በአገሪቱ የቴክኖሎጂ ብዜት የተጀመረው የግብርና ምርምርና ኤክስቴንሽን ሥራ በተቀናጀ መልኩ መካሄድ ከጀመረበት ከ1940 ዎቹ ዓመታት አካባቢ የጅማና ዓለማያ እርሻ ኮሌጆች መመስረት ጋር ተያይዞ ሲሆን፤ በ1958 ዓ.ም የዛሬው የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቀድሞ አጠራሩ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ሲቋቋም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎችና የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት (በመልካ ወረር እና በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከላት) ውስጥ ሥራዎችን በማስተባበር ሙሉ ኃላፊነትን ወሰደ።
በወቅቱ በምርምር የወጡ የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ሥራ ይከናወን የነበረው በውስን ቦታዎች በመሆኑና ቴክኖሎጂዎቹ በአግባቡ ተባዝተው ለተጠቃሚው የሚደርሱበት አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ በተለይ የዘር ብዜት ሥርዓት ባለመመቻቸቱ እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ የሚያወጣቸውን ቴክኖሎጂዎች የሚያስተዋውቀው በተወሰኑ አካባቢዎች የተወሰኑ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ስለነበረ አብዛኛው አርሶ አደር ብዙም ተጠቃሚ እንዳልነበረ በምርምር ማዕከሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆነው የሠሩ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአምቦ ግብርና ምርምር ተቋም የሚሠሩት ወይዘሮ የኔነሽ ዱጉማ የቅድመ ማስፋፋት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ቀደም ሲል ተጠቃሚ ያልነበረውን አርሶ አደር አሠራሩን በመሰረታዊነት ቀይሮ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትንና ተቀባይነትን እያሳደገ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜትና አቅርቦት
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተልዕኮ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ በምርምር የፈለቁ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማባዛት መነሻ የሚሆን ቴክኖሎጂ ወይም የተሻሻለ ዘር ለቴክኖሎጂ ብዜት ተቋማት ማቅረብ ነው። በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክቶሬት በየዓመቱ አገራዊ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የመነሻ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በጥራት ቴክኖሎጂ ለሚያባዙ ተቋማት በማቅረብ ላይ ይገኛል።
የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክቶሬት ለግብርና ልማቱ ግብዓት የሚሆኑ ውጤታማ የሆኑ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በመሬትና ውሃ ሀብት፣ እንዲሁም በግብርና ሜካናይዜሽን ምርምር ዘርፍ በምርምር የቀረቡ ቴክኖሎጂዎችን በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ ፍላጎት ከተፈጠረ በኋላ ተቀባይነት ያገኙትን ቴክኖሎጂዎች እና መነሻ የሚሆን የግብርና ቴክኖሎጂ ለሚያባዙ ተቋማት በስፋት እንዲያባዙና እንዲያሰራጩ ያቀርባል።
ማሳያነት
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቀጥታ በስሩ የሚተዳደሩ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ 17 የምርምር ማዕከላት ያሉት ሲሆን፤ በዳይሬክቶሬቱ አማካኝነት በየማዕከላቱ በሚገኙ የዘር ብዜት የእርሻ ቦታዎችን በመጠቀም እና ሥነ-ምህዳርን በመከተል መነሻ የቴክኖሎጂ ብዜት ሥራዎች ያከናውናል። ከሚከናወኑት የቴክኖሎጂ ብዜት ሥራዎች መካከል በሰብል (አራቢ፣ቅድመ መሥራችና መሥራች ዘሮች)፣ በእንስሳት (የተሻሻሉ መኖዎች፣ የወተት ጊደሮችና ኮርማዎች፣ የዶሮ ጫጩቶች፣ የዓሣ ጫጩቶች እና የሐር ትሎች)፣ በተፈጥሮ ሀብት (የተመረጡ የዛፍ ዘሮች፣ የሕያው ማዳበሪያ፣ የአፈር ለምነትና የውኃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂዎች እና መረጃዎች)እንዲሁም የተሻሻሉ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለተለያዩ ተጠቃሚዎች፣ ለአርሶ አደሮችና ለአባዥ ድርጅቶች አቅርቧል።
በተለይ የዘር ብዜትን ለማከናወን ኢንስቲትዩቱ 734 ሄክታር መሬት ያለው ሲሆን፤ በርካታ ዝርያዎችን፣ የተለያዩ የሰብል ችግኝ/ቁርጥራጮች መነሻ ዘር በመኸርና እንዲሁም መስኖን በመጠቀም በበጋ ወቅት መነሻ ቴክኖሎጂዎችን በማባዛት ለተጠቃሚው እያደረሰ ይገኛል። መነሻ ቴክኖሎጂ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ያለው ሚና ጉልህ ነው። የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም ከተለያዩ ፕሮጀክቶች እና ዘር አባዥ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ብሎም ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ያላቸው የመነሻ ቴክኖሎጂ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል።
የተከናወኑ ተግባራት
ኢንስቲትዩቱ ለቴክኖሎጂ አባዦች መነሻ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባሻገር በራሱ ለሚያካሂደው የቴክኖሎጂ ማስተዋወቅና የምርምር ስርጸት ሥራዎች መነሻ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ተጠቃሚዎችንና አርሶ አደሮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
በዚሁ መሠረት ማዕከሉ ካከናወናቸው የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት መካከል በሰብል ብዜት በ33 ሰብሎች እና ከ200 በላይ የሰብል ዝርያዎች ማለትም (የዳቦ ስንዴ፣ የዱርም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ድቃይ በቆሎ፣ የምግብ ገብስ፣ የቢራ ገብስ፣ ሩዝ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ምስር፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሽምብራ፣ ቦለቄ፣ አኩሪ አተር፣ አብሽ፣ ተልባ፣ ጎመን ዘር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፤ ለውዝ፣ ጥጥ፤ ድንች፣ የአበሻ ነጭ ሽንኩርት፤ የአበሻ ቀይ ሽንኩርት፣ የፈረንጅ ቀይ ሽንኩርት፣ ቡና/Specialty/፤ ቡና/Selection/፤ ጎደሬ፤ እርድ፤) በ707.81 ሄ/ር መሬት ላይ ዘር በመሸፈንና በመንከባከብ 10,525.8 ኩንታል የሰብል ዘር እና 101,875 የሰብል ችግኝ ቁርጥራጭ ተባዝቷል።
በሌላ በኩል በእንስሳት ምርምር በበጀት ዓመቱ 130,171 የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት፣ 652,745 የዓሣ ጫጩት፣ 107,500 የሐር ትል እንቁላል፣ 15 ኮርማ፣ 100 ጊደር/ላም፣ 237(50 በመረጣ የተሻሻለ የመንዝ አውራ በግ፣ 108 50% የዶርፐር ዲቃላ በግ፣ 79 ንጹህ የዶርፐር አውራ በግ)፣ 40 በመረጣ የተሻሻለ ፍየል በድምሩ 890,808 የተለያዩ እንስሳት ምርምር ብዜት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ በንቦች ቀፎ ዙሪያ የተሠሩ 110(65 የንብ ጠላት ማጥመጃ ቀፎና 45 በኬሚካል ሳቢያ የሚከሰተውን የንቦች እልቂት የሚቀንስ ቴክኖሎጂ (ቀፎ) ተባዝቷል። እንደዚሁም በእንስሳት መኖ ዙሪያም የተሠሩ ሥራዎች 88.15 ኩንታል የእንስሳት መኖ ዘር እና 467,500 የእንስሳት መኖ ቁርጥራጭ የማባዛት ሥራም ተሠርቷል።
በተጨማሪም በግብርና ሜካናይዜሽንም በተመሳሳይ 626 የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎች ለማባዛት ተችሏል። በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፉም በበጀት ዓመቱ 267.127 የተለያዩ የሰብል ችግኞች/ቁርጥራጭ (ሙዝ፣ ቡና፣ አፕል፣ ኮክ፣ ፕለም፣ አናናስ፣ ስኳር ድንች፣ ሸንኮራ አገዳ) በቲሹ ካልቸር፣ 316 በሲንክሮናይዜሽን ጥጆች የማስወለድ እና የፅንስ ዝውውር ምርምርን በመጠቀም 3 ጥጆችን የማስወለድ ሥራ መሠራቱን ወይዘሮ የኔነሽ ያስረዳሉ።
ከላይ የተጠቀሱት የቴክኖሎጂ ብዜት ውጤቶች ከብዙ በጥቂቱ ሲሆኑ፤ የኢንስቲትዩቱ የቅርብ ጊዜ ትሩፋቶችም ናቸው። ስለሆነም አዳዲስ ቴክኖሎጂና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሠራሮችን ለአርሶ አደሮችና ተጠቃሚዎች በየጊዜው በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመቀናጀት በሚያገኘው ድጋፍ ዘር አባዥ ማህበራትን በማቋቋም በአንድ አካባቢ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋና አርሶ አደሮችና ተጠቃሚዎች ከግብርና ልማቱ ተጠቃሚ ሆነው የአገሪቷንም የግብርና ኢኮኖሚ እንዲገነቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተያያዘም አዳዲስ የፈለቁ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች የማስተዋወቅና የማስፋፋት እንዲሁም ከስነ ምህዳሩ እና ከአየር ፀባዩ ጋር በቀላሉ የተላመዱና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ወይም ተቀባይነት ያገኙ ቴክኖሎጂዎች ሆነው ሲገኙ ደግሞ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ ተጠቃሚዎችና አርሶ አደሮች በማዳረስ ከተለያዩ የክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በሌላ በኩል የአቅም ግንባታ ስልጠናን አስመልክቶ ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚውን አቅም ለማጎልበት በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮች፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የግል ባለሀብቶች እና ከተለያዩ ድርጅቶች ለሚመጡ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ክልሎችና ልዩ ድጋፍ በሚሹ አካባቢዎች (አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ኦሞ እና ቤንሻንጉል) የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን፣ የእንስሳት መኖና
የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን መስኖን መሠረት በማድረግ በማስተዋወቅና በማላመድ በቅድመ ማስፋፋት አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል።
እንደዚሁም የዘር አባዥ ማህበራት ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ከክልል ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጥራት ያለው ዘር እንዴት ይመረታል የሚለውን በስልጠና መልክ ከወሰዱ በኋላ መነሻ ዘር በመስጠት ወደ ሥራ የሚገቡበት ዕድል የማመቻቸት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። እንዲሁም የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ሥራዎችን ሜካናይዝድ በሆነ መልኩ ለመሥራትና ዘመናዊና ውጤታማ ለማድረግ በየማዕከላቱ ለብዜቱ ሥራ ስኬታማነት የሚያገለግሉ የእርሻ መሳሪያዎች፤ የዘር፤ ማዳበሪያና ኬሚካል መጋዘኖች፤ የእርሻ መሳሪያዎች መጠለያ፤ የመስኖ ፋሲሊቲዎችና መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የዘር ላቦራቶሪ አቅም ግንባታዎች የተደረገና በመደረግ ላይ ይገኛል።
በዚሁ መሠረት በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ሥራዎች ከ2008 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር መሻሻል ያሳየ ሲሆን፤ ይህ መሻሻል ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ለግብርና ምርምሩ ዕድገት የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት አቅርቦቱንና ፍላጎቱን ለማመጣጠን እየሠራ መሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው።
ተግዳሮት
ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ገብተው የተላመዱና በአገር ውስጥ የፈለቁ ቴክኖሎጂዎች በበቂ መጠንና ጥራት ተባዝተው ለተጠቃሚው ለማዳረስ የሚያስችል የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት አናሳ በመሆኑና የቴክኖሎጂ ውጤቶች መነሻ ብዜት ለማከናወን የሚያስችል ሥነ-ምህዳርና የአየር ሁኔታ መሠረት ያደረገ ቅድመ ዝግጅት አናሳ በመሆኑ አሁን እንደሚታየው የዘር አቅርቦቱና የተጠቃሚው ፍላጎት ተመጣጣኝ አይደለም።
ሌላው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ዘር አባዥ ተቋማት ውስንነት በቴክኖሎጂ ብዜት ሥራው ላይ ትልቅ ማነቆ ሲሆን፤ ያሉትም ተቋማት የተወሰነ ሰብል ላይ አተኩሮ
የብዜት ሥራውን የሚያከናውኑ ናቸው። ስለሆነም ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ የተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተባዝተው በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ተጠቃሚዎች ጋር ደርሰው ምርት ላይ እንዳይውሉ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ሂደቶች አንዱ ነው። በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ ካለው የመሬት ስፋት አንፃር የምርምር ቦታና የዘር ማባዣ ቦታ እጥረት ያለ በመሆኑ በዘር ብዜት ሥራው ላይ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ከማሟላት አንፃር ያለውን ውጤት ቀንሶታል።
የቴክኖሎጂ ብዜት የወደፊት አቅጣጫ
ኢንስቲትዩቱ በዋናነት የተጠቃሚውንና የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ፍላጎት መሠረት ያደረገ በመጠን፣ በጥራት እና በተደራሽነት ውጤታማ ለማድረግ ዘር አባዥ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ፣ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት የዘር ብዜት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ እና ከዘር አባዥ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት የመነሻ ቴክኖሎጂ አቅርቦትን ማረጋገጥ ዋናው የትኩረት አቅጣጫው ነው።
ሌላው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥራት ከማስጠበቅ አንፃር በአሁን ወቅት በቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክቶሬት ሥር ከመነሻ ዘር ብዜት በተጨማሪ የዘር ጥራት ችግር ፈቺ የሆኑ በአራት ፕሮጀክቶች ስር የተቀረጹ 31 የምርምር ሥራዎች ሂደታቸው እንዲቀጥል እየተሠራ ሲሆን፤ የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ በበቂ ሁኔታ ማምረት እንዲቻል እንዲሁም ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ዝርያዎችን በመፈተሽና ጥራት ያለው የመነሻ ዘር ለተጠቃሚ ማቅረብ ሌላኛው የዘርፉ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነው።
መሰናበቻ
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ሥራዎቹን በ5 ዓበይት የምርምር፣ በ7 የምርምር ድጋፍ ሰጪ ዘርፎችና በ26 የምርምር ብሄራዊ ኬዝ ቲሞች በታቀፉ 64 ኮሞዲቲዎች አማካይነት በኢንስቲትዩቱ ስር በቀጥታ በሚተዳደሩ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 17 የፌዴራል የምርምር ማዕከላት እና በቀጥታ በኢንስቲትዩቱ በማይተዳደሩ ነገር ግን በትብብር በሚሠሩ 7 የክልል ግብርና ምርምር ተቋማትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነት ዕቅዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው።
በዚሁ መሠረት ኢንስቲትዩት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተቀመጠውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ አዋጭና ውጤታማ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ዕቅድ በመንደፍ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት በሰብል፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በግብርና ሜካናይዜሽን የምርምር ዘርፎች ጠቀሜታቸው የተረጋገጠላቸው በርካታ የመነሻ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማባዛት እያቀረበ ይገኛል። በተለይም በሰብል (አራቢ፣ ቅድመ መሥራችና መሥራች ዘሮችን)፣ በእንስሳት (የተሻሻሉ የመኖ፣ የወተት ጊደሮችና ኮርማዎች፣ በግና ፍየሎች፣ የዶሮ እንቁላልና ጫጩቶች፣ የዓሣ ጫጩቶች፣ የሐር ትል ) ፣ በተፈጥሮ ሀብት (ሕያው-ማዳበሪያዎች) እና የተሻሻሉ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለተለያዩ ተጠቃሚዎችና አባዥ ድርጅቶች በማቅረብ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ኢንስቲትዩቱ በዘርና የዘር ጥራት ላይ የተለያዩ ፕሮፖዛሎች በመቅረጽ ምርምር በመካሄድ ላይም ይገኛል። በምርምር የተገኙና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ ስነ-ምህዳሮች በሚገኙ ምርምር ማዕከላት አማካኝነት በማባዛት ለመንግሥታዊ እና ለግል ዘር አምራች ድርጅቶች እንዲሁም በቅድመ-ማስፋት ፕሮግራም ለአርሶ አደሮች የመነሻ ዘርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ተደራሽነቱን ለማስፋት ግንባር ቀደም ሥራ እየሠራ ይገኛል።
በአጠቃላይ እንደዚህ ዓይነት መልካም ተሞክሮዎችን የማስፋትና የመነሻ ቴክኖሎጂ ብዜት ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች የማስተዋወቅና የመተግበር ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል የግብርና ልማቱ ቀጣይ እንዲሆን ከየአቅጣጫው ትኩረት ተሰጥቶት ከቀጠለ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንስቶ አገሪቷ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ የምታስገባውን የምግብ ሰብል እንደሚያስቀር እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ማስመዝገብ የምትፈልገውን ውጤት እንደምታመጣ አያጠያይቅም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2012
አብርሃም ተወልደ ሕይወት በገጠር