የፊልሙ ርዕስ፡- ሰማያዊ ፈረስ
ደራሲና ዳይሬክተር፡- ሠራዊት ፍቅሬ
የተሰራበት ዘመን፡- ታህሳስ 1997 ዓ.ም
የፊልሙ ርዝማኔ፡- 1፡52፡07
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ‹‹ሰይፉ በኢ ቢ ኤስ›› የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው አንድ ነገር ተናግረው ነበር። ይሄውም፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እንዲህ አይነት የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ መቅረባቸው ከወጣቶች እና ታዳጊ ልጆች ጋር በቀላሉ እንዲገናኙ ያደርጋቸዋል ነበር ያሉት።
ሚኒስትሩ ትክክል ናቸው። ለዚህም የወጣቶችን እና የልጆችን የፕሮግራም ምርጫ ማየት በቂ ማሳያ ይሆነናል። ወጣቶችና ታዳጊዎች ጠንካራ ጉዳዮችን (Hard Issues) አይከታተሉም። ጠንካራ ጉዳዮችንና ፖለቲካዊ ቃለ መጠይቆችን የሚከታተሉት አዋቂዎችና ጎልማሶች ናቸው። እንዲህ አይነት ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ቀለል ባለ አቀራረብ በመዝናኛ መልክም መቅረብ አለባቸው።
ለመሆኑ የዓባይ ጉዳይ፤ ጠንካራ ፖለቲካ ነው? ለወጣቶች የሚሆን መዝናኛ ነው? ለልጆች የሚሆን ተረት ተረት ነው? ካወቅነው ሁሉንም ነው!
‹‹የብቻዬ ይሁን!›› ከምትለው ግብጽ ጋር እናነፃፅረው። ግብጽ ውስጥ ዓባይ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ጉዳያቸው ነው። ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ የምርምር ተቋማት ዓባይ ህልውና ነው። በሁሉም ደረጃዎች ትምህርት ይሰጥበታል።
ጥቅም ላይ አላዋልነውም እንጂ ዓባይ ለኢትዮጵያም ሁሉንም ነገር ነው። ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን፤ ፖለቲካ ነው፣ መዝናኛ ነው፣ ተረት ተረት ነው… በቃ ሁሉንም ነገር ነው።
ወደ ፊልሙ ከመግባታችን በፊት ኪነ ጥበብ እና የአገራችንን ፖለቲካ ማየት ጥሩ ነው።
አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ የቀዳማዊ ኢህአዴግ ‹‹አድር ባይ ነው›› በሚል ሀሜቶች ይደጋገሙበታል። እንዲህ አይነት የፖለቲካ ብሽሽቆች የኪነ ጥበብን አይን ያጠፋሉ። ሰዎች በኪነ ጥበብ ውስጥ የሚታያቸው ፖለቲካው ብቻ ነው። በጥላቻ የታየ ነገር ደግሞ የቱንም ያህል ቢያምር አይጣፍጠንም፤ የምንወደው ሰው ደግሞ የቱንም ያህል አበላሽቶ ቢሰራው እናደንቀዋለን። ጥላቻና የፖለቲካ ብሽቀት ኪነ ጥበባዊ ለዛዎች እንኳን እንዲያስጠሉን ያደርጋል።
ለምሳሌ፤ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ እና ሙሉ ዓለም ታደሰ የሚሰሯቸው ማስታወቂያዎች አስቂኝ ናቸው። ግን በእነዚያ ማስታወቂያዎች ተደጋጋሚ ቁጣና የማህበራዊ ሚዲያ ስድብ ወርዶባቸዋል። አንዱን እንደ ማሳያ እንውሰድ። ‹‹ሻማ ለልደት፤ ኩራዝ ወደ ሙዚየም!›› የሚለው የመብራት ኃይል ማስታወቂያቸው ፈጠራው ጥሩ ነው፤ ግነት ደግሞ የየትኛውም ማስታወቂያ ባህሪ ነው። በዚያ ላይ ‹‹ሆነ›› ሳይሆን ‹‹ይሆናል›› ነው ያሉት። ሳይሆን በመቅረቱ የሚመለከተው አካል ይወቀስበት። እስኪ የየትኛው ምርት እና አገልግሎት ማስታወቂያ ነው በሚባለው ልክ በትክክል ተግባር ላይ ያለው? እንኳን በማስታወቂያ (ግነት መሆኑ እየታወቀ) ትልልቅ የመንግስት ተቋማት የማሳያኩትን ራዕይና ተልዕኮ ነው በየበራቸው ላይ በትልልቅ ሰሌዳ የሰቀሉት። ይሳካል የተባለበት ዓመት አልፎ እጥፍ ጨምረውም አላሳኩትም። በነገራችን ላይ የብዙ መስሪያ ቤቶች ራዕይ 2012 ዓ.ም ነበር።
አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በዚህ ማስታወቂያ (ሻማ ለልደት ኩራዝ ወደ ሙዚየም) ብዙ ተወቀሰ። ሠራዊት ፍቅሬ አርቲስት ነው፤ ሳይንቲስት አይደለም። በየትኛውም ማስታወቂያ ውስጥ እንዳለው ግነት አጋነነው።
ዛሬ ስለሰራዊት ፍቅሬም ሆነ ስለማስታወቂያ ስራዎቹ ያነሳሁት እንዲሁ ለዋዛ አይደለም፤ ዛሬ የምናየው ፊልም የአርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ስለሆነ ነው። ከላይ በገለጽኳቸው ምክንያቶችም ሥራዎቹ ላይ ተፅዕኖ ስላለው ነው። የሚወዱት እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙትም ነበሩ። የሚቃወሙት የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ናቸው።
ወደ ፊልሙ
‹‹ሰማያዊ ፈረስ›› ፊልም ድንቅ ሀሳብ ያለው ፊልም
ነው። በውጭው ዓለም የምንቀናባቸውን ፊልሞች በከፊልም ቢሆን ለመተግበር ሞክሯል። የሆሊውድ ፊልሞች የሚታወቁት በሳይንስ ፈጠራ ነው። ራሳቸውን ችለው ለሳይንሱ ዘርፍ ግብዓት ይሆናሉ፤ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ ደግሞ ምንጭ (መነሻ) መሆን የሚችሉ ናቸው። እንዲህ አይነት ፊልም ለመሥራት የሚያስችል የቴክኖሎጂ መሳሪያም አላቸው። የአገራችን ፊልሞች ግን ምንም ማብራሪያ ሳያስፈልገው ከእንዲህ አይነት ነገር የራቁ ናቸው።
ሰማያዊ ፈረስ ቢያንስ ሀሳቡ ይደነቃል። አንድ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ አንስቷል፤ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ትልቅ የቴክኖሎጂ ምናብ ፈጥሯል። በሌላ በኩል የአገሪቱን በሙስና የተጨማለቀ ነባራዊ ሁኔታንም አሳይቷል። የዕለት ጉርስ የማያገኝ ህዝብ ባለባት አገር ውስጥ ሆነው፤ ለአገሪቱ የሚጠቅም አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ለመሸጥ ሲቋምጡ ያሳያል። በቴክኖሊጂው ምናብ ታላቁን የዓባይ ወንዝ ወደ ሰማይ በማትነን እንደገና በዝናብ መልክ እንዲመጣ ያደርጋል። በዚህ የምናብ ቴክኖሊጂ አገሪቱን ድርቅ እንዳያጠቃት ማድረግ ይቻላል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና ላይ የተመሰረተ ነው፤ ግብርናው ደግሞ በዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ኢኮኖሚያችን ዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው። የሰማያዊ ፈረስ ፊልም የምናብ ቴክኖሎጂ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ያገናዘበ ነው።
አጥኚው ኢንጂነር እስክንድር የሚባል ተመራማሪ ነው። በእንግሊዝ አገር ጥናትና ምርምር ያደረገ ነው። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱን አቅርቧል። ይሄን የምርምር ውጤቱን ነው አገሩ ላይ ዕውን ማድረግ የፈለገው። በአገር ውስጥ ደግሞ አንድ የኢንቨስትመንት ቡድን (ግሩፕ) አለ። ‹‹ሚክሰር ኢንቨስትመንት ግሩፕ›› ይባላል። እዚህ የኢንቨስትመንት ቡድን ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች የኢንጂነር እስክንድርን ፕሮፖዛል ሰርቀው
መሸጥ ይፈልጋሉ። በውይይታቸው መጀመሪያ ላይም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያቀረበውን ጥናት በምስልና በድምጽ አዳራሽ ውስጥ ያዩታል። ትረካውን እናካፍላችሁ።
‹‹ሰሜን ላይ በትንሽ ወጪት ትልቅ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ምንጭ ይተክላል። በሶላር ሲስተም ፀሐይን ይጎትታል። እስከአሁን ባልተደረሰበት ሁኔታ፤ ወንዙን ካተነነ በኋላ እንደምታዩት (በፊልሙ ላይ ደመና ይታያል) ደመና ይሰራል። ሃሃሃሃሃሃ… ከዚያ በኋላ ለምለሚቱን ኢትዮጵያ ይናፍቃል››
‹‹ሜክሰር ኢንቨስትመንት ግሩፕ›› የተባለው ቡድን የኢንጂነር እስክንድርን ፕሮፖዛል ከእጁ ለማስገባት ብዙ ጥረት አድርጓል። ለዚህም ፍሬሰላም የተባለችዋ ሴት የስለላና ክትትል ሥራ እንድትሰራ ተደርጓል። ተልዕኮዋ ኢንጂነር እስክንድርን ከገባበት ገብታ ተከታትላ ፕሮፖዛሉን መቀበል ነው።
ፍሬሰላም ደራሲ ናት። በጻፈችው መጽሐፍም ታስራለች። ይሄን የመጻፍ ችሎታዋን ተጠቅመው ነው ለዚህ ዓላማ ያሰቧት። በልቦለድ ጽሑፎቿ ነገሮችን የማስተዋልና ሳታስነቃ የመሰለል ብቃት ይኖራታል ተብላ ነው በሰላይነት ልትመረጥ የቻለችው።
በነገራችን ላይ ፊልሙን የምናየው በፊልም መገምገሚያ መስፈርቶች አይደለም፤ ሀሳቡን ብቻ ነው። ሀሳቡን እና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያለውን ግንኙነት።
የኢንጂነር እስክንድርን ፕሮፖዛል ማጨናገፍ ከሚፈልጉት የሚክሰር ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባላት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ፤ ልጁ ‹‹መቼ ነው ጢስ ዓባይ ፏፏቴን የምታሳየኝ ?›› ስትለው ፏፏቴው አደገኛ እንደሆነ እያስፈራራ ይነግራታል። ለአገሩ አለመቆርቆሩ ሳያንስ ታዳጊ ህጻናት አገራቸውን እንዳያውቁ እና እንዳይወዱ የሚያደርጉትን የገሃዱን ዓለም ሰዎች በጴጥሮስ በኩል እናገኛቸዋለን።
ፍሬሰላም እንደተባለውም ጎበዝ ናት። ማጥመድ ትችልበታለች። ኢንጂነር እስክንድር ያረፈበት ሆቴል ውስጥ ገብታ ብቻዋን ቁጭ ብላ እራት ትበላለች። ኢንጂነር እስክንድር በመገረም ‹‹ኢትዮጵያ ተለውጣለች ማለት ነው፤ ሴት ልጅ ብቻዋን?›› እያለ በሆዱ ያወራል፤ ፍሬሰላምም ብቻዋን በሆዷ ‹‹ስድስት ሚሊዮን ዶላሬ በእጄ ሲገባ! ያኔ እጋብዝሃለሁ የኔ መሃንዲስ›› ትላለች።
ኢንጂነር እስክንድር ሥራውን የሚሰራው በመንግስት ድጋፍና ትብብር ነው። መንግስት ለሥራው መሳካት ያበረታታዋል፤ ሥራውንም ያደንቃል። ጥበቃ ሁሉ ይደረግለታል (እሱ አልፈልግም ቢልም)። ለአስፈላጊ ወጪዎቹም ከየትኛውም ቅርንጫፍ ገንዘብ ማውጣት እንዲችል ተደርጓል።
የሚክሰር ኢንቨስትመንት ግሩፑ ጴጥሮስ፤ የአገሪቱ ጋዜጦች ‹‹ዓባይ ዓባይ…›› ማለታቸውን እንደ ማሽቃበጥ በመቁጠር ያናድደዋል። ፊልሙ በ1990ዎቹ የነበረ ነው፤ ይሄ አይነት ነገር ግን አሁንም አለ። ልማታዊ ጉዳይ የያዙ ጋዜጦች ሁሉ እንደ አሽቃባጭ ይቆጠራሉ። ጋዜጣ ማለት ጦርነትና ግጭት ብቻ መዘገብ ያለበት ይመስል ልማታዊ ነገሮች ይጠላሉ። የዓባይ ጉዳይ ግን የመንግስት ሳይሆን የህዝብ ነበር። ፊልሙ በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታም ያሳያል ማለት ነው።
ፍሬረሰላም ኢንጂነር እስክንድርን ለማጥመድ ትኩረት የሚስቡ ነገሮችን ትጠቀማለች። የሚክሰር ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባላት ሴትነቷን ተጠቅማ ኢንጂነር እስክንድርን እንድታጠምደው ቢነግሯትም እሷ ግን የተሻለ ዘዴ ተጠቅማለች። የሆቴሉ በር ላይ ሄዳ በትወና ክዋኔ ትጮሃለች። ኢንጂነር እስክንድር ‹‹ምን ተፈጠረ!›› ብሎ ሲወጣ ‹‹ይቅርታ!›› ብላው ትቀመጣለች። ተውኔት እየተለማመደች ነው ብሎ ሲገምት ሌላ ሌላ የፍስልስፍና ቃላትን እያወራች ትኩረቱን ትስባለች። ማንም ሰው ደግሞ ወጣ ያለ ነገር ሲያይ ትኩረት መስጠቱ አይቀርም።
‹‹ፍሬሰላም›› የምትባለዋ ገጸ ባህሪ ላይ ግን አንድ የተደበላለቀ ነገር ያለ ይመስለኛል። ምናልባትም ግን ታስቦበት የተሳለ ሊሆንም ይችላል። ፍሬሰላም ዓላማዋ የኢንጂነር እስክንድርን ፕሮፖዛል እጇ ማስገባት ነው። ይሄን የሚያደርግ ሰው የራስ ጥቅምን እንጂ ጥልቅ የአገር ፍቅር ሊኖረው እንደማይችል እሙን ነው። የሰው የፈጠራ ውጤት ሰርቆ መሸጥ ከአገር ወዳድ አይጠበቅም። ግን በደራሲነቷና ብቻዋን በምታነበንባቸው ንግግሮች የምታወራው ስለኢትዮጵያ ታላቅነትና የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነት ነው። ትወና በሚመስል ንግግሯም ‹‹የእናት ጡት ነካሾች!›› ትላለች። ማንን ይሆን? እነዚህ የአገር ፍቅር ስሜቶቿ ኢንጂነር እስክንድርን ለማታለል ከሆነ እሱን ስታገኘው ብቻ ማለት ይበቃ ነበር። እርግጥ ‹‹እስክንድርን ለማጥመድ ዳሌ እና ጭን ቦታ የላቸውም›› ብላለች። እስክንድርን ለማታለል ነበር ለማለት ያስችለናል። በመጨረሻም የሆነው ሆኗል፤ እዚያ ላይ አገር ወዳድነቷንና ታማኝነቷን አሳይታለች።
በመጨረሻም ፍሬሰላም ከኢንጂነር እስክንድር ፍቅር ይይዛታል፤ በኢንጂነር እስክንድር ፍቅር ትሸነፋለች። እየተሸነፈች መሆኑን ቀድማ አውቃ ነበር። የሚክሰር ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባላትም እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረ። ፍሬሰላም ክህደት በመፈጸሟ ጴጥሮስ አስሮ አሰቃይቷታል። በፀጥታ ሃይሎችም ነገራቸው ሁሉ ይከሽፋል፤ የኢንጂነር እስክንድር ፕሮፖዛልም ከመሸጥ ተርፏል።
መግቢያው ላይ የተባለውን በድጋሚ እናስታውሰው። ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችም የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ መቅረብ አለባቸው። ዓባይ ደግሞ ሁሉንም ነገር ነው።
ሌላው ችግራችን፤ የፖለቲካው ብሽሽቅ ኪነ ጥበብ ውስጥ መግባቱ ነው። ለምሳሌ፤ ሰማያዊ ፈረስ ፊልም ስለዓባይ በተሰሩ ፕሮግራሞች ሁሉ መታወስ ነበረበት። የውጭ ፊልሞችን ሲሆኑ በማሳያነት እናቀርባቸዋለን፤ የራሳችንን ግን ለማበረታታት እንኳን አናቀርባቸውም። አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በዚህ ወቅት የሰራዊት ፍቅሬን ፊልም ቢያሳይ ምን እንደሚባል ስለሚያውቅ ነው። ከኪነ ጥበብ ይልቅ ለፖለቲካው ተገዛ ማለት ነው።
እንዲህ አይነት የምናብ ፈጠራ እና አገራዊ ጉዳይ ያላቸውን ፊልሞች ከፖለቲካ ብሽሽቅ ነፃ ሆነን እናበረታታ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ዋለልኝ አየለ