየጊዜው እያደገ የመጣውን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ዕድገት፣ ዘላቂነትና ፍትሐዊነት፣ ለማረጋገጥ የእነዚህ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጰያ ከህዝብ ብዛቷ ጋር በተሰናሰለ መልኩ ተደራሽነት እና ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ጥገና እና እንክብካቤ ስራ ማካሄድ እንዳለበት ይታመናል።

ይህንንም ቀጣይነት ባለው መልኩ ማስኬድ የሚያስችል የልማት ማዕቀፍ ተዘርግቶ ሲሰራበት መቆየቱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ አመላክቷል። ሚኒስቴሩ ‹‹የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና›› የተሰኘ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም አካሂዷል። በፕሮግራሙ አዲስ የገጠር መንገዶች ግንባታ፣ የመንገድ ጥገና፣ የተንጠልጣይ ድልድዮች ግንባታ እና የተሻጋሪ ድልድዮች ስራ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተጠቁሟል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በመድረኩ ላይ እንዳብራሩት፤ ባለፉት ዓመታት በገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም የአገሪቱን የመንገድ አውታር መጠን እና ተደራሽነት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል። ፕሮግራሙ በሀገሪቱ የገጠር ቀበሌዎችን በሙሉ በአቅራቢያቸው ከሚገኝ ደረጃውን ከጠበቀ ዋና መንገድ ለማገናኘት ታሰቦ የቀረበ ነው። በዚህ ፕሮግራም ብቻ 50 ሺህ ኪሎ ሜትር የተለያየ ደረጃ ያላቸው መንገዶች ተገንብተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ሌሎች ዘርፎችን ለማነቃቃት ለመስራት ታስቦ ሲሰራ መቆየቱን ሚኒስትሯ አስታውሰው፣ በፕሮግራሙ ሁሉንም የገጠር ቀበሌዎች በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች ጋር ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለማገናኘት የተቀመጠው ግብ በተሟላ መልኩ አለመሳካቱን አስታውቀዋል።

የመንገድ ተደራሽነት የገጠሩ ህዝብ ኑሮ እንዲቀየር እንዲሁም ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ያለው ተደራሽነት እንዲሻሻል በማድረግ በኩል መሰረት የጣለ እንደነበር ጠቅሰው፤ ይህም “የገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ድጋፍ ፕሮግራም” የተሰኘው አዲሱ ፕራግራምም በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባለቤትነት ሲከናወኑ የነበሩ የገጠር መንገድ ስራ ንዑስ ፕሮግራሞችን ወደ አንድ አገራዊና ወጥ የአሰራር ስርአት እንዲመጡ ለማድረግ እንደሚያስችል አመልክተዋል። ፕሮግራሙ የተቀረጸውም ነባሩን ፕሮግራም በመገምገም እና ለቀጣይ አስር ዓመት የተቀመጠውን ሀገራዊ ራዕይ በማካተት ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ ለግንባታው የዓለም ባንክ እና የኢፌዴሪ መንግሥት ሚያዝያ 11 ቀን 2024 ባደረጉት ስምምነት መሠረት ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ፤ እንዲሁም ከክልል መንግሥታት 107 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት ተመድቦ በድምሩ 407 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ፈንድ ፀድቋል። በአጠቃላይም ከ2017 የበጀት ዓመት ጀምሮ ፕሮግራሙን ለአምስት ዓመታት በሁሉም ክልሎች እና በድሬዳዋ የከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጀት ሥራዎች ተጠናቀዋል።

የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማም የገጠሩን ማህበረሰብ እርስ በርስ እና ከማአከላት ጋር በማስተሳሰር እና ተነጥለው ያሉ አካባቢዎችን በማገናኘት እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የገጠሩን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እና ለምግብ ገበያ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ያለውን ተደራሽነት ማሳደግ ነው።

ፕሮግራሙ ከያዛቸው ግቦች መካከል የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን አቅራቢያቸው ከሚገኝ ዋና መንገድ ጋር ማገናኘት የግብርና ምርት እና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸውን መንደሮች እና መዳረሻዎች ማገናኘት፣ በመልከአ ምድራዊ አቀማመጣቸው ምክንያት ተነጥለው ያሉ የገጠር አካባቢዎችን ተደራሽ ማድረግ እና በቆላማ አካባቢዎች ያሉ የመሻገሪያ ችግሮችን መፍታት የሚሉት ይገኙበታል። ፕሮግራሙ በ12ቱ ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ ከ120 በላይ ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ በፕሮግራሙ በዋናነትም የሰባት ሺህ 554 ኪ.ሜ የወረዳ መንገድ ግንባታ፣ የአስር ሺህ 71 ኪ.ሎ ሜትር የወረዳ መንገዶች ጥገና፣ የ373 ተንጠልጣይ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች (Trial Bridges) ግንባታ እና የ715 የቆላማ አካባቢ መሻገሪያ ድልድዮች (Special Structures) ግንባታ ይካሄዳል።

በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክቱ ከ11 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ የመንገድ ግንባታው በቀጣይ 5 ዓመታት የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ለ200 ሺህ ዜጎች በቀጥታ እንዲሁም ለ360 ሺህ ዜጎች ደግሞ በተዘዋዋሪ የሥራ እድል ይፈጥራል።

ፕሮግራሙ ከመንገድ ተደራሽነት ባሻገር በገጠሩ አካባቢ የሚካሄደውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራምም የመንገድ ስራ ፕሮግራሙ አካል ሆኖ እንደሚተገበርም ተናግረዋል፡፡ የግብርና ግብይት ዲጅታል ሥርዓት ግንባታ እንደሚካሄድም ጠቅሰው፤ ሥራው በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ተግባራዊ እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡ ገዢዎችን ከገበሬዎችና ነጋዴዎች ጋር በቀጥታ ለማገናኘት የዲጂታል የግብርና ምርት ገበያ መድረክ የማዘጋጀት፣ የግብርና ምርት መከታተያ ሥርዓትን የመንደፍና የመዘርጋት፣ የኮንትራት ግብርና አስተዳደር ሥርዓትን የመንደፍና የመዘርጋት እና የመንግሥት-የግል ሽርክናዎች የዲጂታል ገበያ ሥርዓት ሙከራ ስራንም ማቀፉን አብራርተዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን በሚጠይቁ መንገዶች ግንባታ ላይ የመሳተፍ ድርሻቸው አሁንም አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፤ ይህንን አለመመጣጠን ለማስተካከል በመንገድ ልማት ዘርፉ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት ዘርፉን የሚቀላቀሉበት እና እያደጉ የሚሄዱበት ተመጋጋቢ ስራ መንደፍን እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።

አዲሱ “የገጠር ተደራሽነትና ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም” በዚህ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ፕሮግራሙን በቅንጅት እንዲመሩና እንዲተገብሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ የትምጌታ አስራት እንዳብራሩት፤ የፕሮገራሙ 10 ዓመት እቅድ ሲዘጋጅ እነዚህም በዓለም አማካይ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት አማካይ፣ ከአፍሪካ አማካይ፣ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት አማካይ እና አነስተኛ ገቢ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት አማካይ የሀገራችን የመንገድ አውታር ታይተዋል። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ የመሬት ስፋት፣ የህዝብ ብዛት እንዲሁም የመልማት አቅም አኳያ ሲታይ ያላት የመንገድ አውታር ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

በመንገድ ጥግግት በኩል በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ስኳር ወሰጥ የዓለም አማካይ የመንገድ ጥግግት 944 ሲሆን፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገራት አማካይ 1244 ኪሎ ሜትር ነው። የኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 130 ኪሎ ሜትር አካባቢ ነው።

በቀጣይ አሥር ዓመት እቅድ ኢኮኖሚው በፍጥነት ማደግ እንዲችል ያለንን የመንገድ አውታር ለማሳደግ ብዙ መንገድ መገንባትና ደረጃን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የ10 ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ ከመንገድ ጋር የተያያዙ ሁለት ዋናዋና መገለጫዎች አሉት፡፡ አምራች የኢኮኖሚ ዘርፎች በፍጥነት ማደግ አለባቸው። ይህም የመንገድ መሰረተ ልማት እድገትን ይፈልጋል። ለሁሉም አካባቢዎች መሰረታዊ የሆነ የመንገድ ተደራሽነት ማቅረብ ያስፈልጋል።

የ10 ዓመቱ እቅድ ሁለቱንም ሚዛናዊ አድርጎ ይዟል። ኢኮኖሚው በፍጥነት ማደግ እንዲችል ትላልቅ መንገዶችን፣ የፍጥነት መንገዶችን፣ የጉዞ መንገዶችን መገንባት አንዱ የእቅዱ አካል ተደርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ መሰረታዊ የሚባሉ በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ ለመንገድ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ያለውን ተደራሽነት ለማሻሻል የገጠር መንገዶችን በስፋት መገንባት በእቅዱ ተይዟል።

ከመንገድ አውታር ጋር ተያይዞ የ10 ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ ወደ 144 ሺህ ኪሎ ሜትር አካባቢ መንገድ እንደነበረ አስታውሰው፣ ይህን አሀዝ በአስር ዓመቱ ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እንደ ሀገር ግብ መቀመጡን አስታውሰዋል።

ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳብራሩት፤ በአምስት ዓመት ውስጥ 91 ሺህ ኪሎ ሜትር፣ በ10 ዓመት ውስጥ ደግሞ ከ245 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ ሊኖር ይገባል። በመሆኑም መካከለኛ ገቢ መደገፍ የሚችል የመሰረተ ልማት ሊኖር የሚገባ ከሆነ ይሄንን ያህል መጠን መንገድ ያስፈልጋል የሚል በ10 ዓመቱ እቅድ ተቀምጧል።

በሀገሪቱ የመንገድ አቅርቦት ሥርዓት ያልተማከለ ነው። የመንገድ ግንባታዎች በፌዴራል ደረጃ፣ ፣ በክልል ደረጃ ፣ በከተማ መስተዳድር ወይም በማዘጋጃ ቤት ደረጃ ይካሄዳሉ። ሀገራዊ የመንገድ አውታር የሚባለውም የእነዚህ አራት የመንገድ ባለቤቶች የሚተዳደሩ መንገዶች ድምር ነው።

በ10 ዓመቱ ውሰጥ በፌዴራል ደረጃ የመንገድ አውታር መጠን ከ28 ሺህ ወደ 38 ሺህ ኪሎ ሜትር መጨመር አለበት። ይህም ከቀደመው አሀዝ ወደ 10 ሺህ ኪሎ ሜትር ጭማሪ አለው።ይህም በአማካይ በዓመት ወደ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ተጨማሪ መንገድ መስራትን ይጠይቃል።

አብዛኛው የመንገድ ስራ ያለው በክልል እና በወረዳ ደረጃ መሆኑን አመልክተዋል። በክልል ደረጃ በ10 ዓመት ውሰጥ ከ35 ሺህ ወደ 63 ሺህ፤ በወረዳ ደረጃ ደግሞ ከ55 ወደ 108 ሺህ ኪሎሜትር እጥፍ ለማድረግ ይሰራል ሲሉም ጠቁመው፤ የአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ጥያቄ መመለስ የሚቻለው በክልል ደረጃ እና በወረዳ ደረጃ በሚሰሩ የመንገድ አውታር ስራዎች መሆኑን አስገንዝበዋል።

የክልል የገጠር መንገዶችን ግምገማ በመድረኩ ያቀረቡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተስፋዬ ወልደሚካኤል እንዳብራሩት፤ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከኮንስትራክሸን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሸን ባለስልጣን እና ከፋይናንስ ሚኒስቴር የተውጣጡ የግምገማ ቡድን አባላት በሀገሪቱ ሁሉም አቅጣጫዎች ላይ ተመሰርተው ጂኦግራፊያዊ ግምገማ አድርገዋል።

ግምገማው የተደረገው የዓለም ባንክ ለገንዘብ ሚኒስቴር ያስገባውን 65 ሚሊዮን ዶላር የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ወደ ክልሎች ለማሰራጨት ታስቦ መሆኑን አስታውቀዋል። ክልሎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በክላስተር ላይ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ በግንባታው ዙሪያም በመጀመሪያ በሁሉም ክልሎች ላይ በጋራ፣ በአንዳንዶቹ ትራንስፖርት እና መንገድ ቢሮ፣ አንዳንድ ቦታ በመንገድ ቢሮ፣ በሌሎች ዘንድ ደግሞ በመንገዶች ባለሥልጣን ክልላዊ ባለድርሻዎች እና ቢሮዎች ፋይናንስን የማማከር ስራ ተደርጓል ሲሉም አብራርተዋል።

ከአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲዎች እና ባለሥልጣኖች እንዲሁም ከግዥ /ፕሮኪዩርመንት/ አስተዳደር ኤጀንሲዎች እና ከክልል ፀረ ሙስና ተቋማትና በክልል ደረጃ ከሚገኙ የፕሮግራሙ ባለድርሻዎች ጋር ግምገማ ተደርጓል። ገንዘብ ከሄደ በኋላ በሚገባ ተሰርቶ ሪፖርት መደረገ ያለበት ስለመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተደርገዋል።

የግምገማ ቡድኑ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ፣ ሀረሪ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ትግራይ ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮች እና ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሚመለከተው ጋር መወያየቱን አስታውቀዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You