ምስቅልቅሉ በወጣበት በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሙ አሃዞች እና ሁነቶች እጅጉን ያስደነግጣሉ። በተለይም ደግሞ የኮረና ቫይረስ በበለፀጉ አገራት ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ሲሰላ እና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ሲገመት እጅግ ከፍተኛ ሆኗል። ስለ በሽታው ጆሮ ዳባ ልበስ በሚባል ደረጃ በመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ቸል ብላ የነበረችው አሜሪካም ዛሬ ከበርካታ ውጥንቅጦችና ችግሮች ውስጥ ገብታለች።
የአገሬውም መሪ ቢሆኑ ጣታቸውን ወደ ሌሎች አገራት ለመቀሰር እንጂ በሽታውን ቁርጠኛ ሆነው ለመከላል እየሰሩ አይደለም በሚል በተቀናቃኞቻቸው በየቀኑ ሲብጠለጠሉ ይውላሉ። የአገሬው መገናኛ ብዙሃንም በየሰዓታቱ የሟቾችን ቁጥር ለማሳወቅና የኮረና ቫይረስ አስከፊነትን ለመዘገብ ተገደዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎች አርምጃዎችም የኮረና ቫረስ አስከፊነትና ተላላፊነትን ለማገድ አልተቻላቸውም። በየደቂቃው አስከፊ ዜናዎች ከታላቋ አገር መገናኛ ብዙሃን መስማት ግድ ሆኗል።
አሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሞቱባት ዜጎች ቁጥር በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን እና በኮሪያ ጦርነቶች በድምሩ ከሞቱት ዜጎች በእጅጉ የበዛ ሲሆን የዓለም መገናኛ ብዙሃን በሰፊው እየዘገቡት ሲሆን ለአገሪቱ ባለስልጣናት ራስ ምታት ሆኗል፤ ዜጎችንም ጭንቅ ውስጥ ከቷል። በሌላም በኩል አሜሪካ በሟቾችም ሆነ በወረርሽኙ በተያዙ ሰዎች ቁጥር አንደኛ መሆኗን ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በመረጃው ያብራራል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የምጣኔ ሀብታቸው ጉምቱ የሚባሉ አገራትም ይይዙ ይጨብጡትን አጥተዋል። ፈረንሳይ፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ራሺያና የመሣሠሉት አገራት የፍዳው የጀመሪያ ቀማሽ ናቸው። ወዲህ ደግሞ ቫይረሱ እየከሰመ ነው ብሎ ለህዝባቸው የእፎይታ መልዕክት ካስተላለፉ ሳምንታት በኋላ ደግሞ የወረርሽኙ መልሶ ማገርሸት መልሶ ስጋት ውስጥ እየከተታቸው ይገኛል። ለአብነት የቫይረሱ መነሻ ናት ተብላ በምትገመተው ቻይና እስካሁን ብዙዎች የሞቱባት ቢሆንም ቫይረሱን ተቆጣጠርኩ ካለች ሳምንታት በኋላ በቤጂንግ በ45 ሰዎች ላይ ቫይረሱ በመገኘቱ በሰፊው እየተሰራጨ መሆኑን የአገሬው ባለስልጣናት አብራተዋል።
ዓለም ውጥንቅጧ ብዙ በሆነበት በዚህ ወቅት ደግሞ በርካቶችም በሽታውን ለመከላከል የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ነው። በዓለም ዙሪያ በሽታውን ሥርጭት ለመግታት ዜጎች በርካታ ውሳኔዎችን እርምጃዎችንም በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ለይቶ ማቆያ ስፍራ ለመሄድ ለያዥ ገራዥ ሲያስቸግሩ ጥቂቶች ደግሞ ከዚህ ስፍራ እያመለጡ ለቫይረሱ መሠራጨት ዕድል ይሰጣሉ ወዲህ ደግሞ አንዳንዶች ከሚጠበቀው በላይ በመጠንቀቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
የዛሬው እንዲህም ኖራል አምድ እንግዳችን ከሀገር ሸሽተው፣ ባሕር አቋርጠው የተሻለ ሕይወት ለመምራት ወስነው መዳረሻቸውን ሶማሌ ላንድ አድርገው ከነበሩ አንድ ግለሰብ ላይ ያተኩራል። ወደ የመን ለመግባት አመች ሁኔታ ይፈጠራል በሚል በሶማሌ ላንድ ቦሳሶ ወደብ አቅራቢያ ለሁለት ወራት ያክል መሽገውም ነበር እኚህ ሰው። ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም አዲሱ ክስተት መሆኑን ተከትሎ ይገቡበት ቤት፣ ይጠጉበት ጎረቤት ቢያጡ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። “ማን እንደ ሀገር?” ብለውም በጅግጅጋ በኩል የትውልድ ቀያቸው ደርሰዋል፤ የቆቦ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው -አቶ አማረ በላይ።
የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አማረ ‹‹የኮሮና ቫይረስ ሊኖርብኝ ይችላል›› የሚል ስጋት ነበራቸው፤ እርሳቸውን ጨምሮ ወደ ለይቶ ማቆያ ለመግባት ፍላጎት ከነበራቸው 20 ገደማ ተጓዦች ጋር በመመካከርም ወደ
ወልዲያ ከተማ ከመግባታቸው በፊት ለይቶ ማቆያ መግባት እንደሚፈልጉ ለመንግሥት አካላት ቀድመው አሳወቁ። ወደ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ ተወስደውም ከ14 ቀናት ቆይታ በኋላ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ያለ ምንም ስጋት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለውም ቤተሰባዊ ፍቅራቸውን ማጣጣም ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።
‹‹ተመርምሬ ከቫይረሱ ነፃ መሆኔን በማረጋገጤ የተለየ ስሜት ተሰምቶኛል፤ ይህን በማድረጌ ከፀፀትና ከህሊና ክስ ነፃ ሆኛለሁ›› በማለት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ይናገራሉ። ማንኛውም አጠራጣሪ ሁኔታ ሲገጥም እራስን ለይቶ ማቆየት የተሻለ መፍትሔ እንደሆነም ይመክራሉ። ሰዎች ቫይረሱ ቢኖርባቸውም እንኳን እንደሚድኑ ውስጣቸውን ማሳመን፣ በሽታውን ለቤተሰቦቻቸው ላለማስተላለፍ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።
ነገር ግን ይህ እየሆነ አለመሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል። አብረዋቸው ከሶማሌ ላንድ የተመለሱ እንደመጡ ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉ ግለሰቦች እንደነበሩም መስማታቸውንም ተናግረዋል። በሌላ በኩል ወረርሽኙ አሳሳቢ መሆኑ እየታወቀ ወደ ማቆያ ከገቡ በኋላ መዳረሻቸውን የሚያጠፉ ግለሰቦች እየተበራከቱ መሆኑንም ሲሰሙ እዳሳዘናቸው ይናገራሉ።
በዚህ ሁኔታ ሰሞኑንም በርካታ ሰዎች ከማቆያ ስፍራ አመለጡ ሲባል መስማት እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ለአብነት ሰሞኑን በመናኸሪያ አካባቢ ቫይረሱ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ ከ16 ያላነሱ
ሰዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ተሰምቷል። ቀደም ሲል አንድ ሰው ከአዲስ አበባ አምልጦ ወደ ደሴ ከተማ እንደገባ እና ከ15 ቀናት ፍለጋ በኋላ መገኘቱ ይታወሳል። ይህ ብቻ አይደለም የአምቡላንስ መስኮት ሰብረው ያመለጡና ለያዥ ገራዥ ያስቸገሩ ሰዎች እንደነበሩም ሰምተናል። ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በንፋስ ፍጥነት እየተላለፈ የሚገኘውን የኮረና ቫይረስ ለመከላከል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ ድርጊት ነው።
ታዲያ አቶ አማረን የመሰሉ ሩቅ አሳቢ ሰዎች ደግሞ ራሳቸውን ለመጠበቅና ሌሎችንም ለመታደግ እንዲህ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፤ በሌላ ጎራ ያሉት ደግሞ ከመንግስትና ጤና ባለሙያዎች ጋር የድብብቆሽ እየተጫወቱ በራሳቸውም እና በሌሎች ሕይወት ላይ ሲፈርዱ ማየት ነገሩ ለየቅል ያስብላል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱን ሥርጭት በየጊዜው እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። በቀን በአማካይም ከ150 እስከ 200 ሰዎች ቫይረሱ እየተገኘባቸው ሲሆን፤ አሃዙ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ስለመምጣቱም ማሳያ ነው። በተለይም ደግሞ ከሃምሌ ወር ጀምሮ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርና ነገሮችም የከፉ እንደሚሆኑ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት የሚሰጧቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን 440ሺ የሚሆኑት
ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም የቫይረሱ ስርጭት አደገኛነትን የሚያሳይ ሲሆን በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ የሚገኝ የክፍለ ዘመኑ መጥፎ ወረርሽኝ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በምርምር በርካታ ተስፋ ሰጪ ግኝቶች አሉ ቢባልም እስካሁን ሁነኛ መፍትሄ አመለገኘቱ ችግሩን የባሰ አስፈሪና ውስብስብ አድርጎታል። አገራት እንደነባራዊ ሁኔታቸውና አንደ አገራቸው ጤና ፖሊሲ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ሲሆን መድሃኒት አገኘን ብለው የሚናገሩም አልጠፉም። እስካሁን ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህ ፍቱን መድሃኒት ነው ተብሎ እውቅና የተሰጠው መድሃኒት የለም።
በመሆኑም እስካሁን ባለው ርቀትን በመጠበቅ፣ ጭንብሎችን አድርጎ በመንቀሳቀስና ንጽህናን በመጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እኛ ኢትዮጵያንም ይህን ተግባራዊ አድርገን ወረርሽኙን በጋራ ልንከላከልና ይህን አስቸጋሪ ወቅት በጋራ ልንሻገር ይገባል የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር