ለኛ ኢትዮጵያውያን አባይ ሁሉም ነገራችን ነው። ይሄ እውነትም በተደጋጋሚ በአደባባይ በመገናኛ ብዙሃን፣ በኪነ ጥበቡ፣ በስነ ጽሑፍም ሆነ በተለያየ መንገድ ለዘመናት ሲነገር የቆየ ነው። አባይ ድንበር ተሻግሮ ከሚሄድ ወንዝነቱ ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ እንደ በኩር ልጁ የሚያየው ነው። እውነቱ ይሄ ቢሆንም በበቂ ሁኔታ አባይ ለአገራችን ኢኮኖሚ የሚሰጠውን የላቀ ጠቀሜታ ማወቅ ግን የተሳነን ይመስላል። ለመሆኑ ችግራችን ምን ይሆን?
ምሁራን፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎች አባይን በዘፈንና በግጥም ከማወደስ በዘለለ የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት የሚቀይር አንጡራ ሃብታችን መሆኑን በአግባቡ የማስረዳት ኃላፊነታቸውን የተወጡ አይመስልም።
ከዚህ የተነሳ ማህበረሰቡ ጋር የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ይሰማኛል። ምክንያቱም ስለ አባይ ወንዝ አውቀናል ቢባል እንኳን ድርጊታችንና ግንዛቤያችን ለየቅል ሆኖ ነው የምናገኘው። ማህበረሰባችን በየጊዜው ግንዛቤ እንዲፈጠርለት ይፈልጋል፤ ይህ የተፈጥሮ ሃብት ከልቦናው ሳይጠፋ እንዲኖር ፍላጎት አለው። ነገር ግን ግንዛቤውን በተገቢው መንገድና ልክ አቅርበንለታል ወይ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሳችን በፍጹም የሚል ነው የሚሆነው።
አባይ ለኢትዮጵውያን ልዩ ዋጋ የሚሰጠው ነው። የኢኮኖሚ ምንጫችን፣ ስሜታችንና ምስጢራችን የሚገለጥበት። ይህ እውነታው ቢሆንም በምን መልኩ ማልማትና መጠቀም፤ ጥቅማችንን የሚጎዳ ነገር ቢፈጠር እንዴት መመከት እንደምንችል ወጥ የሆነ ብልሃት አልቀየስንም።
እስቲ በምሳሌነት ግብጾችን እንመልከት። ከራሳቸው በማይነሳና ምንጫቸው ባልሆነው ወንዝ እየተጠቀሙ ሌላ ማንኛውም አካል በጭልፋ እንኳን እንዳይወስድ አሁንም ድረስ ሙጥኝ ማለታቸውን አላቆሙም። ሁልጊዜ ‹‹ ስግብግብ›› የመሆን አባዜያቸውን በሚያነሱት ሀሳብ ሲያሳዩ እንመለከታለን። ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው አህያ በየጊዜው በሚደረጉ ድርድሮች አይኗን በጨው አጥባ ትሞግታለች።
ይህንን ወኔ የሰጣቸው ምን እንደሆነ መገመት አያቅትም። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ግን ህዝቡ በቂ እውቀት፣ የእኔነት ስሜት እንዲኖረው አድርገው ትውልድ አልፈጠሩም።ጠንካራ ግንዛቤ እንዲኖረው በበቂ መልኩ አልሰሩም። የህልውና ጉዳይ አድርጎ እንዲመለከተውና ‹‹ግድቡም ሆነ የአባይ ውሃ የእርሱ እንደሆነ›› ጠንካራ እምነት እንዲይዝ አልተደረገም።
የግብፅን አሻፈረኝ ባይነት በሁሉም መንገድ መመከት
ያስፈልጋል። አባይ ለእኛ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና እንደሆነ ልንነግራቸው ይገባል። ለእኛ ዘላለም አይናይኑን የምናየው ቅርስ ብቻ ሳይሆን ከድህነት መውጫ መሰላላችን መሆኑን በአንድ አቋም ልንነግራቸው ያስፈልጋል። ህጻኑም፣ ሽማግሌው ሆነ ወጣቱ ግንዛቤው ኖሮት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከግብ እንዲደርስ መስራት ይጠበቅብናል። በሃሳብ ብቻ ይሆን በሁሉም መንገድ ድጋፋችንን ማድረግ አለብን።
ግብጾች አባይን የሙጥኝ ብለው ‹‹ህልውናችን ነው›› በማለት የህፃናት አእምሮ ጭምር በዚህ እሳቤ ተኮትኩቶ እንዲያድግ ሰርተዋል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት አጋዥ የሆናቸው መገናኛ ብዙኃኑ እንደሆነ የሚካድ አይደለም። ነጋ ጠባ ስለ አባይ ሳያነሱ አይቀሩም። በግብፅ ምድር በየቀኑ ስለ አባይ ሲወሳ ህይወት ያለ እርሱ እንደማይታሰብ ይሰበካል። ከዚያ በላይ የሉአላዊነት ጉዳይም አድርገው ይዘግቡታል።
የመገናኛ አውታሮቻቸው ህልውና ስለሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሉታዊ ጎን ምን ያህል እንደሚያቀነቅኑ የሚታወቅ ነው። በዚህም የፕሮፓጋንዳ ሥራቸው ብዙዎች ወዳጆቻችን የምንላቸው የአረብ አገራት ሳይቀሩ ከእነርሱ
ጎን እንዲቆሙ አድርገዋል። አባይ ለኛ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ከእነርሱ እኩል ለዓለም ህዝብ ማስረዳት ባለመቻላችን ብዙ ነገር አሳጥቶናል። ዛሬ ግን መንቃት አለብን። አባይ ከግብጽ በላይ የሚያስፈልገን መብራት፣ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ለማንችለው ለእኛ ነውና ግንዛቤ መፍጠሩና ከበቂ መረጃ ጋር መስጠቱ ላይ መረባረብ ያስፈልገናል። አዲስ መጪው ትውልድም ይሄን የህልውና ጉዳይ አውቆና ተረድቶ ሊያድግ ይገባል። በተለይ መገናኛ ብዙኃንና ባለሙያዎች ይህንን ኃላፊነት ወስደን መስራት ይጠበቅብናል።
የመገናኛ ብዙኃኖቻችን በአገራችን ስላለው የመብራት ስርጭት ለዓለም ህዝብ ማስረዳት አለባቸው። 45 በመቶ ዜጎች ብቻ የመብራት ተጠቃሚ እንደሆኑ ማሳወቅ ብንችል ግድቡ እንዳይሞላ የሚል ሀሳብ የሚያራምዱሀገራትን እና ግለሰቦችን አስተሳሰብ መቀየር ይቻላል። ስንቱ አርሶ አደር ዝናብ ጠብቆ በዓመት አንዴ ብቻ እንደሚያመርትና ዓመታዊ ምርቱም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮውን ሊደጉምለት እንደማይችል በድህነት እንደሚማቅቅ ማሳወቅ ብንችል ከጎናችን ሁሉም እንደሚቆም አምናለሁ።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እውነቱን እውነት ፣ ሀሰቱን ደግሞ ሀሰት ማለት መጀመርም አለባቸው። ተከታታይ ዘገባዎችንም ሊሰሩ ይገባል። በዋናነት የኢትዮጵያና የግብጽ ሚኒስትሮች ለድርድር በሚሰበሰቡበት ወቅት ለመዘገብ የሚሰለፉ የመገናኛ ብዙኃኖች ትልቅ ማሳያዎች ናቸው። በኛ በኩል ድርድሩ ከአገር ውጭ ከሆነ ከአንድ የተመረጠ የሚዲያ ተቋም ውጭ ለመዘገብ እንደማይሄድ በተደጋጋሚ አስተውለናል። በተቃራኒው ደግሞ በግብጽ በኩል ድርድሩ በአገራቸው ይሁን ከአገራቸው ውጭ የመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ለቁጥር አታካች መሆኑን ታዝበናል። ይህ ስለጉዳዩ ማን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የሚያመላክት ይመስለኛል። ይህ ስህተት መስተካከል አለበት።
አባይን በተመለከተ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት አለብን። አሁን አሁን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወጣ ብለው የኢትዮጵያን ፍላጎትና መብት በመረጃ ተደግፈው የሚሞግቱ መገኘታቸው ይበል የሚያስብል ነው። በአባይ ጉዳይ የማናነሳው ሃሳብ የማናቀርበው መረጃ ሊኖር አይገባም። በተለይም ጥቅሞቻችንን የሚያሳጡ አጀንዳዎችን በቸልተኝነት ማለፍ የለብንም ። ከሁሉ በላይ ግን እያንዳንዱ ዜጋ ከህዳሴው ግድብም ሆነ ከአባይ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው ሊያውቅና ሊገነዘብ ይገባል። ይህን ማድረግ ስንችል በኢትዮጵያ ሰማይና ምድር ላይ ዝንብ ዝረ ቢል እንኳን እንደ ንብ ተምሞ የአገርን ዳር ድንበርና ጥቅም የሚያስጠብቅ ዜጋ መፍጠር እንችላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው